Wednesday, 04 April 2012 10:02

የሁለት ሱሶች ወግ ቻትና ጫት!

Written by  ቢኒያም ሐብታሙ
Rate this item
(2 votes)

የዛሬው ወጋችን (ቻታችን) በሁለተኛ ዘመነኛ ሱሶችና ፋሽኖች ላይ ያጠነጠነ ይሆናል፤ በቻትና በጫት ዙሪያ፡፡ ቻት (Chat) አሁን አሁን ቃሉ አማርኛ እስኪመስለን ድረስ እንደወረደ እየተጠቀምንበት ያለ የእንግሊዝኛ ቃል ሲሆን ሜሪት የእንግሊዝኛ-አማርኛ መዝገበ ቃላት ግሱን ተጫወተ፣ አወራ፣ አወጋ ሲለው፤ ሰዋሰውን ደግሞ ጭውውት ይለዋል፡፡ እኔ እምለው፣ መቼም ዘመን የማይተካው ነገር የለም፤ ስለ ዲክሽነሪ ሳስብ አይኔ ላይ ምን ድቅን እንዳለብኝ ታውቃላችሁ? የአምሳሉ አክሊሉ ያቺ ባለ ሰማያዊ ቀለም ቅልብጭ ያለች ዲክሽነሪ፡፡ ልጅ እያለሁ እሷን ዲክሽነሪ ከሽማግሌ ፈረንጅ ሁሉ አዋቂ አድርጌ ነበር የምቆጥራት፤ “አ-ቤ-ት ያ ሁሉ ቃላት!” በያኔው ጭንቅላት፡፡ ለማንኛውም “The Classic” ብያታለሁ፡፡ እንደ መረቀነ ሰው ወግ አደበላለቅሁ አይደል? በሉ ወደ ቻታችን …

ቻት (ጭውውት) ድሮ ድሮ ሰዎች በአካል በአይነ-ሥጋ ተገናኝተው ሸጋ ሸጋ ወግ የሚለዋወጡበት ማህበራዊ-ሥርዓት ነበር፤ አሁን አሁን ግን በአካል በአይነ-ሥጋነቱ ቀርቶ በድረ-ካሜራ (Web-cam) በአካል ተራርቆ በምስል እየተያዩ፣ በፈጣን የፅሁፍ መልዕክት የሚጨዋወቱበት ማህበራዊ የድረ-ገፅ ሥርዓት ሆኗል፤ በዚህ የኢንተርኔት ትውልድ፡፡

ታዲያ፣ ድሮ ድሮ ጭውውትን የናፈቁ ጓደኛማቾች “መስመር ላይ አትታይም እስኪ እንደ ድሮው እንገናኛ፤ አንጠፋፋ” ሲባባሉ፤ የዘንድሮ ጓደኛሞች ደግሞ “አትጥፊ ጀለሴ፣ ኦን ላየን (online) እንገናኝ” ሆኗል!

በአሁኑ ሰዓት አያሌ የማህበራዊ ድረ-ገፆች (Social-networks) ይህንኑ ቻት በተሳለጠ ሁኔታ ማቀላጠፍ ሆኗል ስራቸው፡፡ ከነዚህ ድረ - ገፆች መካከል እነ ፌስ ቡክ (facebook)፣ ያሁ (Yahoo)፣ ጂሜይል (gmail) እና ሆት ሜይል (hotmail) በዋነኝነት በአገራችን ውስጥ ብዙ ተጠቃሚዎችን ያፈሩ ናቸው፡፡ በተለይ ፌስቡክ የሚባለው ድረ-ገፅ በአሁኑ ሰዓት ከህፃን እስከ አዋቂ፣ ከተማሪ እስከ አስተማሪ፣ ከሰራተኛ እስከ ቦዘኔ … ሁሉም በአንድነት ተጠምዶ የሚውልበት የወግና የስላቅ መለዋወጫ ማህበራዊ ድህረ ገፅ-ሆኗል፡፡

ይህ ድረ ገፅ ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን መከወኑ፣ አዝናኝነቱና ለአጠቃቀም መቅለሉ በአለም አቀፍ ደረጃ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል፤ በአገራችንም በተለይ በአዝናኝነቱ የብዙዎችን ቀልብ ለመግዛት ችሏል፡፡

መቼም ማንኛውም ነገር ጥሩና መጥፎ ጎኖች እንዳለው የማይታበይ ሃቅ ነው፤ ታዲያ የእነዚህ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ዋነኛ አሉታዊ ጎን ጊዜ ተሸሚነታቸው ነው፤ በዚህም አሉታዊ ጎናቸው ተማሪዎችን ከጥናታቸው፤ ሰራተኞችን ከስራቸው እያስተጓጎሉ ይገኛሉ፡፡ ለልማትና ለበጎ ስራ ሊውሉ የሚገባቸው ውድ ጊዜያት በቧልትና በቀልድ እንደዋዛ ይባክናሉ፤ በነዚህ ማህበራዊ ድረ-ገፆች፡

በአሁኑ ሰዓት የፌስቡክ (አካውንት) የለኝም ማለት ወይም ፌስቡክ ተጠቃሚ አይደለሁም ማለት እንደ ትልቅ ነውርና ውርደት እስከ መቆጠር ደርሷል፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከወጣት እስከ አዋቂ የፌስ ቡክ አካውንት ባለቤት ነው፡፡ እንደውም አንድ በዚሁ ድረ-ገፅ ያነበብኳት ቀልድ መሰል ተግሳፅ /ሲሪየስ-ኮሜዲ ልንለው እንችላለን/ ትዝ አለችኝ፡፡ እንዲህ ትላለች፤ “ሰው የባንክ አካውንት ይከፍታል አንተ የፌስ ቡክ አካውንት ክፈት!” ትላለች፡፡ እቺው ፅሁፍ ከታክሲ ላይ ፅሁፎች የተወሰደ በሚል እንዲህ ተቀይራ ቀርባለች “ሰው አካውንት ይከፍታል አንተ አፍህን ክፈት! (lol) በነገራችን ላይ ይህች ቃል በእነዚህ ድረ-ገፆች በብዛት የምንጠቀማት የእንግሊዘኛ ምህፃረ - ቃል ናት፤ ሙሉ ቃሉም “Laugh out loud” (በሳቅ ፈረስኩ እንደ ማለት) ሲሆን ለአማርኛችን እንዲስማማም Sbs ተብላለች፤ ሳቅ - በ-ሳቅ እንደማለት፡፡

መቼም በአግባቡና በስርዓቱ ለተጠቀመባቸው እንደዚህና የመሳሰሉትን አይነት ቀልዶችና ቁምነገሮችን በትርፍ ሰዓት እያነበቡ መዝናናትና መማር ስለሚቻልባቸው እነዚህ ማህበራዊ ድረ-ገፆች በጎ ማህበራዊ ፋይዳ አላቸው ለማለት ያስደፍራል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ማህበራዊ ፋይዳቸው ሳይሆን ዕዳቸው እየጎላ መጥቷል፡፡ ምክንያቱም  ከአዝናኝነትና መረጃ ሰጪነታቸው ባሻገር ሱስ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ በየትምህርት ቤቱ በትምህርት ሰዓት ሳይቀር እነዚህን ድህረ-ገፆች በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ሲጠቀሙ የተያዙ ተማሪዎች፣ ወላጅ እንዲያመጡ እየተደረጉ መሆኑ አንዱ ማሳያ ሲሆን ሌላው ደግሞ በየቢሮው “በስራ ሰዓት ፌስቡክ መጠቀም ክልክል ነው” የሚሉ ማስታወቂያዎች በየግድግዳው ተለጣጥፎ መታየቱ ነው፡፡ ኧረ እንደውም አንዳንድ ቢሮዎች ባስ ሲልባቸው እነዚህን ድህረ-ገፆች ብቻ ለይተው ያዘጋሉ (block) ያስደርጋሉ፡፡

እንደው በአጋጣሚ ጥሏችሁ (ማለቴ ሱስ ጥሏችሁ) ወይም እንደኔ ለሪሰርች (lol) ወደ ጫት ቤት ጎራ ያላችሁ ከሰኞ እስከ ሰኞ፣ ከጠዋት እስከ ማታ ጫት ቤቶች በጫትና በቻት ተጠምደው ውለው ማምሸታቸውን ሳትታዘቡ አልቀራችሁም፡፡ ከተማሪ እስከ ቢሮ ሰራተኛው ሁሉም በየፊናው፣ ከየፊናው የፎረፈባትን ሰዓት በጫቱና በቻቱ ተጠምዶባት ታያላችሁ፡፡ ይህን ጉዳይ ካስተዋልኩ በኋላ የድሮ ወጣቶች ትዝ አሉኝ፣ በጣም ድሮም አይደለም፤ ያኔ በ70ዎቹ ምናምን ያሉ ወጣቶች፤ “በምን ይሆን ያኔ ቢዚ የሚሆኑት ብዬ ጠየቅሁ?” እእእ…አዎ ትዝ አለኝ፤ የያኔው ሱስ ፖለቲካ ነበር፤ በየካፌው፤ በየጥጋ ጥጉ በየዩኒቨርስቲው የጦፈ ፑትለካ ይካሄድ ነበር፤ በተለያዩ ጽንፎች ጐራ በመያዝ ወጣቶች በፖለቲካዊ ሱስ የተጠመዱበት ዘመን፡፡

የዘንድሮ ወጣትም ታዲያ እንዲሁ በሁለት ጐራ ሀይለኛ ሱሳዊ ጦርነት ይዟል፤ በቻትና በጫት፤ ጫቱን እየቃመ ቻቱን ያደራዋል፤ የረባውን ያልረባውን፣ የባጡን የቆጡን፣ ከአገር ውስጥ እስከ አለምአቀፍ፤ ከፈጠራ ወሬዎች እስከ ፈጠራ ቀልዶች…ወዘተ የማይደሰኮር ነገር የለም፤ በቻትና በጫት ቤት፡፡

ወደ ርዕሰ ወጌ ስመለስ ቻትና ጫት ከቃሎቹ ዜማዊ ምት መመሳሰል ባሻገር እንደ ሱስ ምን ይሆን የሚያመሳስላቸው ስል አወጣሁና አወረድኩ፤ እናም አንዳንድ የተገለፁልኝን ነጥቦች እነሆ፡፡

ከላይ ለመግለጽ እንደ ሞከርኩት ቻት በአሁኑ ሰዓት ወጣት፣ አዋቂ ሳይል በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንደ ሱስ የተዛመደ የማህበረሰብ ነቀርሳ መሆኑ ከጫት ጋር የሚያመሳስለው ሲሆን፡፡ በሌላ አነጋገር ቻትም ጫትም ሁለቱም ጊዜን በከንቱ የምንገድልባቸው ከንቱ ሱሶች ናቸው፡፡

ሌላው መመሳሰላቸው የሚመነጨው ሁለቱም በአብዛኛው የቧልትና የፌዝ መድረኮች መሆናቸው ነው፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ ማህበራዊ ድረ ገፆች ከጽሑፍ ልውውጥ (ቻት) በዘለለ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችና ትምህርቶች የሚተላለፉባቸው መድረኮች ቢሆኑም በአብዛኛው የሚውሉት ለቀልድና ለስላቅ መሆኑ ከጫት ማስቃሚያ ቤቶች ጋር ያመሳስላቸዋል፡፡

ሶስተኛው ነጥቤ፣ ቻትም ጫትም የሁለትና ከዛ በላይ ግለሰቦችን ከንቱ ጊዜያት የሚፈልግ መሆኑ ነው፡፡ መቼም ጫትን ለብቻም መቃም ይቻላል ትሉኝ ይሆናል፤ ለዚህ ደግሞ ሁነኛ መልሴን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፤ አንድ ሰው ብቻውን እንኳን ጫት ቢቅም ብቻውን ነው አይባልም፤ ምክንያቱም የጫቱ (የምርቃናው) ባህሪ ብዙ ማንነቶችን በቃሚው ላይ ስለሚፈጥር እንዲሁም በሃሳብ አነውልሎ በውስጡ ካሉት ገፀባህሪያት ጋር መነጋገር ስለሚጀምር በእርግጥ ብቻውን ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ታዲያ ቻትም በተመሳሳይ መልኩ የሁለትና ከዛ በላይ ግለሰቦችን ከንቱ፣ ባካኝ ጊዜ የሚጠይቅ ነው (ቁምነገራዊ ቻቶችን አያካትትም) በነገራችን ላይ፣ ጫት ቤት አካባቢ በቡድን/በግሩፕ የመቃምን ሂደት ጀመአ በማለት ሲጠሩት፤ በቻት ቤት ደግሞ የቡድን ጭውውት (group chat) ይሉታል፡፡

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ቻትም ጫትም የሚፈጥሩት የማህበራዊ ህይወት ክፍተት ነው፡፡ ጫት በባህሪው ቁጭ ማለትን የሚጠይቅ ሲሆን አንዴ ቁጭ ከተባለ ደግሞ ስለሚያደነዝዝ የመነሳት ስሜትን ያጠፋል፡፡ ታዲያ ይህ ባህሪው ከቻት ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ አንድ ሰው ቻት ላይ ከተጣደ ተነስ ተነስ አይለውም፡፡ ረዥም ሰዓታትን ቁጭ ብሎ ያሳልፋል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ከሰዎች ጋር ያለን ማህበራዊ ግንኙነት እንዲቀንስ ብሎም እንዲጠፋ ያደርገዋል፡፡

እንደውም ትንሽ የቆየን እንደሆን ለቅሶን፣ ሀዘንን፣ እንዲሁም የታመመ ሰው ጥየቃን ሁሉ በነዚሁ ድረ - ገፆች እስከ መጠቀም ሳንደርስ አንቀርም፤ አሁንስ አልተጀመረም ብላችሁ ነው? በዚህ አኳኋናችን እርግጠኛ ነኝ ወደፊት የሙዝና የብርቱካን ስዕል ፌስ ቡክ ላይ Tag በማድረግ (በመለጠፍ) የታመመን ሰው መጠየቅ እንደምንጀምር፤ አልያም RIP እገሌ (እገሌን ነብሱን ይማር) የሚል ግሩፕ በፌስ ቡክ ፈጥረን ቻት በማድረግ ለቅሶን መድረስ ባንጀምር…

ሌላኛው ተመሳሳይነታቸው በተጠቃሚው ላይ የሚያደርሱት አካላዊ ጉዳት ነው፡፡ መቼም ስለ ጫት የጤና ጠንቅነት መዘርዘር አይጠበቅብኝም፤ ምክንያቱም አብዛኞቻችን በቂ መረጃ አለን ብዬ ስለምገምት፡፡ ጫት የሚያደርሰው አካላዊ ጉዳት እንዳለ ሆኖ፣ ቻትን አዘውትሮ መጠቀም ለተለያዩ አካላዊ ጉዳቶች ያጋልጣል፡፡ ለምሳሌ ብዙ ጊዜ ቻትን በኮምፒውተር ስለምንጠቀም ለረጅም ሰዓት ኮምፒውተር ላይ በማፍጠጥ ለሚከሰት የአይን ብርሃን ጉዳቶች እንዳረጋለን…ወዘተ…ወዘተ፡፡

እርግጥ ነው በአሁኑ ሰዓት የነዚህን ሁለት አደገኛና አደንዛዥ ሱሶች ስርጭት ለመግታት የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ነው፡፡ በጫት በኩል ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በመሆን ጫት ማስቃሚያ ቤቶች እንዲታሸጉ እያደረገ ሲሆን በቻት በኩል ደግሞ በየትምህርት ቤቱና በየቢሮው ያሉ ኮምፒውተሮች ላይ እነዚህ ድረ ገፆች ቢያንስ በስራ እና በትምህርት ሰዓት እንዲዘጉ (block እንዲደረጉ) እየተደረጉ ነው፡፡ ዳሩ ግን ሁለቱንም ሱሶች በዚህም መልክ ከነአካቴው ልናስቀራቸው አንችልም፡፡ ምክንያቱም ጫት ቤቶችም ቢታሸጉ በየግል ቤታቸው እና የስራ ቦታቸው ጫትን የሚቅሙ ወጣቶች አይጠፉም፡፡ በቻት በኩል ደግሞ የቢሮና የት/ቤት ኮምፒውተሮች እንኳን ብሎክ ቢደረጉ በግል ሞባይሎቻቸው መጠቀማቸው አይቀርም፡፡ የወጣቱ ልብ እስካልተለወጠ ድረስ ብናሽገው፣ ብንዘጋው፣ ብናስረው፣ ብንገስፀው በዚህም ሆነ በዚያ ብሎ ሱሱን ከማስታገስ ወደ ኋላ አይልም፡፡ እዚህ ላይ አንድ የእንግሊዝኛ አባባል ትዝ አለችኝ “ሱስን ጨርሶ ማጥፋት አይቻልም ባይሆን በሌላ ሱስ መቀየር ይቻላል እንጂ” የምትል፤ አባባሏ እውነትነት ካላት እነዚህን ደባል ሱሶች(ቻትና ጫት) የምናስተውበት ቀጣዮቹ የወጣቶቻችን ሱሶች ምን ይሆኑ? ሰላም!

 

 

Read 6151 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 10:11