Wednesday, 04 April 2012 10:31

ሠለሞናዊ ወግ

Written by  ሚልኪ ባሻ
Rate this item
(0 votes)

ጠቢቡ ሰለሞን እንደወትሮው በካህናቱ፣ በባለስልጣናት እና በቦዲ ጋርዶቹ ተከቦ በፍርድ ወንበሩ ላይ በመሰየም ከየክልሉ የሚመጡትን ክርክሮች በሚሰማበት አንድ ቀን፤ ሁለት ሴቶች በወታደሮች ታጅበው እየተመናቀሩ ወደ እርሱ ተጠጉ፡፡ ከወታደሮቹ አንደኛው ህፃን ልጅ ታቅፏል፡፡ ሴቶቹ እርቃናቸውን ብቻ የሚሸፍን ብጫቂ ቀሚስ አድርገዋል፡፡ ፊታቸውም በሜክ አፕ ተለቅልቋል፡፡ የቡና ቤት ሴቶች እንደሆኑ ከሩቅ ያስታውቃሉ፡፡ ህዝቡ ገና ሲያያቸው ማጉተምተም ጀመረ፡፡ ሰለሞን ፈገግ አለ፤ ካህናቱ ደግሞ መስቀሎቻቸውን እያወጡ አማተቡ፡፡ የደፈረሰውን የፍርድ ቤቱን ፀጥታ ለማስመለስ ሰለሞን በመዶሻው ጠረጴዛውን ደበደበ፡፡ የፍርድ ሂደቱ ከመጀመሩም በፊት የፍርድ ቤቱ ደንብ በመሆኑ፣ ዘቦቹ ሴቶቹን ለባለሥልጣናቱ እና ለንጉሱ ጐንበስ ብለው እጅ እንዲነሱ፤ ካህናቱን ደግሞ መስቀል እንዲሳለሙ፣ እና ጉልበት እንዲስሙ አዘዟቸው፡፡

ሴቶቹም እንደ ጠባያቸው ምንቅር ምንቅር እያሉ፣ በፌዝ አጐንብሰው ባለሥልጣናቱን ካከበሩ በኋላ፣ የካህናቱን መስቀል እየተሳለሙ እና ጉልበታቸውን እየሳሙ ሳለ፣ አንደኛዋ የቡና ቤት ሴት ቀና ብላ እያየቻቸው፤

“አባ - የሚያሳልሙኝ ሌላ ነገር የለዎትም?” ብትላቸው ነገሩ የገባቸው ካህንም በያዙት ግንድ የሚያክል መስቀል ግንባሯን ካልተረተርኩ ብለው ሲጋበዙ፤ ሌሎች ካህናት መሃል ገቡና እሷን ረግመው፣ ቄሱን ደግሞ ገስፀው ጠቡን አበረዱት፡፡

የቄሱ እና የቡና ቤቷ ሴት ፀብ ጋብ ካለ በኋላ፣ ሌላኛዋ ሴት ለመናገር ዕድል ሳይሰጣት፤ በገዛ ፍቃዷ እንደ ተልባ መንጣጣት ጀመረች፡፡ ጠቢቡ ሰለሞን እና ባለሥልጣናቱም ሁኔታዋ ቢያስገርማቸውም፣ ለተቀመጡበት ወንበር ክብር ሲሉ እንደ ምንም ሳቃቸውን ተቆጣጥረው ንግግሯን ሳያቋርጡ፣ ዝም ብለው ያዳምጧት ጀመር፡፡ ሀይለኛ እንደሆነች ታስታውቃለች፡

“ይሄውላችሁ እኔ እና ይቺ ሴት ሸለሌዎች ነን፡፡ አንድ ክፍል ቤት ለሁለት ተከራይተን እየሸቀልን አብረን እንኖር ነበር፡፡ አንድ ቀን ኮንዶም ሳልጠቀም ከወንድ ጋር ተኝቼ በማርገዜ ልጅ ወለድኩኝ፡፡ እሷም እንዲሁ እንደኔ ያለ ነገር አጋጥሟት ኖሮ፣ ከሶስት ቀን በኋላ እሷም ወለደች፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ምሽት፣ እርሷ ድብን ብላ ሰክራ መጥታ ልጇ ላይ ተኝታበት ታፍኖ ሞተ፡፡ ሌሊት ላይ ስካሯ በርዶላት ያደረገችውን ስታውቅ ጊዜ፣ እኔ ሳላውቅ ልጄን ከጐኔ ሰርቃ፣ የራሷ አልጋ ላይ አስተኝታ፣ የሷን እሬሳ ለእኔ አስታቀፈችኝ፡፡ ነግቶ ልጄን ጡጦ ልሰጠው ስነሳ ልጁ የእኔ እንዳልሆነ አወቅሁኝ፡፡”

ለባለሥልጣናቱ እና ለጠቢቡ ሰለሞን ይህንን ተናግራ ስታበቃ፣ ወደ ጓደኛዋ ዞራ በጧቷ እየዛተችባት “አንቺ ሰካራም አሮጊት! ልጅሽን በገዛ እጅሽ በልተሽ ደግሞ ልጄን ልትነጥቂኝ ያምርሻል? እሞታታለሁ እንጂ የፈለገ ቢሆን በህይወት እያለሁ ልጄን አታገኝውም!” አለቻት፡፡

ሌላኛዋም ቀበል አድርጋ “አፍሽን ሰብስቢ አንቺ ጥንብ! እኔ ሰካራም አሮጊት አይደለሁም፡፡ የሞተውም ያንቺ ልጅ ነው እንጂ የእኔ አይደለም” ብላ ስትመልስላት፣  ያቺኛዋ ልታንቃት ወደርሷ ስትንደረደር፣ የፍርድ ቤቱ ዘቦች ጣልቃ ገብተው ገላገሏቸው፡፡

ሁለቱም ሴቶች ንግግራቸውን ካቀረቡ በኋላ እና ሁለቱም ማስረጃ ማቅረብ የማይችሉ መሆናቸውን ከገለፁ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ በታላቅ ፀጥታ ተውጦ የተለመደውን አስደናቂውን የጠቢቡን ፍርድ ለመስማት አቆበቆበ፡፡ ነውጠኛዋ የቡና ቤት ሴት፤ በንዴት በሚንቀጠቀጡ ጣቶቿ ሲጋራ መለኮስ ሞክራ ሲያቅታት፣ ጓደኛዋ አይታት፣ ቀጭን ሳቅ ሳቀችባት፡፡ ያቺም ደም በጐረሱ አይኖቿ ክፉኛ ገላመጠቻት፡፡

(ሁላችሁም በምታውቁት መሠረት ይሄ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በቀረበው መልኩ አስደማሚ በሆነ ሁኔታ ባይደመደም ኖሮ ከሚከተለው መልኩ በአንዱ ሊደመደም ይችል እንደነበረ ማሰቡ ባይጠቅምም አይጐዳም፡፡)

እልህ

ጠቢቡ ሰለሞን፤ ጢሙን እያሻሸ ለሩብ ሰዓት ያክል ጉዳዩን በታላቅ ተመስጦ ሲያብሰለስል ከቆየ በኋላ፣ ጉሮሮውን “እህህ”…ብሎ አጥርቶ በአስገምጋሚ ድምፁ ሰይፍ እንዲመጣለት ሲያዝ፣ ከህዝቡ ዘንድ ከባድ ጉምጉምታ ተሰማ፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ልጁን በጠረጴዛ ላይ እንዲያጋድሙለት ትዛዝ ሰጠ፡፡ የህዝቡ ጉምጉምታ ባሰበት፡፡ ንጉሡ ሠለሞን እስከዛሬ ከገጠሙት ክርክሮች ይልቅ ይሄኛው እጅግ አዳጋች እንደሆነበት አውቆታል፡፡ እውነተኛዋን እናት ለመለየት አንድ አደገኛ ዘዴ ከመጠቀም በቀር ምንም ምርጫ የለውም፡፡ ሰይፉን አንስቶ እንዲህ ሲል ሴቶቹን አናገራቸው፤ “እንግዲህ ሁለታችሁም ህፃኑ የኔ ነው የምትሉ ከሆነ፣ በዚህ ሰይፍ ሁለት ቦታ ቆርጬው አንዳችሁ አንደኛውን ቁራጭ፤ አንዳችሁ ደግሞ ሌላኛውን ቁራጭ ትወስዳላችሁ፡፡”

ሰለሞን ይህንን ብሏቸው ሰይፉን ጠረጴዛ ላይ በተጋደመው ህፃን ትክክል ቀስ ብሎ ከፍ አደረገው፡፡ ሰለሞን ሰይፉን በቀስታ ወደ ላይ ከፍ ያደረገበት ምክንያት፣ እውነተኛ የህፃኑ እናት ልጇን ለማትረፍ ስትል፣ ለሌላኛዋ ሴት ህፃኑ እንዲሰጥ እንደምትጠይቅ እርግጠኛ ሆኖ ጊዜ ሊሰጣት ስለፈለገ ነበር፡፡ ከሁለቱም ሴቶች አፍ የወጣ አንድም ቃል ግን አልነበረም፡፡ ሰለሞን ልቡ ድው - ድው አለበት፡፡ አሁን ሰይፉ እስከ መጨረሻው ከፍ ብሏል፡፡ ህዝቡ በድንጋጤ እንደተዋጠ ትዕይንቱን ይከታተላል፡፡ ሰለሞን ሰይፉን አየር ላይ ለቅጽበቶች አቆየው፡፡ በዚህ መካከል ነውጠኛዋ ሴት፣ በንዴት እና በእልህ ጓደኛዋ ላይ እንዳፈጠጠች፤ “ልጄ ሲያምርሽ ይቀራል እንጂ አታገኚውም!” ስትል ሰምቶ ተስፋ ቆረጠ፡፡ ዘዴው እንዳልሰመረለት ገባው፡፡

ስህተቱን ለማስተካከል ግን በጣም ዘግይቶ ነበር፡፡ ሁለቱ ሴቶች ያቀረበላቸውን ሀሳብ ለመቀበል እስከተስማሙ ድረስ፣ ሰይፉን ከእንግዲህ ለመመለስ እንደማይችል ተረድቶ፣ በምትኩ የት ቦታ ቢቆርጠው፣ ህፃኑን እኩል ሁለት ቦታ መክፈል እንደሚችል ማሰብ ጀመረ፡፡

ኩራት

ጠቢቡ ሰለሞን ጢሙን እያሻሸ ለሩብ ሰዓት ያክል ጉዳዩን በታላቅ ተመስጦ ሲያብሰለስል ከቆየ በኋላ ጉሮሮውን “እህህ”…ብሎ አጥርቶ በአስገምጋሚ ድምጹ ሰይፍ እንዲመጣለት አዘዘ፡፡ የዚህን ተዐምረኛ ፈራጅ ጥበብ የለመደው ህዝብ፣ ሰለሞን ሰይፍ የጠየቀው ለምን እንደሆነ ለማወቅ በመጓጓት አሰፈሰፈ፡፡ የሰለሞን ቦዲጋርዶች ምን የመሰለ ሰይፍ ከነሰገባው እጁ ላይ አስቀመጡለት፡፡ ሰለሞን ከወንበሩ ተነስቶ ሰይፉን ከሰገባው ውስጥ ከመዘዘ በኋላ፣ በትካዜ እና በሀዘን እንደተዋጠ አንገቱን ደፍቶ በህዝቡ ፊት ለአያሌ ደቂቃዎች ወዲያ ወዲህ እያለ ተንጐራደደ፡፡ ከዚያም ጠረጴዛው ላይ ለብቻው ወደተጋደመው ህፃን ሄዶ ትክ ብሎ ያስተውለው ጀመር፡፡ በድንገትም ቀና ብሎ የተንጠለጠለውን ትልቅ የፍርድ ቤት ሰዓት ተመለከተ፡፡ ለወትሮው እጅግ ውስብስብ የተባለውን ክርክር ለመዳኘት እና ፍርድ ለመስጠት አስር ደቂቃ እንኳን አይፈጅበትም ነበር፡፡ የዛሬው ግን ይኸው ተኩል ሰዓት ሊሞላው ምንም አልቀረውም፡፡ የህፃኑን እውነተኛ እናት ማንነት ማረጋገጥ ተስኖት! ተሻግሮ ወደ መውጫ በሩ ሲመለከት ተረኛ ባለጉዳዮች ረድፍ ይዘው ለመግባት ሲቁነጠነጡ ተመለከተ፡፡ ህዝቡን ግን ቀና ብሎ ፊት ለፊት ሊያየው አልደፈረም፡፡ ስንቱን ጉድ፤ ስንቱን ምስጢር ፈትቶ አገር ምድሩን ጉድ ባሰኘበት የፍርድ ወንበር፤ የእነዚህን ምናምንቴ ሴቶች ክርክር መዳኘት አቅቶት በሚያደንቀው፣ በሚያከብረው እና በፍርዱም በሚታመንበት ህዝብ ፊት ሊዋረድ እና ሊቀል እንደሆነ አስቦ ውስጡ ተቆጣ፡፡ ይሄ ውርደት የሞት ሞት እንደሆነ ተሰማው፡፡ ከዚህ እፍረት ለዘለዓለሙ የሚገላገለውም አንዳች ነገር ሲያደርግ ብቻ እንደሆነ አወቀ፡፡ የክብር ሞት ሲሞት - ያኔ እፍረቱ በክብር ይለወጣል፡፡ ይሄን ውሳኔ በልቡ እንደወሰነም  ህዝቡን ፊት ለፊት አየው፡፡ ከዚያም ጠረጴዛው ላይ የተቀመጠውን የሚዛን ቅርጽ በግራ እጁ ካነሳ በኋላ፣ በቀኝ እጁ የያዘውን ሰይፍ ወደ ደረቱ ውስጥ ሻጠው፡፡

3. እብደት

ጠጢቡ ሰለሞን ጢሙን እያሻሸ ለሩብ ደቂቃ ያክል ጉዳዩን በተመስጦ ሲያሰላስል ከቆየ በኋላ ጉሮሮውን “እህህ …” ብሎ አጥርቶ የብስጭት ቃና ባለበት አስገምጋሚ ድምጽ ሰይፍ እንዲመጣለት አዘዘ፡፡ የመጣለትን ሰይፍ በእጁ እንደያዘ፣ በህዝቡ ፊት ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ ንግግር ማድረግ ጀመረ፤ “የተከበራችሁ ያገሬ ህዝቦች፤ ሁላችሁም እንደምታውቁት እኔ የሰባት መቶ ሚስቶች ባል እና የሶስት መቶ ዕቁባቶች ውሽማ ነኝ፡፡ መቼም ይህ ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆነ ሚስት ያለው ሰው ሁሉ ያውቀዋል፡፡ (እዚህ ላይ ሲቃ ስለያዘው ለአፍታ ንግግሩን ያቋርጣል፡፡ ከባለስልጣኖቹ አንዱ ተነስቶ ትከሻውን ቸብ ቸብ አድርጐ ካጽናናው እና ሃይላንድ ውሃ ከሰጠው በኋላ ተጐንጭቶ ንግግሩን ይቀጥላል)

“ታዲያ ይሄ ሀዘን እና መከራ ሳያንሰኝ ከእነርሱ የወለድኳቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ውሪዎች የቤተመንግስቴን ሰላም እና ፀጥታ አውከውታል፡፡ እነርሱን ሽሽት የአትክልት ቦታዎችን ብሰራም እዛም ድረስ ተከትለው እየገቡ ይበጠብጡኛል፡፡ እኔን መረበሻቸው ሳያንስ የአትክልት ዛፎቹን ሁሉ ፍሬ ገና ሳይበስል ከስር ከስሩ ለቅመው ጨርሰው፣ አሁን ደግሞ ግንዱን መጋጥ ጀምረዋል መሠለኝ ዛፎቹ ሁሉ እየደረቁ ነው፡፡  ከብዛታቸውም የተነሳ ህፃን የማላገኝበት አንድም ስፍራ በቤተመንግስቴ ውስጥ የለም፡፡ ከእናቶቻቸው ጋር አልጋ ውስጥ እየተጫወትኩ እንኳ እያለ አልጋው ስር እቃቃ ሲጫወቱ ያገኘሁዋቸው ጊዜ ሁሉ አለ፡፡ የተከበራችሁ ያገሬ ህዝቦች - ከእነዚህ ፈልፈሎች የተነሳም ለጥናት እና ለምርምር የሚያስፈልገኝን ፀጥታ ከማጣቴ የተነሳ፣  ከፈጣሪ የተሠጠኝን የጥበብ ፀጋ ብቻ ሳይሆን የአይምሮ ጤንነቴንም ለማጣት ተቃርቤአለሁ፡፡ የቤቴ ጉድ ሳያንሰኝ፣ ይሄ ውሪ ደግሞ ስንት ቁም ነገር በምሰራበት ፍርድ ቤት ድረስ መጥቶ ያውከኛል፡፡ ስለዚህ ለዚህ ድፍረቴ በዚህ በያዝኩት ሰይፍ ሁለት ቦታ ቆርጬ በማካፈል፣ እነዚህን ባላንጣዎች ልገላግላቸው ወስኛለሁ” በማለት ፍርዱን ለህዝቡ አሳወቀ፡፡ ህዝቡም በታላቅ ጭብጨባና ፉጨት የንጉሡን ፍርድ ተቀበለ፡፡

4. ስልጣኔ

ጠቢቡ ሰለሞን ጢሙንም ሳያሻሽ፤ ሩብ ደቂቃም ሳይቆይ፤ ጉዳዩንም ያን ያህል ሳይመሰጥበት፤ ጉሮሮውንም “እህህ” ብሎ ሳያጠራ፤ ሰይፉ እንዲመጣለትም ሳያዝ፤ በለሰለሰ ድምጽ የዲ.ኤን.ኤ ምርመራ ውጤት ለ ----- ቀን እንዲቀርብለት በማዘዝ  ሁለቱን የቡና ቤት ሴቶች በቀጠሮ አሰናበታቸው፡፡

 

 

Read 3985 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 10:39