Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Wednesday, 04 April 2012 07:29

“11 በመቶ በምን መሰረት ላይ ነው?”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አቶ ሙሼ ሰሙ የኢ.ዴ.ፓ ሊቀመንበር

በላሊበላ ሕዝባዊ ስብሰባ ጠርታችሁ ነበር፡፡ እስቲ ስለስብሰባው ያብራሩልኝ?

ህዝባዊ ስብሰባው ላለፈው አንድ አመት ተኩል ስናካሂድ የነበረው ንዑስ ድርጅታዊ ስብሰባ አካል ሲሆን ከሕዝብ ጋር ለረዥም ጊዜ ካለመገናኘት የሚፈጠረውን ክፍተት ለማጥበብ የምናደርገው እንቅስቃሴ ውጤት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በ2002 ዓ.ም ምርጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተወካዮች ምክር ቤት ወንበር አላገኙም፡፡ በፊት አነሰም በዛም የማህበረሰቡን ጥያቄዎች አሰባስበው፣ ለምክር ቤትም ለመንግስትም የማቅረብ ሥራ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ያ ነገር አሁን የለም፡፡ ለዚህ አንዱ መነሻ ደግሞ የምርጫ ውጤቱ ተጽእኖ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በመንግስትም በኩል ተከታታይነትና ቀጣይነት ያለው ሥራ አለመሠራቱ ክፍተቱን ፈጥሮታል፡፡ ክፍተቱ እየሰፋ በመጣ ቁጥርም አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ከሕዝቡ ጋር ካልተገናኘ ትርጉም አይኖረውም፡፡

እናም የ2007 የምርጫ ውጤት እንደተጠናቀቀ፣ በጠቅላላ ጉባዔአችን ተወያይተንበት፣ በቀጣይ ምን መሥራት አለብን ብለን በእቅድ ከያዝናቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ አንዱ ነው - የላሊበላው ህዝባዊ ስብሰባ፡፡ በወላይታ ዙሪያ በሚገኙ 13 ወረዳዎችም ተመሳሳይ ጉባኤ አካሂደናል፡፡ የነበረውን አመራር ለውጠን ያለውንም የማጠናከር ሥራ ሰርተናል፡፡ ደቡብ ክልል ላይ ሐዋሳ ላይ ነበር ቅርንጫፋችን፡

አሁን ግን ስናየው በዚያ መቀጠል ስላልተቻለና ተጨማሪ በማስፈለጉ፣ በሕዝቡ ግፊት በወላይታ ሶዶ እና አለታ ወንዶ ቅርንጫፎች ከፍተናል፡፡ በእነዚህ ቦታዎችም ተመሳሳይ ስብሰባ አድርገናል፡፡ ከዚህም ሌላ ተዘግቶ የነበረውን የደሴ ቢሮ እንደገና ከፍተናል፡፡

ለምን ነበር የተዘጋው? መቼ ተከፈተ?

ቢሮው ነው ተዘግቶ የነበረው፡፡ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አልተቋረጠም፡፡ ከምርጫ 97 ችግሮች ጋር በተያያዘ የደሴ ቢሮ ሥራውን አቁሞ ስለነበር ነው፡፡ ግን ከምርጫ 2002 በኋላ በዚያ አካባቢ ኢዴፓ ከሕብረተሰቡ ጋር ያለው ትስስር እያንሰራራ ስለመጣ 2002 ላይ ቢሮ ከፍተን በአካባቢው ተወዳድረናል፡፡ የዚያ ቀጣይ ሂደት ነው የላሊበላው ስብሰባ፡

የላሊበላውን ጉባኤ አስመልክቶ ባወጣችሁት መግለጫ ላይ፤ አንዳንድ አባላቶቻችሁ አገልግሎት ፍለጋ ወደ መንግሥታዊ ተቋም ሲሄዱ “ኢዴፓ ይስጣችሁ”፣ “ከኢዴፓ ውሰዱ” እንደሚባሉ ጠቁማችኋል፡፡ ትክክለኛነቱ በማስረጃ ተረጋግጧል?

እንዲህ ያሉ መረጃዎች የሚመጡት ከህዝቡ ነው፡፡ ከዚሁ ችግር ጋር በተገናኘ ሕዝባዊ ስብሰባው ላይ ለመሳተፍ የፈሩ አባላት ጽሕፈት ቤታችን ድረስ መጥተው ነግረውናል፡፡ ነገሩ ትክክል ነው አይደለም የሚለውን በተመለከተ በሂደት አጣርተን የምንደርስበት ነው፡፡ ግን መቼስ ሕዝባዊ ስብሰባን የሚያክል ነገር ላይ አንድ ሰው ወጥቶ በአጠራጣሪ ሁኔታ ራሱን ይገልፃል ብለን አናምንም፡፡ ለመስተዳድር አካላት ጉዳያቸውን እንዳስታወቁና አግባብ የሆነ መልስ እንዳላገኙ ነግረውናል፡፡ እኛ የሄድነው ለሕዝባዊ ስብሰባ ነው፡፡ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ደግሞ መረጃ አለህ ወይ ብለን አንጠይቅም፡፡ ጉዳዩን ከሁለት ሰው በላይ ካነሳው እንደ አቤቱታ እንወስደዋለን፡፡

ስብሰባ በምታካሄዱባቸው ስፍራዎች እክሎች ይገጥማችኋል?

ይህን ጉዳይ ለማስፈፀም ቦታው ላይ ጽሕፈት ቤትና ኮሚቴ አለ፡፡ ያንን ሥራ የሚሰራው እሱ ነው፡፡ ስብሰባውን ማካሄዳችን በራሱ በመስተዳድሩ አካባቢ ቀጥተኛ እንቅፋት ላለመኖሩ መስካሪ ነው፡፡ ይሄ ቢያንስ ቀጥተኛ የሆነ ተጽእኖ ለመፍጠር ፍላጐት አለመኖሩን ያሳያል፡፡ እስካሁን ስብሰባ አታደርጉ አላሉንም፡፡ ለነገሩ ይሄ መብታችን ነው፡፡ እናም መብታችንን ግን አረጋግጠውልናል - እንቅፋት ባለመሆን ማለት ነው፡፡ አዳራሽ ተፈቅዶልናል፡፡ ቀጥተኛ ክልከላ አልነበረም፡፡ በእርግጥ መብታችንም መሆኑ እየታወቀ በተለያየ አስተዳደራዊ መንገዶች እነዚህ መብቶች ሊደፈሩ ይችላሉ፡፡ እዚያ ቦታ ላይ የመወያየት እድል አግኝተናል፡፡

እድሉ ግን በራሱ ሙሉ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሕገመንግስት፣ ሕጐች፣ ደንቦች እና መመርያዎች አሉ፡፡ እነዚህ በራሳቸው ሙሉ ሆነው አያውቁም፡፡ ትግልም የሚያስፈልገው እነዚህን ለማሟላት ነው፡፡ ለምሳሌ የእኛ ስብሰባ መኖሩ እየታወቀ (እዚያው እያለን) የአካባቢውን ጠቅላላ እድሮች አስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቶ ነበር፡፡ መጥራቱ ብቻ ግን አይደለም ችግሩ፡፡ እኛ በገባንበት ቀን ምሽት ነው የእድሮቹ ጥሪ የተጀመረው፡፡ የተጠራበትም ሰዓት ከኛ የስብሰባ ሰዓት ጋር መሣ ለመሳ የሚገጥም ነው፡፡ እንዲህ ያሉት ነገሮች ስጋት ይፈጥራሉ፡፡ እድሩ የተጠራው ቀደም ብሎ ቢሆን ምንም አልነበረም፡፡ ግን….

ስብሰባው በተለይ በላሊበላ የተካሄደበት ምክንያት አለው?

ኢዴፓ በቢሮ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ አስራ አንድ ጽሕፈት ቤቶች አሉት፡፡ ከነዚህም ውጪ አምስት በሕዋስ ደረጃ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አሉ፤ ገና ወደ ቢሮ አላደጉም፡፡ ወደ ቢሮ ደረጃ ካደጉ ሕዋሶቻችን አንዱ የላሊበላው ነው፡፡ ስለዚህ መርሃ ግብር አወጣንላቸው፡፡ ከሕዝቡ ጋር አመቻችተው ጠሩን፤ ከሕዝቡ ጋር እንድንወያይ ያደረገን የሕዝቡም ግፊት ነበር፡፡ አሁን ካለው የምጣኔ ሀብትና ሌሎችም ችግሮች በመነሳት የስብሰባ ጥያቄ ያነሳው ሕዝቡ ነው፡፡ ያንን መሠረት አድርገን ነው የሄድነው፡፡ ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ ባህርዳር ላይ ተመሳሳይ ጉባኤ አለን፡፡ በሐዋሳና በወላይታ ሶዶም አካሂደናል፡፡ ጠንካራ ቢሮዎች ካሉን ቦታዎች አንዱ ደግሞ ላሊበላ ነው፡፡ ጉባኤው በላሊበላ የተደረገው የአካባቢው ሕብረተሰብ የተለየ በደል ደርሶበት አይደለም፡፡ ላሊበላ የአቶ ልደቱ የትውልድ ወይም የምርጫ መወዳደርያ ቦታ ስለሆነም አይደለም፡፡ የአቶ ልደቱ ትግል ጠንካራነት በመላ ኢትዮጵያ ነው፡፡

አቶ ልደቱ አሁን በፓርቲው ውስጥ ያላቸው ቦታ (ድርሻ) ምንድነው? ከእንግሊዝስ አልተመለሱም?

ከፓርቲው ጋር ያላቸው ግንኙነት ባላቸው ሃላፊነት ደረጃ ቀጥሏል፡፡ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አይደሉም፡፡ የፓርቲው ማዕከላዊ ምክር ቤት አባል ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ በየሦስት ወር በሚያደርገው ስብሰባ በሚያካሂደው ልክ  ነው ተሳትፎአቸው፡፡ እሳቸው ደግሞ አሁን ያሉት እንግሊዝ ሀገር በከፍተኛ ትምህርት ላይ ነው፡፡ ከዚያ ሲመለሱ ደግሞ ይቀጥላሉ፡፡ የሄዱት በግል ትምህርት ነው እንጂ ከፓርቲው ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ በእርግጥ እንግሊዝ ውስጥ ጠንካራ መዋቅር አለን፡፡ ሆኖም ግን የማዕከላዊ ምክር ቤት አባል ሆነህ ውጪ ልትኖር አትችልም፡፡

ኢህአዴግ ለስድስት ፓርቲዎች ከለገሰው 1ሚ. ብር ውስጥ ፓርቲያችሁ ደርሶታል?

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በ2002 ምርጫ የተወካዮች ምክር ቤት አባል የመሆን እድል አጥተዋል፡፡ ከዚህ በፊት ያፀደቅነው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማቋቋሚያ እና ፓርቲዎች እንዴት ፋይናንስ እንደሚደረጉ የሚያካትተው የምርጫ ሕግ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገንዘብ ሊያገኙ የሚችሉት በተወካዮች ምክር ቤት ባለው መቀመጫ ቁጥር ልክ ነው ይላል፡፡ ያ ነገር ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም፡፡ ባለመቻሉም ደግሞ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመገናኛ ብዙሃን መድረክ ውጪ ናቸው፡፡ የእለት ተእለት የፓርቲ ሥራዎችን ለማከናወን ከመንግስት ሊመደብላቸው ከሚገባው በጀት ውጪ ሆነዋል፡፡ ይህ ትልቅ ተፅእኖ የሚፈጥር ነው፡፡ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ከኢኮኖሚ ችግርም አንፃር ስንወስደው፣ ፓርቲዎቹን አጠናክሮ የመዝለቅ እድል ጠባብ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ አማካይነት፣ ይኼ ሕግ እንዲለወጥ ጥረት አድርገናል ከኢህአዴግ ጋር በመወያየት፡

ሕጉ ተለውጦ መንግስት በሚመድበው በጀት አማካይነት ፋይናንስ እንድንደረግ ነው የምንፈልገው፡፡ ያ ሊሆን አልቻለም ማለት ግን የፖለቲካ ሥራችንን ለማስኬድ የሚያስችለንን ግብአት እናጣለን ማለት አይደለም፡፡

በውይይቱ መሠረት ኢህአዴግ ባሉት ወንበሮች ልክ ካገኘው ገንዘብ ላይ የተወሰነውን ለምርጫ ቦርድ ነው የመለሰው፡፡ ምክንያቱም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ባለው ሁኔታ የፖለቲካ ሥራቸውን ለመስራት የሚያስችል የፋይናንስ አቅም እንደሌላቸው ስለሚታወቅ፣ ምርጫ ቦርድ ገንዘቡን ሕጋዊ በሆነ መንገድ በሚቀመጠው መስፈርት እንድንከፋፈልና እውቅና በተሰጠው ኦዲተር አማካይነት ኦዲት አስደርገን የሠራንበትን ሠርተንበት፣ ያልሠራንበትን እንድንመልስ ነው ስምምነቱ፡፡ ስለዚህ የመስጠትና የመከልከል ነገር አይደለም፡፡ ምርጫ ቦርድ አስፈፀመው ማለት ገንዘቡ የመጣው ከምርጫ ቦርድ ነው ማለት ነው፡፡ ለነገሩ ፓርቲአችን እሱን እየጠበቀ አይደለም ሥራ የሚሠራው፡፡ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ካሉ ኢትዮጵያውን በምናገኘው ድጋፍም ነው የምንሠራው፡፡

ኢዴፓ ታማኝ ተቃዋሚ ነው የሚሉ አሉ፤ ታማኝ ተቃዋሚ ምን ማለት ነው? እንደዚያ ነን ብላችሁ ታስባላችሁ?

ታማኝ ተቃዋሚ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚያውቁት እነሱ ናቸው፤ መስፈርቱንም ያወጡት እነሱ ስለሆኑ መዝገበ ቃላት ላይ ታማኝ ተቃዋሚ ሲባል አላውቅም፡፡ “Loyal opposition” የሚል ቃል አለ፡፡ ይኼ ለማን ነው ታማኝነቱ? ለመንግስት፣ ለሕገመንግስቱ፣ ለሥርዓቱ እንጂ ለፖለቲካ ፓርቲዎች አይደለም፡፡ እኛም አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ፣ ሕገመንግስቱ ላይ የማንፈልጋቸው በርካታ አንቀፆች ቢኖሩም፣ አሁን ሥርአቱ እየሄደ ያለበት ብዙ የዲሞክራሲ እንቅፋቶት ቢኖሩም ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን በዘለቄታው ለማረጋገጥ እየተሰራ ያለው አመርቂ ነው ብለን ባናምንም ግን፣ ሰላማዊ ትግል የሚያደርግ ኃይል ከሥርአቱ ጋር ቅጥ ባለው መንገድ ተሳስሮ መቀጠል አለበት፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን ማናቸውም አካላት ጉዳያቸውን የሚያስፈጽሙት በመንግስት ተቋማት አማካይነት ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ደግሞ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ስለሆነ ተወደደም ተጠላም እሱ በሚመርጣቸው፣ በሃላፊነት በሚሾማቸው የሚመሩ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ ሆነህ የፖለቲካ ሥራ ልትሰራ አትችልም፡፡ ለምሣሌ ኢህአዴግ አምስት ዓመት በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሲጠቀም ቆይቶ፣ የምርጫ ዘመቻ ሲመጣ 40% ለራሱ፣ 60% ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የአየር ሰዓት ይመድባል፡፡ ይኼ ክፍፍል ፍትሀዊ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ግን ማናችንም ይኼ ፍትሀዊ የሰዓት ክፍፍል ስላልሆነ አንቀበልም አንልም፡፡ ኢህአዴግ እዚህ ላይ ሰጪም ከልካይም ነው፡፡ ይኼን ገንዘብ መውሰድ ታማኝ ተቋዋሚ ካሰኘ በሚዲያው መጠቀምም ታማኝ ተቃዋሚ ያሰኛል፡፡ መስፈርቶችን ስንወስድ ከምክንያታዊነት በመነጨ ስናደርጋቸው፣ ለፖለቲካው ትግል ወይም ለሚገኘው ድል ጥሩ ግብዓት መሆን ይችላሉ እንጂ ጥራዝ ነጠቅ በሆነ መንገድ አንዳንድ ገጠመኞች እየመዘዙ፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል ጠቃሚ አይደለም፡፡ አንድ ኃይል ታማኝ የሚባለው አጋር ሲሆን ነው፤ እኛ አይደለንም፡፡

ታማኝ ናችሁ ከሚሉን ተቃዋሚዎች፣ የበለጠ እንጂ ያነሰ አልተከራከርንም - በፖለቲካው መድረክ፡፡ “እርስ በርሷ የምትለያይ ቤት አትፀናም” ይላል መጽሐፍ ቅዱስ፡፡ እኛ ሊበራል ዲሞክራት ነን፤ እነሱ አብዮታዊ ዲሞክራቶች ናቸው፡፡ በ1997 በተፈጠረው ሁኔታ የነበረውን ልዩነት አሁንም መጋለብ ወቅቱ አልፎበታል፡፡ የማህበረሰቡም ንቃተሕሊና ከዚያ የበለጠ በልጽጓል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለማምጣት የምንፈልገው መልካም ነገር ሁሉ ኢዴፓን በመታገል ይመጣል ብዬ አላምንም፡፡ የሥልጣን፣ የገንዘብ፣ የፖሊስ፣ የመከላከያ ባለቤት ኢህአዴግ ነው፡፡ ያንን ሃይል ገለል አድርገህ ከኢዴፓ ጋር እሰጥ አገባ መግጠሙ ትርጉም የለውም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ ስናቋቁም፣ አንዳንድ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር አንነጋገርም አይደለም ያሉት፤ ኢዴፓ ይውጣልን እንጂ፡፡

ገንዘቡ የተሰጠው ተቃዋሚ ፓርቲዎቹን ለመከፋፈል ነው የሚሉም አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የኢዴፓ አቋም ምንድነው?

ተቃዋሚዎች የሚከፋፈሉት በምንድነው? በግብ ነው በአካሄድ? አካሄድ ለግብ አንድ መሥፈርት ነው፡፡ ግን ምንድነው ግባችን ግባችን እኮ በርብር በመንግሥት ተቋማት አማካይነት ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ደግሞ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ስለሆነ ተወደደም ተጠላም እሱ የሚመርጣቸው በሃላፊነት በሚሾማቸው የሚመሩ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ ሆነህ የፖለቲካ ሥራ ልትሰራ የምትችልበት ሁኔታ የለም፡፡ ለምሳሌ ኢህአዴግ አምስት ዓመት በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ሲጠቀም ቆይቶ የምርጫ ዘመቻ ሲመጣ 40 በመቶ ለራሱ 60 በመቶ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የአየር ሰአት ይመድባሉ፡፡ ይሄ ክፍፍል ፍትሃዊ እንዳልሆነ እናውቃን፡፡ ግን ማናችንም ይሄ ፍትሃዊ የሰአት ክፍፍል ስላልሆነ አንቀበልም አንልም፡፡ ኢህአዴግ እዚህ ላይ ሰጪም ከልካይም ነው፡፡ ይኼን ገንዘብ መውሰድ ታማኝ ተቋዋሚ ካሰኘ፣ በሚዲያው መጠቀምም ታማኝ ተቃዋሚ ያሰኛል፡፡ ለእኔ ምንድነው መስፈርቶችን ስንወስድ ከምክንያታዊነት በመነጨ ብናደርጋቸው ለፖለቲካው ትግል ወይም ለሚገኘው ድል ጥሩ ግብአት መሆን ይችላሉ እንጂ ጥራዝ ነጠቅ በሆነ መንገድ አንዳንድ ገጠመኞች እየመዘዙ ለፖለቱካ ፍጆታ ማዋል ጠቃሚ አይደለም፡፡ አንድ ኃይል ታማኝ የሚባለው አጋር ሲሆን ነው እኛ አየደለንም፡፡ ታማኝ ናችሁ ከሚሉን ተቃዋሚዎች የበለጠ እንጂ ያነሰ አለተከራከርንም በፖለቲካው መድረክ የማህበረሰቡም ንቃተ ሕሊና ከዚያ የበለጠ በልፅጓል፡፡ በኢትዮጵያ ወስጠ ለማምጣት የምንፈልገው መልካም ነገር ሁሉ ኢዴፓን በመታገል ይመጣል ብዬ አላምንም፡፡ የሥልጣን፣ የገንዘብ፣ የፖሊስ፣ የመከላከያ ባቤት ኢህአዴግ ነው፡፡ ያንን ኃይል ገለል አድርገህ ከኢዴፓ ጋር እሰጥ አገባ መግጠሙ ትርጉም የለውም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ ስናቋቁም አንዳንድ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር አንነጋገርም አይደለም ያሉት ኢዴፖ ይውጣልን እንጂ፡፡

ገንዘቡ የተሰጠው ፓርቲዎቹን ለመሰነጣጠቅ ነው በሚሉ ላይ የኢዴፓ አቋም ምንድነው?

ተቃዋሚዎች የሚከፋፈሉት በምንድነው? በግብ ነው በአካሄድ? አካሄድ ለግብ አንድ መስፈርት ነው፡፡ ግን ምንድነው ግባችን? ግባችን እኮ በርብርብ አንድ ኃይል ያመጣል፡፡

ስለዚህ የተገኘው ገንዘብስ መከፋፈል አያመጣም እያሉኝ ነው?

ይኼንን መከፋፈል የሚያመጣው ኢህአዴግ አይደለም፡፡ ይህንን ያመጡት ራሳቸው ተቃዋሚዎች ናቸው፡፡ አቀራረባቸው ነው መከፋፈሉን ያመጣው፡፡ በቴሌቪዥን ክርክር ወቅት ያጣናቸውን መብቶች ለማግኘት ሁላችንም መታገል ነው ያለብን፡፡ ኢህአዴግ ገንዘቡን መልሶ እንድንከፋፈል ተደረገ እንጂ አንተ አጋር አንተ ተቃዋሚ አላለም፡፡ ይኼን እየተናገሩ ያሉት ሌሎች ናቸው፡፡ ውስጥ ለውስጥ የሚሰራውን ግን አላውቅም፡፡ ከደሙ ንፁህ ነው ለማለት የሚያስችለኝም መረጃ የለም፡፡

በአባይ የህዳሴ ግድብ ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገለልተኛ ሆነዋል ይባላል፡፡ ኢዴፓስ ምን ይላል? ለግድቡስ አዋጥታችኋል?

ግድቡን በተመለከተ አቋማችንን ደግመን ደጋግመን ገልፀናል፡፡ ይኼ ጥያቄ የልማት ጥያቄ ነው፡፡ የልማት ጥያቄን ደግሞ በአግባቡ መንግስት እንዲመልሰው የታገልንለት ጥያቄ ነው፡፡ በፕሮግራማችን ውስጥ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አሁን ካለበት ወደ አስር ሺህ ሜጋ ዋት ማደግ አለበት የሚል ፕሮፖዛል አቅርበናል፤ በማኒፌስቶአችን፡፡ ልዩነቱ ማን ሰራው ነው፡፡ እንደ ፓርቲ አዋጡ ተብለን አልተጠየቅንም፡፡ በተቀጣሪ ሠራተኝነቴ ግን ተገቢውን መዋጮ አድርጌአለሁ፡፡ በአሰራሩ ላይ እኛ ሌሎች አማራጮችን ልንዳስስ እንችል ይሆናል፡፡ ኢህአዴግ ግድቡን እንዲያጠናቅቅ ግፊት ማድረግ እንጂ ግድቡ በጥርጣሬ እንዲታይ ማድረግ አያስፈልግም፡፡ ይኼ ነገር እንዳይሳካ የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች አሉ፡፡ እነዚህ የውጭ ኃይሎች በውስጥ ያለውን ችግር አባብሰውት፣ የሕዝቡ ፍላጐት እንደሌለበት አድርገው ሊያሳዩ ይሞክራሉ፡፡ በኛ በኩል ስህተቶች እንዲታረሙ ገንዘብ አያያዙ ትክክለኛ እንዲሆን… እንፈልጋለን፤ ተፅእኖም ለማሳደር እንፈልጋለን፡፡

መንግሥት ምጣኔ ሀብቱ 11 በመቶ አደገ ማለቱ ከሕዝቡ የእለት ከእለት ኑሮ ጋር እንዴት ያያይዙታል?

11 በመቶ ያደግነው በምን መሰረት ላይ ነው? ከዚህ እንነሳ፡፡ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እጅግ ደካማ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የማህበረሰባችንም ህይወት እጅግ በጣም የደቀቀ ነው፡፡ ከጐረቤት ሀገራት እንኳ ሲነፃፀር ኑሮአችን ዝቅተኛ ነው፡፡ ከዚህ ኢኮኖሚ ላይ ተነስተህ 11 በመቶ አድጓል ማለት ከምንም ወደ ምንም ነው፡፡ ሃያ እና ሰላሳ ትሪሊየን ዶላር የሚያንቀሳቅሱ ሃገሮች አጠቃላይ አመታዊ ምርት አንድ በመቶ እድገት ማለት የኢትዮጵያን የሚቀጥሉ ሃያ አመታት ወይም ሰላሳ አመታት እድገት ነው የሚያህለው፡፡ የኢትዮጵያን ባለህ ብርቱካን እንመስለውና፣ አስር ብርትኳን ኖሮህ አስር በመቶ አደግህ ማለት አስራ አንድ ብትቱካን ብቻ አለህ ማለት ነው፡፡ የምንፈልገው ነገር እና ሀገሪቷ እያደገችበት ያለው ሁኔታ የሚጣጣም አይደለም፡፡ የእድገቱ ምንጭ ምንድነው ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ የእድገቱ ምንጭ በአብዛኛው መሰረተ ልማት ነው፡፡ መሰረተ ልማት ያስፈልጋል፡፡ ግን የማህበረሰቡን ሕልውና ጠብቆ ካልሆነ አሁን የተባለው እድገት የህብረተሰቡን ኑሮ ከመለወጥ አኳያ ሚና አይኖረውም፡፡ መሰረተ ልማት የረዥም ጊዜ እድገት መገለጫ እንጂ የሕዝቡ ኑሮ እንዲለወጥ ሚና የላቸውም፡፡ ከፍተኛ ገንዘብ ነው የሚጠይቁት፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አሰራራችን ለብክነትና ለሙስና በተጋለጠበት ሁኔታ ወጪያቸው ትልቅ ነው፡፡ ይህን ይዘህ ወደ ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ስትገባ፣ በአቅርቦት የተደገፈ ስለሚሆን ተፅእኖ ያመጣል፡፡ መንግሥት ይህን ረስቶ ፊቱን ያዞረው ወደ መብራት፣ ስልክ፣ ውሃ… ነው፡፡ እነዚህ ግብአት ናቸው እንጂ አቅርቦትን የሚተኩ አይደሉም፡፡ መንግሥት ከሀገር ውስጥ የሚበደረውን ማቆም አለበት፡፡ ግሽበት የሚያባብሰው እሱ ነው፡፡ በሞተ እድገት ላይ ምጣኔ ሀብት በ11 በመቶ አደገ ማለት የሚያመፃድቅ አይደለም፡፡ እድገቱ የመጣው በብድር ነው፤ ለነገ ትውልድ እዳ በማከማቸት፡፡ ከእነ ቻይና የሚገኘው ብድር ወለዱ ከፍተኛ የሚመለስበት ጊዜ አጭር ነው፡፡

በፓርቲዎች የጋራ መድረክ የተጀመረው ውይይት ምን ይመስላል?

እየተካሄደ ነው፡፡ እንደተፈለገው ግን ሊሆን አልቻለም፡፡ በጋራ መድረኩ መነሻነት የአባይ ግድብ ኮሚቴ አባላት ነን፡፡ ከዚህ ውጪ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊመለሱ የሚገባቸው እልፍ ጥያቄዎች አሉ፡፡

አሁን ካሉት ፓርቲዎች ኢህአዴግ የዚህችን ሀገር እድገት የማመጣው እኔ ነኝ በሚል ለ30 እና 40 ዓመታት ሥልጣን ላይ ለመቆየት መመኘቱ በሌሎች ፓርቲዎች ሕልውና ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖው ምንድነው?

ይህንን ነገር በሁለት መንገድ ከፍለን ማየት አለብን፡፡ በሚቀጥለው አርባ አመት ሥልጣን ላይ ቆይቼ እሰራለሁ እመኛለሁ ብሎ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መናገሩ ስህተት አይደለም፡፡ መመኘት እኔም በምርጫ አሸንፌ ስልጣን ላይ ማገልገል እመኛለሁ፡፡ አርባ አመት እገዛለሁ ማለት ግን ስህተት ነው፡፡ ለምን ኢህአዴግ ይመኛል አንልም፡፡ መብቱ ነው፡፡ ግን የሀገሪቱን ሀብት፣ የመንግስትን መዋቅር፣ ገንዘብ በጀቱን ተጠቅመህ ለሚቀጥለው አርባ አመት ሥልጣን ላይ እቆያለሁ ማለት ግን አምባገነንነት ነው፡፡ የተቃዋሚዎችን እንቅስቃሴ የማቀጨጭ አለማቀጨጭ ጉዳይ ሳይሆን ግልጽ የሆነ አምባገነንነት ነው፡፡ ማቀጨጭ በአስተዳደርና በሌላም ጉዳይ ሥራቸውን እንዳይሰሩ ማድረግ ነው፡፡ ለአርባ ዓመት ሥልጣን አትይዙም ስትል ግን የለየለት አምባገነንነት ነው፡፡ ማንኛውም መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ ተጽእኖ ማሳደር ይችላል፡፡ ግን የሀገሪቱን ሀብት ተጠቅሜ እንዲህ እሆናለሁ ማለት አምባገነንነት ነው፡፡

የሰሞኑን የሴኔጋል ምርጫ እንዴት አያችሁት?

የሴኔጋል ምርጫ በእውነቱ ሕዝብ መታገል አስፈላጊ ነው ብሎ አምኖ በተነሳበት፣ መሪዎች አምባገነንነትን ማስፈን እንደማይችሉ ያሳየ ነው፡፡ አብዱላሂ ዋዴ ሕገመንግስቱ የሚፈቅድላቸውን ጊዜ ከተጠቀሙ በኋላ ሥልጣኑን ለልጃቸው ለማሸጋገር ነው የፈለጉት፡፡ በነገራችን ላይ የአፍሪካ ሊበራል ፓርቲዎች አባል ነን፡፡ ዋና ፀሐፊው ላሚንባ በዋዴ መንግስት ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ነበሩ፡፡ ሕገመንግስቱን ለመለወጥ በተደረገው ጥረት ውስጥ ከባድ ተቃውሞ አድርገው ከሥልጣን የተባረሩ ሰው ናቸው፡፡ በኔ እምነት ሕገመንግስት በሰዎች መስማማት ለሕዝብ የሚበረከት ቃል ኪዳን ነው፡፡ ሕዝቦች ከሕዝቦች እና ከመንግስት ጋር ባላቸው ግንኙነት በሥምምነት የሚያፀድቁት ሕግ ነው፡፡ ያንን ሕግ ባለሥልጣናት፣ ከሥልጣን ጥማት በመነጨ ወይም ዳግም ሥልጣን ላይ በመቆየት፣ በተለይ ከመለማመድ የተነሳ ከኔ ውጭ አማራጭ ሊመጣ አይችልም በሚል መንፈስ በፈለጉ ጊዜ ወይም ከእንቅልፋቸው በባነኑ ቁጥር ሊለውጡ እንደማይችሉ ያስተማረ ነገር ነው፡፡ ሊለውጡ አይችሉም ያስባለኝ ምክንያት ምንድነው፣ ግፊቱ የመነጨው ከሕዝቡ ብቻ አይደለም፡፡ ሥልጣን ላይ ከነበሩ የሳቸው ባለሥልጣናት ጭምር ነው፤ የነገርኩህን ሰው ጨምሮ፡፡ ይኼ ለአፍሪካ ትልቅ ምሣሌ ነው፡፡ በተለይ ለኢትዮጵያ ትልቅ ምሳሌ ነው፡፡ ኢህአዴግ የሚለው የሥልጣን መተካካት የሕገመንግስት መተካካት እንዳያመጣ ነው ሥጋታችን - ሕገመንግስት አሻሽለህ በሥልጣን ላይ የመቆየት አጀንዳ እንዳይፈጥር፡፡

ከሌሎች ተቃዋሚዎችም ሆነ ከኢህአዴግ ጋር ያላችሁ ማህበራዊ ግንኙነት ምን ይመስላል?

በአካባቢዬ ካሉ የኢህአዴግ አባላት ጋር የአንድ እድር አባል ነን፡፡ በአጋጣሚ ከፍተኛ አመራር አባላት በአካባቢዬ የሉም፡፡ ካሉት ጋር አብረን እንበላለን እንጠጣለን፤ በእድርም ውስጥ ሀዘን በጋራ እንወጣለን፡፡ ደስታችንንም እንካፈላለን፡፡ ይኼ ከሌላ ከምንም የሚመነጭ ሳይሆን የዚህች ሀገር የጋራ ባለቤቶች ከመሆናችን የተነሳ ነው፡፡ የፖለቲካው መድረክ ሲያገናኘን በፖለቲካ ቋንቋ እንናገራለን፡፡ በተለያየ መድረክ ውይይት ላይ እንገናኛለን፡፡ በውይይቱ መሃል የሻይ እረፍት አለ፡፡ እነዚህ ነገሮች ተጽእኖ አሳዳሪ እንዲሆኑ አድርጐ መጠቀም፣ ትክክለኛ የፖለቲካ አሰራር ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ይኼ የፓርቲ መመሪያ ሆኖ የሚወርድ ነገር አይደለም፡፡ ሕዝብ ከመሪዎቹ የመማር ዝንባሌ አለው፡፡ እኛ ይዘነው የምንመጣው ልዩነት እና ግጭት ከፖለቲካ ውጪ በሚሆንበት ጊዜ ግጭቱ በእሱው ልክ ወደ ጥላቻ ያመራል፡፡ ማግለሉ የፖለቲካውን ነገር ትተህ በልማት ላይ ራሱ፣ በልጆቻችን በቤተሰባችን ላይ ተጽእኖ አለው፡፡ ተወደደም ተጠላም በዚህች ሀገር መፃዒ እድል ላይ የመወሰን ሥልጣን ለማናችንም በተለይ አልተሰጠም፡፡ ራሳችን ነን በሂደትና በምንሠራው ሥራ የምናረጋግጠው፡፡ ሀገር ለማፍረስ የመጣ፣ ትምክህተኛ ጐጠኛ ካልክ፣ ማብቂያ የሌለው ጦርነት ነው የሚሆነው፡፡ በ1992 ዓ.ም አስታውሳለሁ ኢዴፓ መጀመሪያ ሲቋቋም ተቃዋሚው ኃይልና ኢህአዴግ ከውይይት በኋላ ለሻይ በየጐራው ሲቀመጡ፣ ኢዴፓዎች ነን ፖለቲካዊ ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ በማለት የተቀላቀልነው፡፡ እንደሰው ለሻይ ቡና ስንሰለፍ የምንኳረፍበት ምክንያት የለንም በሚል መንፈስ ጨብጠናቸዋል፡፡

ይኼንን መንፈስ በመፍጠር ኢዴፓ ትልቅ ሚና አለው፡፡ ስንጀምረው የማይሆን ስም ተሰጥቶን ነበር፡፡ አሁን አሁን ምናልባት የማየት እድሉ ገጥሞህ ከሆነ፣ ከስብሰባ በኋላ ተቃዋሚው ወደ ገዢው፣ ገዢው ወደ ተቃዋሚው ሄደው ሲያወሩ ታያለህ፡፡ ያ ልምድ የዛሬ አስራ ሁለት አመት ኢዴፓ ሲቋቋም ተለጣፊነት ነበር፡፡

ለምሣሌ አቶ ልደቱ ከእነ አቶ ስብሃት ነጋ ጋር ተገናኘ ተብሎ ያ ሁሉ አሳፋሪ ውርጅብኝ ተካሂዷል፡፡ ከዚያ በኋላ በወጡ መፃሕፍት ግን ፕሮፌሰር መስፍን፣ ዶ/ር ሽመልስ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ራሳቸው ቤታቸው ሄደው ይነጋገሩ እንደነበር የመጽሐፍ ገጽ ጠቅሶ መናገር ይቻላል፡፡ እንዲህ አይነት ነገሮችን ለፖለቲካ ፍጆታ ለመሸጥ ሲባል የተደረገው ነገር ማህበራዊ ግንኙነቱን ጐድቶታል፡፡ በኢህአዴግ በኩል ከምርጫ 97 በፊት ኢህአዴግ ነኝ የሚል አባል እንዳልነበረ ይታወቃል፡፡ ዛሬ ተለውጧል፡፡ ምክንያቱም ገዢ ፓርቲ ከመሆንም ባለፈ አምስት ሚሊዮን አባላት አሉኝ ስለሚል፡፡ ይህንን ለአፍራሽ ተጽእኖ መጠቀም አያዋጣም፡፡ እናም በሻይ ሰዓት ላይ ነገ እኔን ለማግኘት እድሉ የሌለውን አስተዳዳሪዬን ባናግር ክፋት የለውም፡፡ ፖለቲካ በዚህ መንገድ ነው የሚሰራው፡፡

 

 

Read 2646 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 07:34