Sunday, 12 February 2017 00:00

አረና፤”መፍትሄው አንድነት መፍጠር ነው” ይላል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

*ከጎንደር ለተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች ተጠያቂው ኢህአዴግ ነው
*እኛ ስንመረጥ “ኤፈርት”ን የፓርቲ ሳይሆን የህዝብ እናደርገዋለን
*ከህወሓት የተሻለ የሰለጠነ ፖለቲካ ማራመድ እንፈልጋለን
*ለወልቃይት ችግር የመጨረሻው አማራጭ ህዝበ ውሳኔ ነው

   የ”መድረክ” ግንባር መስራች የሆነው “አረና ትግራይ ለፍትህና ለሉአላዊነት” ፓርቲ ባለፈው ቅዳሜና እሁድ አራተኛ ጠቅላላ ጉባኤውን
ያካሄደ ሲሆን በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግም የተለያዩ አቋሞችን ወስዷል፡፡ የፓርቲውን አዲስ ሊቀመንበርና
ምክትል ሊቀመንበርም መርጧል፡፡ ፓርቲው በሁለት ቀናቱ ጉባኤ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳዮችን አንስቶ በስፋት መወያየቱን ያብራሩት
አዲሱ የአረና ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ፤ በውይይቶቹና በተደረሰባቸው ውሳኔዎች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር
ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡

የፓርቲያችሁ ጉባኤ በምን ጉዳዮች ላይ ተወያየ? ምንስ አዳዲስ ውሳኔዎችን አሳለፈ?
በመጀመሪያ ትኩረት አድርገን የተወያየነው አሁን በሀገሪቱ ባለው ቀውስ ላይ ነው፡፡ ችግሩ ወዴት ሊያመራ ይችላል? መፍትሄውስ ምንድን ነው? እኛስ በዚህ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ እንዴት ነው መንቀሳቀስ የምንችለው? ሀሳባችንን ለህዝብ እንዴት ነው ማድረስ የምንችለው? በምን አግባብ ነው፣ ህዝብን ከጎናችን አሰልፈን መታገል የምንችለው? በሚሉት ላይ ሰፋፊ ውይይቶች አድርገን፣ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፈናል፡፡ በትግል ህዝብን ከጎን አሰልፎ የስልጣን ባለቤት መሆን፣ ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች መፍትሄ መሆኑንም አስምረንበታል፡፡
በጉባኤያችሁ እንወያይበታለን ካላችሁት አጀንዳ አንዱ የ”ኤፈርት” ጉዳይ ነበር፡፡ ምን አይነት ውይይት አድርጋችሁ፣ምን ውሳኔ አሳለፋችሁ?
በዚህ ጉዳይ ላይ በሚገባ ተወያይተናል።  ህወሓት፤ “ኤፈርት” የህዝብ ነው ቢልም፣ በተግባር የህወሓት የግል ንብረት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል፡፡ እኛ ስንመረጥ በትክክል የህዝብ ንብረትነቱን ለማረጋገጥ፣ በነፃነት ከህዝቡ በሚመረጥ አስተዳደር እንዲመራ ይደረጋል፡፡ ከተቋሙ የሚገኘው ገንዘብም ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ የሚውል ይሆናል፡፡ “ኤፈርት”ን የፓርቲ ሳይሆን የህዝብ እናደርገዋለን፡፡ መንግስት በድርጅቱ ላይ ጣልቃ አይገባም፡፡
ከጎንደር የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆችን ጉዳይም እንወያይበታለን ብላችሁ ነበር? ምን ላይ ደረሳችሁ?
በመጀመሪያ ደረጃ ከጎንደር የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች፣ የተፈናቀሉበትን ምክንያት ገምግመናል፡፡ እነዚህ ሰዎች የተፈናቀሉት ገዥው ፓርቲ በህዝቦች ላይ አፈና በመፈፀሙ፣ ዲሞክራሲ ማስፈን ስለተሳነው፣እንዲሁም  የህዝቦችን ጥያቄ ባለመመለሱ ምክንያት በተነሳ የህዝብ ቁጣ ነው፡፡ ስለዚህ ለመፈናቀላቸው ተጠያቂው ኢህአዴግ ነው። ሁለተኛ ደግሞ በነበረው ሁኔታ ላይ የብአዴንም የህወሓትም እጅ አለበት፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም ተፈናቃዮቹ እርዳታ እየተደረገላቸው አይደለም፡፡ ከህዝብ የተዋጣው ገንዘብ እየተሰጣቸው አይደለም። አሁን ላይ ሁመራ አካባቢ በየቤተክርስቲያኑ ተጠግተው ነው የሚገኙት፣ በገንዘብና በሌላም የሚያግዛቸው አካል አላገኙም፡፡ እነዚህ ዜጎች አስቸኳይ መፍትሄ ማግኘት አለባቸው የሚል አቋም ይዘን፣ “የክልሉ መንግስት የተሰበሰበውን ገንዘብ ሊሰጣቸው ይገባል፣ ዜጎቹ አደጋ ላይ እንዳይወድቁ ድጋፍ የመስጠት ኃላፊነት አለበት” የሚል ማሳሰቢያ እያስተላለፍን ነው፡፡
በተለይ በአማራ ክልል ለተቀሰቀሰው ተቃውሞ መነሻ የነበረው የወልቃይት ጉዳይ ነው፡፡ ፓርቲያችሁ ወልቃይትን በተመለከተ ያደረገው ውይይትና የውሳኔ ሀሳብ ምን ይመስላል?
በመጀመሪያ ያደረግነው በአካባቢው የሚገኙ ሰዎችን አግኝተን ማነጋገርና መረጃ መሰብሰብ ነበር። የወልቃይት ሰዎችን አነጋግረን ጥናት አድርገን አቅርበናል፡፡ የችግሩ መነሻ ምንድን ነው? ውጤቱ ምን ነበረ? በሚለው ላይ ተወያይተናል። ተወላጆቹ እንዳቀረቡት ከሆነ፣”የወልቃይት ህዝብ ትግራይ ነን፣ አማራ ነን” እያለ ውዝግብ ውስጥ የሚገባ ህዝብ አልነበረም፤ በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ የሚኮራ ህዝብ ነበረ፡፡ ነገር ግን በክልሉ አስተዳደር ከፍተኛ አድሎ ይፈፀምበታል፤ ከመሬቱ ይፈናቀላል፤ ለህወሓት ደጋፊ ካድሬዎች መሬቱ ይሰጥበታል፤ በተደጋጋሚም የእኩልነትና የፍትህ ጥያቄያዎች ሲያቀርብ እንደነበርና መፍትሄ ማጣቱን ተወላጆቹ ነግረውናል። ጥያቄ ሲያቀርቡ የክልሉ መንግስት ምላሹ በኃይል የታጀበ መሆኑና ቀና ምላሽ አለመስጠቱ ችግሩን እንዳባባሰው፣ እንዲሁም የክልሉ መንግስት መፍትሄ፣ ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራት ህዝቡን ማስፈራራት መሆኑ የተሳሳተ ነው ብለውናል፡፡ ጥያቄ ያነሱ ሰዎች በክልሉ መንግስት የኃይል እርምጃ ሲወሰድባቸው፣ ወደ አጎራባች አካባቢዎች በመሸሽ፣ የአማራ ክልልን ድጋፍ ጠይቀው፣ ወደ አማራ ክልል መከለል እንደሚፈልጉ በግልፅ መናገራቸውን ተረድተናል፡፡
የብአዴን ሰዎችም “ወደ አማራ ክልል መካለል ከፈለጋችሁ፣ አከላለሉ በብሔር ስለሆነ አማራ ካልሆናችሁ ትቸገራላችሁ” ማለታቸውን ተከትሎ፣ የአማራ ነን ጥያቄ መነሳቱን ነግረውናል፡፡ መጀመሪያ ላይ የነበረው ጥያቄ ማንነት ላይ ያተኮረ አለመሆኑንም ከዚህ ተረድተናል፡፡
ለዚህ ችግር እናንተ ያስቀመጣችሁት መፍትሄ ምንድን ነው?
እኛ መንግስት ሆነን ከተመረጥን፣ ወልቃይት ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ከትግራይ ህዝብ እኩል የሚተዳደርበት፤ ራሱ መፍትሄ የሚያመነጭበት ሁኔታ እንዲፈጠር መደረግ እንዳለበት እንዲሁም የራሳቸውን መሬት በራሳቸው አስተዳዳሪነት መጠቀም የሚችሉበትን ሁኔታ እንደምናመቻችና ችግሩን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደምንችል ነግረናቸዋል። ፓርቲውም የወሰደው አቋም ይኸው ነው፡፡ በዚህ ካልተመለሰ እንኳ ህዝበ ውሳኔ ተደርጎ ህዝቡ ወደፈለገው መካለል እንደሚችል ገልጸንላቸዋል። የወልቃይትን ችግር ለመፍታት በዋናነት ባለቤቶቹ ራሳቸው የወልቃይት ሰዎች እንደሆኑ ተነጋግረናል፡፡
እስከ ህዝበ ውሳኔ የሚያደርስ መፍትሄ ያስፈልጋል ነው የምትሉት? …
በተለያዩ ዲሞክራሲያዊ መንገዶች መፍታት ካልተቻለ ወይም የአስተዳደር መፍትሄ ካልፈታው የመጨረሻው አማራጭ ህዝበ ውሳኔ ነው መሆን ያለበት። በዲሞክራሲ አግባብም የመጨረሻው መፍትሄ ህዝበ ውሳኔ ነው፡፡
የአረና የወደፊት የፖለቲካ አቅጣጫ ወዴት ነው የሚያመራው?
 አላማችን አሁን ክልሉን ከሚመራው ህወሓት፣ በሀሳብ ተሽለን በመገኘት፣ በምርጫ አሸንፈን ስልጣን መያዝ ነው፡፡ እኛ የያዝነው የፖለቲካ ፕሮግራም ለህወሓትም ጭምር የሚጠቅም ነው። ፕሮግራማችን እነሱንም ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርግ ስለሆነ እንደ ተፎካካሪ እንጂ እንደ ጠላት አናያቸውም፡፡ እኛ ከነሱ የተሻለ የሰለጠነ ፖለቲካ ነው ማራመድ የምንፈልገው። ግለሰቦችን ሳይሆን ስርአቱን እንደ ስርአት ነው የምንቃወመው። በዚህ ላይ ተስማምተናል፡፡ በሌላ በኩል አሁን ያለው ሁኔታ የሀገርና የህዝቦችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ፣ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው በስፋት ተወያይተናል፡፡  
ምን ዓይነት መፍትሄ?
የችግሩ መሰረታዊ መነሻ የዲሞክራሲ፣ የፍትህና የነፃነት እጦት ነው፡፡ ህዝቡ እነዚህን በትዕግስት ጠይቆ መልስ ባለማግኘቱ ነው አመፅ የመጣው፡፡ አመፁም “ኦሮሞ መጀመሪያ”፣ “ትግራይ መጀመሪያ”፣ “አማራ መጀመሪያ” ወደሚል አላስፈላጊና ከፋፋይ አካሄድ ነው የገባው፡፡ ስለዚህ ሀገርን የማዳንና የህዝቦችን አንድነት የመጠበቅ ኃላፊነት አለብን። እነዚህን ችግሮች መፍታት የምንችለው ከክልላዊ አስተሳሰብ ወጥተን ሀገር አቀፍ ፓርቲ ስንመሰርት ነው በሚለው ተስማምተናል፡፡ ይህን ስናደርግ በሌሎች አካባቢዎች የራሳችንን ሰዎች ከመመልመል ይልቅ በየአካባቢው ካሉ ፓርቲዎች ጋር ተግባብተን ተስማምተን፣ ፖሊሲያችንን አጣጥመን፣ ውህድ ፓርቲ የምንመሰርትበትን ሁኔታ እናመቻቻለን። ይሄ ካልተሳካ እኛ ራሳችንን ወደ ሀገራዊ ፓርቲ እናሳድጋለን፡፡ ሀገራዊ ፓርቲ የመሆን እቅድ አለን። አሁን ያለውን ስርአት ማሸነፍ የሚቻለው በሀገር ደረጃ አንድ ጠንካራ ውህድ ፓርቲ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ገዥውን ፓርቲ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን አሁን ሀገሪቱን እንደ ሀገር ማቆየት የሚቻው ወደ አንድነት መምጣት ስንችል ነው። የህዝብና የሀገር አንድነት ለመጠበቅ መጀመሪያ የፓርቲ አንድነት ያስፈልጋል፡፡
ተቃዋሚዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር የጀመራችሁት ድርድር ተስፋ ሰጪ ይመስላችኋል?
ድርድሩ ሁለት መልክ አለው፡፡ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ከሀገር አቀፍ ፓርቲ፣ ክልላዊ ፓርቲ ከክልሉ ገዢ ፓርቲ ጋር ነው የሚደራደረው፡፡ ስለዚህ እኛም በቀጥታ ከህወሓት ጋር እንደራደራለን፡፡ እስካሁን ግን የተጀመረ ድርድር የለም፡፡ ጥሪም አልቀረበልንም፡፡ በመድረክ አባልነታችን ግን ከመኢአድና ሰማያዊ ጋር አብረን የመደራደሪያ ሀሳቦች እያቀረብን ነው፤ ድርድሩ ላይ እንሳተፋለን፤ ውጤቱ በኋላ የሚታይ ይሆናል፡፡

Read 1884 times