Wednesday, 04 April 2012 08:39

ለከተማ ነዋሪዎች ውሃ የሚያጠጣው የገጠር ቀበሌ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቱ ያሉ ሁሉም የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከተሞች ማለት ይቻላል፣ ለመጠጥ ለአካባቢና ለግል ጤና አጠባበቅ የሚያውሉት በቂ የንፁህ ውሃ አቅርቦት የላቸውም፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአዲስ አበባ ከተማ የውሃ አቅርቦት 73 በመቶ እንደነበር የከተማዋ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለሥልጣን ሲገልጽ ነበር፡፡ ይህ ማለት ከነዋሪው ሕዝብ መካከል የውሃ አቅርቦት የሚያገኘው ከመቶ ሰዎች ውስጥ 73ቱ ብቻ ናቸው ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ 27 ሰዎች ከሌሎች ድርሻ እየተቀነሰ የሚያገኙ ናቸው እንደማለት ነው፡፡የዛሬ ሁለት ሳምንት ባለሥልጣኑ፣ የአቃቂ ከርሰ ምድር ውሃን ባስመረቀበት ወቅት፤ የመዲናዋ የውሃ አቅርቦት 93 በመቶ መድረሱን ሲያውጅ፤ ብዙዎች ለዘመናት የቆየው የውሃ ሰቀቀናቸው የሚቃለል መስሏቸው በደስታ ፈንድቀው ነበር፡፡ ውሃ የማያገኝ ሰው ቁጥር ከ27 ወደ ሰባት ዝቅ ብሏል ሲባሉ ለምን አይደሰቱ!

ምን ዋጋ አለው ታዲያ - ደስታው ከአንድ ቀን አላለፈም፡፡ ተሻሻለ የተባለው አቅርቦት ቀደም ሲል የነበረውንም ሲያሳጣ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ የከርሰ ምድሩ ውሃ እሁድ ተመርቆ፣ በማግስቱ ሰኞ ለብዙ ጊዜ ቀን እየጠፋ ማታ የሚመጣው ድፍርስና ቆሻሻ ውሃ እንኳ ከነጭራሹ ጠፋ፡፡ በታንከር የተጠራቀመ ውሃ ተሟጦ፣ የሚጠጣ ቀርቶ ምግብ ማብሰያና ዕቃ ማጠቢያ እንኳ ችግር ሆኖ ነበር፡፡ በሳምንቱ እሁድ ሌሊት ውሃ ሲመጣ የነበረው ደስታ ቀላል አልነበረም፡፡ በማግስቱ ባይመጣስ በሚል ገርጂ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ያንኑ ድፍርስ ውሃ እየተሻሙ፣ ባላቸው ዕቃ ሁሉ ሲቀዱ አስተውያለሁ፡፡

ከዚሁ የውሃ እጥረት ጋር በተያያዘ አንድ ያስገረመኝን ነገር ላጫውታችሁ፡፡ አንድ የገጠር ቀበሌ ለዞን ዋና ከተማና ለሌላ አነስተኛ ከተማ ንፁህ የመጠጥ ውሃ እያቀረበ (እየሸጠ) ነው ማለትን ብትሰሙ ትቀበላላችሁ? እስካሁን ባለው አሠራር፣ የከተማ አስተዳደር ባቅራቢያው ላለ የገጠር ቀበሌ ውሃ ቢያቀርብ እንጂ በተቃራኒው ውሃ ከገጠር ወደ ከተማ ሲፈስ ማየት የተለመደ ስላልሆነ መቀበል ይከብዳል፡፡ ነገር ግን ሰሞኑን ወደ ባሌ ዞን በሄድኩባት ወቅት ያስተዋልኩት እውነት ይሄ ነው - ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅራቢው የሮቤ መሊዩ ቀበሌ ሲሆን ተቀባይዋ ደግሞ የባሌ ዞን ዋና ከተማ ሮቤ ናት፡፡

እንዴት መሰላችሁ? የዛሬ 10 ዓመት ገደማ ማኅበረሰቡ፣ መንግስት፣ ዎተር አክሽንና ወተር ኤድ በመተባበር ሦስት ምንጮች አጐልብተው ለማኅበረሰቡ አስረከቡ፡፡ የውሃው አስተዳደር ከሕዝቡ በተመረጠ ቦርድ የሚመራ ሲሆን፣ እስካሁን ባደረገው እንቅስቃሴ ከ56 ኪ.ሜ በላይ ርዝመት ያለው ዋና የቧንቧ መስመር፣ 91 ኪ.ሜ የውስጥ ለውስጥ የማከፋፈያ መስመሮችና 80 የውሃ ማደያ ጣቢያዎች (ቦኖዎች) መሠራታቸውን የሮቤ መሊዩ የገጠር መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጅማ ታደሰ ገልፀዋል፡፡

ጽ/ቤቱ ለ17 የሰፈራ መንደሮች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን አንዱ መንደር እስከ 10ሺ ነዋሪ ሊይዝ ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሮቤ የዞኑ ዋና ከተማ ሆና የውሃ እጥረት ስላጋጠማት ለ44ሺ 443 የከተማዋ ነዋሪ፣ ለ22ሺ 133 የአለም ገና ነዋሪ፣ እንዲሁም ለ72 ሺ 367 የገጠር ሕዝብ በአጠቃላይ ከ139ሺ በላይ ሕዝብ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንደሆነ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ከገጠሩ ነዋሪ ሕዝብ 149 ሰዎች የግል የቧንቧ ውሃ መስመር አስገብተዋል፡፡ አንድ ሰው በግል የቧንቧ ውሃ ለማስገባት ጥያቄ ሲያቀርብ ማሟላት ያለበት ግዴታ አለ፡፡ መፀዳጃ ቤት የሠራ፣ ንፁህ ግቢ ያለውና የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ያዘጋጀ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ዓይነት ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ መፀዳጃ ቤትና ንጽህናው የተጠበቀ ግቢ ያላቸው 3ሺ 279 አባወራዎች እንዳሉ አቶ ጅማ ተናግረዋል፡፡

የሮቤ መሊዩ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ሲወጠን፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለሌለው የገጠሩ ሕዝብ እንጂ ለሮቤ ከተማ ጭምር አልነበረም፡፡ ነገር ግን የዞን ዋና ከተማ ሆና የውሃ እጥረት ስላጋጠማት፣ ከፕሮጀክቱ ውሃ አንድትጠቀም ቢደረግም  ክፍፍሉ ግን ፍትሃዊ እንዳልሆነ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡ ከፍተኛ የውሃ ድርሻ እየተጠቀመ ነው - ያውም በዝቅተኛ የታሪፍ ክፍያ፡፡ የገጠሩ ሕዝብ ለአንድ ሜትር ኩብ ውሃ (ለአንድ ሺ ሊትር) 1.30 ሲከፍል፣ የሮቤ ከተማ መጠጥ ውሃ ጽ/ቤት ተመሳሳይ መጠን ያለው ውሃ በ0.23 ሳንቲም ገዝቶ ለደንበኞቹ በጥሩ ትርፍ ገደማ ይሸጥ ነበር እስከ 1999 ዓ.ም፡፡

ከአራት ዓመት በፊት የታሪፍ ማሻሻያ ተደርጐ የገጠሩ ሕዝብ  በሜትር ኩብ 1.50 እንዲከፍል ሲደረግ፣ የሮቤ ከተማ መጠጥ ውሃ ጽ/ቤት ግን ተመሳሳይ መጠን ውሃ በ0.72 ሳንቲም ገዝቶ፣ ለደንበኞቹ በ2.50 በመሸጥ ከፍተኛ ትርፍ እያገኘ ነው፡፡ ስለዚህም ውሃ አምራቹ ቦርድ የጥገና ወጪ ችሎ፣ የሠራተኞች ደሞዝ ከፍሎ፣ የማስፋፊያ ሥራዎችን አከናውኖ፣ ገቢና ወጪን አጣጥሞና ሕልውናውን አስጠብቆ በዘላቂነት መቀጠል የሚያስችል የተመን ማሻሻያ እንዲደረግ ከሕዝቡ ጋር መምከራቸውን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ መፀዳጃ ቤት፣ ሻወር፣ የዕቃ ማጠቢያና ማድረቂያ፣ የቆሻሻ መድፊያ፣ … ያላቸው 17ቱ መንደሮች፣ በ1971 ወይም 1972 በሰፈራ የተሰባሰቡ እንደሆኑ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡ የእያንዳንዱ ገበሬ ግቢ በጣም ሰፊ ሲሆን አንዱ ከሌላው በቁልቋል አጥር ተለይቷል፡፡ ቤቶቹ፣ እንደየግለሰቡ ገቢ የተለያዩ ናቸው - የቆርቆሮና የሳር፡፡ ሁሉም ግቢ ማለት ይቻላል የተጫነ ጋሪ ማስገባት የሚችል የቆርቆሮ ወይም የቁልቋል መግቢያ በር አለው፡፡

መንደሮቹ በፕላን የተሠሩ ስለሆነ አንድ መስቀለኛ ላይ ቆሞ ረዥም ርቀት ማየት ይቻላል፡፡ እስቲ አንዱን ግቢ ላስጐብኛችሁ፡፡ ገና ወደ ውስጥ ሲገባ መጀመሪያ ቀልብን የሚስበው ንፅህናው ነው፡፡ የወዳደቀ ቆሻሻ በፍፁም አያዩም - ፅዱ ነው፡፡ መኻል ላይ መኖሪያ ቤት፣ ከጐን ወይም ከኋላ ኩሽናና እንግዳ ሳይኖር ቡና ተፈልቶ ቤተሰቡ አረፍ ብሎ እየተጫወተ የሚዝናናበት ቤት ያያሉ፡፡ ወደ አንዱ አቅጣጫ ሲያማትሩ፣ ዕቃ ማጠቢያ ወይም ሻወር ቤት ይኖራል፡፡ የሻወር ቤቱንና የዕቃ ማጠቢያውን አሠራር ልንገራችሁ፡፡ ሻወር ቤቱ አንድ ሜትር ጥልቀት ይቆፈርና ጉድጓዱ ከወንዝ በተለቀመ ድቡልቡል ድንጋይ ይሞላል፡፡ በቆርቆሮ ወይም በሳር ዙሪያውና ጣሪያው ይከደንና ይታጠቡበታል፡፡ ሲታጠቡበት ታዲያ ውሃ ወደ ውጭ አይፈስም - ወደ ውስጥ ይሰርጋል፡፡ ዕቃ ማጠቢያውም ተመሳሳይ ሲሆን አፉ ጠበብ ብሎ ወንፊት ነገር ክዳን አለው፡፡ ወንፊቱ ለምን መሰላችሁ? ውሃውን ብቻ አሳልፎ የምግብ ትርፍራፊዎች እንዲያስቀር ነው፡፡ ዕቃዎቹ ከታጠቡ በኋላ የሚደርቁበት መደርደሪያም አላቸው፡፡

የተመለከትኳቸው ቤቶች በሙሉ የቧንቧ ውሃ መስመር አስገብተዋል፡፡ ከወደ ጓሮ ደግሞ የዶሮ ቤት፣ የከብቶች ቤት፣ የእህል ጐተራ፣ ራቅ ብሎ ደግም ንፁህ ክዳን ያለው ጣሪያና ዙሪያው የተሸፈነ ሽንት ቤት፣ ትንሽ ራቅ ብሎ አትክልት ውስጥ የቆሻሻ መጣያ ጉድጓድ ያያሉ፡፡

ዋናው ቤት የተለየና የሚገርም ነው፡፡ ወለሉ ውድ ውድ ምንጣፎች ያልለበሰ ሳሎን አያገኙም፡፡ ዙሪያውን ፍራሽ ተነጥፎ በሚያማምሩ የጥልፍ ልብሶች አሸብርቆና ትራስ ተደርድሮ ያያሉ፡፡ ኮርኒስና ግድግዳው ላይ የተለያዩ ባህላዊና የወግ ዕቃዎች፤ የሚያማምሩ የውጭ አገር ሥዕሎችም ተሰቅለውና ተለጥፈው ያገኛሉ፡፡ መኝታ ቤቱም ተመሳሳይ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ በእያንዳንዱ ቤት የተለያዩ ዘመናዊ ዕቃዎች የያዘ ብፌ መኖሩ ነው፡፡

ሐጂ ፊይሰል፣ ሁሉም ነገር ተሟልቶላቸው ዘመናዊ ኑሮ እየኖሩ እንደሆነ ነገር ግን  አንድ ነገር ስለጐደላቸው ቅር እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ “ንፁህ የመጠጥ ውሃ በማግኘታችን ልጆቻችን በውሃ ወለድ በሽታ አይታመሙብንም፡፡ ግቢያችንን በንፅህና እንይዛለን፡፡ ቆሻሻ የትም አይጣልም፤ ጉድጓድ ቆፍረን እንጨምራለን፡፡ እንደ ድሮው በየጫካው፣ በየቁጥቋጦው፣ … መፀዳዳት የለም፤ ሽንት ቤት ቆፍረን፣ ዝንብ እንዳይገባ ከድነን፣ ተጠቅመን ስንወጣ እጃችንን በሳሙና እንታጠባለን፡፡ የጐደለንና ቅሬታ የፈጠረብን ነገር የመብራት እጦት ነው፡፡ መብራት ቢገባልን፣ ቴሌቪዥን፤ ማቀዝቀዣ፣ … እንገዛለን፡፡ ኢንተርኔት እንጠቀማለን፡፡ በቅርባችን ልጆቻችንን ልከን የምናስተምርባት ሻሎ የተባለች ከተማ አለች፡፡ መንግሥት ከዚያ መብራት ጠልፎ እንዲያስገባልን እንማፀናለን” ብለዋል፡፡

የሮቤ-መሊዩ የውሃ ፕሮጀክት ቢሮ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ የአካባቢ ንፅህናና የግል ጤና አጠባበቅ ትልቅ ራዕይ እንዳለው አቶ ጅማ ይናገራል፡፡ ከፍ ሲል በተጠቀሱት የጤና ዘርፎች በቀበሌ፣ በወረዳና በዞን ደረጃ ተሸልሟል፡፡ አሁን የሚወዳደረው በክልል ደረጃ ካሉ ተመሳሳይ ተቋማት ጋር ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በምሥራቅ አፍሪካና በአኅጉር ደረጃ፣ በመጨረሻ ደግሞ ሁሉንም የጥራት መስፈርቶች አሟልቶ ከዓለም አቀፍ የደረጃ መዳቢ ድርጅቶች (አይ ኤስ ኦ) የጥራት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት በማግኘት አገሩን ማስጠራት እንደሆነ አቶ ጅማ ታደሰ አስታውቋል፡፡

የውሃ ፕሮጀክቱ ቢሮ፣ 39 ቋሚ ሠራተኞች፣ አንድ ክሬሸር (ድንጋይ መፍጫ) እና አንድ የጭነት መኪና አለው፡፡

 

 

Read 2506 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 08:44