Sunday, 05 February 2017 00:00

ማራኪ አንቀፅ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  ብሔርተኝነት፣ ፅንሰ ሐሳቡና መዘዙ

     ብሔርተኝነት ከብሔር ጋር ተጣምሮና ተያይዞ የሚፍታታ አይዲዮሎጂ፣ ስሜትና በሁለቱ ላይ ተመርኩዞ የብሔሩን ዓላማ ለማሳካት የሚደረግ እንቅስቃሴ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያ በላይ ደርዝና ጥልቀት ያለው ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ በቅድሚያ ብሔር የተሰኘውን ግንዛቤ ፍቺና ለፈረንጂኛው አቻ ትርጉም ማግኘቱ ነው ለብዙዎቹ የሚቀለው፡፡ የኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የጆዜፍ እስታሊንን ስመ ጥር ፍቺ ዋና ማጠንጠኛ በማድረግ የተከተለውም ይህንን አቅጣጫ ነው፡፡ እሱም ቀደም ሲል የተጠቀሰውን ብሔር ማለት በታሪክ ሂደት በጋራ ቋንቋ፣ መሬት፣ ኢኮኖሚያዊ ህይወትና በጋራ ባህል (ካልቸር) በሚገለጽ/ በሚንጸባረቅ ስነ ልቦናዊ ቅኝት (Make Up) ላይ የተመሰረተ የተረጋጋ ሕዝብ ነው የሚለው ነው፡፡ በፍቺው ውስጥ ስለተቀመጠው እያንዳንዱ ቃል ብዙ፣ ብዙ ማለት ይቻላል፣ ተብሏልም፡፡ ይህንን ትርጉም እስታሊን አቶ ባወር (1881-1938) ከተባለው የኦስትሪያ የትዮሪ አፍታችና ፖለቲከኛ የተዋሰው ነው የሚሉ አሉ፡፡ ወደ እዚያ አንገባም፡፡
ፅንሰ ሀሳቡን ከበርካታ የእይታ ማዕዘናት ሲመለከቱት፣ ልክ እንደ ማንነት አስቸጋሪ ንባብ ቃል ነው፡፡ በርካታ መጽሐፍትና ድርሳናት እንደሚያመለክቱት፤ በዚያ የታሪክ መጋጠሚያ ላይ ብሔሩ ወይም ስብስብ ማጠንጠኛ አድርጎ አፅንኦት በመስጠት የራሱን ጥቅልል መንግስት ወይም መንግስት አከል አሃድ ለመመስረት ይገባኛል ጥያቄ አስነስቶ፣ የራሴ ወገን የሚላቸውን መቀስቀስ መቻሉ ላይ ነው የቁም ነገሩ እንብርትና አንደርዳሪው ግፊት። ይህ ስሜት፣ አይዲዮሎጂና እንቅስቃሴ ነው በአንድ ላይ ብሄርተኝነት የሚሰኘው፡፡ ዓላማውን ከግቡ ለማድረስ ብሔርተኝነት ከላይ ያመለከትናቸውን የጋርነቶች ሁሉ መቀስቀሻ ሊያደርግ ይችላል፤ ተራ በተራ ወይም ሁሉንም በአንድ ላይ፡፡
ኤትኔሲቲ ማኅበራዊ አደረጃጀት ነው ከተባለ ደግሞ፣ እሱም በተራው ከብሔርተኝነት ጋር ያለውን ተዛምዶና ተያያዥነት መመልከቱ ተገቢ ይሆናል። ልክ እንደ ብሔርተኝነት ኤትኒሲቲም አንድ ዓላማ ግብ ለማስመታት እስከ ተደረጀ ድረስ በሦስቱም የጋራነቶች ቀስቃሽነት በዓላማው ላይ ያነጣጠረ አካሄድ ይከተላል፡፡ ለዓላማው ግብ መምቻ ሌሎች የጋራነቶችንና አላባዎችንም ለመጠቀም ይሞካክራል። ለቅስቀሳውና ለውዝግብ የሚቀርቡት የመፍትሔ ሀሳቦች ግን የተለያዩ መሆናቸው አይቀርም፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ የዘር ፖለቲካ የተሰኘው መስተጋብር ከአጠቃቀሙ አኳያ ሲታይ ይበልጥ ኤትኒሲቲን የሚገልጽ ይመስላል፡፡
ብሔርተኝነትን እንደማንነት ማደራጃ፤ እንደ ስሜት እንደ እንቅስቃሴና እንደ አይዲዮሎጂ ጠልቀን ለመተንተንና ለማፍታታት መሞከሩ የሚያዛልቅ አይሆንም፡፡ ስብስቦችን የሚያፋጥጣቸውና የሚያጋጥማቸው የጋራነትን መመርኮዣ አድርገው በአንድ ርእሰ ጉዳይ ላይ ሳይስማሙ ሲቀሩ (ሲወዛገቡ) ነው ብለናል፡፡ በሌላ አባባል በመሃላቸው የውዝግብ ምክንያት ሲፈጠር ነው፡፡ የውዝግቡ መነሻም በአመዛኙ ብሔርተኝነተ እራሱ ነው፡፡ እሱም በተራው ከብሔራዊ መንግሥታት ምሥረታ ወዲህ የተለያዩ ስብስቦች ተቧድነው የሚሻኮቱበት፣ በአንድ መንግሥት ሥር ተጠቃልለን በአንድነት እንኑር ወይስ እያንዳንዳችን ለየራስ መንግሥት ምሥረታ እውን መሆን በየፊናችን እንንቀሳቀስ በሚለው ርእሰ ጉዳይ ላይ መስማማት ሲያቅታቸው ነው ጠቡ የሚጫረው፣ ከታሪክ መዛግብት እንደታየው፡፡ በዘመነ መንግሥተ ብሔር ምሥረታ የአብዛኛው የውዝግቦች መነሾ ይኸው ብሔርተኝነት ነበር፡፡ ገባ ተብሎ ማፍታታት ሊያስፈልግ ነው፡፡
ብሔርተኝነት ብሔሮች (ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች) የራሳቸውን መንግሥት ለመመሥረት ማንኛውም መብቶች የሚሏቸውን ሁሉ ለማስከበር ወይም ለማስመለስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በሙሉ በዚህ ውስጥ መካተታቸው ሊያነጋግር ይችል ይሆናል። በዚህ መጽሐፍ ይህን የተጠቀምኩት የራስን መንግሥት ለመመሥረት ከሚደረገው ተጋድሎ ጋር በአመዛኙ የተያያዙ ስሜቶችን፣ እንቅስቃሴዎችንና አይዲዮሎጂን እንዲያመለክት ነው፡፡ ከዚህ በታች የሚገኙትን ወይም እንደ ልዕለ ብሔርተኝነት ያሉትን ስሜትም ሆነ አይዲዮሎጂ ወይም እንቅስቃሴ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር አልተካተቱም፡፡
በኋላ ላይ እንደምንመለከተው በኦሮሞ ጥያቄ ዙሪያና ሳቢያ የተቀሰቀሰውን ስሜትና የተቀረፀውን ርዕዮተ ዓለም እንዲሁም መመለሻ ሐሳቦች ብሔርተኝነት ነው ያልኳቸው፡፡ በስልጤና በጀበርቲ የመብት ጥያቄ ሳቢያና ዙሪያ የተቀሰቀሱትን ግን እንደ ትሕተ ብሔርተኝነት ስለተመለከትናቸው ብሔርተኛ አልተባሉም፡፡ ነገር ግን ከወዲሁ ተገቢ ግንዛቤ ማግኘት ያለበት፣ ጉዳዩ መታየት የሚኖርበት ስብስቡ ካነሳው የመብት ጥያቄ አንፃር እንጂ ከእድገት ደረጃው ጋር ምንም ተዛምዶ ወይም ግንኙነት ሊኖረው እንደማይገባ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ በአገራችን የሚገኙ ሁሉም ስብስቦች የእድገት ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን ብሔረሰብ የተሰኘው፣ በተቻለ መጠን፣ የተጋነነ ግምትና ትርጉም እንዳይሰጠው ተብሎ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት አጠቃቀምን በመከተል በማንኛውም የእድገት ደረጃ ላይ ሲገኝ ማንኛውም ስብስብ፣ ብሔረሰብ በሚለው አማካይ ስያሜ እንዲታወቅ መመረጡን የቱን ያህል ችግሩን እንዳቃለለ አናውቅም፡፡
ናሽናሊዝም ወይም ብሔርተኝነት ያንድ ስብስብ አባላት ከየብሔራቸው (ኔሽን) ጋር የፈጠሩት ጠንካራ ቁርኝት ነው ሊባል ይችላል፡፡ ይህ ትስስር አይዲዮሎጂ ሆኖ ከሌሎቹ ተለይተን የራሳችን መንግሥት መመሥረት አለብን ሲሉ ነው፣ ከስሜት አልፎ ከሌሎች ስብስቦች ጋር ወደ መፋጠጥና ግብግብ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚገቡት፡፡ በዚህ መነሻነት ከሌሎች ዓላማቸውን ከሚፃረሩ ወይም የሚፃረሩ ከሚመስሏቸው ጋርም ይጋጫሉ፡፡ ይህ ስሜትና አይዲዮሎጂ ከጥንቱ ከጧቱ የነበረና ወደፊትም የሚኖር ነው ባዮች አሉ፡፡ በእነሱ አመለካከት መሰረቱና መነሻው ደምና የአጥንት የዘር ትውልድ ዝምድና ነው፡፡ ይህንን አመለካከት ነው ፈረንጆቹ The primordialist perspective/ የበኩራዊነት አተያይ ብለው የሚጠሩት፡፡
ሌላው አመለካከት ፈረንጆቹ The modernist perspective/ የዘመነኝነት አተያይ የሚሉት ፍረጃ ነው፡፡ እሱም ብሔርተኝነት ከተወሰነ የማኅበረሰብ አወቃቀር ጋር ተያይዞ በቅርብ ዘመን ብቅ ያለ ክስተት እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱበት አረዳድ ነው። ዋናው ቁም ነገር ግን ስብስቡ በአባላቱ መካከል ባለው የዘር፣ የካልቸር፣ የሃይማኖትና የሌሎች ተዛማጅ የጋራነቶች ምክንያት እያንዳንዱ ብሔረሰብ በራሱ ጠቅልል መንግሥት ሥር መጠቃለል አለበት የሚለውን መሠረተ ሀሳብ የሚያቀነቅን መሆኑ ነው፡፡ በባለብዙ ብሔር አገር ውስጥ የጋራነቶችን የማይጋሩትን ራሳቸውን በራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት አደረጃጀት ይኑር ባዮች በዚህ ውስጥ ይካተቱ ወይስ አይካተቱ የሚለው ደግሞ ራሱን የቻለ ክርክር ነው፡፡ ለጊዜው እዚያ ውስጥ እንገባም፡፡     
ምንጭ፡- (ከደራሲ ዩሱፍ ያሲን ‹‹ኢትዮጰያዊነት፤ አሰባሰቢ ማንነት፤ በአንድ አገር ልጅነት›› የተሰኘ መፅሃፍ
የተቀነጨበ፤ ህዳር 2009)

Read 4184 times