Print this page
Monday, 10 April 2017 11:30

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና ዶክተር አሸብር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(5 votes)

  42ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን  ከሳምንት በፊት ያካሄደው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ  ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስን  በፕሬዚዳንትነት ሾሟቸዋል፡፡ ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ወደ ስፖርቱ አመራርነት የተመለሱት   ከ6 ወራት በፊት የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጥ ሲሆን፤ ይህን ፌደሬሽን በመወከል  በምርጫው ብቸኛ እጩ ሆነው ከቀረቡ በኋላም የጉባኤውን ሙሉ ድምፅ በማግኘት ሃላፊነቱን ተረክበው በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ታሪክ 10ኛው ፕሬዝዳንት ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የመጀመርያው ፕሬዝዳንት ከ1958 - 1972 ዓ.ም ያገለገሉት ይድነቃቸው ተሰማ ነበሩ፡፡ ከይድነቃቸው ተሰማ በኋላ አቶ ፀጋው አየለ ከ1972- 81 ዓ.ም ፤ ሻለቃ ግርማ ይልማ ከ1981- 84፤ አቶ ልዑለስላሴ ቴማሞ ከ1985 - 88 ዓ.ም ፤ ያሚ ከበደ ከ1988- 89 ፤ ኢንጅነር ግዛቸው ተክለማርያም ከ1989 - 95 ዓ.ም ፤ አቶ አሰፋ ማሞ ከ1995- 97 ዓ.ም፤ ወይዘሮ ዳግማዊት ግርማይ 1997 -2000 ዓ.ም እንዲሁም አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም ከ2001- 2009 ዓ.ም ከዶክተር አሸብር በፊት የኦሎምፒክ ኮሚቴውን የመሩ ፕሬዝዳንቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተሾሙ በኋላ  ዶክተር አሸብር ሲናገሩ የአገሪቱን ስፖርት ለማሳደግ  የተጠና እና እውቀት የተሟላበት፤ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ስትራቴጂን እንደሚከተሉ  ገልፀው፤ የውድድር ስፖርቶችን ማስፋፋት፤ የአገሪቱን መልካም ገፅታ መገንባት፤ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ማጠናከር  እንዲሁም ስፖርተኞች፤ አትሌቶች እና ሙያተኞችን ያማከለ አሰራር መዘርጋት እንደሚፈልጉም አስታውቀዋል፡፡  
በሌላ በኩል ከዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ የፕሬዝዳንትነት ምርጫ ባሻገር የኦሎምፒክ ኮሚቴውን ባለፈው ሳምንት ባደረገው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለቀጣይ አራት ዓመታት የሚመሩት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላት ምርጫም አካሂዷል፡፡  የስራ አስፈፃሚ  ቦርድ አባላቱ ብዛት ከ9 ወደ 11 ማደጉ ልዩ ለውጥ እንደሆነ ለስፖርት አድማስ አስተያየት የሰጠው የኦሎምፒክ ኮሚቴው የኮምኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዳንኤል አበበ፤ የፓራ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በስራ አስፈፃሚ ቦርዱ ለመጀመርያ ጊዜ እንዲገባ መደረጉ፤ ከኦሎምፒክ 10 ስፖርቶች አምስት ስራ አስፈፃሚ ሊሆኑ መብቃታቸው እንዲሁም የሴቶች የአመራነት ተሳትፎ በ30 በመቶ ማደጉ አይነተኛ ክስተቶች እንደነበሩ ጠቃቅሷል፡፡ በኦሎምፒክ ኮሚቴው የስራ አስፈፃሚ ቦርድ የገቡት 11 አባላት ፕሬዝዳንቱን ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ጨምሮ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወከሉት  አቶ ተክለወይኒ አሰፋ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የወከለው አትሌት ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ፤ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርን በመወከል በሚኒስቴር መ/ቤቱ የስፖርት ተሳትፎና ውድድር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ  አቶ ተስፋዬ በቀለ ፣ ከኢትዮጵያ ፓራ ኦሊምፒክ ኮሚቴን በመወከል የተከበሩ አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ ፣ ኦሊምፒያኖችን በመወከል ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ ፣ የኦሊምፒክ ውድድሮች ያልሆኑ ስፖርቶችን በመወከል ከቦውሊንግ አሶሴሽን ወይዘሮ ሔሮዳዊት ዘለቀ ፣ የአለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል የሆኑት ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይ፣  የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ ዶክተር ዳዲ ወዳጆ ፣ ከኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን አቶ ዳዊት አስፋው፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን አቶ ኪሮስ ሀብቴ ናቸው፡፡ በኦሎምፒክ ኮሚቴው የስራ አስፈፃሚ ቦርድ 3 ሴቶች በአመራርነት ሚና መግባታቸው ለአገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት እና ፌደሬሽኖች ተምሳሌት የሚሆን አቅጣጫ እንደሆነ የሚናገረው ዳንኤል አበበ፤ ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል የሆኑ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች የአመራርነት ድርሻ እስከ 2020 እኤአ በወንዶች እና በሴቶች እኩል 50 በመቶ እንዲሆን ያስተላለፈውን መመርያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚቻልበት አይነተኛ ርምጃ ነው ብሏል፡፡
በአጠቃላይ የኦሎምፒክ ኮሚቴው ጠቅላላ ጉባኤ በአስራ ሁለት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ መክሮ ውሳኔዎችን አስተላልፏል ያለው፤ የኮምኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ ዳንኤል አበበ ከአጀንዳዎቹ መካከል የ2016 የእቅድ አፈፃፀም፣ የፋይናንስ፣ የኦዲት ሪፖርቶች    ምክክር ተደርጎባቸው በሙሉ ድምጽ መፅደቃቸውን አመልክቶ፤ የኮሚቴው የአራት አመት የስትራቴጂክ እቅድም ተቀባይነት ማግኘቱን ጠቅሷል፡፡ የኦሎምፒክ ኮሚቴው የስትራቴጂ እቅድ ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ 2020 አጀንዳ ብሎ ካቀመጠው ፍኖተካርታ ጋር ተጣጥሞ የሚሄድ ነው የሚለው ዳንኤል፤ በ5 ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የኦሎምፒክ ኮሚቴው እንደሚንቀሳቀስ ዘርዝሯል፡፡ የመጀመርያው በተቋማዊ ለውጥ ላይ የሚያተኩር አቅጣጫ ሲሆን የኦሎምፒክ ኮሚቴውን አደረጃጀት እና አሰራር ዘመናዊ በማድረግ ሌሎች አገር አቀፍ ፌደሬሽኖች እና ማህበራት መዋቅራዊ ለውጥ ተምሳሌት ማድረግ ፤ በሁለተኛ ደረጃ የኦሎምፒክ ኮሚቴውን ጅምር የልማት ስራዎች ማቀላጠፍ ፤ በ3ኛ ደረጃ  በስፖርት ዴቨሎፕመንት አቅጣጫ ቴክኒክ ስልጠናዎችን ለባለድርሻ አካላቱ በመስጠት ተቋማዊ ሽግግር መፍጠር ፤ በማርኬቲንግ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በማጠናከር የኦሎምፒክ ኮሚቴውን የገቢ አቅም ማሳደግ እንዲሁም በህዝብ ግንኙነት ስራዎች የኦሎምፒክ ፍልስፍና እና እንቅስቃሴን በመላ አገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ ማዳረስ ናቸው፡፡ የስትራቴጂክ እቅዱ ሌላው ዋና የትኩረት አቅጣጫ ከመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች አንስቶ፤ በኦል አፍሪካ ጌምስ፤ በ2018 እኤአ በሚደረጉት የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ እና የዓለም ወጣቶች ኦሎምፒክ እንዲሁም በ2020 እኤአ ላይ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያን ተሳትፎ እና ውጤታማነት በማሳደግ መስራት እንደሆነም ዳንኤል አበበ አብራርቷል፡፡
የዶክተር አሸብር 6 ዓመታት በእግር ኳስ ፌደሬሽን
የ51 ዓመቱ ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ በስፖርቱ አመራርነት በመስራት አዲስ አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን  ፕሬዝዳንት ሆነው በሁለት  የስራ ዘመናት ለ6 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽን በዶክተር አሸብር ፕሬዝዳንትነት ሲመራ በነበረበት ወቅት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተሳትፎው በክፍለ አህጉር ደረጃ የተወሰነ ነበር፡፡ በሴካፋ ዞን ሁለት የሻምፒዮናነት ድሎችን በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ማስመዝገቡ ትልቁ ውጤት ሲሆን በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ በታሪክ ከፍተኛውን የ86ኛ ደረጃን ያስመዘገበበት ጊዜም እንደነበርም ይታወሳል፡፡ የቀድሞው የፊፋ ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ማድረጋቸውንም እንደ አበይት ምዕራፍ አድርጎ መጥቀስ የሚቻል ሲሆን፤ የጎል ፕሮጀክት እንቅስቃሴዎችን ለማጠናከር በፌደሬሽኑ በኩል የተመቻቹ ጅምር ሁኔታዎችም የፈጠረም ነበር፡፡ በሴካፋ ምክር ቤት እና በሲኒዬር ቻሌንጅ ካፕ ውድድር የነበራቸው የተለየ አስተዋፅኦ መዘንጋት የለበትም፡፡  ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌደሬሽን በፕሬዚዳንትነት ለ6 ዓመታት ሲመሩ  ኢትዮጵያ  ሁለት የሴካፋ ሻምፒዮናዎችን እንድታስተናግድ ከማድረጋቸውም በላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  በሴካፋ ዞን ሁለት የሻምፒዮናነት ድሎችን በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ማስመዝገቡ የሚታወስ ሲሆን  የሴካፋ ፕሬዝዳንት ሆነውም አገልግለዋል፡፡  ሼክ መሐመድ አላሙዲን  በዶክተር አሸብር የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንትነት ዘመን የሴካፋሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕን ለ3 ዓመታት በ1.5 ሚሊዮን ዶላር የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ የታደጉ ሲሆን፤ በእነዚህ ሶስት የውድድር ዘመናት የዞኑ ሻምፒዮና አላሙዲ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ተብሎ እንዲካሄድ እና  ባለሃብቱ በዚህ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከካፍ እና ከፊፋ እውቅና በማግኘት የክብር ሽልማት እንዲቀበሉ አስችሏል፡፡
በሌላ በኩል ግን በዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ የተመራው የእግር ኳስ ፌደሬሽን በአገር ውስጥ ውድድሮች ያን ያህል አበረታች ውጤቶች የማያስመዘግብ ነበር፡፡ ከትልልቅ ክለብ አመራሮች ጋር በየጊዜው ይጋጭ ስለነበርም የስልጣን ዘመናቸው በውዝግብ የተናጠ ነበር፡፡ በተለይ ዶክተር አሸብርን በመቃወም  የክለቦች ህብረት የተባለ ቡድን ተመስርቶ ከሌሎች የእግር ኳሱ ባለድርሻ አካላት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት ተሰበሰቡና የመጀመርያውን የስራ ዘመን 4 ዓመታት  ጨርሰው በሁለተኛ የስራ ዘመን 2 ዓመታትን የሰሩትን ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስን ከፌደሬሽኑ የፕሬዝዳንትነት ስልጣን   እንዲወርዱ  ውሳኔ አሳለፉ ፡፡ ዶር አሸብር ግን ውሳኔ በመቃወም ከስልጣን አልወርድም አሉ፡፡ መደበኛ ስራቸውን ለማከናወን በአዲስ አበባ ስታድዬም ወደ የሚገኘው ቢሯቸው ለመግባት ሞክረውም ሳይሳካላቸው ቀረ፡፡ በዚህም ሳቢያ በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ላይ የተፈጠረው ውዝግብና ቀውስ በከፍተኛ ደረጃ ተባባሰ፡፡ በዚህ ጊዜ ጉዳዩን በቅርብ ይከታተል የነበረው ፊፋ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ የስልጣን ዘመናቸው ሳይጠናቀቅ በጠቅላላ ጉባኤ ከሃላፊነት መውረዳቸውን በመቃወም፤ በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የውስጥ አስተዳደር እና ችግር መንግስት ጣልቃ ገብቷል በሚል ምክንያትም ኢትዮጵያ በፊፋ የነበራትን አባልነት በጊዜያዊነት ማገዱን ገልፆ የቅጣት ውሳኔ አሳለፈ፡፡ በዚሁ የእገዳ ቅጣት ሳቢያ በ2010 እኤአ ላይ በአፍሪካ ምድር በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት ለተስተናገደው 19ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሞሮኮ አቻው ጋር የሚያደርገው የደርሶ መልስ ግጥሚያ መሰረዙ ከፍተኛ ኪሳራ ነበር፡፡
ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ሌላው በስፖርት አመራርነት ያላቸው ልምድ ከስድስት ወራት በፊት በተመረጡበት የቅርጫት ኳስ ፌደሬሽን በአጭር ጊዜ ውስጥ ያከናወኗቸው ተግባራት ናቸው፡፡ ይሄውም በኢትዮጵያ ቅርጫ ኳስ ፌደሬሽን እና በአሜሪካው የቅርጫት ኳስ ማህበር ኤንቢኤ መካከል ግንኙነት መፍጠራቸው እና ብሄራዊ ቡድኖች ለማቋቋም ያደረጉት ጉልህ አስተዋፅኦ ይጠቀሳል፡፡
ዶክተር አሸብር ከስፖርቱ አመራርነት ባሻገር በፖለቲካው
በህክምና ዶክትሬት ማእረግ የተመረቁት ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ የዓለም የሰላም አምባሳደር ሲሆኑ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አመራነታቸው ከተነሱ በኋላ በቀጥታ ፊታቸውን ያዞሩት ወደ ፖለቲካ ነበር፡፡  በትውልድ ከተማቸው ቦንጋ ለፓርላማ ተወካይነት በገለልተኛ እጩነት ተወዳድረው አሸንፈው ፓርላማ የገቡ ብቸኛው የግል ተወዳዳሪ ለመሆን በቅተዋል፡፡  በተወካዮች ምክር ቤት ለአራት ዓመታት  ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በፓርላማውም የሳይንስ፣ የመገናኛና ቴክኖሎጂ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም የኢትዮ ጀርመን ወዳጅነት ኮሚቴን በምክትል ሊቀመንበርነት በመምራት አገልገለዋል፡፡ በፓርላማ ብቸኛ የግል ተወካይ ሆነው ማገልገል እንደጀመሩ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ በሚልም በስፋት ተወርቶ ነበር፡፡
በፓርላማ ተወካይነታቸውም ወቅት የአፍሪካ ህብረት የሕግ አውጪ አካል የሆነው የፓን አፍሪካ ፓርላማን በአባልነት መቀላቀል ችለዋል፡፡ በአህጉራዊው ተቋም ፓን አፍሪካ ፓርላማ የስፖርት ዘርፍ ሊቀመንበርነት ማገልገል ችለዋል፡፡ በተወካዮች ምክር ቤት በግል ተወዳዳሪነት ለሁለተኛ የስራ ዘመን ለመመረጥ ተወዳረው ግን ሳይሳካለቸው ቀረ፡፡ ከ2 ዓመት በፊት የሃገራቸውን ፓርላማ ወክለው በፓን አፍሪካ ፓላማ አባልነት መቀጠል ባይችሉም አሸብር የአህጉራዊው ተቋም 4ኛ የክብር ምክትል ፕሬዘዳንት ሊሆኑ በቅተዋል፡፡

Read 4942 times