Wednesday, 04 April 2012 10:20

ድጋፍ የተነፈገው የማሊ ኩዴታ

Written by  ኤልሳቤት እቁባይ
Rate this item
(0 votes)

ከ1946-2004 ባሉት አመታት አህጉሪቱ በተከታታይ መፈንቅለ መንግስቶች ትናወጥ ነበር፡፡ ከመፈንቅለ መንግስቶቹ መካከል የብዙዎችን ህይወት የቀጠፉ ይገኙበታል፡፡ መፈንቅለ መንግስቶች በብዛት ከተካሄዱባቸው አገሮች መካከል ሱዳን ሃያአምስት ናይጀሪያ ሃያሁለት፣ ሴራሊዮን አሥራ አራት፣ ላይቤሪያና ቶጐ አስራሶስት፣ ጋና፣ ኮንጐብራዛቪል፣ ኮሞሮስ እና ብሩንዲ አስራሁለት ሞሪታኒያ አስራአንድ እና ቤኒን፣ ሴንትራል አፍሪካ ሪፖብሊክ፣ ቻድ፣ ጊኒ እና ጊኒ ቢሳዎ አስር ጊዜ ተካሂዶባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በተጠቀሰው አመታት ውስጥ ስድስት መፈንቅለመንግስቶች ሲካሄዱባት በማሊ ስድስት ጊዜ ተካሂዷል፡፡

ባለፈው ሳምንት በማሊ የተፈፀመው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት እንኳንስ ለተገልባጩ ይቅርና ለገልባጩም ድንገተኛና ቅፅበታዊ እንደነበር እየተነገረ ነው፡፡ በእርግጥ በመንግስቱ ሠራዊት ውስጥ ቅሬታዎችና ማጉረምረሞች ነበሩ፡፡ በቅርቡ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ አማፅያን መንግስት ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት መፈፀማቸውን ተከትሎ፣ የማሊ የጦር ሃይል አጥጋቢ ምላሽ ባለመሰጠቱና መንግስት ጦሩን ለአማፂያን ጥቃት አጋልጧል በሚል ወታደሮች ቅር ተሰኝተውም ነበር፡፡

የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ወደ አንደኛው የወታደሮች ካምፕ ሲያቀኑ አገር አማን ነው ብለው ነበር፡፡ የጠበቃቸው ግን ዱብ ዕዳ ነው፡፡ የመሳሪያ ተኩስና የድንጋይ ውርጅብኝ አስተናግደዋል፡፡ በዚያው ነው ቅፅበታዊ መፈንቅለ መንግስት የተከሰተው፡፡ መፈንቅለ መንግስቱን የተቀላቀሉ ወታደሮችና መኮንኖች ቤተመንግስቱን፤ የቴሌቪዥን ጣቢያውንና የተለያዩ ወታደራዊ ካምፖችን በብርሃን ፍጥነት ተቆጣጠሩ፡፡ የሚገርመው ደግሞ የቤተ መንግስት ጠባቂዎችና ወታደሮች ቤተመንግስቱ ላይ ጥቃት ሲፈፀም ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዳቸው ነው፡፡

እስከአሁን ባለው መረጃ፤ የአገሪቱ ፕሬዚደንት በመፈንቀለ መንግስት ተዋናዮቹ እጅ አልወደቁም፡፡

በማሊ የተከሰተውን ኩዴታ አስመልክቶ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ጄን ፒንግ፤ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤት በሰጡት መግለጫ፤ ስለፕሬዚደንቱ የተረጋገጠ መረጃ እንዳልተገኘ አመልክተው፣ ፕሬዚደንቱ በታማኞቻቸው ከፍተኛ ጥበቃ እተደረገላቸው እንደሆነ የሚጠቁሙ መረጃዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚደንቱ፤ ባማኮ በሚገኝ አንድ ያልታወቀ ኤምባሲ እንደተጠለሉም እየተነገረ መሆኑን አክለው ገልፀዋል - ኮሚሽነሩ፡፡

መፈንቅለ መንግስቱ ከተደረገ በኋላ የመፈንቅለ መንግሥቱ አድራጊዎች ቃል አቀባይ አማዱ ኮናሬ ባደረጉት ንግግር፤ “ብቃት የሌለው የቱሬ መንግስት በወታደራዊ ሃይል መተካቱንና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለሚመረጥ ፕሬዚደንት ስልጣኑን እንደሚያስረክቡ” ገልፀዋል፡፡ ራሱን “የመንግስት ህዳሴ እና የዲሞክራሲ አስመላሽ ኮሚቴ” በሚል የሚጠራው የመፈንቅለ መንግስቱ ቡድን መሪ የሆኑት ካፒቴን አማዱ ሳንጎ፤ ተጨማሪ መግለጫ እስኪሰጥ ድረስ የ24 ሰዓት ሰዓት  እላፊ መታወጁን አስታውቀዋል፡፡ መፈንቅለ መንግሥቱን ህጋዊ አይደለም በሚል ለሚቃወሙ ወገኖች ምላሽ የሰጡት አማዱ፤ “ህግ የተቀመጠው ሠዎችን ለማገልገል ነው፡፡ ህጋዊ አይደለም በሚል ሰበብ የማሊ ህዝብ የፕሬዚደንቱ ሥልጣን እስከሚያበቃ ድረስ መጠበቅ አለበት ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የስልጣን ጊዜያቸው ያበቃ እንደነበር ታውቋል፡፡

እስከ አሁን ባለው መረጃ፤ የማሊን መፈንቅለ መንግስት የደገፈ አገርም ሆነ ድርጅት አልተገኘም፡፡ የኦባማ አስተዳደር መፈንቅለ መንግስቱ አድራጊዎቹ ስልጣኑን ለህጋዊው አካል እንዲያስረክቡ እና ችግሮችን በመወያያት እንዲፈቱ በመጠየቅ፣ ለማሊ የሚሰጠውን እርዳታ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡

መፈንቅለ መንግስቱ ሲደረግ፣ በማሊ ዋና ከተማ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምእራብ አፍሪካ ልኡክ ሰኢድ ጂኔት ጋር ስብሰባ ላይ የነበሩት የኬኒያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሞሰስ ዌታንጉላ፤ “ይህ በአፍሪካ የመጨረሻው መፈንቅለ መንግስት መሆን አለበት፤ ደስ ያላቸው ወታደሮች ብድግ እያሉ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣን ላይ የወጣን መንግስት ማስወገድ  የለባቸውም” ብለዋል፡፡

ደቡብ አፍሪካ በበኩሏ፤ በባማኮ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ዘግታለች፡፡ የማሊ የቀድሞ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይም ከአገሪቷ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጣለች፡፡ የአለም ባንክ፤ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የአሜሪካ የእርዳታ ድርጅቶችም ኩዴታውን በማውገዝ ለማሊ ያደርጉት የነበረውን ድጋፍ አቁመዋል፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመጪው አገራዊ ምርጫ እጩ ፕሬዚዳንት በቡከር ኬይታ፤ ኩዴታውን “ኋላ ቀር” ሲሉ ኮንነውታል፡፡ የምእራብ አፍሪካ የኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኤኮዋስ) በበኩሉ፤ ጉዳዩ በጣም እንዳሳሰበው ጠቅሶ፤ የወቅቱ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር በኮትዲቯር ፕሬዚደንት የሚመራ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

የጦር ትምህርታቸውን በአሜሪካ የተከታተሉት ካፒቴን ሳንጎ፤ የኩዴታውን ዓላማ ሲናገሩ፣ ጦሩ ብቃት ያለው እንዲሆን ማድረግ፤ በጥሩ ሁኔታ የሚኖርበት ቤትና የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝና ሁሉም ወታደር መብላት መቻሉን ማረጋገጥ መሆኑን ጠቅሰው ከዚያ በኋላ ትኩረታችንን ጥራት ወዳለው ወታደራዊ ስልጠና እናዞራለን ብለዋል፡፡

የመፈንቅለ መንግስቱ ተባባሪ ወታደሮችም የዚህን እውን መሆን በተስፋ የሚጠብቁ ይመስላሉ፡፡

በቅፅበታዊ ኩዴታ ያሉበት የማይታወቁት ፕሬዚደንት ቱሬ፤ በየወሩ የሚቀያየረው የአፍሪካ ህብረት የፀጥታና ደህንነት ምክር ቤት ሊቀመንበር ነበሩ - ዛሬ የኩዴታ ሰለባ ቢሆኑም፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ የአፍሪካ ህብረት፤ በኩዴታው የተነሳ የፀጥታና ደህንነት ምክር ቤቱን ሊቀመንበርነት ከማሊ ወደ አንጎላ እንዳዛወረ ገልጿል፡፡

በአፍሪካ አህጉር የሚካሄዱ ኩዴታዎችን የሚኮንኑት አንድሪው ሚለር የተባሉ ምሁር፤  ባለፈው አመት ባወጡት ፅሁፍ፤ በአፍሪካ የሚደረጉ አንዳንድ ኩዴታዎች ጥሩ ናቸው በሚል የሚከራከሩ ወገኖችን ተችተዋል፡፡

በኒጀር የተደረገውን መፈንቅለ መንግስት አስመልክቶ “ክርስቲያን ሳይንሰ ሞኒተር” ባወጣው ፅሁፍ፤ አፍሪካ ወታደራዊ ሀይልን ለበጎ ዓላማ መጠቀም ትችላለች ሲል የገለፀ ሲሆን “ኒውስዊክ” በተቃራኒው ጥሩ መፈንቅለ መንግስት አለ ወይ ሲል ይጠይቃል፡፡ አፍሪካ ውስጥ የተካሄዱ መፈንቅለ መንግስቶች ጨቋኝ እና ሙሰኛ መንግስታትን ከስልጣን ያስወገዱ ቢሆኑም ከዚያ በኋላ ዘላቂ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ስርአትና ተቋማትን በማምጣት አልታደሉም በማለት ጥሩ መፈንቅለ መንግስት የሚለውን ጉዳይ ጨርሶ እንደማይቀበሉ ምሁሩ ይገልፃሉ፡፡

የኦክስፎርድ ኢኮኖሚስት ፓውል ኮይለር በ2009 ባወጡት ፅሁፍ ደግሞ፤ “መጥፎ መንግስታት በኩዴታ እስከተወገዱ ድረስ ኩዴታዎቹ ጥሩ ሊባሉ ይችላሉ፡፡ ዚምባቡዌያውንና አለም፤ ሙጋቤ በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ቢወገዱ አይጠሉም” ይላሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ልክ እንደ ሚለር በማን ይተካሉ የሚል ስጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡ በ2005 ዓ.ም በሞሪታኒያ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ ቡባከር ንዳዬ በፃፉት ፅሁፍ፤ መፈንቅለ መንግስቱ በስልጣን ላይ ያለውን ወታደራዊ መንግስትና አፍራሽ ፖለቲካዎቹን እንዲያከትም ማድረጉ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ምንም እንኳን የሰሜን አፍሪካ አረብ አገሮች ባለፈው አመት ከመፈንቅለ መንግስት በዘለለ፣ በህዝባዊ አመፅ መንግስታትን መለወጥ የቻሉ ቢሆንም ፀሀፊው የሞሪታኒያው  የመፈንቅለ መንግስት ልምድ ለነዚህ አገሮች የፖለቲካ ለውጥ ሞዴል ሊሆን እንደሚችሉ ጠቁመው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ከ1945 እስከ 2008 ባሉት አመታት ውስጥ በአፍሪካ ባጠቃላይ 363 መፈንቅለ መንግስቶች እንደተደረገ ይታወቃል - የታሰቡና የከሸፉትን ጨምሮ፡፡

ከ1980 ጀምሮ ግን በአህጉሪቱ ኩዴታ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ሙሉ በሙሉ ላለመቆሙ ግን ራሷ ማሊ ጥሩ ማሳያ ናት፡፡ የኩዴታው አቀናባሪ ካፒቴን ሳንጎ፤ ስልጣኑን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለሚመረጥ ፕሬዚደንት አስረክባለሁ እያሉ ቢሆንም እንዴት እና መቼ ለሚለው አስተማማኝ መልስ አልሰጡም፡፡ ቃሌን እንደምጠብቅ የሚያሳዩ እኔን የሚገልፁ ቃላቶች “ታማኝ” እና “ቀና” የሚሉት ናቸው ያሉት ካፒቴኑ፤ ከዚህ ውጪ ምርጫ የሚካሄድበትን ትክክለኛ ጊዜ የሚወስነው ነገሮች የሚሄዱበት ፍጥነት ነው ብለዋል፡፡ “ሶስት ወር፤ ስድስት ወር፤ ዘጠኝ ወር ለማለት ይከብዳል፤ መጠንቀቅ የምንፈልገው ለተልእኮው እንጂ ምርጫው ስለሚካሄድበት ትክክለኛ ጊዜ አይደለም” ሲሉ የበለጠ ጥርጣሬ ፈጥረዋል፡፡ ለነገሩ እውነት ምርጫውንስ ያካሂዱት ይሆን? ከሆነስ ምን አይነት ምርጫ?

 

 

 

 

 

 

Read 3668 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 10:24