Sunday, 05 February 2017 00:00

የፓርቲዎች ድርድርና ድብድብ - በጦቢያ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(18 votes)

ትራምፕ ለ1 ሰዓት ንግግር 1.5 ሚ. ዶላር ይከፈላቸው ነበር (ፕሬዚዳንት ሳይሆኑ)
   በስማቸው ከ15 በላይ ስኬታማ የቢዝነስ መፃህፍት አሳትመዋል
  የተቃዋሚዎችንና የኢህአዴግን ወቅታዊ የድርድር ሂደት እንዴት አገኛችሁት? (በጎሪጥ እንዳትሉኝ!) እውነት ለመናገር … የጦቢያ ኋላ ቀር የፖለቲካ ባህል የሚለወጥ ከሆነ … የሚለወጠው በንግግር ብቻ ነው፡፡ በድርድር ብቻ፡፡ በውይይት ብቻ፡፡ ሌሎች ተያያዥ የአገር ችግሮችም … መፍትሄ የሚያገኙት በሌላ መንገድ ሳይሆን በውይይት ብቻ ነው፡፡ በድርድር፡፡ እናላችሁ … በአንድ በኩል የፓርቲዎች ድርድር … በሌላ በኩል የፓርቲዎች ድብድበ እያየን ነው በጦቢያ ምድር!! (ከሰማያዊ ፓርቲ የሚሰማው ዜና ይሄን ይመሰክራል!)
በነገራችን ላይ … የዚህች አገር አንዱ ትልቅ ችግር ምን መሰላችሁ? የፓርቲዎች ውዝግብ! ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ገዢው ፓርቲ አንዱ ለሌላው ያለው የጠላትነት ስሜት ነው - ትልቁ ችግር!! (ከአንድ አገር ማህፀን የወጡ አይመስሉም እኮ!)
እውነቱ ግን የአንድ አገር ልጆች ነን - ኢህአዴግም ተቃዋሚዎችም!! ሁለታችንም ኢትዮጵያውያን ነን!! የጦቢያ ልጆች!! ግን በዚህ ጉዳይ መግባባት ላይ አልተደረሰም፡፡ ለህዝብ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ከመደራደራችን በፊት … ለራሳችን ጥያቄዎች መልስ መስጠት አለብን፡፡ ለአገር እርቅ መውረድ ከመትጋታችን በፊት …ለራሳችን እርቅ ማውረድ አለብን፡፡ ኢህአዴጎችና ተቃዋሚዎች …. ተቃዋሚዎችና ተቃዋሚዎች (እርስ በርስ) … የሚተያዩበትን መንገድ መቀየር አለባቸው፡፡ “አገር ከፋፋይ”፣ “ሰላም አደፍራሽ”፣ “ፀረ-አንድነት”፣ “ፀረ-ልማት”፣ “ዘረኛ”፣ “መንደርተኛ”፣ “ጠባብ”፣ “ነፍጠኛ”፣ … “የድሮ ሥርዓት ናፋቂ”፣ … ወዘተ የሚሉ ፍረጃዎችን ከልባችን ይሁን ከሆዳችን (ብቻ ካለበት) ማውጣት ይኖርብናል - አውጥተን
መጣል!! ኢህአዴግና 20 ምናምን የሚደርሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች … ለድርድር ወደ አዳራሽ ሲገቡ ልባቸውን ይሁን ሆዳቸውን … ወይም አዕምሮአቸውን ሙልጭ አድርገው … አጥበው መሆን አለበት!! ከጥላቻ … ከንቀት … ከክፋት … ከምቀኝነት … ከእብሪት … ከተንኮል … ከድብቅ አጀንዳ … (Plan B እና ድብቅ አጀንዳ ይለያያል!) እኒህን አሉታዊ ሃይሎች … ተሸክመን የምናደርገው ድርድር ይሁን ውይይት … እንኳን ለአገር … ውጤት ሊያመጣ ቀርቶ ወደ ቀጣዩ የድርድር ሂደት አያደርሰንም፡፡ (መንገድ ነው የምንቀረው!) እንኳንስ ዘላቂ ሰላምና ዘላቂ መፍትሄ ልናመጣ … የለየለት ፀብና ክፍፍል ፈጥረን እናርፈዋለን!! ባለፉት 25 ዓመታት በሁለቱ የፖለቲካ ጎራዎች መካከል የተደረጉ ድርድሮች (ተደርገዋል እንዴ?) ለምንድን ነው ፍሬ አልባ የሆኑት? በቅንነት ሳይሆን በእብሪት የተደረጉ በመሆናቸው ይመስለኛል፡፡ በአቻነት ወይም በእኩልነት ስሜት የተፈፀሙ ባለመሆናቸው ይመስለኛል፡፡ በብልጣ ብልጥነት ስሜት የተቃኙ ስለነበሩ ሊሆን ይችላል። የሰጥቶ መቀበልን … የመከባበርን … የመቻቻልን … የመደማመጥን … መርህ ያለመከተል ውጤት ይሆናል፡፡ ከፓርቲ ይልቅ ለአገር ቅድምያ ያለመስጠት ችግርም የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ስልጣን ተኮር በመሆናቸው የተከሰተ ይሆናል፡፡ እናም በእነዚህና ሌሎች ምክንያቶች የድርድር ሙከራዎችና ጥረቶች እየተቋረጡና እየተቀጩ በመንገድ ላይ ቀርተዋል፡፡ የአሁኑስ … ከቀድሞዎቹ በምን ይለያል? ፓርቲዎቹም በዓመታት ብዛት ብስለት አግኝተዋል? (ፈፅሞ!) እናላችሁ… ቢያንስ .. በተደጋጋሚ የፈፀምናቸውን ስህተቶች ዛሬም እንዳንደግማቸው እንጠንቀቅ! (አዲስ ስህተት ብንሰራ እኮ ይሻላል!)
ኢህአዴግም … ተቃዋሚዎችም … ለምን አሁን ድርድርና ውይይት እንደፈለጉ … እስቲ በብሄራዊ ቴሌቪዥናችን በቀጥተኛ ስርጭት (Live ማለቴ ነው) በግልፅ ይንገሩን!! ለጋዜጠኛ ለመናገር ያጠኑትን ሳይሆን የልባቸው ነው የምንፈለገው!! ለመሆኑ የድርድሩ ዓላማ ምንድን ነው? ምን ለማምጣት? ወዴት ለመሄድ? ግባቸው የአጭር ጊዜ ነው? የረዥም ጊዜ? እንደተለመደው በሁለተኛው ድርድር ላይ አክሽፈውት … በየሚዲያው ይካሰሳሉ ወይስ የድርድሩን ዕድሜ ያራዝሙታል? (ውጤት ባይመጣም!) ይሄን ሁሉ የምዘባርቀው ግን ድርድሩ Fail እንዳያደርግ ወሳኝ ምክር ለመለገስ እንዳይመስላችሁ፡፡ የ“ድርድር” ትምህርትም ሆነ ዕውቀት የለኝም፡፡ (ባይሆን የትራምፕን “The Art of The Deal” እንደገና አነባለሁ!
አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው … የፖለቲከኞች መታሰርም ሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድርድሩን ለማካሄድ ሁነኛ ምክንያት ይሆናል እንጂ ላለመደራደር ሰበብ ሊሆን አይችልም ብለዋል። (ቅድመ ሁኔታን ምን አመጣው?) እስቲ ለአፍታ ወደ ኃያሏ አገር አሜሪካ፣ ባህር ተሻግረን ደረስ ብለን እንምጣ (በኤር ፎርስ ዋን ባይሆንልን - በትራምፕ አውሮፕላን!) በነገራችን ላይ በአወዛጋቢነታቸው የቀጠሉት አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ The Art of the Deal የተሰኘውን ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገበ (ከ1 ሚ. ኮፒ በላይ ተሸጧል) የቢዝነስ መፅሀፍን ጨምሮ ከ15 በላይ የስኬትና ቢዝነስ ላይ ያተኮሩ መፃህፍትን አሳትመዋል፡፡ (ትምራፕ ዘንድ ፎቅና መፅሀፍ በሽበሽ ነው!) በአሜሪካ የተሳካላቸው ደራሲ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ትራምፕ፤ ካሳተሟቸው መፃህፍት መካከል “Think Big”, “The American we Deserve”, “How to Get Rich”, “Time to Get tough, Make America Great Again”፣ የሚሏቸው ይጠቀሳሉ፡፡ (ለካስ “Make America Great Again” ለምርጫ ዘመቻ የተፈጠረች መፈክር አይደለችም
ከመፅሐፋቸው ሌላ ትራምፕ በተለይ በእኛ አገር የማይታወቅላቸው የሚመስለኝ አፍ የሚያስከፍቱ ተናጋሪ መሆናቸው ነው - የፖለቲካ ሳይሆን የቢዝነስ። ሰዎችን ለቢዝነስና ለስኬት የሚያነቃቁ ንግግሮች በማድረግ ተወዳዳሪ የላቸውም ነው የሚባለው። ሁለት ሦስት የሚሆኑ የንግግራቸውን ቪዲዮ ተመልክቼአለሁ፡፡ (ከፖለቲካ ይልቅ ቢዝነስ ማውራት ሳይቀላቸው አይቀርም!) የሚገርመው ደግሞ ለተለያዩ ትላልቅ የቢዝነስ ድርጅቶች (ሪል እስቴቶችን ጨምሮ) እየተጋበዙ ንግግር ያደርጋሉ፡፡ በሰዓት ስንት እንደሚከፈላቸው ብትሰሙ … ሌላው ቢዝነስ ምን ይሰራላቸዋል? ነው የምትሉት፡፡ ለ1 ሰዓት የቢዝነስ ንግግር፣ ከ1 ሚ. ዶላር - 1.5 ሚ. ዶላር ይከፈላቸዋል። ፎርብስ እንደሚለው፤ በንግግር ከፍተኛ ክፍያ በማግኘት ከዓለም በአንደኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን ደግሞ ሁለተኛው ከፍተኛ ተከፋይ ናቸው፡፡ ትራምፕ እ.ኤ.አ ከ2006-2007 በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ “Learning Annex” ለተባለው ኩባንያ 18 ንግግሮች አቅርበዋል - ለእያንዳንዱ 1.5 ሚ. ዶላር እየተከፈላቸው:: 18 x 1.5 ሚ. ዶላር ማለት ነው፡፡  
“Hearing Annex” የተባለው ኩባንያ ፕሬዚዳንት ቢል ዚንከር፣ ለ1 ሰዓት ንግግር 1.5 ሚ. ዶላር ለትራምፕ መክፈል አይበዛም ወይ? .. ዓይነት ጥያቄ ቀርቦለት ነበር፡፡ እንዲህ አለ፡- “በዚህ ቢዝነስ …….ውስጥ ለ30 ዓመት ያህል ቆይቻለሁ፡፡ ከዶናልድ ትራምፕ የተሻለ የቢዝነስ ንግግር አቅራቢ የለም፡፡ እሱ ይናገራል ከተባለ ከየቦታው ሰው ሁሉ ይሰባሰባል፤ አዳራሹ ጢም ይላል” (ምንም ቢከፈለው አያስቆጭም! እንደማለት ነው!) ይታያችሁ … ይሄን ያህል ይከፈላቸው የነበረው ደግሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት ነው። ከስልጣን ሲወርዱ ስንት ሊከፈላቸው እንደሚችል አስቡት? (ዕድሜ ይስጣቸውና!)
በተረፈ ትራምፕ በአሜሪካ በቀዳሚነት የሚታወቁት በሪል እስቴት ቢዝነሳቸው ነው፡፡ ኒውዮርክን ጨምሮ በትላልቅ የአሜሪካ ከተሞች የትራምፕ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች ዓይንና ቀልብን ይስባሉ፡፡ ለየት ያሉና ውበት የተላበሱ ናቸው፡፡ በጥራትና በቅንጡነት  ዝነኛ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል - Trump Towers! በአሜሪካ ብቻ ከ30 የማያንሱ በትራምፕ ስም የሚጠሩ ሸበላ ሸበላ ህንፃዎች ባለቤት ናቸው ይባላል፡፡ 7 የተንጣለለ የጎልፍ መጫወቻ ሜዳም አላቸው፡- በአሜሪካ ብቻ (ስኮትላንድን ሳይጨምር ማለቴ ነው!)
ሰውየው የዋዛ እንዳይመስሏችሁ … በኢስታንቡል፣ በፓናማ ሲቲ፣ በሙምባይ፣ በፊሊፒንስ፣ በቶሮንቶ፣ በኡራጋይ፣ በቫንኮቨር … ቢያንስ አንድና ከዚያ በላይ ህንፃ አላቸው “ትራምፕ ታወር”!፡፡ ግማሾቹ ባለ 5 ኮከብ ሆቴሎች ሲሆኑ የተቀሩት ለዝነኞች በውድ ዋጋ የሚከራዩ የአፓርትመንት ህንፃዎች ናቸው፡፡(ውድና ቅንጡ ህንፃዎች!) ትራምፕ ያልገቡበት የቢዝነስ ዘርፍ የለም ቢባልም፣ ዋና ዋናዎቹ ላግዠሪ ሪል እስቴት (ትራምፕ ላግዠሪ ሆምስ፣ አፓርትመንት እና ዘመናዊ ኮንዶሚኒየሞች)፣ ትራምፕ ሆቴልስ፣ ትራምፕ ጎልፍ፣ ትራምፕ ዋይነሪ .. እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በነገራችን ላይ ትራምፕ  ዋይት ሀውስ ከገቡ ጊዜ አንስቶ በአሜሪካና በተቀረው ዓለም በስማቸው የተመዘገቡ 500 ገደማ የሚደርሱ ኩባንያዎቻቸውን በኃላፊነት የሚመሩላቸው ሁለት ወንድ ልጆቻቸው እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ አሁን በትራምፕ አውሮፕላን ወደ ጦቢያ ተመልሰናል!፡፡ የፓርቲዎች ድርድርና ድብድብ እንዴት ነው?!

Read 6382 times