Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Wednesday, 04 April 2012 08:08

“ዐባይን ጭብጦዬን ከቀማኝ ወዲህ አላምነውም” አገርኛ ተረት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንዲት በቅርቡ ባሏ የሞተባት ሴት ወደ ባሏ መቃብር በየዕለቱ እየሄደች በለቅሶ እጦቷን ትናገራለች፡፡

ከዚያ መቃብር አቅራቢያ የሚያደርስ አንድ ገበሬ ደግሞ ሁሌ እንዲህ ብሎ ያስባል:-

“ይህቺ ሴት ሚስቴ ብትሆን’ኮ ትልቅ ዕድል መጐናፀፍ ነው፡፡ ታማኝነቷ ከቶም አያጠራጥርም፡፡ ስለዚህ ለሀዘኗ ትብብሬን ላሳያትና ፈቃደኝነቷን ላጣራ” ይላል፡፡

እንዳቀደው ወደ ሴቲቱ ሄደ፡፡ እሷ እንደተለመደው ባሏ መቃብር ፊት ለፊት ተንበርከካ ታለቅሳለች፡፡ ገበሬው አጠገቧ ተቀመጠና እንደሷው እያለቀሰ ማንባት ጀመረ፡፡

ሴትዮይቱ ወደሱ ዘወር ብላ፤

“ስለምን ታነባለህ? ለምንስ እንባህን ታፈሳለህ?” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡

እሱም፤

“በቅርቡ ባለቤቴ ሞታብኛለች! እጅግ በጣም የምወዳት ሚስቴ ነበረች፡፡ ስለዚህ ዕንባዬን ማፍሰሴ ሀዘኔን ይቀንስልኛል፤ ብዬ ነው” አላት፡፡

እኔ ደሞ አለች ሴቲቱ፤

“ባሌን በቅርቡ አጣሁ! ስለዚህ በየጊዜው እየመጣሁ እንባዬን አፈስሳለሁ!” አለችው፡፡

ለጥቂት ጊዜ ሁለቱም በሀዘን ተዋጡ፡፡

ከዚያም ገበሬው የዝምታውን በረዶ ሰብሮ፤

“የእኔና የአንቺ ሀዘን አንድ ዓይነት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንዳ ብንጋባ ምን ይመስልሻል?”

“እንዴት ይሆናል?”

“በቃ፡፡ እኔ የአንቺን ሟች ባል ቦታ እወስዳለሁ፡፡ አንቺ ደግሞ የእኔን ሟች ሚስቴን ቦታ ትወስጃለሽ!” አላት ፍርጥም ብሎ፡፡

ሴትዮዋ ባቀረበላት ሀሳብ ተስማማች፡፡ ደሞም ትክክል መሆኗን እርግጠኛ ናት፡፡

ዕንባቸውን አደራረቁ፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ፤ ለካ ሌባ የገበሬውን ሁለት በሬዎችና ሞፈር ቀንበሩን ጠራርጐ መስዷል፡፡

ሌባ ሆዬ፤

“ወይ ንብረቴ! ወይ ሀብቴ! ወይ ዕድሌ!” እያለ ደረቱን እየመታ እዬዬውን ያቀልጠዋል!

ሴትዮዋ ለቅሶውን ስትሰማ፤

“እንዴ! ይሄን ያህል ምን ያስለቅስሃል? ቀደም ብለህ ያለቀስከው አይበቃም?” ብላ ትጠይቀዋለች፡፡

ገበሬው እንዲህ ሲል መለሰ

“አዎን ያ ይበቃ ነበር፡፡ ሆኖም ያሁኑ ለቅሶዬ የምር ነው!”

***

ዕውነተኛው ለቅሶ የንብረት ለቅሶ ሆነ!

የማስመሰል ለቅሶ ከማስመሰል አያልፍም! የማስመሰል ተባባሪነትም ከማስመሰል አያልፍም፡፡ የማስመሰል የፖለቲካ ሰውነትም ዜማ እንጂ ዕንባ የለውም፡፡ የሰው የፖለቲካ ለቅሶ ላይ መሳተፍ፤

“ቢደላ ለጊዜው፣ ወረቱ እስካለቀ

የሰው ቤት የሰው ነው፣ ቁርጡ የታወቀ!”

ከሚለው የዓለማየሁ እስቴ ማስገንዘቢያ መልዕክት አያልፍም፡፡ ዕጦት ሁሉ እኩል እንዳልሆነ ሁሉ፤ ችግር ሁሉ እኩል ችግር ነው አይባልም፡፡ ቤቱን ሊጨርስ ሲሚንቶ አጠረኝ የሚለውና የተከራየው ቤት ጓዳ ሌማት ባዶ ሆነብኝ የሚለው እኩል አይደሉም፡፡ ተበድሮ ዳቦ የሚገዛና ከባንክ ወስዶ ህንፃውን ለመጨረስ አንድ - ሐሙስ የቀረው “ባለሀብት” እኩል ችግርተኛ፣ እኩል ተበዳሪ አይሆኑም፡፡ እናቱ ወንዝ የወረደችበትና እናቱ የሞተችበት አንድ እንዳልሆኑ ሁሉ! አንዱ እንደ እናት ልጅ ያማረ ቪላ ሲያገኝ፤ ሌላው እንደ እንጀራ ልጅ የከረከሰች ቀሽም ጐጆ አሮበት ሜዳ በሚያድርባት አገር፤ የእናት ዲሞክራሲና የእንጀራ እናት ዲሞክራሲ ያለ ያስመስልብናል፡፡ የኑሮ ልዩነት በተዛምዶ የሚታይ ነው እንጂ በየትም አገር ይከሰታል! ይህ አይሁን አይባልም፡፡ ቢመኙትም አይሳካም!

“ያልታየ አገር አይናፍቅም

ቢያሰኝም አይታወቅም!”

እንዳለው ነው ሼክስፒር (በፀጋዬ አንደበት)፡፡ ሆኖም ልዩነቱን ማጥበብ ይጠበቅብናል፤

አለበለዚያ በሃይማኖቱም፣ በትምህርቱም፣ በፖለቲካ ትክክም መናቆሩ ይሰፋል፡፡ ሌላ ሥራ አይኖርም፡፡

“ያንቺን ባል እኔ እተካለሁ፣ የኔን ሚስት አንቺ ከተካሽ

ይህ ነው መተካካተ ብላሽ!

የዕድሜ አበባችን ስትሰንፍ

ለሰው ሥልጣን መባከን፣ አዕምሮን ለንዋይ ማስነፍ

ለሰው ወንበር መብከንከን፣ በከንቱ አባዜ መለከፍ”

ከዚህ በላይ ቅስፈት አለ፣ ያለጊዜያችን መቀጠፍ” ይላል ሌላው ያገር ገጣሚ፡፡

በሀገራችን፤ አንዱን እንጠግናለን ስንል ሌላው እየተሰበረ፣ የተሠራው እንዳልተሠራ፣ ያልተሠራው እንደተሠራ እየተቆጠረ፤ አያሌ ድካም ከንቱ የሚቀርበት ሁኔታ በገፍ ይታያል፡፡ የሙስናውን በር ዘጋን ስንል፣ የኑሮ ውድነት መስኮት ይከፈትብናል፡፡ ፖለቲካዊ ችግርን ለመፍታት መፍትሔ ስንፈልግ፣ ሙስናው መልሶ ችግር ይሆናል፡፡

የበላው ተነቅቶበት ከሥልጣን ሲወርድ፣ ያልበላው አፉን ለማሟሸት ይዘጋጃል እንጂ ከትላንትናው አይማርም፡፡ ተተካኪ ችግሮች እንጂ ተተኪ ትውልድ ለመፍጠር አልቻልንም፡፡ ችግርን ሁሉ በአንድ መነጽር እያየን አንዘልቀውም፡፡ “ቢያንስ በአዲስ መንፈስ እንውደቅ” ያለውን ፀሐፊ አንርሳ፡፡

አንዴ፤ ጃልሜዳን እሸጣለሁ ብለህ ከተስማማህ በኋላ ቆይተህ ከካድክ ወዲያ ምንም ያህል ታማኝነት፣ የቱንም ያህል ልግስናና ደግነት ብታሳይ መታመንን አያስመልስም፡፡ ዓባይ ዳር በሶውን እያበሰበሰ፤ ጭብጦውን እየጨበጠ ያለ ባላገር፤ ድንገት ደራሹ ውሃ መጥቶ ጭብጦውን ይዞበት ሄደ፤

“አዬ! “ዐባይን ጭብጦዬን ከቀማኝ ወዲያ አላምነውም” አለ ይባላል፡፡ ዕውነቱ ይሄን ይመስላል፡፡

 

 

Read 4204 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 08:11

Latest from