Print this page
Sunday, 26 February 2017 00:00

ህዝብ፤ “ንጉስ” መሆኑን አትጠራጠሩ!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(38 votes)

 (የዚህ ዓምድ ወቅታዊ ዓላማ፤ ድንጋይ የመወራወር ባህልን ተረት በማድረግ፣ ሀሳብ የመወራወር ባህልን         ማዳበር ነው!!)

                     ህዝብ፤ “ንጉስ” መሆኑን አትጠራጠሩ!!

                  - ሥራ ለመፍጠር፣ሥራ መንጠቅ … መፍትሄ አይደለም!
                  - መንግስት ሁሌም አገልጋይ ነው፤ ህዝብ ደንበኛ ነው!
                     
    ባለፈው ማክሰኞ ጠዋት ላይ ነው፡፡ ካዛንቺስ በሚገኝ የወንዶች ፀጉር ቤት ውስጥ ነኝ፡፡ ፀጉሬን እየተቆረጥኩ ነበር፡፡ ከገባሁ ጊዜ አንስቶ ቴሌቪዥኑ ላይ አፍጥጫለሁ፡፡ (ኢቢሲ እንዴት ናፍቆኝ ነበር!!) በተለያዩ ምክንያቶች ከሁለት ወር በላይ ከኢቢሲ ጋር አልተያየንም፡፡ ጸጉሬን እየተቆረጥኩ የኢቢሲ ናፍቆቴን እወጣለሁ ብዬ ነበር፡፡ ችግሩ ግን ወዲያው በጣቢያው እየተላለፈ በነበረ አንድ “ልማታዊ ዘገባ” ወዲያው መጨስ ጀመርኩ። (“ወደሽ ከተደፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ!” ትዝ አለኝና መለስ አልኩ!) በተፈጥሮዬ ልማት የምወድ ሰው ነኝ፡፡ ልማት በኢቢሲ ግን አይመቸኝም፡፡ ልማቱና ፕሮፓጋንዳው አይመጣጠንም፡፡ (“I don’t buy it!” አለ ፈረንጅ!)
እኔ የኢህአዴግ ሃላፊ ብሆን ------ ካድሬዎች እንዳሻቸው በቴሌቪዥን እንዲዘባርቁ ጨርሶ አልፈቅድም ነበር፡፡ (የፓርቲውን ገጽታ ያበላሻሉ!) እናላችሁ -----  ለጋዜጠኛ ቃለ-ምልልስ መስጠት ካለባቸውም በቅጡ ተዘጋጅተው መሆን አለበት፡፡ የሚናገሩትን ቀድመው እንደ ተውኔት እንዲያጠኑት (Rehearsal) እፈልጋለሁ፡፡ 20 ኪሎ የልማት ወሬ ላይ 80 ኪሎ ፕሮፓጋንዳ መሞጀር ተዓማኒነት ያሳጣል፡፡ (ፕሮፓጋንዳ ወጥ ውስጥ እንደሚጨመር ጨው መመጠን አለበት!!) በተለይ በዚህ የዝምታ ድባብ ባረበበበት ወቅት ተናግረው የሚያሳምኑ ትንታጎች እንጂ አሰልቺ ካድሬዎችን ወደ ሚዲያ አላቀርብም - እኔ የኢህአዴግ ሃላፊ ብሆን፡፡ (“If I were a boy” አለች ቢዮንሴ!)
ወደ ጸጉር ቤቱ ልመልሳችሁ፡፡ ጸጉሬን እየተቆረጥኩ ------ ፊት ለፊቴ የተከፈተውን ቴሌቪዥን ስመለከት ነበር ብያችኋለሁ፡፡ ምንድን ነው የምትመለከተው አትሉኝም? መቼም “የንስር ዓይን”፣ “የውበት እስረኞች”፣ “ልጅቷ”፣ “ኩዚ ኩኒ” ---- ወዘተ የሚሉ ፊልሞች አትጠብቁም፡፡ ጣቢያው ቃና ሳይሆን ኢቢሲ እኮ ነው፡፡ እናላችሁ ----- የምመለከተው በልማታዊ ጋዜጠኛ ተከሽኖ የተሰናዳ ልማታዊ ዘገባ ነበር፡፡ (ግን ፕሮፓጋንዳ ተሞጅሮበታል!) በነገራችን ላይ ኢቢሲ እንደ እነ አዲስ ዘመን ጥልቅ ተሃድሶ ያደረገ አይመስለኝም። የጥልቅ ተሃድሶ ውጤቱ እኮ ----- ጥልቅ ለውጥ ነው፤ አፍራሽ ሳይሆን ገንቢ!! (ኢቢሲ ጋ ሁለቱም የሉም!) እንደ አሸን እየፈሉ ከሚመስሉት አዳዲስ የቴሊቪዥን ጣቢያዎች ጋር ለመፎካከር የተዘጋጀ አይመስልም - ልማታዊው የቴሌቪዥን ጣቢያችን።  (በየዓመቱ ቢያንስ 10 አዳዲስ ጣቢያዎች ጠብቁ!)
ወደ ጉዳያችን እንመለስ፡፡ የኢቢሲ ዘገባ ስለ ፐብሊክ ትራንስፖርት ነበር፡፡(ስለ ቢሾፍቱ ባሶች ማለት ነው!) የጋዜጠኛው አቀራረብ ግን የክ/ዘመኑ ታላቅ የምርምር ግኝት አስመስሎት ነበር። በመዲናዋ እየተባባሰ የመጣውን የትራንስፖርት እጥረትና ሰልፍ ተከትሎ ቢያንስ ለራሱ የመንግስት ሰራተኞች አገልግሎት ለመስጠት - ጠዋት ወደ ሥራ ለማድረስና ማታ ወደ ቤት ለመመለስ ታስቦ የተጀመረ ይመስለኛል - ፐብሊክ ትራንስፖርት፡፡ በኢቢሲ ሲናገሩ ያየኋቸው ሃላፊዎች ግን የአገሪቱ ሜጋ ፕሮጀክት አስመስለው ነው ያቀረቡት፡፡ (ይሆን እንዴ?)
የመንግስት ሰራተኞች ወደ ሥራ እያረፈዱ በሚገቡበት ወቅት የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳይባባስ ለመከላከል ፐብሊክ ትራንስፖርት መጀመሩን አንድ ኃላፊ ለኢቢሲ አስረድተዋል፡፡ (ቢሆንማ በማን ዕድላችን!) እኛ እስከምናውቀው ድረስ ግን ፐብሊክ ትራንስፖርት የመጣበት ዋና ምክንያት ሌላ ሳይሆን የአዲስ አበባ የትራንስፖርት እጥረት ለዓመታት መፍትሄ በማጣቱ ነው፡፡ (ጠዋትና ማታ የቬኔዝዌላን የራሽን ወረፋ ነበር የሚመስለው!) እኔ የምለው ግን ----- ለመዲናዋ የትራንስፖርት እጥረት ተጠያቂው ማነው? የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮም አያውቀው!! አንዳንድ ምሽት ላይ በኢቢሲ ብቅ ብለው የመዲናዋን የትራስፖርት ችግርና መንስኤ የሚተነትኑ የሚመስሉትን የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ጨርሶ እንዳታምኗቸው፡፡ ለነገሩ ጆሮ ሰጥታችሁ ከሰማችኋቸው በንዴት ቲቪያችሁን ሰብራችሁ ልትተኙ ሁሉ ትችላላችሁ፡፡ ሙልጭ አድርገው የሚሰድቡት እኮ እኛኑ ነው፡፡ (ቤታችን ድረስ በኢቢሲ እየመጡ!) አዎ … እናንተን … እኔን. .. በአጠቃላይ መኪና የለሹን የትራንስፖርት ተጠቃሚ ----- ሞልጨው ይሄዳሉ፡፡ ምክንያታቸው ሁለት ነው፡፡ አንደኛው፤ “ህዝቡ ጠዋት በተመሳሳይ ሰዓት ከቤቱ እየወጣ እጥረቱንና ወረፋውን አባብሶታል” የሚል ነው፡፡ (“ሆን ብሎ” ማለት ብቻ ነው የቀራቸው!) ሁለተኛው፤ “ህብረተሰቡ በቢሾፍቱ ባስ የመሳፈር ፍላጎት የለውም” የሚል ጥናት ላይ ያልተመሰረተ ነገር ፍለጋ ነው፡፡ እናም ጆሮም ልብም ንፈጓቸው፡፡
የኢቢሲን ልማታዊ ዘገባ አልጨረስንም፡፡ እናም በትራንስፖርት እጥረት ተንገላተው የተበሳጩ ሰራተኞች፤ ስራቸውን በደስታ አያከናውኑም። ሥራቸውን ደስ ብሏቸው ካልሰሩ ደግሞ ልማታዊውን ህዝብ … በቅጡ  አያስተናግዱም፡፡ ስለዚህ ፐብሊክ ትራንስፖርት አስፈለገ፡፡ … ይለናል፤ የኃላፊው ማብራሪያ፡፡ … እኛ ግን የምናውቀው … የትራንስፖርት ችግሩ እየተባባሰ ሲመጣ፣ ጠዋት ሥራ የሚገባ ሰራተኛ በመጥፋቱ የተዘየደ መላ መሆኑን ነው፡፡ (የሥራ ሰዓት መግቢያ እኮ ከረፋዱ 4 ሰዓት ግድም ሆኖ ነበር!) በነገራችን ላይ ለአፍሪካ መዲና፣ የትራንስፖርት ችግር መባባስ ተጠያቂው ማነው የሚለው ጉዳይ ትልቅ የቅሌት ታሪክ ወይም ዘገባ ይወጣዋል፡፡ (አዲስ አበባን ወክሎ ፓርላማ የገባ የለም እንዴ?)
ፐብሊክ ትራንስፖርቱ የመጣው … “በፖለቲካ ውሳኔ” መሆኑን ሲናገሩም ሰምተናል- በዘገባው። የፐብሊክ ትራስፖርትን አደረጃጀት በተመለከተ ደግሞ በተለይ አንዲት የካድሬ ድምፀት ያላቸው ኃላፊ የሰጡት ማብራሪያ ከሁሉም የበለጠ ተመችቶኛል (ፕሮፓጋንዳ ቢበዛውም ቋንቋቸውን ወድጀዋለሁ!) የፐብሊክ ትራንስፖርቱ ሹፌሮች (በእነሱ ቋንቋ ‹ካፒቴኖች›) የአገልግሎት ተጠቃሚውን (የመንግስት ሠራተኛውን ማለት ነው!) ሳያመናጭቁ፣(“ደንበኛ ንጉስ ነው” በሚል መርህ!) እንዲያስተናግዱ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል ተብሏል፡፡ “የምንሰራው ለአገራችን ነው፤ መኪናው የራሳችን ነው” (“አድርጎት ነው” እንዳይሉ!) - በሚል መንፈስ እንዲሰሩ … አስፈላጊው ሥልጠና እንደተሰጣቸው … የአመለካከት ለውጥ ለመፍጠር መሰራቱንም .. ኃላፊዋ በተቀላጠፈ የካድሬ ቋንቋ ተናግረዋል፡፡ የውጤታማነት መለኪያዎች … እነ ቢፒአር፣ ካይዘን እና ሌሎች መተግበራቸውንም አብራርተዋል፡፡
ከዚህ በተረፈ ደግሞ … በ1ለ5 ተጠርንፈው እርስ በርስ ይገማገማሉ ተብሏል - ካፒቴኖቹ፡፡ እንግዲህ ለፐብሊክ ትራንስፖርት ካፒቴኖቹ ቢሰራም ባይሰራም … “ደንበኛ ንጉስ ነው!” በሚል መርህ ደንበኞችን እንዲያስተናግዱ መደረጉን በፕሮፓጋንዳ በታጀበው የEBC ዘገባ ሰምተናል፡፡ ግን እኮ “ደንበኛ ንጉስ ነው!” ወይም “የምሰራው ለአገሬ ነው”፤ ወይም “ለልማቱ ነው” ወዘተ --- በሚል ብቻ … የአዳም ዘር ተግቶ ይሰራል ማለት የዋህነት ነው፡፡ ይልቅስ የሚያተጋው - የሚያበረታታው - ኢንሴንቲቭ - ቢታሰብለት ለራሱ ብሎ የሚጠበቅበትን ያሟላ ነበር፡፡ ኃላፊዋ የጠቀሱት የልማታዊነትም ሆነ የአገር ፍቅር ስሜት ---- በግድ  አይመጣም!! (ያውም በአንድ ጀንበር!)
እኔ የምለው ------ መንግስት፤“ደንበኛ ንጉስ ነው! በሚለው የቢዝነስ መርህ ቢመራን ብዙ ነገሮች አይለወጡም ትላላችሁ? (“ጮማ ሃሳብ” ይመስላል!) ታዲያ ንጉስነቱን ከልቡ ማመን አለበት፡፡ ለነገሩ በደንብ … ስታስቡት እኮ፣ ህዝብ የምርም “ንጉስ” ነው!! (መንግስት ንጉስ የነበረበት ዘመን አልፏል!) ይሄ ማለት ግን ራሳቸውን እንደ ንጉስ  የሚቆጥሩ ወይም እንዲቆጠሩ የሚፈልጉ መንግስታት ------ በተለይ በምስኪኗ አፍሪካ የሉም ማለት አይደለም። በሰለጠነው የ21ኛው ክ/ዘመን ውስጥ ብንኖርም፣ እንደ 17ኛው ክ/ዘመን የሚያስቡ ሞልተዋል፡፡ መብታቸው ነው፡፡ እኛ ግን እንደ ዘመኑ እናስብ፤እንደ ዘመኑ እንሁን፡፡  እናም ህዝብ ንጉስ ነው!! መንግስት አገልጋይ ነው!! ይሄንን እውነታ ለዛሬዎቹም ሆነ ለነገዎቹ መንግስታት ደጋግመን እንንገራቸው!! (ለኢህአዴግና ለተቃዋሚዎች ማለቴ ነው፡፡)  
የቢዝነስ ደንበኛ … በአገልግሎት አሰጣጥ ቅር ሲሰኝና እርካታ ሲያጣ ምን ያደርግ መሰላችሁ? … አኩርፎ ይቀርና የተሻለ አገልግሎት ፍለጋ ሌላ ቦታ ያማትራል፡፡ ይኼን ጊዜ ማን ይጎዳል ብትሉ …? አገልጋዩ ነው፡፡ ደንበኛው ወይም “ንጉሱ” ፈፅሞ ሊሆን አይችልም፡፡ እሱማ ገንዘቡን ይጭነቀው! … ከመንገድ ተቀብሎ በእንክብካቤ እንደ ልቡ የሚያስተናግደውን ያገኛል፡፡ አገልግሎት ሰጪው ግን አንድ ደንበኛ  እንደ ዘበት ያጣል፡፡ አንድ “ንጉስ” ማጣት የሚያስከትለውን ጉዳት ደግሞ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ (“ደሞዝ የሚከፍለው እኮ ድርጅቱ ሳይሆን ደንበኛው ነው!!)
ህዝብ በመንግስት አገልግሎት ወይም አያያዝ አሊያም ደግሞ መስተንግዶ ቅር የተሰኘ ጊዜስ? እንደዚያኛው በኩርፊያ ብቻ የሚቀር እንዳይመስላችሁ፡፡ በርግጥ ከማኩረፉ በፊት ብዙ ይታገሳል፡፡ ብዙ ይችላል! (ሀበሻ እኮ ቻይ ነው!) የባሰ ዕለት ግን አይጣል ነው፡፡ ዱብዕዳ ነው!! እኔ የምለው ግን .. ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የህዝብን  ‹‹ንጉስነት›› ከልባቸው ያምኑበታል? ወይስ አሁንም እንደ ጥንቱ ‹‹ንጉሶቹ›› እኛው ነን ባይ ናቸው? (በህዝብ ሥልጣን?!)
በነገራችን ላይ ንጉስና አገልጋይ ስንል … የበላይና የበታች፣ የተመሪነትና የመሪነት ጉዳይ ሳይሆን… የአገልጋይና የደንበኛ ግንኙነት ማለት ነው!! (ደንበኛ ደግሞ ‹‹ንጉስ›› ነው!) ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? በእኛ አገር ለአያሌ ዓመታት … ‹‹ጭቁኑ ህዝብ›› እያሉ መጥራት … በእጅጉ ስለተለመደ (ማቆላመጣቸው ይሆን?!) ‹‹ንጉስ ህዝብ›› ብለን ለመጥራት እንቸገር ይሆናል፡፡ ዋናው ግን በመርህ ደረጃ መቀበሉ ነው፡፡ ቀስ እያለ መስረጹ አይቀርም።  
(“ዲሞክራሲ ሂደት ነው” እየተባለ 25 ዓመት አለፈው አይደል?!) እግረ መንገዳችንንም … ‹‹ደንበኛ ሁልጊዜ ትክክል ነው›› (The Customer is Always Right) የሚለውን ልብ እንበል! እኛና መንግስት … የደንበኛና የአገልጋይ ግንኙነት (ብቻ) ቢኖረን… ብዙ ነገሮች እንደሚለወጡ ገመትኩ! (ፓርቲዎች በድርድሩ ላይ ቢያነሱት አይከፋም!)
በቀጥታ ወደ ሌላ አጀንዳ እንለፍ (ድርድር አስመሰልኩት አይደል?!) የኦሮሚያ ክልል … 1.2 ሚሊዮን ለሚደርሱ የኦሮሚያ ሥራ አጥ ወጣቶች … የሥራ ዕድል ለመፍጠር እያደረገ ያለው ትጋት በእጅጉ የሚደነቅ ነው፡፡ (እንደውም ዘግይቷል!) ግን የሚያሳስበው ምን መሰላችሁ? ሥራውን ለመፍጠር ያሰበበት መንገድ ነው፡፡ ክልሉ ማዕድን ማውጫ ጉድጓዶችን … ከኢንቨስተሮች እየቀማ ለወጣቶች ያከፋፍላል ተብሏል (“ዲዛስተር” - አለ ፈረንጅ!) ከዚሁ ጋር በተያያዘ… “ደርባ ሲሚንቶ” ፋብሪካ ባለፈው ሳምንት … ምርት አቁሞ ነበር፡፡ (ክልሉ የመንጠቅን ተሞክሮ ከየት ኮረጀው?)
ትንሽ ጥናትና የፈጠራ ሃሳብ ቢኖር እኮ … ኢንቨስተሮቹ ሳይነኩ … ለወጣቶቹም የሥራ እድል መፍጠር ይቻል ነበር፡፡ ችግሩ አንገብጋቢና ፈጣን ምላሽ የሚፈልግ መሆኑ አላጣሁትም፡፡ በቅጡ ያልታሰበበትና ያልተጠና መፍትሄ ደግሞ ዘላቂነቱ አያስተማምንም!! (‹‹ሥራ ለመፍጠር ሥራ መንጠቅ›› የባሰ ችግር መፍጠር ነው!!) አያችሁልኝ… ችግሮች እስኪከማቹና ተራራ እስኪያህሉ ድረስ ቁጭ ብሎ መጠበቅ ውጤቱ ይሄው ነው፡፡ መቼም ይሄ ሁሉ ሥራ እጥ ወጣት በአንድ ጀንበር አልተፈጠረም፡፡ ወዳጆቼ፤ ህዝብ “ጭቁን” ሳይሆን “ንጉስ” መሆኑን እንዳትዘነጉብኝ!! ሰናይ ሳምንት!!

Read 7031 times