Sunday, 19 February 2017 00:00

መንግሥት፤ ንግዱ ቀርቶበት በቅጡ ይምራን?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(30 votes)

   - መንግስት ቢዝነስ ውስጥ ሲገባ - እጥረት፣ ወረፋና ኪሳራ አይቀሬ ናቸው
                - የ11 ቢ. ብር የወጣቶች የሥራ ፈጠራ ፈንድ - “በጥናት ነው በድፍረት?”
               - ከኢህአዴግ ጋር በድርድሩ እስከ መጨረሻው ለዘለቀ የ1ሚ.ሽልማት!!
            
     የአሜሪካ አዲሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ … በ7 አገራት ላይ ያሳለፉት ወደ አገሪቱ ያለመግባት ክልከላ፣ በፍ/ቤት መታገዱን ሰማችሁልኝ አይደል? (አሜሪካ ምንጊዜም አሜሪካ ናት!!) ቢሊዬነሩ ትራምፕ ሆኑ፣የሃርቫርድ ምሩቁ ኦባማ … ግራ ዘመሞቹ ዲሞክራቶች ሆኑ፣ ቀኝ ዘመሞቹ ሪፐብሊካን ------ በአሜሪካ አንድ የማይለወጥ ነገር አለ - የህግ የበላይነት!!  (ማንም ከህግ በላይ አይደለም!) አንድ ፕሬዚዳንት ወይም አንድ ገዢ ፓርቲ ስለፈለገ ብቻ ያሻውን ከቶውንም ማድረግ አይችልም፡፡ (የህግ የበላይነት----የህግ የበላይነት ነው!!) መንግስት ወይም ፕሬዚዳንቱ የሚያስፈራሩበት መፈክር አይደለም! (በአሜሪካ ማለቴ ነው!!)
በቅርቡ እዚህች ጎረቤት አገር ኬንያ የሆነውንም ሳትሰሙ አትቀሩም፡፡ የአገሪቱ መንግስት የስደተኞች መጠለያን ለመዝጋት ዳድቶት ነበር፡፡ ታዲያ ማን መለሰው አትሉኝም? የአገሪቱ ከፍተኛ ፍ/ቤት!! የጦቢያንና የኬንያን ልዩነት አያችሁልኝ?! (ቪቫ  የህግ የበላይነት!!) እስቲ በሞቴ------ኢህአዴግ ሊያደርገው ፈልጎ ፍ/ቤት የከለከለውን ወይም ያገደውን አንድ ነገር ጥቀሱልኝ፡፡ አትድከሙ፤ባለፉት 25 ዓመታት ምንም አታገኙም፡፡ መቼም መንግስት በዚህ ማፈር አለበት!! (አያኮራማ!!)
በነገራችን ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢህአዴግ የሚናገራቸው ነገሮች ------ ፈጽሞ “ኢህአዴግ ኢህአዴግ አልሸትህ” እያሉኝ ተቸግሬአለሁ። (የኢህአዴግን “ሽታ” አሳምረን እናውቀዋለን!) ግን እኮ ክፎ ወይም መጥፎ ነገር ተናግሮ አይደለም፡፡ እንደውም ባይገርማችሁ ------ ምርጥና አሪፎች ናቸው፡፡ ክፋቱ ምን መሰላችሁ? ያለመድኩት በመሆኑ፣ተንኮል አስቦ እንዳይሆን እያልኩ፣ በጥርጣሬና በስጋት ኪሎዬ አለቀ፡፡ ለምሳሌ… እኒያ የፈረደባቸው አዲሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤በአሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንን (የ”ሬሚታንስ” ጌቶቻችንን ማለቴ ነው!!) ቢያባርሯቸው ----- “እጄን ዘርግቼ እቀበላቸዋለሁ” ብሏል፡፡ በዚህ የኢህአዴግ የደግነት ምላሽ ተገርሜ ሳላበቃ ምን ቢል ጥሩ ነው? “በትጥቅ ትግል ሲቃወሙን የነበሩ ኢትዮጵያውያንም ጭምር አገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞአቸውን መቀጠል ይችላሉ” አለና አረፈው። (መደነቅም መደንገጥም አቃተኝ!) ቆይ ግን ይሄን አምኜ እንድቀበል ትጠብቃላችሁ? ይሄ ማለት እዚህ በየምክንያቱ የታሰሩ ፖለቲከኞችም ይፈታሉ ማለት እኮ ነው፡፡ (በግልጽ ይነገረና!) እስከዚያ ግን የኢህአዴግ “ደግነት” በበዛ ቁጥር እኔም ጥርጣሬዬ ያይልብኛል፡፡ (አትፍረዱብኝ!)  
አንድ ሌላ ኢህአዴግ ኢህአዴግ የማይሸት ነገር ልጨምርላችሁ፡፡ (ልብ ካላላችሁት ብዬ እኮ ነው!) ከተቃዋሚዎች ጋር የጀመረውን ድርድር አስመልክቶ ------ ምን አለ መሰላችሁ? “ከፀሐይ በታች የማንደራደረው ጉዳይ የለም!!” (እውነት ባይመስልም ደስ ይላል!!) ድሮ እኮ ኢህአዴግ ---- “በመቃብሬ ላይ” (on my dead body!) እያለ ----- ስንቱን ድርድር አክሽፏል መሰላችሁ! (አሁንና ያኔ ምን አገናኛቸው?) በነገራችን ላይ ---- የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊና በጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት የዲሞክራሲ ግንባታ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሰጡት መግለጫም፤ “የምንደራደረውን እንደራደራለን፤ የምንከራከረውን እንከራከራለን” ብለዋል - ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ፡፡ (የ”ጥልቅ ተሃድሶ” ውጤት ይሆናል!) በእርግጥ ሁሉንም የተናገረው በቃሉ ነው (ዲስኩርና ተግባር ለየቅል ናቸው!!)
ኢህአዴግ ኢህአዴግ የማይሸት ሌላም ነገር ገጥሞኛል፡፡ ምን መሰላችሁ? “ኢህአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲ በምርጫ ቢያሸንፉ … አገሪቱን በጋራ የሚያስተዳድሩበትን ሁኔታ የሚደነግግ ረቂቅ ህግ ወጥቷል” አሉ፡፡ ለምሳሌ “አረና” የትግራይ ክልልን ቢያሸንፍና የቀረውን ኢህአዴግ ቢቆጣጠረው ማለት ነው (ወይም አቀያይሩት!) ይሄኔ ኢህአዴጎች፣ “የሰይጣን ጆሮ አይስማው!” እያሉ ነው! (25 ዓመት መች ሰማ?!) አይገርማችሁም ----- ድሮ እኮ ኢህአዴግ “ክንዴን ሳልንተራስ ከተቃዋሚ ጋር ሥልጣን አልጋራም እያለ እምቧ ከረዩ ይል ነበር፡፡ (“በድሮ በሬ ያረሰ የለም” አትሉኝ!)
እኔ የምላችሁ-----ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች እንደ ምንም ለ3ኛ ዙር ድርድር ሊደርሱ ነው አይደል? (ተመስጌን እኮ ነው!!) ያውም እኮ ከ20 በላይ ፓርቲዎች ናቸው የሚደራደሩት - በ3 ቡድን ተከፍለው፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች ግን ብቅ ያሉት ለድርድር አይመስለኝም፤የፋይናንስ ድጋፍ የሚሰጥ መስሏቸው ነው፡፡ ወይም ደግሞ ምርጫ የደረሰ መስሏቸውም ሊሆን ይችላል፡፡ ለድርድርማ ---- መጀመሪያ እኛን ሊያውቁን ይገባል፡፡ (አያውቁን አናውቃቸው!!) እኔ ምርጫ ቦርድን ብሆን ኖሮ፣ ቢያንስ በጣም ለምጠረጥራቸው ፓርቲዎች እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀርብላቸው ነበር፡- “ባለፈው ዓመት “መሬት አንቀጥቅጥ” ህዝባዊ ተቃውሞ የተቀሰቀሰው በየትኛው ክልል ነበር?” (የፓርቲ ብቃት መገምገምያውን “ክርኤቲቭ” ላደርገው ፈልጌ ነው!)
ሌላ ክርኤቲቭ ሃሳብ አለኝ፡፡ ከኢህአዴግ ጋር በተጀመረው ድርድር እስከ መጨረሻ ዘልቀው ከውጤት ላይ ለደረሱ ሁለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ለእያንዳንዳቸው 1ሚ.ብር የመሸለም ሃሳብ አለኝ - በስፖንሰር!! ከ20 ምናምን ፓርቲዎች፣በየፌርማታው ተንጠባጥበው ለውጤት የሚበቁት ከሁለት አይበልጡም ብዬ ነው፡፡ ገና ከጅምሩ ጥቂቶቹ፤ ለድርድር ብቁ አይደለንም ብለው በራሳቸው ጊዜ የሚወጡ ይመስለኛል፡፡ (ምርጫ ቦርድ የቤት ሥራውን በቅጡ የሰራ አይመስለኝም!) በነገራችን ላይ የ1ሚሊዮን ብር ሽልማቱ ገዢውን ፓርቲ አይመለከትም፡፡ (1ሚ. ብር ምን ልትሆነው ነው?) እናላችሁ ---- እነ አውሮፓ ህብረት፣ አፍሪካ ህብረት፣ ኤምባሲዎች፣ እነ ዓለም ባንክ፣ አይኤምኤፍ ወዘተ ---- በድርድሩ መዝለቅ ለቻሉ 2 ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚሰጠውን የ2 ሚ.ብር ሽልማት ተባብረው ስፖንሰር ያደርጉልናል ብዬ አስባለሁ፡፡ የፖለቲካ ቀውሱ በተባባሰ ወቅት፣ መንግስትና ተቃዋሚዎች ውይይትና ድርድር ማድረግ አለባቸው እያሉ ሲወተውቱ አልነበር እንዴ?! ስለዚህ የማበረታቻ ሽልማቱን ስፖንሰር አድርገው ለድርድሩ ስኬት የድርሻቸውን ያዋጡ፡፡ (እነሱም እዚህ የሚኖሩት ሰላም ሲሰፍን ነው!) በነገራችን ላይ አንድም ተሸላሚ ፓርቲ ካልተገኘ፣ የሽልማቱ 2ሚ.ብር ወደ እኔ ገቢ እንደሚሆን ከወዲሁ አስታውቃለሁ፡፡
እኔ የምለው … ለጥልቅ ተሃድሶ እየተባለ ሳምንቱን ሙሉ የመንግስት ቢሮ ከርችሞ መጥፋት ቆመ ወይስ ቀጥሏል? ጥልቅ ተሃድሶው መደረግ ያለበትስ በሥራ ሰዓት ነው እንዴ? ደሞስ ደንበኞች በአገልግሎት ማጣት ከተጉላሉና .. የመንግስት ሥራም ከተበደለ … ምኑን ጥልቅ ተሃድሶ ሆነ? እንደው ግን ጥልቅ ተሃድሶ ስንት ቀን ይፈጃል? (ለጠቅላላ ዕውቀት ያህል ነው!) ወደ ሌላ አጀንዳ እንሻገር፡፡
የህዝብ ጥያቄን ለመመለስ ታስቦ … ይፋ የተደረገውን የ11 ቢ. ብር የወጣቶች የሥራ ፈጠራ ፈንድን እንዴት አያችሁት? (ወጣቶች ብቻ ሳትሆኑ አዋቂዎችም ተሳተፉ!) እርግጠኛ ነኝ --- ብዙዎች በጉጉት እየጠበቁት ነው፡፡ (ሞሳኞችን ጨምሮ ማለት ነው!!) ግን የአዋጭነት ጥናት ተሰርቷል? (እንደ ጦር የምንፈራውን “ፊዚቢሊቲ ስተዲ”ማለቴ ነው) ብድር አሰጣጡስ ምን ያህል ፍትሃዊ ነው? ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ ነው?  በኋላ “ተምረንበታል” የሚል መልስ እንዳይመጣ ከወዲሁ መጠንቀቅ ነው። (ለህዝብ ሀብት እንዘን እንጂ!) በእርግጥ ‹እንዘን› ከመባባልም አልፈን የተጠያቂነት ሥርዓት መዘርጋት የግድ ነው፡፡  
ልማታዊ መንግስታችን አላዳርሰው  ብሎ እንጂ! … በሁሉም የኢኮኖሚና … ቢዝነስ ዘርፍ ውስጥ እጁን ቢያስገባ  ደስታውን አይችለውም (ኢኮኖሚያችን እኮ መንግስት - መር ነው!) ከመሰረታዊ ሸቀጦች ማስመጣትና ማከፋፈል አንስቶ ያልሞከረውና ያልገባበት የንግድ ዘርፍ የለም፡፡ (ዎል ማርትን ይተካል የተባለው “አለ  በጅምላ” የት ገባ?) የልማታዊ መንግስት ባህርይ ነው ብለን እንዳናልፈው እኮ ----- ብዙዎቹ የሚገባባቸው ዘርፎች ውድቀት እንጂ ስኬት ሲያስመዘግቡ አይታዩም፡፡ የስኳርን፣ የዘይትንና የስንዴን ገበያና ስርጭት ተመልከቱልኝ፡፡ የአዲስ አበባን ለዓመታት የዘለቀ የትራንስፖርት እጥረት የምታውቁት ነው፡፡ (ዕድሜ ለታፔላ!) የዳቦ ቤት ወረፋም የደርግን ዘመን አስታዋሻችን ሆኗል (የደርግ ርዝራዦች ሆን ብለው የፈጠሩት ይሆን እንዴ?)
አሁን ደግሞ “የውበት እስረኞች” የተባሉት ሊፋን ታክሲዎችን ታሪፍ በመተመን የትራንስፖርት ዘርፉን፣ የግሉ ሴክተር እንዲሸሸው እያደረገ ነው። እኔ ልማታዊውን የኢህአዴግ መንግስት ብሆን ኖሮ፣ መጀመሪያ የማፈርሰው መ/ቤት የቱ እንደሆነ ታውቃላችሁ? “የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ”ን ነበር፡፡ ለዓመታት የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር አባባሰ እንጂ መፍትሄ አላመጣም፡፡ እና ምን ይሰራል? በነገራችን ላይ መንግስት የግል የኪራይ ቤቶች ታሪፍን የማውጣት ዕቅድ ሁሉ እንዳለው ሰምተናል፡፡ ባለ ጭቃ ቤት 500 ብር፣ የብሎኬት ቤት 1000 ብር … ባኞ ቤት ያለው 2000 ብር፣ እያለ ዋጋ ሊተምን ነው ማለት ነው፡፡ እየገነባን ያለነው የሶሻሊዝም ሥርአት ነው ካፒታሊዝም? ኢህአዴግ ለኢኮኖሚ ፖሊሲውም ጥልቅ ተሃድሶ ያስፈልገዋል!
በነገራችን ላይ ---- ልማታዊ መንግስታችን … በየወረዳው ነዳጅ ማደያ ለመክፈት ዕቅድ አለው ተብሏል፡፡ (ነዳጅም ሊቸረችር?) መቸርቸሩንስ ይቸርችር … መንግስት ከገባበት ግን ያ የምንፈራው እጥረትና ሰልፍ ይከተላል! (ኢህአዴግ በዳቦና በታክሲ ወረፋ ማፈር አለበት!) ለመሆኑ የመዲናዋን የትራንስፖርት እጥረት ይቀርፋል የተባለው የሳይክል ትራንስፖርት የት ገባ? በነገራችን ላይ አንዳንድ የአዲስ አበባ ወጣቶች፣ “ሜዳችንን መልሱልን” የሚል ጥያቄ እያቀረቡ ነው ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ድሮ ኳስ የሚጫወቱበት ሜዳ ለወጣቶች ሁለገብ ህንፃ ቢገነባበትም … አገልግሎት ስለማይሰጥ ነው ሜዳችን ይመለስ ያሉት ተብሏል፡፡ (መንግስት የነካው ነገር … አሉ!) አሜሪካኖች “መንግስት ችግር እንጂ መፍትሄ አይደለም” … የሚሉት ወደው አይደለም፡፡ 

Read 7101 times