Wednesday, 04 April 2012 08:44

አዲስ አበባ በንስር ተምሳሌትነት

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

አስተዳደሩ ከተማዋ ውስጥ ቆሻሻ መጣልን የሚከለክል ህግ ማውጣት እንዴት አቃተው?

በሲንጋፖር ጐዳና ላይ መስቲካ እንኳን መጣል ክልክል ነው!

የአዲስ አበቤዎች ችግር “የማህበራዊ እሴት መላላት ነው”… አንድ ምሁር

የአእዋፍ ዝርያ የሆነው ንሥር ሕይወቱ ተምሣሌታዊ ነው፡፡ የእይታ ችሎታው፤ ከባላንጣዎቹ ለማምለጥ የሚጠቀምበት የከፍታ ምጥቀትና ከእርጅናና ውድቀት ራሱን ነፃ ለማውጣት የሚያደርገው ተጋድሎ ሁሉ አስደናቂ ነው፡፡

እኔም ዛሬ ላወራላትና ላወራባት ለመረጥኳት አዲስ አበባ ከነዚህ ተግባራቱ አንዱን ቅርንጫፍ ገንጥዬ እወሥዳለሁ፡፡ የምወስደውም ንሥር ከእርጅና ራሱን ለመታደግ የሚወሥደውን መሥዋዕትነት የተሞላ ተሀድሶ ነው፡፡ ንሥር ጥፍሮቹ በእርጅና ሲቆለመሙና መንቁሩ ሲታጠፍ የሚያደርገው ነገር ቀላል አይደለም፡፡ ጊዜ ወስዶ፣ በከፍተኛ ሕመም መንቁሩን በአለት እያጋጨና እየታገለ ነው፡፡

አዲስ አበባም በዚሁ ዓይነት ሕመምና ለውጥ ውስጥ ያለች ይመሥለኛል፡፡ የዛጉ ጣሪያዎችዋን፤ የዘመሙ ግድግዳዎችዋንና መተናፈሻ ያጣ ብብቷን በወጉ ለማበጀት እየፈራረሰች ነው፡፡ መፈራረስ ያምማል፤ የለመዱትን ሠፈር፣ ዕቁብና ዕድር መበተን፤ የተዳሩበትን ተወልደው ያደጉበትንና አምጠው የወለዱበትን ቀዬ መራቅ ሆድ ያባባል፡፡ ግን ደግሞ ሕይወት ለውጥ ነውና ለለውጥ መታገል የግድ ነው፡፡ እንኳንስ በራስ አገር በባዕድ አገርም ይሄ ሁሉ ወፈ ሰማይ ህዝብ የሚጐርፈው እየታመመ ለመሻሻል ነው፡፡

በእርግጥም ይህቺ በቆሻሻዋ ብዛትና በዛጉስቁልናዋ የተሣቀባት፣ በመጥፎ ሽታዋ አፍንጫ የምትሰረስረው አዲስ አበባችን በብዙው እየተቀየረች ነው፡፡ መንገዶችዋ እንደ ጥቁር ምንጣፍ መንታ እየሆኑ ተዘርግተዋል፡፡ ፎቆችዋ ደመናው ጉያ ውስጥ ሊገቡ እያሻቀቡ ነው፡፡ የአውሮፓን ከተሞች የሚለካኩ አዳዲስ ሠፈሮች እየተገነቡ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ በየመንገዱ የወደቁ የጐዳና ተዳዳሪዎች ከቀቢፀ-ተስፋ ሕይወት፣ ነገን ወደ ማለም እየተሸጋገሩ ነው፡፡ ይህ እጅግ ደስ የሚያሠኝና “እሰይታን!” የሚያስዘምር ተግባር ነው፡፡ ቀን ፀሐይ፣ ሌት ብርድና ዝናብ የሚፈራረቅባቸው ታዳጊዎችና ወጣቶች ወደ አዲስ የኑሮ ምዕራፍ መሸጋገራቸው፣ ከከተማዋ ፅዳት አንጻር የሚኖረው ሚናም ቀላል አይደለም፡፡ የነሱ ባለተስፋ መሆንም በሌላ ጐኑ ለከተማዋ በጐ አስተዋፅዖ አለው፡፡ እንግዲህ የአፍሪካዋ መዲና አዲስ አበባችን አንድም ማፈሪያችን አሊያም መኩሪያችን የምትሆንበት እድል በእጃችን ነው፡፡ ይሁንና ብዙዎቻችን ግን ይሄን የተረዳን አንመሥልም፡፡ ብዙ ጊዜም የሃላፊነት ስሜት አይታይብንም፡፡ በከተማዋ ለውሃ መውረጃ የተዘጋጁ ቱቦዎች ላይ ያሉ የብረት መክደኛዎች ተሠርቀው አፋቸውን መክፈታቸውን ሳታዩ አትቀሩም፡፡ አንዳንዶቹ ቱቦዎችም በድንጋይ ተሞልተዋል፡፡ ክረምት ሲመጣ እነዚያ በድንጋይ የተሞሉ ቱቦዎች፣ የሚፈጥሩት ችግሮች ደግሞ ቀላል አይደለም፡፡ የከተማዋን ጐዳናዎች በጐርፍ ሲያጥለቀልቁት በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ ስለ ቱቦ ክዳኖች ሳስብ የሚገርሙኝ ሠራቂዎቹ ብቻ አይደሉም፡፡ ያንን ብረት መዝነው የሚገዙት “ልማታዊ ባለሀብቶችም” ጭምር እንጂ፡፡ ለመሆኑ ከዚያ ከተሰረቀ ብረት የሚያገኙት ትርፍ፣ በአገሪቱ ላይ ከሚፈጥረው ጉዳት ጋር ሲነፃፀር ምን ያህል ይሆን? … ወይስ ነጋዴዎቻችን ይቺን እንኳን ለማሰብ የምትሆን  አቅም አጥተዋል?

ስለአዲስ አበባ ተሃድሶ ስናስብ ግን ለውጥ ማምጣት የእያንዳንዳችን ሃላፊነት መሆኑን መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም፡፡

ብዙዎቻችን ግን ጥሎብን የራሳችን ግቢ ካልሆነ በስተቀር ለጋራ ተቋሞቻችን ያለን አመለካከት ጤነኛ አይደለም፡፡ የከተማዋ ጐዳና ቢቆሽሽ፣ ቱቦ ቢዘጋ የራሳችን አይመስለንም፡፡ የመንግስት ነው ብለን የምናስብ ይመስላል፡፡ መንግስት የሚሠራው ልማት፣ በኛ ገንዘብ እንደሆነም እንረሳለን፡፡ ስለዚህ ከተማችንን መለወጥ አቅቶናል፡፡

አንድ ገጣሚ እንዳለው “ሀገርህ ናት በቃ! ወይ አብረሃት ተኛ፣ ወይ አብረሃት ንቃ” ነው ነገሩ፡፡ እንግዲህ ምርጫችን ሁለት ነው፡፡ አንድም በቆሻሻ በተከበበች ቆሻሻ ከተማ ውስጥ መኖር፣ አሊያም በጽዱና ውብ ከተማ ውስጥ በደስታ መመላለስ!

የከተማችን ጽዳትና ውበት በአንድ ሰሞን ዘመቻ ብቻ የሚስተካከል አይደለም፡፡ በአንድ ወገን ጥረት ብቻም የሚፈለገው ለውጥ አይመጣም፡፡ ቀበሌዎች፣ ዕድሮችና ሌሎች ማህበራዊ ተቋማት በሙሉ ቀጣይ ዘመቻ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ስለ ቀበሌ ስናነሳ በጣም የሚገርመኝን የአየር ጤና አካባቢ ቀበሌ ላስታውስ፡፡ አየር ጤና አደባባዩን እንደተሻገራችሁ፣ ወደ ጅማ ስትሄዱ ያለውን የውሃ መውረጃ ቦይ ሰውን አያስጠጋም፡፡ አመቱን ሙሉ የሞቱ ዶሮዎች፣ ፌስታሎችና አፍንጫ የሚቆርጥ የሽንት ሽታ አይለየውም፡፡ ታክሲ ለመጠበቅ የቆመ ሰው፤ ካልለመደው የሞት ያህል ይከብደዋል፡፡ አሁን በቅርቡ በማዘጋጃ ቤት ሠራተኞች ተጠርጓል፡፡ ግን መጥፎ ሽታ ዛሬም አፍንጫ ሊቆርጥ ይደርሳል፡፡ ታዲያ ይህቺ ናት የአፍሪካዋ መዲና? እጅግ ያሳፍራል! እዚያ የሚሸናው ሰውና የሚያሸናው ቀበሌ - ሁለቱም ይገርማሉ! ሰዎች እዚያ አካባቢ እንዳይሸኑ የሚቆጣጠር ሠራተኛ ለምን አይቀጠርም? ከዚያ በፊት ግን በተወሰነ የሣንቲም ክፍያ አገልግሎት የሚሰጥ የህዝብ መፀዳጃ ሊሰራ ይገባል፡፡ በዚያ አልጠቀምም ያለውን ግን መቅጣት፡፡ በአጠቃላይ ግን በከተማ ውስጥ ቆሻሻ መጣልን የሚከለከል ሕግ ማውጣት አስተዳደሩን ለምን አቃተው?

የአዲስ አበባ አስተዳደር ችግር ግን ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ በትራንስፖርት ላይ ያለውን ችግር ማሻሻል አልቻለም፡፡ ግብር መክፈል የሕዝቡ የውዴታ ግዴታ እንደሆነ ሁሉ፣ የሕዝቡን ፍላጐቶች ማሟላት የመንግስት የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ሕዝቡን ግብር ክፈል ብቻ ማለት አግባብ አይመስለኝም፡፡ አንዳንዴ ሳስበው መንግስት ብዙ ሥራዎቹን የሚሠራው ለዝና ብቻ ይመስለኛል፡፡ በቁጥር የሚሰሉ ዩኒቨርሲቲዎችንና በኪሎ ሜትር የሚለኩ መንገዶችን ብቻ ሳይሆን የማይታዩ የጓዳ ችግሮቹን መፍታት ይጠበቅበታል፡፡

ባለሀብቶችና ነጋዴዎችም በከተማይቱ ዕድገትና ልማት ላይ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ከተማዋን የሚመጥኑ ሆቴሎች፤ መዝናኛዎች፣ ሱፐር ማርኬቶች መገንባትም ለሀገር ልማት እንደመስራት የሚቆጠር ነው፡፡ በተለይ ከስግብግብነት ነፃ ሆኖ እየተጠቀሙ ሀገርን ለመጥቀም መዘጋጀት ትልቅ ባለውለታነት ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ባህላዊ ሆቴሎችን በመክፈት ባንድ ወገን ለባህር ማዶ ሰዎች ሀገርንና ባህልን ማስተዋወቅ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ራስንና ሀገርን መጥቀም ነው፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ የግል ድርጅቶች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና አንዳንዶቹ በአንድ ቀን መክበር የፈለጉ ይመስል ዋጋቸው አይቀመስም፡፡ በዚያ ላይ ለስሙ ነው እንጂ ባህላዊ የሚያሰኛቸውን በቂ ዝግጅት አያደርጉም፡፡ አልፎ አልፎ ግን ጥሩዎች አይጠፉም፡፡ በተለይ አንድ ሁለት ጊዜ ከወዳጆቼ ጋር ያየሁት፣ ሦስት ቁጥር ማዞሪያ አካባቢ ያለው “ዲማ የባህል አዳራሽ” ለአብነት የሚጠቀስ ነው፡፡ የሄድኩትም ውበት አድናቂ ከሆኑ የጥበብ ሰዎች ጋር ስለነበር አብሬ ተደምሜአለሁ፡፡ ወደላይ ቀና ሲባል በጣሪያው ግማሽ ልክ የተሠሩት (ባንድ ወገን በገና በሌላ ወገን ክራር) እጅግ ማርከውኛል፡፡ ሙዚቃ ከሚቀርብበት መድረክ ጀርባ ያለው የባህላዊ ቅርሶች ምስል መቀያየር፣ አዳራሽ ውስጥ ያለው ትልቅ የመሶብ ቅርጽ በሰው እጅ ሳይሆን በሌላ ቴክኒክ ሲከፈት ማየቱና ግቢው መግቢያ ላይ ያለው የዝሆን ቅርጽ የማንንም አይንና ቀልብ የሚስብ ነው፡፡ ዛሬ በዚህ አጋጣሚ አነሳሁት እንጂ የዋጋውም ነገር እኔና ጓደኞቼን አስገርሟል፡፡

ምናልባት እንደሰማሁት ባለቤቱ ባህር ማዶ ሄደው የተመለሱ ሰው ስለሆኑ፣ የሀገር ጣዕም ገብቷቸውና የሀገር ፍቅር ግድ ብሏቸው ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሌሎቹም ኪሳችንን በአንድ ቀን ከሚላጩን፣ ቀስ እያሉ ተመጣጣኝ አገልግሎት እየሰጡን ቢበሉን ይሻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ጥሎብን የሀገራችንን ፍቅር የምንገልፀው፣ አትሌቶቻችን ኬንያን ቀድመው የወርቅ ሜዳሊያ ሲያመጡ ወይም የአድዋ ድል በዓል ሲከበር ብቻ ይመስላል፡፡ እንዲህ መሆን ያለበት ግን አይመስለኝም፡፡ የሀገር ፍቅር ከተማ በማጽዳትና ለሕዝብ ተገቢውን አገልግሎት በመስጠትም ይገለፃል፡፡ ተሾመ ነጋሽ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ምሁር የአዲስ አበቤዎችን ችግር “የማሕበራዊ እሴት መላላት ነው” ይሉታል፡፡ “የአዲስ አበባ መንገዶች የተበላሹትና የቆሻሻ መጣያ ገንዳ የሚመስሉት፣ በማህበራዊ እሴት መላላት መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ጤነኛ አእምሮ ያለውና ጤነኛ ነኝ የሚል ሰው እንዴት ቢሆን ነው የጫት ገራባ መንገድ ላይ የሚወረውረው?” ሲሉ ይጠይቃሉ - ስለ ሥነ ምግባር በፃፉት መጽሐፋቸው፡፡ ምሁሩ ንጽህናንና ልማትን በተመለከተ ሲንጋፖርን በአድናቆት ይጠቅሳሉ፡፡ “ንጽህና ሲነሳ ሁሉም ሲንጋፖርን ይጠቅሳል፡፡ እንዳየኋት ውብ ሀገር ነች፡፡ በሲንጋፖር ጐዳና ስትራመዱ በአፋችሁ ያለውን ማስቲካ እንኳ ጐዳና ላይ መጣል አትችሉም፡፡ ይህን መሰል ድርጊት ብትፈጽሙ ወዲያው ቅጣት ይከተላችኋል፡፡ ስለዚህም Singapore is a fine country” ተብላለች ይላሉ፡፡

(መቅጣት የምትወድ አገር ለማለት ይመስለኛል)እኛስ የከተማችንን መልክና ስም መቀየር አንችልም? መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ ከታገለ፣ ነጋዴዎች በአግባቡ ነግደው ለማትረፍ ከተጉ፣ እኛ ከተማዋን በማቆሸሽ ካልተሳተፍንና የሚያቆሽሹትን ከተቃወምን፣ አዲስ አበባ ፀአዳና ውብ ከተማ የማትሆንበት ምን ምክንያት ሊኖር ይችላል? ከተባበርን ይቻላል! ግብን ቀርፆ መትጋት ግን ይጠይቃል፡፡

 

 

Read 10902 times Last modified on Friday, 06 April 2012 11:12