Print this page
Wednesday, 04 April 2012 08:15

ፈውስ ያልተገኘለት የጤና ችግር

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

ፈውስ ያልተገኘለት የጤና ችግር

አልበርት አነስታይን የኦቲዝም ተጠቂ ነበር…

በአገራችን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ኦቲስቲክ ልጆች አሉ…

የአለማችን እውቁ ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን የኦቲዝም ተጠቂ እንደነበር ይነገራል፡፡ በአገራችንም ከአመታት በፊት በድንቅ የሂሣብ ችሎታው ጉድ ያሰኘውና ገና በ16 ዓመቱ፣ በ1984 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሂሳብ ፎርሙላውን ያበረከተው እንድሪስ መሀመድ ኦውቲስቲክ ነው፡፡ ወጣቱ በአሁኑ ወቅት እጅግ በሚያሳዝንና በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ህይወቱን እየገፋ ይገኛል፡፡

መንስኤውና መድሃኒቱ እስከዛሬም ድረስ ሊታወቅ ያልቻለውና በብዙ ተመራማሪዎች ጥናት እየተካሄደበት ያለው የኦቲዝም (የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ችግር) ዛሬ የበርካታ የዓለም ህዝቦች ራስ ምታት ሆኗል፡፡ በአለም ላይ ከ100 ልጆች አንዱ የዚህ ችግር ተጠቂ ሲሆኑ በአሜሪካ ብቻ 1ሚ 500ሺ ኦቲስቶች አሉ፡፡ በኢትዮጵያም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ኦትስቲክ ልጆች መኖራቸው ይገመታል፡፡

ኦቲዝም የአዕምሮ ዕድገት መዛባት ሲሆን ይህም የአንጐልን የሥራ ሂደት በማወክ በአንጐላችን የሚከናወን የመረጃ አጠቃቀምን ያዛባል፡፡ የኦቲዝምን መንስኤ ለማወቅ ብዙ ጥረት ቢደረግም እስከዛሬ ድረስ ስለ መንስኤውና መፍትሔው በእርግጠኝነት ለመናገር አልተቻለም፡፡ ለችግሩ ቋሚ መፍትሔ ሊገኝ ባለመቻሉም  የችግሩ ተጠቂዎችን በልዩ የትምህርት ዘዴና እንክብካቤ ለውጥ እንዲያመጡ ማድረግ ብቸኛው አማራጭ ሆኗል፡፡

አንዳንድ ጥናቶች ለኦቲዝም መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው ካስቀመጧቸው ነጥቦች መካከል:-

አካባቢ በመርዛማ ኬሚካሎች መበከል

በእርግዝናና በወሊድ ወቅት የሚፈጠሩ ኢንፌክሽኖች

በአንጐል ውስጥ የሚገኝ የኬሚካል መጠን መዛባትና የሆርሞን አለመስተካከል

በዘር የሚተላለፍ መሆን እና

በህፃናት አስተዳደግ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ነገሮች የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ህፃናት ከስድስት ወር ጀምሮ እስከ ሶስት ዓመት ዕድሜያቸው ድረስ የዚህ ችግር ተጠቂ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ችግሩ የሚታወቀው ህፃኑ በሚያሳየው ባህርይና ሁኔታ እንጂ በሌላ የምርመራ ዘዴ አይደለም፡፡ ይሄም በህፃኑ ላይ ችግሩ ሳይታወቅ እንዲቆይ ያደርገዋል፡፡ ኦቲዝም ራሱን ችሎ ወይንም ከሌሎች ችግሮች ጋር በተጓዳኝነት የሚመጣ ሲሆን ከዚህ ችግር ጋር አብዛኛውን ጊዜ የሚጥል በሽታና መስማት የተሳነው መሆን ጐልቶ እንደሚታይ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ የኦቲዝም ችግር ያለባቸው ልጆች ከሚያሳዩዋቸው ባህርያት መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

በራሳቸው ዓለም የሚኖሩ በመሆኑ ሌላውን ለማወቅ ፍላጐት የላቸውም

ቃላት አውጥቶ መነጋገርና መግባባት ያቅታቸዋል

ሌሎች የተናገሩትን መደጋገም ይወዳሉ

የሰሙትን ቃል /ዐረፍተ ነገር/ በሰሙት ድምፅና ቅላፄ መሠረት ደግመው መናገር ይችላሉ

በእናቶቻቸውም ሆነ በሌላ ሰው መታቀፍንና መነካትን አይፈልጉም

መኪና፣ ገደል፣ ፎቅ፣ ፈፅሞ አይፈሩም

ራሳቸውን ከግድግዳና ከሌሎች ግዑዝ ነገሮች ጋር በተደጋጋሚ ያጋጫሉ፤ እጃቸውን ይነክሳሉ፤ ፊታቸውን ይቧጭራሉ

የመንቀዥቀዥ የመቁነጥነጥ ባህርይን ያሳያሉ

ድንገት ስሜታቸው ይለዋወጣል፡፡ ከት ብለው ሊስቁ ወይንም ስቅስቅ ብለው ሊያለቅሱ ይችላሉ

አብዛኛዎቹ የምግብ አበላል፣ የመፀዳጃ ቤት አጠቃቀምና የአለባበስ ሥርዓትን አያውቁም

በጣም ረዥም ነገሮች ላይ መንጠልጠል፣ መዝለል ይወዳሉ

በአንዳንድ ነገሮች ላይ በጣም ፍርሃት ሲያሳዩ በሌላው ደግም የሚያስደንቅ ድፍረት ይኖራቸዋል፡፡ ለምሳሌ ከፊታቸው የቆመን ትልቅ  ነገር ተጋጭተው ሲያልፉት በጣም ጥቃቅን የሆኑ ነገሮች እንዳይገጯቸው ሲጠነቀቁና ሲፈሩ ይስተዋላሉ፡፡

የኦቲዝም ችግር ተጠቂ የሆኑ ልጆች፤ በአካላቸውና በገፅታቸው ላይ ምንም አይነት ለውጥ ስለማይኖራቸው፣ ችግራቸውን ቶሎ ለመረዳትና ተገቢ እንክብካቤ ለማድረግ አስቸጋሪ ይሆናሉ፡፡ ችግሩ ሁነኛና ዘላቂ ፈውስ ያልተገኘለት ቢሆንም የችግሩ ተጠቂዎችን በልዩ ስልጠና እና እንክብካቤ ለተሻለ ህይወት ማብቃት ይቻላል፡፡ ኦቲስቲክ ከሆኑ ሰዎች መካከልም እጅግ ከፍተኛ ብቃትና ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች እንደነበሩ የታሪክ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ኦቲስቲክ ልጆች ያሏቸው ወላጆች በህብረተሰቡ ዘንድ የመገለል፣ በማህበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ እንደ ልብ ተሣትፎ ለማድረግ እንዳይችሉ የመደረግ ችግርም ይገጥማቸዋል፡፡ ልጆቻቸው በችግሩ ምክንያት የሚያሳይዋቸው የተለያዩ ባህርያት ከሥነ ሥርዓት ጉድለት ጋር ስለሚያያዝባቸው ህብረተሰቡ ያገላቸዋል፡፡ ስለዚህም አንዳንድ ወላጆች ኦቲስቲክ ልጆች እንዳላቸው መናገርና ማሣየት አይፈልጉም፡፡ በተቻላቸው መጠን ልጆቹ ከቤት እንዳይወጡና ለሰው እንዳይታዩ በማድረግ፣ በቤት ውስጥ ዘግተው ወይንም አስረው ያስቀምጡዋቸዋል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት ከተወለደ ጊዜ ጀምሮ ወደ ውጪ እንዳይወጣና እንዳይታይ ተደርጐ በጨለማ ክፍል ውስጥ ያደገውና ከሃያ አምስት አመት እድሜው በኋላ ነፃነቱን ሊጐናፀፍ የቻለው አንድ ወጣት ታሪክ የዚህ ችግር ሁነኛ ማሣያ ነው፡፡

ኦቲዝም የዓለም ህዝብ ችግር ቢሆንም ስለ ችግሩ በስፋት ለመወያየትና መፍትሔ ለማፈላለግ ጥረት ሲደረግ በብዛት አይታይም፡፡ ከአስር ዓመታት በፊት በኒያ ፋውንዴሽን የተቋቋመውና ጆይ ኦቲዝምና ተዛማጅ ልዩ የእድገት ፍላጐት ያላቸው ልጆች ማዕከል፤ ለችግሩ የመፍትሔ አካል በመሆን እየሠራ ይገኛል፡፡ ማህበሩ የተቋቋመበትን 10ኛ ዓመት በአልና በአለም አቀፍ ደረጃ በያዝነው ወር እየተከበረ ያለውን የኦቲዝም ቀን ምክንያት በማድረግ ሰፊ ፕሮግራም አዘጋጅቷል፡፡ ካዛንቺስ በሚገኘው አዲሱ ራዲሰን ብሉ ሆቴል ሰሞኑን በተዘጋጀ ጋዜጠዊ መግለጫ የተጀመረው ፕሮግራም፤ በኢሲኤ አዳራሽ በሚደረግ ታላቅ ሲምፖዚየም፣ የእግር ጉዞና የሙዚቃ ዝግጅት የፋሽን ትርኢት የሚቀጥል ሲሆን በሸራተን አዲስ በሚከናወን የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ፕሮግራም ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

“ተረዱን ተቀበሉን አካቱን” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የዘንድሮ የኦቲዝም ቀን በዓል አስመልክቶ፣ የጆይ ኦቲዝምና ተዛማጅ ልዩ የእድገት ፍላጐት ያላቸው ልጆች ማዕከል መስራችና ማኔጅንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ ዘሚ የኑስ እንደተናገሩት፤ “የኦቲዝም ችግር ለአመታት ምስጢር ሆኖ የቆየና የችግሩ ተጠቂ ልጆችም በቤት ውስጥ በገመድ ታስረው እስከመቀመጥ ድረስ እንዲደርሱ ያደረገ ችግር ነው፡፡

“እነዚህ ሕፃናት የሚደርስላቸውና ከታሰሩበት ገመድ ፈትቶ ነፃ በማውጣት፣ ህይወታቸውን በተስተካከለ መንገድ እንዲመሩ የሚያስችላቸው ስልጠናና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ለዚህ ደግም እያንዳንዱ ሰብአዊ ፍጡር ኃላፊነት አለበት” ብለዋል፡፡ ልጆቹ በራሣቸው ዓለም ውስጥ የሚኖሩና የራሣቸው ባህርያት ያሉዋቸው በመሆኑ እነዚህን ባህርያት ተቀብለን ልንረዳቸውና ልንንከባከባቸው ይገባል፡፡ መንግስትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት፣ በጉዳዩ ላይ ትኩረት በመስጠት ልጆቹ ስልጠናና ትምህርት የሚያገኙባቸው ማዕከላት በየአካባቢው ማቋቋምና ልጆቹን መቀበል ይገባልም ብለዋል፡፡ በእሣቸው የተቋቋመው ማዕከል በአሁኑ ወቅት 68 ልጆችን ተቀብሎ ትምህርትና እንክብካቤ በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከ480 በላይ ልጆች በስልጠና እንደሚገኙና ከቦታቸው ውስንነት የተነሣም የሕብረተሰቡን ፍላጐት ለማሟላት እጅግ መቸገራቸውን ጠቁመዋል፡፡ መንግስት እነዚህን ልጆች ሊታደጋቸውና ቢያንስ በየክፍለ ከተማው አንድ የኦትስቲክ ልጆች ስልጠና ማዕከል መቋቋም እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙት ከሁለትና ሶስት የማይበልጡ ማዕከላት ልጆቻቸውን ለማስመዝገብና ስልጠና አግኝተው የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ ለማድረግ ጥረት ያደርጉ የነበሩ በርካታ ወላጆች ጥረታቸው አለመሳካቱን ሲናገሩ ይሰማል፡፡ ለዘመናት በዝምታ ተቆልፈው፣ በር ተዘግቶባቸውና እንደ ልዩ የፈጣሪ ቁጣ እየታዩ ተገለው ይኖሩ የነበሩ ኦትስቲክ ልጆች፤ ዛሬ በተሻለ ሁኔታ አደባባይ ወጥተው ለመታየትና ለችግራቸው መፍትሔ ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርጉ አካላት በመፈጠራቸው እንቅስቃሴውን በማሣደግ ልጆቹ የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ በማስቻሉ በኩል መንግስትም ሆነ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል፡፡ የህፃናቱ ስቃይና ሰቆቃ ሊገታና ከተደበቁበት ወጥተው ነፃ ህይወት መምራት ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁላችንም ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡

 

 

Read 4669 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 08:17