Wednesday, 04 April 2012 08:39

ጫፍ ፍቅር ሀይቅ ጋ ወራጅ አለ!

Written by  ረድኤት መስፍን rediat.kedan@gmail.com አዋሳ
Rate this item
(2 votes)

አዲስ አበባ የምር ናፍቃኛለች፡፡ ልክ ፍቅረኛውን ፒያሣ መሀሙድ ጋር እንደቀጠረ ጐረምሳ፡፡ እኔ አዋሳ ነው ያለሁት፡፡ አዋሳ ደግሞ ሙቀት አለ፡፡ ሙቀት ስላችሁ የፀሐይ እንዳይመስላችሁ፡፡ የመሬት ሙስና የወለደው የፖለቲካ ሙቀት እንጂ፡፡ እሳት እንደነካው ፌስታል አንጀት የሚያኮማትር ትኩሳት! እንጨት እንደወጋው የፊት ቁስል ሆድ የሚያሳምም ወላፈን! ቀጣዩ በረሀ ወለድ ሃሜት ግን ጭራሽኑ ተስፋ አስቆረጠኝ፡፡ የፌደራሉ መንግስት ሀዋሳን እንደ ማደጐ ልጅ ወስዶ በሞግዚትነት ሊያሳድጋት ነው፡፡ አላመንኩም፤ አይደረግም ብዬም ልጮህ ነበር፡፡ አላደረኩትም፡፡ የመንግስቴን ሰምና ወርቅ ፀባይ አውቀዋለሁ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት ሽፈራው ሽጉጤ “የሆነ በሬ ወለደ ዓይነት የኪራይ ሰብሳቢዎች አሉባልታ” ሲሉ ጭንቀቴ ላይ ቀዝቃዛ ልማታዊ ውሀ አፈሰሱበት፡፡

አዋሳ ላንጋኖ ለሽርሽር ሄጄ ያየሁሽ…

ይገባኛል፡፡ ከአዱ ገነት መውጣት ያስጨንቃል፡፡ መራቅ ያስፈራል፡፡ መሸሽ ሆድ ያባባል፡፡ ደግሞስ ወዴት ይኬዳል? የክፍለ ሀገራት ቅጥ ያጣ የዘውጌ ፖለቲካ፣ ወንዝ የማያሻግር የሠፈር ኢኮኖሚ እና ባህላዊ የአኗኗር ዘይቤያቸው አንገት ያስደፋል፡፡

በዚያ ላይ ባቅላባ የላቸውም፡፡ የኛ ዓላማ ግን አዋሳን መውረር ነውና የምግብ ጥያቄ ተቀባይነት የለውም፡፡ ታጋይ ሆዳም ነው እንዴ?

የመሀል ሠፈሪ ልጆች አዲስ ከተማ ት/ቤት ጐን ካለው መነሀርያ ትኬት መቁረጥ ትችላላችሁ፡፡ ከሳሪስ በታች ወይም የጥጉ መደብ ባለቤቶች፡፡  ከአዲሱ የቃሊቲ መነሀሪያም የአዋሳን “በሮ ገዳይ” ሚኒባሶች ታገኛላችሁ፡፡ ዕቃ እንዳትረሱ፡፡ መታወቂያ ካሜራ፣ ደብተር፣ ብዕር፣ እርሳስ፡፡ ት/ቤት የምንሄድ አስመሰልኩት እንዴ? በፍፁም! አዋሳ ለሚቆዝም፣ ለሚያዜም፣ ለሚጽፍና ለሞንጭሮ አደር ተመራጭ ናት፡፡ እጅግ የተከበሩት የአለም ሎሬት ጋሽ አፈወርቅ ለምን ሁለተኛ ቪላቸውን አዋሳ ላይ የገነቡ ይመስላችኋል? ከወፎቹ እና ከምሽቷ ፀሐይ ጋር የሚደንሰው ሃይቅ አፍዟቸው እኮ ነው፡፡ ምርጡ እና ብልጡ ሯጭ አትሌት ሃይሌ ለምን ሀዋሳ ላይ 250 ሚሊዮን ብር የከሰከሰ ይመስላችኋል? በጥፊ የማይማታው ነፋስና የማይሰለቸው የቱሪስት ገበያ መስጠት እኮ ነው፡፡ ሀመልማል ማዲንጐና ላፎንቴኖች ለምን ወደ ሀዋሳ እያሰለሱ የሚበሩ ይመስላችኋል ከቀረጥ ነፃ የሆኑ ግጥምና ዜማ ለመመንተፍ እኮ ነው፡፡ እዚህ አዋሳ ሁልጊዜ ጥምቀት ነው፡፡ ሸገር በዓመት አንድ ጊዜ አይደል የብሔር (ብሔረሰቦች) ሙዚቃ የምትኮመኩመው፡፡ (ህዳር 29!)

ባይገርማችሁ ራሱ ቴዲ አፍሮ የአዋሳ ቀንደኛ ቲፎዞ ነው፡፡ የአዋሳ ወዳጆቼ “ላምባዲና” የተፀነሰው፣ የተወለደውና መዳህ የጀመረው አሞራ ገደል ነው ብለው ምለውልኛል፡፡ እኔ ያረጋገጥኩትን ልንገራችሁ፡፡ ያውም ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ከሰጠው ቃለ መልልስ “ጃ ያስተሰርያልን ለመጨረስ ብዙ ደክሜያለሁ፡፡ ባጠናቀኩበት

ምሽት ከፍተኛ የእርካታ ስሜት ተሠምቶኛል፡፡ ከዚያም መኪናዬን አስነስቼ በረርኩ፡፡ ወደ አዋሳ ነበር፡፡ እያለቀስኩ፣ እያነባሁ፣ እየተንሠቀሠኩ፡፡ /ቃል በቃል አይደለም፡፡ ትንሽ ሳላከብደው አይቀርም/

አለላችሁ ደግሞ የመፀሀፍት ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ ያልሆነ ፍንዳታ ደራሲ፡፡ ዴርቶጋዳን አንብበው ሳይጨርሱ ሮማቶሀራን፣ ተልሚድን ለመግዛት የደመወዝ ቀኑን ሲጠብቁ ተከርቸመን በአናት ባናቱ እየቀፈቀደ ያሥቸገረ፡፡ ይስመዓከ ወፍራም የማንጐ ጁሡን እየጠጣ መፀሀፍት የት እንደሚያምጥ ያውቃሉ? ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ቦሌ፣ ቄራ ሜክሲኮ፡፡ ወዳጄ ተሸውደዋል፡፡ አዋሳ ሪፈራል ሠፈር ሂዱና ጠይቁ፡፡ ፎርጅዱን ሳይሆን ኦርጅናሉን የወርቁን ልጅ ታገኙታላችሁ፡፡ ዕድለኛ ከሆናችሁም የቀጣዩን መፀሀፍ “ዴራቲም” (አባ - ግምት ብጤ ነው) አጤሬራ ላፍ አርጋችሁ መመረሽ፡፡

እንደመታደል የደቡብ መንገዶች እንደ ሌሎቹ አንጀት አይደሉም፡፡ በሠቀቀንም ስጋን የሚጨርስ፣ በፍርሀት ነፍስን የሚያስጨንቅ ተፈጥሮ የላቸውም፡፡ እዚህ የአባይ በረሀ ብሎ አስደንጋጭ ገደል፣ የደብረሲና የመሬት ውስጥ አስፈሪ ብሎ የዋሻ መንገድ የለም፡፡ 275 ኪሎ ሜትሩን ለሽ ብለው አለበለዚያ በኤርፎን የሂቦንጐ ሙዚቃን እያጣጣሙ ወይም በሾፌሩ የግዴታ ምርጫ ጨምባላላን እየኮመኮመ አዋሳ ከች ነው፡፡

Occopy Awassa

“ጉዞ ወደ አዋሳ

የሀገሩ ጐጆው ዳሰሳ

የሚመገቡት ዓሣ

ብራቸው በዓካፋ”

የግጥሙ ባለቤቶች በ1952 ዓ.ም ወደ አዋሳ የፈሠሡት አርሶ አደሮች ናቸው፡፡ በአቶ ቤቴና ሆጤሳ የተዘጋጀው መፀሀፍ እንደሚጠቁመው … በተለይ በ1953 ዓ.ም በኢትዮጵያና በዩጐዝላቭያ መንግስት ትብብር የሚካሄድ የእርሻ ፕሮጀክት ተከፈተ፡፡ በመጀመሪያ ኦቾሎኒ፣ ቃጫ፣ በቆሎና ሡፍ ማምረት ጀመረ፡፡ በእርሻው ውሥጥ በቋማነትና በጊዜያዊነት የተቀጠሩ ሠራተኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ በጫካ የተከበበችውን ምድር ሞሏት፡፡ በወቅቱ በአካባቢው እንደዚህ ያለ ትልቅ ኢንዱስትሪና ብዙ ገንዘብ የሚያሥገኝ የስራ መስክ ባለመኖሩ እንግዶቹ በገቢያቸው መርቅነው ከላይ የተቀመጠችውን ቅኔ ተቀኝተዋል፡፡

የአዋሳ ዕድሜ ከወጭ ቀሪ ሲሰላ 52 ዓመት ብቻ ነው፡፡ የሸገር ታናሽ፣ የጅማ ታናሽ ታናሽ፣ የደሴ ታናሽ ታናሽ እንደገና ታናሽ… የመቀሌ ግን ብንተወው ይሻላል፡፡ በ13ኛው ክ/ዘመን ከተቆረቆረ ሽማግሌ ከተማ ጋር ማዛመድ የኪራይ ሰብሳቢ ፀሐፊ ፀባይ ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ የአዋሳ ቅርጽ ነዳፊ፣ አባባ ጃንሆይ ናቸው፡፡ ንድፍን ወደ ተግባር የለወጡት ደግሞ በወቅቱ የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ የነበሩት ራስ መንገሻ ስዩም፡፡ ሰውየው ባለፈው ዓመት ከተማዋ 50ኛ ዓመቷን ስታከብር ጠርታቸው ነበር፡፡ ለረጅም ሰዓታትም እጃቸውን አገጫቸው ላይ ጥለው ሲገረሙ ነበር፡፡ ምናልባት ለውስጣቸው እንዲህ እያሉ እያንሾካሾኩ ይሆናል፡፡

ወይ ሚጢጢ አዋሳ

ወይ አዳሬ ሆይ (አዳሬ ማለት የሀዋሳ የቀድሞ፣ እንደገና የቀድሞ ስም)

አገርም እንደ ሰው

እንዲህ ያድጋል ወይ?

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በአሁኑ ወቅት በአዋሳ 7 ክፍለ ከተሞች ይገኛሉ፡፡ ስትመሰረት ከነበሯት 3ሺህ የማይሞሉ ነዋሪዎች ተነስታ አሁን ከ290ሺህ በላይ ልጆቿን አቅፋለች፡፡

የመማፀኛ ከተማ

በመጀመሪያ አዋሳ ወይም በሲዳመኛ ሀዋሳ ማለት ትልቅ (ሰፊ) ማለት ነው፡፡ ከዚያስ? ከዚያማ ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ ታቦር ተራራ ላይ ብቅ ብለው በጫካ እና በዱር አራዊት የተወረረችውን ሥፍራ አስተዋሏት፡፡ ሃይቁ ዓይነ ግቡ ነው፡፡ አየሩ ነፍስን ያለመልማል፡፡ ሜዳው ቦርቁብኝ ያሰኛል፡፡ አፄው ከአሽከሮቻቸው ትንሽ ፈንጠር ብለው አሰቡ፡፡

ይርጋለም የተሰጣት የጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማነት ከብዷት እየተብረከረከች ነው፡፡ አማራጩ አሁን ተገኝቷል፡፡ አዋሳ ለሁሉም ነገር ተስማሚ ናት፡፡ በተለይ እንደ ዶሮ ቆጥ ከሜዳ እየራቁ ላስቸገሩ ከተሞች አዋሳ ምርጥ ምሳሌ ናት፡፡ በተጨማሪም ለቱሪስት መዳረሻነት ምቹ መሆኗ የአባባ ጃንሆይን ልብ ሳያሸፍተው አልቀረም፡፡ እናም ንጉሱ ወደ ምዕራብ አማተሩ፡፡ ያ የሲዳማ አርብቶ አደሮች የተንጣለለ መሬት ነው፡፡ እንደገና ብይ ብይ የሚያካክሉ የንስር ዓይኖቻቸውን ወደ ሰሜን መለሡ፡፡ ይህ ደግሞ የአርሲ ኦሮሞ ገበሬዎች እርሻ ነው፡፡ አዋሳ መሀል ላይ መጣሉን እንደማያውቅ አራስ ልጅ እየተፍለቀለቀች ነበር፡፡ አባ ጠቅልል ፈገግ አሉ፡፡

አዋሳ ከአንድ ትውልድ በላይ ዕድሜ የላትም፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኩነቶች ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ወደ ከተማዋ እንዲጐርፉ አስገድዷቸዋል፡፡ ጨዋታችን እንዲሞቅ ጥቂት ምሳሌዎችን አንስተን እንወርውር፡፡ የመጀመሪያው ከአዲስ አበባ፣ ሀረር፣ ኮረምና ወቅሮ ወደ አዋሳ የገቡት 404 ወታደሮች ናቸው፡፡ ልብ በሉ፡፡ ጊዜው 1953 ዓ.ም ነው፡፡ ከተማዋ ገና ጡት አልጣለችም፡፡ እነዚህ ጡረተኛ ወታደሮች ከተለያዩ የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ከነ ቤተሠቦቻቸው መምጣታቸው በአዋሳ ልዩ ቀለም እንዲፈጠር ግድ ብሏል፡፡ ዛሬ እንኳ በከተማዋ እግራችሁ ሳይቀጥን ብትዞሩ፣ ሠፈሮቿ የቀድሞዎቹን መጤ ሀገር ስም ይዘው ቀርተዋል፡፡ አዲስ ትዝ አላላችሁም፡፡ ጐፋ፣ ዶርዜ፣ ወሎ፣ ጐጃም በረንዳ … ሠፈሮች፡፡

ቱሪዝም ብዙዎች ወደ አዋሳ መጥተው በዚያው ሠምጠው የሚቀሩበት ሁለተኛው ምክንያት ነው፡፡ 94 ኪ.ሜ ሥፋት ያለው ሀይቅ በከተማዋ ይገኛል፡፡ እነርሡ የፍቅር ሀይቅ እያሉ ያቆላምጡታል፡፡ እኔን የተመቸኝ ግን ምኑ መሠላችሁ? ዓሣው! እርስዎየፈሳሽ አድናቂ ከሆኑ የዓሣ ሾርባ አለለዎት፡፡ አስተዳደሩ በበኩሉ ህብራዊት ከተማ እያለ እራሡን ለገበያ አቅርቧል፡፡ እዚህ ቢመጡ እራሥዋን የሚመስል ባህል፣ ወግ፣ ቋንቋና፣ ጨዋታ አያጡም ሲል ያስተዋውቃል፡፡ እኔ ልሙት እውነት ነው፡፡ ባለፈው ጥምቀት በዓይኔ አረጋግጫለሁ፡፡ ጃን ሜዳ መስሎኝ በሀርሞኒኮ አስነክቸዋለሁ፡፡ “ከህልሜ ሥነቃ እዛው ነኝ ለካ” አለ አዝማሪው፡፡

በሌላ በኩል አዋሳ ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሠቦችና ህዝቦች ክልል ርዕሠ መዲና መሆኗ የፖለቲካ ማዕከል እንድትሆን ዕድል ፈጥሮላታል፡፡ ላለው ይጨመርለታል ነው ነገሩ፡፡ ይህም ከ56 በላይ ብሔሮች ያቀፈው ክልል ቢያንስ አንዱን ወኪል ለክልሉ ፌደሬሽን ም/ቤት አባልነት ወደ አዋሳ እንዲልክ ያሥችለዋል፡፡ ይህም አዋሳን ከሌሎች አቻ ክልሎች ሳይለያት አይቀርም፡፡ እባካችሁ ሁለት (የክልል እና የብሔረሰቦች) ምክር ቤት ያላቸው ካሉ ጠቁሙኝ፡፡

We are 99%

ማነው ኢትዮጵያ ያለቻት አንዲት ከተማ ነው ያለው?  ቀሽም በሉት ወይም አክራሪ ኒዮሊበራል! በእርግጥ እውነት አለው፡፡ 40 በመቶው የሀገሪቱ አጠቃላይ ምርት /GDP/ የአዲስ አበባ ነው፡፡ 70 በመቶው የሀገሪቱ ምሁራን የተከማቹት ሸገር ላይ ነው፡፡ 90 ምናምን በመቶው የሀገሪቱ ፖለቲካ የሚሾረው እዚያው አዱ ገነት ነው፡፡ ታዲያ ነቆራውን ምን አመጣው?

እውነት ለመናገር አዋሳ የአዲስ አበባን ኮቴ እየተከተለች ያለች ከተማ ነች፡፡ ወይም ፈላስፋው ብሩህ አለምነህ በመፅሀፉ እንዳለው፤ አዲስ አበባን ለመምሠል እንዲሁም ለመሆን ቀን ከሌት መስታወት ፊት ከሚቆሙት ከተሞች ዋነኛው ናት፡፡ እመኑኝ! በአሁኑ ወቅት ፖለቲካው ወደ ደቡብ /አዋሳ/ አጋድሏል፡፡ ኢኮኖሚውም እንደዚያው ነው፡፡ (ባለፉት ወራት ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ አዋሳ ላይ ቅርንጫፉን ሳይሆን ጋኑን መትከሉን ልብ ይሏል) የሙዚቃውንና የፊልሙን ነገር ተውት፡፡ (“ሠው ለሰው” የቴሌቪዥን ድራማ እንኳ አንዴ በፖሊሱ ወላጅ እናት ሀገርነት ሌላ ጊዜ ለጉብኝት አዋሳን ብለዋል) ማህበራዊ ህይወቱን በተመለከተ ማየት ማመን ነው፡፡ በአንፃራዊነት ከሌሎቹ “ቴንሽናም” የክፍለ ሀገር ከተሞች አዋሳ ሙድ አላት፡፡

ጫፍ ፍቅር ሣቅ ጋ ወራጅ አለ!

አልረሳውም ልጅ እያለን ሥድስት ኪሎ ድባብ ውስጥ ያለው ግድንግድ ሀውልት ትምህርትን የፈጠረው ሠው ምስል ነው ተብለን በልምጭ እና በድንጋይ እንቀጠቅጠው ነበር፡፡ ሌባ ነው፡፡ የጨዋታ ጊዜያችንን እንዴት እንደሠረቀብን አትጠይቁኝ፡፡ ዛሬ ለአቅመ ወጣትነት በቅተናል፡፡ በቅተንም እንጀራ ፍለጋ ከጉለሌ ወጣን፡፡ አዋሳንም አየን፡፡ እነሆ ትገረሙ ዘንድ እንዲህም ዓይነት ውብ ከተማ አለች ተባልን፡፡ እኛም አረጋገጥን፡፡ ከሽሮ ሜዳ ሌላ ሠፈር፣ ከማርክስ የሚልቅ ሌላ ሀውልት፣ ከሽማግሌው ዩኒቨርሲቲ የሚግደራደር ሌላ ብላቴና ዩኒቨርሲቲ፣ ከሀገር ፍቅር ቲያትር ባለፈ ሌላ ትያትር፣ ከአዱ ነነትም ሌላ ታናሽ አዱ ገነት ለማየትና ለማወቅ ችለናል፡፡

እመኑኝ! የአዋሣ ራስ በሆነው ታቦር ተራራ ላይ ሽኮኮ ብትባሉ ሻሸመኔ እየተፍለቀለቀች ትታያችኋለች፡፡ እዛ ጋ ጃማካይካውያን ረጃጅም ፀጉራቸውን እየወዘወዙ

“እርጅና መጣና ድቅን አለ ፊቴ

እባክህ ተመለስ ልጅነት በሞቴን” እያቀነቀኑ እየደነሡ ይሆናል፡፡ እነዚህ ወንድምና እህቶቼ ረጅም ኪሎ ሜትር አቋርጠው ወደ እናት ኢትዮጵያ ሲመጡ እምነትና ተስፋ ሠንቀው ይመስለኛል፡፡ ዛሬ ከአካባቢው ማህበረሠብ ጋር ህብር ፈጥረው ይኖራሉ፡፡ አባባ ጃንሆይ  እኮ አስገራሚ ናቸው፡፡ የአፍሪካ ህብረትን የመሠረተ ዲፕሎማት ንጉስ አዋሳን ለጋራ ማህበራዊ መስተጋብር ሞዴልነት ማነፅ መቼ አቅቶት?! በተጨማሪ ሙሉ ምስጋና ይግባውና ኢህአዴግ ከተማዋ በራሷ መንገድ፣ ከተራ የአርሶ አደር ከተማነት ወደ ሚሊዬነር የፍቅር ከተማነት እንድትለወጥ የአራዳ አባትነት ሚናውን በሚገባ ተወጥቷል፡፡ ህልም አለኝ፡፡ የጊዜውና የቀድሞዎቹ የሀገሪቱ መሪዎች በአፍሪካ ህብረት መቀመጫነት እንደተመሠጋገኑ በአዋሳም አንድ ቀን ትልቁ ትንሹን ያወድሳል፡፡ ትንሹም ትልቁን በክብር ያስታውሠዋል፡፡

እናስ ምን አሰቡ፡፡ እርሥዎስ በአጭር ጊዜ የጋራ ማንነት ወደ ፈጠረችው አዋሳ ቢመጡ ምን ይልዎታል? ምንም፡፡

ሳልነግርዎት… አዋሳ ባጃጅ በሚባሉ የአስፓልት ላይ በረሮዎች የተመታች ከተማ ናት፡፡ እስከ አሁን ተከተሉኝ አይደል? አሁን ፍርሀቱን አገር አቋራጩ አውቶብስ ላይ ይጣሉትና ይውረዱ፡፡

እናም ፈገግ ይበሉ፡፡ ሀዋሳ እኮ ደርሠዋል፡፡ ለማደርያዎ ሲያሰላስሉ ያው ጉደኛ ባዳጅ ከእግርዎ ስር ተነጥፏል፡፡ “ፍሬንድ ጫፍ ፍቅር ሀይቅ ጋ?” ይበሉት! በትክክል!

 

 

Read 4114 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 08:43