Sunday, 26 February 2017 00:00

ለማንጎ በሽታ ፍቱን መድሃኒት ያገኙ ወጣት ተመራማሪዎች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

 ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ ፍራፍሬዎች መካከል አንዱ የሆነው የማንጎ ተክል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወረርሽኝ መልክ በተዛመተ በሽታ ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት ይገኛል፡፡
ከደቡብ ሱዳን እንደመጣ በሚነገረው በዚህ በሽታም የሚደርሰውን ጉዳትና በማንጎ ዛፎች ላይ እየተከሰተ የሚገኘውን በሽታ ለመታደግ የሚያስችል መድኃኒት በሁለት ወጣት ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች ተገኝቷል። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ ከምርምር ሥፍራው በመገኘት ተገኝ ዘለቀና ታደሰ ገ/ኪሮስ የተባሉትን ሁለቱን ወጣት፤ ተመራማሪዎች በአዲሱ ግኝታቸውና በወረርሽኝ መልክ በተከሰተው የማንጎ ዛፍ በሽታ ዙሪያ አነጋግራዋለች፡-
በማንጎ ዛፍ ላይ የተከሰተው አዲሱ በሽታ ምን ይባላል? አመጣጡስ እንዴት ነው?
በማንጎ ላይ የተከሰተው በሽታ አዲስ እንደመሆኑ መጠን፣ ባህርይውንም ሆነ የፈንገሱን አይነት አውቆ፣ ይህ ነው ብሎ መናገሩ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሆኖም እኛ ባደረግነው ምርምር በሽታው በፈንገስ የሚመጣና በንፋስ ከአንዱ ወደ አንዱ የሚሸጋገር መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ ፈንገሱ “ስፖት ታይፕ” ከተባለው ፈንገስ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን የማንጎን ዛፍ ቅጠሎች ለይቶ የሚያጠቃና ከቅጠሉ ወደ ግንዱና ፍሬዎቹ በመሄድ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ በሽታ ነው፡፡
ለዚህ በሽታ መድኃኒት ለማግኘት የሚያስችል ምርምር እንድታርጉ የገፋፋችሁ ምንድነው?
በዚህ በሽታ ላይ ምርምር ለማድረግ የተነሳሳነው አዋሽ መልካሳ ውስጥ ያሉና  ከዚህ ቀደም በምርምር ያገኘናቸውን መድኀኒቶችን የሚያውቁ የምርምር ባለሙያዎች፤ “ለዚህ በሽታ መድኃኒት በማጣታችን ተስፋ ወደ መቁረጡ ተቃርበናል፤ በእናንተ በኩል ማድረግ የምትችሉት ነገር ካለ እስኪ ሞክሩ” የሚል ነገር ነገሩን። ሁኔታው ጊዜ የማይሰጠው አፋጣኝና ፈጣን ምላሽ የሚፈልግ በመሆኑ፣ ነገ ዛሬ እያልን ማጓተት አልፈለግንም። ማንጎ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ተዘዋውረን ሁኔታውን ካየን በኋላ ቀጥታ ወደ ምርምር ስራችን ነው የገባነው፡፡ ከዘጠኝ ወራት አድካሚና እልህ አስጨራሽ ጥረት በኋላ፣ “TT19” የሚል ስያሜ የሰጠነውና በሙከራ አረጋግጠን ሙሉ በሙሉ ፈዋሽነቱን ያረጋገጥነውን መድኃኒት ለማግኘት ችለናል፡፡
በምርምር ጣቢያችሁ ውስጥ በበሽታው የተያዙና መድኃኒቱ ተደርጎላቸው ከበሽታቸው እያገገሙ ያሉ የማንጎ ዛፎች እንዳሉ ተገልጿል። መድኃኒቱን ያገኙት ዛፎች መልሰው በበሽታው እንዳይያዙ መከላከል የሚያስችል ነገር አለ?
አዎ፡፡ በምርምር ያገኘነው መድኃኒት፣ ተክሎቹ ከበሽታቸው እንዲፈወሱ ብቻ ሳይሆን ዳግም በበሽታው እንዳይያዙ ለማድረግ የሚያስችል ነው። አሁን በዚህ የምርምር ስፍራ የሚታዩት የማንጎ ዛፎች መድኃኒቱን ለአንድ ጊዜ ብቻ ሰጥተናቸው/ በርጭት መልክ የሚሰጥ ነው/ የጤንነታቸውን ሁኔታ እየተከታተልንላቸው ነው፡፡ ዛፎቹ ዕለት ተዕለት ከጉዳታቸውና በሽታው ካደረሰባቸው የቃጠሎና የጠባሳ ችግር ሲያገግሙ እያየን ነው፡፡ በበሽታው ተይዘው መድኃኒት ያላገኙ የማንጎ ዛፎች፣ በአቅራቢያቸው ቢገኙም መልሰው በበሽታው አልተያዙም፡፡
በማንጎ ዛፉ ላይ የደረሰው ወረርሽኝ፣ ተክሉን በምን ያህል መጠን የሚጎዳው ነው?
በሽታው በማንጎ ላይ የያዘው ዘመቻ ማንጎን በአጭር ጊዜ እንዲጠፋ የሚያደርግ ነው፡፡ በሽታው አሁን ባለበት ሁኔታ እየቀጠለ የሚሄድ ከሆነ ከሁለትና ሶስት ዓመታት በኋላ ማንጎ በስም ብቻ የምናውቀው ነገር ሆኖ ይቀራል፡፡ ለዚህም ነው ለዚህ ምርምር ሙሉ ጊዜያችንን በመስጠት ለሃያ አራት ሰዓት ሰርተን ውጤታማ የሆነ መድኃኒት ለማግኘት የቻልነው፡፡
በምርምር ያገኛችሁት አዲሱ መድኃኒት በሰው ልጆች ጤና ላይ የሚያስከትለው የጤና ችግር /sideffect/ አለው?
መድኃኒቱ በሰው ልጆች ጤና ላይ ምንም አይነት ችግር የማያደርስ መሆኑን በተደጋጋሚ ሙከራዎች አረጋግጠናል፡፡
የምርምር ውጤታችሁ ዕውቅና እንዲያገኝና ወደህብረተሰቡ እንዲገባና ለችግሩ መፍትሄ እንዲሆን እያደረጋችሁ ያለው ጥረት ምንድነው?
እኛ አሁን ገና የምርምር ውጤታችንን አጠናቀን አስተማማኝ መድኃኒት ማግኘታችንነ ያረጋገጥንበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ቀጣዩን ጉዳይ አሁን በሂደት የምንሄድበት ይሆናል፡፡ ከዚህ ቀደም በምርምር አግኝተን ዕውቅና እንዳገኘንባቸው ሌሎች የምርምር ውጤቶች በዚህም ዕውቅናችንን በቅርቡ እንወስዳለን አሁን ግን የችግሩ ሁኔታ እጅግ አፋጣኝና ጊዜ ሊሰጠው የማይችል በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ መድኃኒቱ በአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች እየተመረተ በተለያዩ አካባቢዎች ባሉና በበሽታው በተጠቁ የማንጎ ዛፎች ላይ እንዲረጭ በማድረግ ማንጎን ከጥፋት መታደግ ነገ ዛሬ የማይባል ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም አካል ሊረባረብ ይገባል። ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግስት መ/ቤቶች ትኩረት ሰጥተውና ተረባርበው ማንጎን ከጥፋት መታደግ ይገባቸዋል፡፡ ይህ አሁን የተገኘው የምርምር ውጤት የእኛ አይደለም የአገር ሀብት ነው፡፡ በራሳችን የገንዘብ አቅም ለዘጠኝ ወራት ያደረግነውን እልህ አስጨራሽ ትግል በውጤት አጠናቀናል፡፡ ይህ የምርምር ውጤት በአስቸኳይ ሥራ ላይ እንዲውልና መድኃኒቱን በስፋት እያመረቱ አደጋ ላይ ያለውን የማንጎ ተክል መታደግ የሁሉም ዜጋ ጉዳይ ሊሆን ይገባል፡፡
በበሽታው የተያዘ የማንጎ ዛፍ ያፈራውን ፍሬ መብላቱ በጤና ላይ ምን ጉዳት ያስከትላል?
በበሽታው የተያዘ ማንጎ መመገቡ በጤና ላይ ሊያስከትል የሚችለውን የጤና ችግር መናገር የሚችሉት የጤና ባለሙያዎች ናቸው። እኛ በበሽታው ላይ ምርምር አድርገን መድኃኒት በማግኘቱ ላይ አተኩረን ነው የሠራነው፡፡
አሁን ካገኛችሁት የማንጎ በሽታ መድኃኒት ሌላ እውቅና ያገኛችሁበት የምርምር ውጤት አላችሁ?
በቲማቲም ላይ የሚወጣና ከጥቅም ውጪ የሚያደርግ በሽታ ገብቶ፣ በሱ ላይ ረዘም ያለ ምርመራ በማድረግ፣ ባክቴሪያና ፈንገሶችን በመግደል፣ ቲማቲምን የሚያድን መድኃኒት አግኝተን የፈጠራ መብት ባለቤትነታችንን ወስደናል፡፡ “ላሽ” እየተባለ የሚጠራውና ፀጉርን በመምለጥ ራስን ባዶ የሚያደርገውን በሽታ መድኃኒት ለማግኘት ረዥም ጥናትና ምርምር አድርገን፣ ሙሉ በሙሉ ፈዋሽ፣ እንዲሁም ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት የሌለው መድኃኒት አግኝተናል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በጫት ላይ የሚረጩ ፀረ አረም ኬሚካሎች ያለባቸውን ምርቶች ለማስቀረት የሚችል፣ ሙሉ በሙሉ ከተክሎች የተሰራ የጫት መድኃኒት በምርምር አግኝተናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለበረሮና ሌሎች ተባዮች ማጥፊያ የሚሆን መድኃኒት አግኝተን ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ጥረት እያደርግን ነው፡፡ በሙከራ ደረጃም እየሰራንበት እንገኛለን፡፤
እነዚህ የምርምር ውጤቶታችሁን ወደ ተግባር ለመለወጥና ህብረተሰቡን ሊጠቅሙ እንዲችሉ ምን ጥረት እያደረጋችሁ ነው?
 የምርምር ውጤቶቹ ወደ ተግባር ሳይለወጡ፣ የሼልፍ ማሞቂያ ሆነው መቅረታቸው ዋጋ የለውም። ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው፡፡ ለዚህም ለሞጆ ከተማ አስተዳደር ጥያቄ አቅርበን፣ በሂደት ላይ ነን፡፡ የምርምርና የፋብሪካ ቦታ ለማቋቋም እቅድ ይዘናል፡፡ ጥያቄያችን ፈጣን ምላሽ ካገኘ፣ ያለቁትን መድኃኒቶች ወደ ምርት በመቀየር ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ዋንኛው ዕቅዳችን ነው፡፡
በዚህ የወጣትነት ዕድሜ ረዥም ጊዜን ለምርምር መስጠት ምን ስሜት ይፈጥራል?
የምርምር ህይወት በጣም ከባድ ነው፡፡ ራስን፣ ቤተሰብንና የምቾት ህይወትን ሁሉ ጥሎ ሁለመናን ለምርምር አሳልፎ መስጠትን ይጠይቃል፡፡ መቁሰል፣ መጎዳት፣ መሞት ሁሉ ሊኖር ይችላል፡፡ ሆኖም አላማ አድርጎ የተነሱለት ጉዳይ ውጤት ሲያገኝ ማየቱ እንዴት ያለ ስሜት እንደሚሰጥ መናገሩ ቀላል አይመስለኝም። እኛ አላማ አድርገን የተነሳንለትና ራሳችንን የሰጠንለት ሙያ ስለሆነ ሁሉንም ነገር በደስታ ነው የምንቀበለው፡፡
የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድነው?
 በምርምር ሥራችን መቀጠል፡፡ ያገኘናቸውን ውጤቶች ህብረተሰቡ እንዲጠቀምበት ማድረግ፣ የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታትና የሚፈለገውን ነገር በአነስተኛ ወጪ ሊያገኝ የሚችልበትን መንገድ መፈለግ … ወደፊት የምናከናውናቸው ዕቅዶቻችን ናቸው፡፡ 

Read 6144 times