Print this page
Saturday, 11 March 2017 12:53

መጫወቻ ፍለጋ

Written by 
Rate this item
(12 votes)

የሠፈር ልጆች ቅዳሜ-ቅዳሜ መጫወቻ ፍለጋ ዙረት እንሔድ ነበር፡፡ ብዙውን ጊዜ ምርጫችን ፈረንጆች ቤት ጓሮ ማንጎዳጎድ ነበር፡፡ ፈረንጆቹ ከቤታቸው አጥር ግቢ ውጪ ጉድጓድ ቆፍረው ቆሻሻውን እዚያ ይጥሉታል፡፡ ዘበኞቻቸውም ጠቃሚ የሆነውን ዕቃ ይቃርማሉ፡፡ በተቀረው ላይ እሳት ለኩሰው ይለቁበታል፡፡ አንዳንዴ ከመቃጠሉ በፊት ደርሰን ደጋግ ዘበኞች ካጋጠመን ደስ ያለንን ዕቃ እንወስዳለን፡፡ ግን ብዙውን ጊዜ የሚያጋጥሙን እርጉም ዘበኞች ስለነበሩ ያባርሩናል፡፡ ሸሽተን ከሌላ ቪላ ቤት ጓሮ ፍለጋችንን እናጧጡፋለን፡፡
ከዕለታቱ በአንዱ ቀን ብትንትኗ የወጣ አሻንጉሊት አገኘን፡፡ ቀጢሳው ከትከሻዋ እስከ ዳሌዋ ያለው የአሻንጉሊቷን አካል ሲያገኝ “ባትጋሩኝ! በትኩስ እንጀራ በመርፌ ቀዳዳ!” ብሎ ጮኸ፡፡
አሻንጉሊቷ ጭንቅላት፣ እጅና እግር እንደሌላት ካስተዋለ በኋላ “በእናታችሁ ልጆች! የተቀረውን አካሏን ካገኛችሁት ትሰጡኛላችሁ? የአሻንጉሊቷ ሙሉ አካል ከተገኘ ልብስ ሰፍተንላት ሁላችንም እንጫወትባታለን፡፡” አለ ቀጢሳው እየተለማመጠን።
ብዙም ሳይቆይ ኃይሉ ዶሮ “ባትጌ!” አለና ጮኸ። የአሻንጉሊትዋን እጆች ሽቅብ እንደ ዋንጫ ሰቅሎ እያሳየን፡፡
“ለቀጢሳው ስጠው!” እያልን ሁላችንም ለመነው፡፡ ሰጠው፡፡
“ዶሮ ደግ ልጅ ነው” አልን ሁላችንም፣ ቆሻሻውን ማገለባበጡን እየቀጠልን፡፡
የቆሻሻው ትንፋግ አይነሳ! አዋቂን ሰው ከአገር ያስለቅቃል፡፡ እኛ ግን መጫወቻው በልጦብን ያንን ክርፋት የልጅነት አፍንጫችን ችሎታል፡፡
ከጥቅም ውጭ የሆኑ የሕክምና ዕቃዎች፣ የምግብ ማሸጊያ ፓኮዎች፣ ቆርቆሮዎች፣ አርተፊሻል ፀጉር፣ የፀጉር ማስያዣ፣ ካርቶኖች፣ ፊኛዎች አገኘን። ፊኛውን እየተቀባበልን ነፋነውና ተጫወትንበት፡፡ (በበኋለኛው የሕይወት ዘመኔ ፊኛ እያልን ስንነፋው የነበረው ኮንዶም እንደነበረ ተገንዝቤያለሁ፡፡)
እዚያው ትንፋጉ ላይ ሆነን አስቂኝ ትዕይንት እየሰራን ያንን መራር ሕይወት እናጣፍጠው ነበር፡፡ ቀጢሳው ግማሽ ጎኑ የተቃጠለውን አርተፊሻል ፀጉር አናቱ ላይ አድርጎ፣ የተሰበረ የፀጉር ጌጥ ሰክቶበት እንደ ፈረንጅ ኮረዳ እየተሽኮረመመ “ዊስ ዋይስ” ብሎ በራሱ እንግሊዝኛ ተናገረ፡፡
ጎቢጥ ያንን አንድ ዓይኑ ላይ መስታወት የሌለውን መነፅሩን አደረገና አፉ ላይ የሲጋራ ቁራጭ ወትፎ እንደ ፈረንጅ ጎረምሳ ጎርነን ባለ ድምፅ፤ “ዋት ኢዝ ዊስ ዋይ?” አለ በብረት ዘንግ ቆሻሻውን እየቆፈረ፡፡ የአሻንጉሊትዋን እግሮች አገኘ፡፡ ለቀጢሳው ሰጠው።
ቀጢሳው ቻርሊ ቻፕሊን ፊልም ላይ ባየነው ስልት በደስታ ተውረግርጎ ሹል አፉን አሞጠሞጠና ሲሳይ ጎቢጥን ሳመው፡፡
ፍለጋችን ቀጠለ፡፡ ውሮ አንድ ነገር ደብቆን ኪሱ ሲከት ሴምላል አየውና፤ “ምን አገኘህ?” ሲል ጠየቀው፡፡ ሁላችንም ካቀረቀርንበት ቀና አልን፡፡ ውሮ ቁንጮውን እያከከ “ምንም አላገኘሁም!” አለ፣ ኪሱን ጨብጦ ላለማስፈተሽ እየሞከረ፡፡
“እስኪ እናቴ ትሙት በልና ማል?!” ሲል ሴምላል ንፍጡን ሽቅብ እየሳበ ጠየቀው፡፡ ውሮ መማሉን ፈራ፡፡ በዚህ ምልልስ ወቅት መኩዬ ቀጫጫው እንደ እባብ ተስባ ከውሮ ኋላ ደርሳ ከኪሱ በፍጥነት አንድ ነገር ስትስብ የአሻንጉሊቷ ጭንቅላት መሬት ዱብ አለ፡፡
“ወይኔ አሻንጉሊቴን!” ሲል ውሮ ጩኸቱን አቀለጠው፡፡ መኩዬ ቀጫጫው የአሻንጉሊት ጭንቅላት ከመሬት አንስታ እየደባበሰች ለቀጢሳው እንዲሰጠው ለመነችው፡፡
ውሮ “እምቢ” አለ፡፡
ሁላችንም ብንለምነው ችክ አለ፡፡ እርሱም የራሱ አሻንጉሊት እንዲኖረው፣ የተቀረውን አካል በሽቦና በጨርቅ ሠርቶ ሊጫወትበት መፈለጉን በልቅሶ ዜማ አወራን፡፡ በዚህ ራስ ወዳድነቱ ሁላችንም አኮረፍነው፡፡ መኩዬ ቀጫጫውም የአሻንጉሊቷን ጭንቅላት አፍንጫው ላይ ወረወረችለት፡፡
(“ልጅነት” ከተሰኘው የደራሲ ዘነበ ወላ
መፅሀፍ ላይ የተቀነጨበ)

Read 6123 times
Administrator

Latest from Administrator