Monday, 03 April 2017 00:00

ኮርኳሪ የፖለቲካ ቀልዶች!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(150 votes)

ዓይኖች ሲገለጡ -----
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ አንድ ማለዳ፣ እየሮጡ የአካል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ፣ የመንገዱ ጥግ ላይ ካርቶን የያዘ አንድ ትንሽ ልጅ ያያሉ፡፡  
 ስለ ልጁ ለማወቅ ጉጉት ያድርባቸውና ጠጋ ብለው፤
“ማሙሽዬ፤ ካርቶኑ ውስጥ ምንድን ነው ያለው?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡
ትንሹ ልጅም፤ “የድመት ግልገሎች ናቸው፤ አዲስ የተወለዱ ሙጭሊቶች!” በማለት መለሰላቸው፡፡  
ጆርጅ ቡሽ ሳቅ አሉና፤ “ግን ምን ዓይነት ሙጭሊቶች ናቸው?” ብለው ጠየቁት፡፡
ልጁም፤ “ሪፐብሊካን!” አላቸው፡፡
“በጣም ደስ ይላል!” አሉና ሩጫቸውን ቀጠሉ፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ ቡሽ፣ ከሥራ ባልደረባቸው ከዲክ ቼኒ ጋር በዚያው መንገድ ላይ ሲሮጡ ትንሹን ልጅ እዚያው ቦታ ላይ፣ ከእነ ካርቶኑ ተቀምጦ በድጋሚ ያዩታል፡፡
“ይሄንን ነገር ማየት አለብህ” አሉና ዲክ ቼኒን ይዘው ወደ ልጁ ተጠጉ፡፡
“እነዚህን ሙጭሊቶች ተመልከት፤ አያምሩም!” አሉ ቡሽ፤ ለባልደረባቸው፡፡
ከዚያም “ማሙሽዬ፤ እስቲ ለጓደኛዬ  ምን ዓይነት ሙጭሊቶች እንደሆኑ ንገረው” ይሉታል፤ ለልጁ፡፡
ትንሹ ልጅም፤ “ዲሞክራት ናቸው!” አለ ፍርጥም ብሎ፡፡
ጆርጅ ቡሽ ግራ ተጋብተው፤ “እንዴ ባለፈው ጠይቄህ እኮ ሪፐብሊካን ናቸው ብለኸኝ ነበር፡፡ አሁን ምን ተፈጠረ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡
ልጁም፤ “አሁን አይኖቻቸው ተገልጧል!” አላቸው፡፡
(ዓይናቸውን ሲገልጡ፣ ፓርቲያቸውን ቀየሩ እንደማለት!)
 *   *   *
“Lenin in Poland”
ከ1960ዎቹ እስከ 80ዎቹ አጋማሽ ግድም ሶቭየት ህብረትን የመሩት ፕሬዚዳንት ብሬዥኔቭ፤ 50ኛውን የሩሲያ አብዮት ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ “Lenin in Poland” (“ሌኒን በፖላንድ”) የተሰኘ ስዕል በክፍያ ለማሰራት ይፈልጋሉ፡፡   
ችግሩ ግን የሩሲያ ሰዓሊያን በሙሉ በሪያሊስት የአሳሳል ዘይቤ የሰለጠኑ ነበሩ፡፡ እናም “በእውን ያልተከሰተ ሁነት መሳል አይሆንልንም” ብለው አሻፈረን አሉ፡፡
በሞስኮ የሚገኙ ታላላቅ ሰዓሊያንን በሙሉ ጠይቀው ያልተሳካላቸው  ብሬዥኔቭ፤ በስተመጨረሻ ሌቪ የተባለ አይሁዳዊ ሰዓሊ ዘንድ ይሄዳሉ፡፡  
ሌቪም አላሳፈራቸውም፡፡ “በእርግጥ እኔ የምመርጠው እውነተኛ ሁነቶችን መሳል ነው፤ ለእርስዎ ለጓድ ብሬዥኔቭ ስል ግን እሰራዋለሁ። ይሄ ለእኔ ትልቅ ክብር ነው” በማለት እሺታውን ገለጸላቸው፡፡
ሌቪ ወዲያው ሥራውን ጀመረ፡፡ ሆኖም ብሬዥኔቭ የደረሰበትን ለማየት ወደ ስቱዲዮው መመላለስ አበዙ፡፡ ሰዓሊው ግን ቁርጡን ነገራቸው። “ሥራዎቼ ከመጠናቀቃቸው በፊት ለማንም አላሳይም” አላቸው፤ ፍርጥም ብሎ። ብሬዥኔቭም አላንገራገሩም፡፡ (ሁለት ወዶ የለማ!!)
በመጨረሻም ስዕሉ ተጠናቆ የሚመረቅበት ዕለት ደረሰ፡፡ ሌቪ በጨርቅ ከተሸፈነው ስዕል ጐን በኩራት ተኮፍሶ ቆሟል፡፡ ብሬዥኔቭ፤ ሌቪን ለታዳሚው አስተዋወቁና ለሩሲያ 50ኛ ዓመት የአብዮት በዓል ለህዝቡ ያዘጋጁት ስጦታ፣ ሌኒን በፖላንድ ያደረገውን ታሪካዊ ጉብኝንት የሚዘክር ምርጥ ስዕል እንደሆነ ተናገሩ፡፡
ስዕሉ የተሸፈነበት ጨርቅ ሲገለጥ ግን ሁሉም በድንጋጤ የሚገባበት ጠፋው፡፡ ሌቪ የሰራው ስዕል አንድ ወንድና ሴት አልጋ ላይ ተኝተው የሚያሳይ ነበር፡፡
“ሰውየው …ማ…ነ…ው?” ብሬዥኔቭ እየተንተባተቡ ጠየቁ፡፡
ሌቪም፤ “ትሮትስኪ ነው ---- ችግር አለ?”
(ትሮትስኪ የእነ ሌኒን ተቀናቃኝ የነበረና ያስገደሉት ፖለቲከኛ ነው)
 “ሴትየዋስ?” ብሬዥኔቭ ጠየቁ
 “የሌኒን ሚስት ናት፤ ጓድ ብሬዥኔቭ”
 “ሌኒንስ የታለ?”
“እሱ ፖላንድ ነው!”
*   *   *
ሙስና ቁጥር አያውቅም!
አንድ የህንድ ሚኒስትር ለጉብኝት ወደ አሜሪካ ይሄዳሉ፡፡ እዚያም በአሜሪካ አቻቸው የመኖሪያ ቤት ውስጥ እራት ይጋበዛሉ፡፡ ሚኒስትሩ በሴናተሩ የተንጣለለ ቪላና እጅግ ውድ በሆኑ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች፣ በልዩ የመዋኛ ገንዳውና በቴኒስ መጫወቻ ሜዳው (tennis court) በእጅጉ ይደመማሉ፡፡ እናም ጠየቁ ሚኒስትሩ፡-
“እኔ የምልህ-----በሴናተር ደሞዝ ይሄን የመሰለ ቤት እንዴት መስራት ቻልክ?”
 ሴናተሩም ፈገግ አሉና፣ የህንዱን ሚኒስትር ወደ መስኮቱ ጋ ይዘው በመሄድ ወደ ውጭ እያሳዩዋቸው፤
“እዚያ ጋ ወንዝ ይታይሃል?”
 “አዎ፤ ይታየኛል” መለሱ ሚኒስትሩ
“መሃል ላይ የተሰራው ድልድይስ?”
“እሱም ይታየኛል!”
“በቃ ከእሱ ላይ 10 በመቶ!”
ሴናተሩ ሃቋን ተነፈሱ፡፡  
(ከድልድዩ ማሰሪያ ላይ 10 ፐርሰንቷን ልፌ ነው ማለታቸው ነው!)
ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የአሜሪካው ሴናተር በተራቸው ለጉብኝት ወደ ህንድ ሄዱ፡፡ የህንዱ ሚኒስትርም ውለታ ለመመለስ ሴናተሩን እቤታቸው እራት ጋበዟቸው፡፡ ሴናተሩ፤ የሚኒስትሩን መኖሪያ ቤት አይተው መጥገብ አልቻሉም፡፡ ትንግርት ሆነባቸው፡፡ ትልቅ ቤተ መንግስት - በተመረጡ ውድ የስዕል ሥራዎች ያሸበረቀ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለሟሎች ወዘተ…
ሴናተሩ ወደ ሚኒስትሩ ጠጋ ይሉና፤
“ቆይ ግን በህንድ የሚኒስትር ደሞዝ፣ ይህን ሁሉ ሃብት ከየት አመጣኸው?”
ሚኒስትሩም ሴናተሩን ወደ መስኮቱ ይዘው በመሄድ፤
 “እዚያ ማዶ ወንዝ ይታይሃል?”  
 “እንዴታ!” መለሱ ሴናተሩ፡፡
 “ድልድዩስ ይታይሃል?”
አሁን ሴናተሩ ግራ ገባቸው፡፡ ቀረብ --- ራቅ እያሉ ሚኒስትሩ ወደ ጠቆሟቸው አቅጣጫ ሲያማትሩ ቆዩና፤ “ፈጽሞ ድልድይ የሚባል ነገር አይታየኝም” አሉ
“በቃ 100 ፐርሰንት!” አሉ፤ የህንዱ ሚኒስትር በድል አድራጊነት ስሜት፡፡
(ለካ የድልድይ ማሰሪያውን በጀት በሙሉ ወደ ኪሳቸው ከተው ነው!)
*   *   *
እሾህን በእሾህ ------
አንድ የመንግሥት ባለስልጣን ከኮንትራክተር ባለሃብት ላይ ጉቦ ይቀበልና በቁጥጥር ስር ይውላል። የቅርብ ወዳጁ የታሰረበት ወህኒ ቤት ሊጎበኘው ይሄድና፤
 “አሁን እንግዲህ ከዚህ ጉድ እንዴት ልትወጣ ነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
የመንግስት ባለስልጣኑም ዘና ብሎ፤ “እኔ ችግር ውስጥ የገባሁት ጉቦ በመቀበል ነው፤ ለሚመለከተው አካል ጉቦ ሰጥቼ ከዚህ ችግር እወጣለሁ” ሲል መለሰለት፡፡
(እሾህን በእሾህ ይሏል እንዲህ ነው!)
*   *   *
የትዳር ፖለቲካ
የ91 ዓመት አዛውንትና የ89 ዓመት ሚስታቸው ከ66 ዓመት የትዳር ህይወት በኋላ ፍቺ ለመፈጸም ወደ ጠበቃቸው ዘንድ ይሄዳሉ፡፡
ጠበቃው ተገርሞ ጥንዶቹን ይጠይቃቸዋል፤
“ሁለታችሁም በትዳር ህይወታችሁ ደስተኛ ካልነበራችሁ፣ ለምን ይሄን ያህል ዘመን አብራችሁ ኖራችሁ?”
ጥንዶቹም መለሱ፤ “ልጆቻችን እስኪሞቱ እየጠበቅን ነበር”
*   *   *
ሚስት ለባሏ እንዲህ ትላለች፡-
“ማሬ፤ ምን እየሰራህ ነው?”
“የጋብቻ ሰርተፊኬታችንን እያነበብኩ”
“ለምን?”
“የጋብቻችን ማብቂያ ቀን (expiry date) መቼ እንደሆነ ለማወቅ ፈልጌ!”
(ያልታደለ ትዳር ኤክስፓየሪ ዴት አለው!)

Read 21531 times