Saturday, 17 March 2012 10:56

ሜሲ የኳስ ንጉስ ወይንስ መሲህ?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

ሊዮኔል ሜሲ የዓለም እግር ኳስ ንጉስ ወይንስ መሲህ  በሚል አጀንዳ ከፍተኛ ክርክር እየተፈጠረ ነው፡፡ ገና በ24 ዓመቱ በአዳዲስ ታሪኮችና የውጤት ሪኮርዶች ስሙ በመጠቀስ ላይ የሚገኘው ሊዮኔል ሜሲ ከስፖርቱ የምንጊዜም ምርጦች ፔሌና ማራዶና ጋር መነፃፀሩም ቀጥሏል፡፡ከሳምንት በፊት ባርሴሎና የጀርመኑን ክለብ ባየር ሌቨርኩዘን 7ለ1 ባሸነፈበት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ 5 ጐሎች በማግባቱ የተቀሰቀሰ አጀንዳ ነው፡፡ አንዳንድ መረጃዎች ተጨዋቹን የምንጊዜም ምርጥ ተብሎ ከፔሌና ከማራዶና በላይ ንጉስ መሆኑን ሲገልፁ  ሌሎች ደግሞ ገና ብዙ ታሪኮችና ሪኮርዶችን ለማስመዝገብ ስለሚችል የስፖርቱ  መሲህ ነው ይላሉ፡፡

“የሜሲን ምርጥነት ቁጥሮችም ይመሰክራሉ፣ ወደፊት 6 ሊያገባም ይችላል” ያለው የባርሴሎና አሰልጣኝ ፔፔ ጋር ዲዮላ ነው፡፡ የቡድን አጋሩ ዣቪ ኸርናንዴዝ በበኩሉ  ‹ወደፊት  የምንጊዜም ምርጥ የእግር ኳስ ተጨዋች መሆኑ አይቀርም” ብሎ ተናግሯል፡፡ ‹ሜሲ ልዩ ተጨዋች ነው፡፡ በአጨዋወቱ  በውስጡ ያለውን ልጅነት አለ፡፡ ህልሙን እውን እያደረገ ነው፡፡ የዛሬ ብቻ አይደለም የነገም ታላቅ ተጨዋች ነው› ብሎ ያደነቀው ፈረንሳዊው የቀድሞ የማን ዩናይትድ ተጨዋች ኤሪክ ካንቶና ሲሆን ‹እንደ ማራዶናባለልዩ ተስጥኦ ነው፡፡ እንደ ቦቢ ቻርልተን የሚከበር ስብዕናም አለው፡፡› በማለት ጀርመናዊው ፍራንስ ቤከን ባወር አወድሶታል፡፡

ከወር በፊት ፔሌ  ሜሲ “ካንተ ይሻላል ወይ” ተብሎ ተጠይቆ ነበር፡፡ ፔሌ በሰጠው ምላሽ “ለመናገር ያስቸግራል 1283 ጐሎችን እንደእኔ ያግባና ሦስት የዓለም ዋንጫዎችን ሲወስድ ጥያቄው ያኔ ይመለሳል ብሏል፡፡ ሊዮኔል ሜሲ  የእግር ኳስ ዘመኑ ሊያበቃ ቢያንስ 10 የውድድር ዘመናት መቅረታቸውን በመጥቀስ ከፔሌና ከማራዶና የሚልቅበት ደረጃ ወደፊት ይመጣልም ተብሏል፡፡ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ከአርጀንቲና ጋር የዓለም ዋንጫ ድልን ካሳካ  ማራዶናን ሙሉ ለሙሉ ሊበልጠው ነው፡፡ እንደ ፔሌ 3 የዓለም ዋንጫ ድል ማጣጣምና ከ1000 ጎል በላይ ማስቆጠር ግን ሊርቀው ይችላል፡፡ በክለብ ደረጃ በርካታ አዳዲስ ክብረወሰኖችን በማስመዝገብ ከቀጠለ ከፔሌም ሆነ ማራዶና የተሻለ ታሪክና ውጤት ይዞ  የምንጊዜም ምርጥ የእግር ኳስ ተጨዋች መሆኑ አይቀርም፡፡

አጨዋወቱ ከሮናልዶ ሲነፃፀር

በባርሴሎና የኳስ ቁጥጥር የሜሲ ሚና 80 በመቶ ነው፡፡ ሮናልዶ  በማድሪድ እንቅስቃሴ 60 በመቶ ድርሻ አለው፡፡

ሜሲ በአጭር ርቀት ፍጥነት በመጨመር ከሮናልዶ ይሻላል፡፡ በ5 ሜትር ተንደርድሮ ፍጥነቱን 20 ኪ ሜ በሰዓት ማድረግ ይችላል፡፡ የሮናልዶ 18 ኪሎ ሜትር በሰዓት ነው፡፡ በረጅም ርቀት ፍጥነት በመጨመር ደግሞ ሮናልዶ ይሻላል፡፡ ከ12 እሰከ 16 ሜትር ተንደርድሮ ሮናልዶ 30 ኪሎሜትር በሰዓት ሲፈጥን የሜሲ 28 ኪሎሜትር በሰዓት ነው፡፡

ከቆመ ኳስ በሮናልዶ ምት የኳሷ ፍጥነት 119 ኪሎሜትር በሰዓት ሲሆን የሜሲ  95 ኪሎሜትር በሰዓት ነው፡፡

ገቢውና የዋጋ ግምቱ

ሜሲ ባለፈው ዓመት በእግር ኳስ 31 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ በማካበት አንደኛ ደረጃ ነበረው፡፡  በደሞዝ 10 ሚሊዮን ዮሮ በተለያዩ የስፖንሰርሺፕ እና የንግድ ገቢዎች 21 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ አግኝቷል፡፡ ዘንድሮ የዓመት ደሞዙ ከቦነስ ክፍያዎች ወደ 11 ሚሊዮን ዩሮ ያደገለት ሲሆን የስፖንሰርሺፕ እና የንግድ ገቢው ከ25 ሚሊዮን ዶላር አልፏል፡፡ ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢውም 40 ሚሊዮን ዶላር እየተገመተ ነው፡፡ ሜሲ በካታላኑ ክለብ ባርሴሎና እስከ 2016 እኤአ የሚቆይበት የኮንትራት ውል አለው፡፡ ይህን ውል አፍርሶ ሊገዛው የፈለገ ክለብ የተሳካ ዝውውር ለማድረግ 250 ሚሊዮን ዩሮ ወጭ ማድረግ አለበት፡፡ ሊዮኔል ሜሲ ለገበያ ቢቀርብ የዋጋ ግምቱ ከ140 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ይሆናል በሚል ተሰልቷል፡፡

የያዛቸውና የሚይዛቸው ክብረወሰኖች

በሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ በአንድ ጨዋታ 5 ሎች በማግባት የመጀመሪያው ነው፡፡

በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አግቢዎች  ደረጃው መሪ ለመሆን የቀረው 13 ጎሎች ናቸው፡፡ ደረጃውን በ71 ጐሎች የሚመራው ራውል ሲሆን ቫንኒስተልሮይ በ54፣ ቲዬሪ ሆንሪ በ51 ተከታታይ ይዘዋል፡፡ ሜሲ በ49 ጎሎች  4ኛ ላይ ነው፡፡

በዓለም ኮከብ ተጨዋችነት ለ3 ጊዜያት ወርቅ ኳስ በመሸለም ከፕላቲኒ፣ ክሩፍ እና ቫንባስተን ጋር ክብረወሰን ተጋርቷል፡፡ በ2012 ለ4ኛ ጊዜ ከተሸለመ ደግሞ ብቸኛው ተጨዋች ይሆናል፡፡

ባለፉት 3 ተከታታይ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮች ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ መጨረሱም ይታወሳል ፡፡ዘንድሮም በ12 ጐሎች ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ሲሆን በአንደኛነት ከጨረሰ በተከታታይ 4 የሻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ዘመናት ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን  ብቸኛ ተጨዋች ይሆናል፡፡

በሻምፒዮንስ ሊጉ 1 ተጨማሪ ጎል ሲያገባ በአንድ የውድድር ዘመን ከፍተኛውን የጎል ብዛት ያስመዘገበ ተጨዋች ይሆናል፡፡

በውድድር ዘመኑ ከቀሩት ከ18 እስከ 21 የሚደርሱ ጨዋታዎች 7 ተጨማሪ ጎሎች ካስመዘገበ በባርሴሎና ክለብ ታሪክ ከፍተኛውን የጎል ብዛት ያስመዘገበ ተጨዋች ይሆናል፡፡ ሜሲ በባርሴሎና በ311 ጨዋታዎች 228 ጎል አለው፡፡ ሴዛር ሮደሪጌዝ የተባለ የቀድሞው የክለቡ ተጨዋች በ235 ጎሎች ክብረወሰኑን እንደያዘ ነው፡፡

 

 

Read 10443 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 11:33