Wednesday, 04 April 2012 10:35

የፍልስፍና እናቶች

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(3 votes)

ሀ. ማነን? ለ. ከየት መጣን? ሐ. ማን አመጣን? መ. እዚህ ምን እንፈይዳለን? ሠ. መሄጃችን ወዴት ነው? ረ. ወዘተረፈ (…)

ዳርዳርታችን ከምንጭ ውሃ የጠራ (ኮለለለለለ…ያለ) በመሆኑ ማብራሪያ ማከል ደክሞ ማድከም በመሆኑ (ላለማድከም መፈለጋችንን የገለጽንበት መንገድ እራሱ አድካሚ በመሆኑ) ወደ ጉዳያችን ቀጥታ!!

እነዚያ እንደጥርስ የደረደርናቸው ጥያቄዎች (ሠላሣ ሁለት አይደሉም እንጂ) ፍልስፍና እንደ እብደት ወፈፍ ሊያደርገን ሲከጅል አግጠው ይመጡብናል፡፡ እነዚህን ፈታሪ ጥያቄዎች ለመመለስ የሰው ልጅ ሁለት አቅጣጫዎችን መከተል ያዘወትራል፡፡ (በግዱ ቢሆንም) አንድ፣ በፈጣሪው እና በራዕዩ እንዲሁም በትንቢቱና በትንግርቱ ይመራል፡፡ ሁለት፣ የሰው ልጅ በራሱ በትዕቢቱ፣ ይቀጥላል፡፡ ፈላስፎች ነንና እነዚህን የሰው ልጅ ሁለት መንገዳት ስንፈላሰፍባቸው አንድም፣ ሁለትም፣ ሦስትም እየሆኑ፣ እየተሙለጨለጩ ያስቸግሩናል፡፡ በፈጣሪው የተመራ እየመሰለው በራሱ የቀጠለ ቢሆንስ? ወይም በራጡ የቀጠለ እየመሰለው በስውሩ ራዕይ ቢመራስ? ወይም በሁለቱም እየመሰለው በሁለቱም ባይሆንስ? ወይም በአንዱ እየመሰለው በሁለቱም ቢሆንስ?

ወይም እኛኑ የፍልስፍና ወፈፍታ ሲጠናወተን ቢሆንስ ወይም፣ ወይም፣ ወይም (ዛሬ ደሞ በወይም ተለክፈናል ወይም የለከፈን መስሎናል ወይም እኛ ለክፈነዋል ወይም…)

አንዷ የፍልስፍና እናት ግሪኮቹ “Epic” የሚሏት ግጥማዊ ተረት እንደሆነች J.B Suard ይነግረናል፡፡ እንግዲህ ጥንታዊው ሰው ለአቅመ ሐሳብ ሲበቃ እነዚያን የእብደት መሹለኪያ ፉካዎች ይወታትፍ የነበረው በተረታ - ተረት ነው ሲለን ወይም ሊለን ሲፈልግ Suard “People begin with epics and end with Philosophy” ጣል ያደርጋል፡፡ ደግሞም እውነቱን እኮ እንደሆነ በጊልጋሜሽ ኤፒክ ልናረጋግጥ እንችላለን፡፡ ከሁለት ሺ አምስት መቶ አመታት በፊት Akkdian በተሰኘ ቋንቋ የተፃፈ ሁለት መቶ ሃምሣ የድንጋይ ምጣድ (አሁን እዚህ አንነካካውም እንጂ)

ሁለተኛዋ የፍልስፍና እናት ደግሞ እመት አፈታሪክ ናቸው፡፡ እጥር ምጥን ያሉ ሴት ወይዘሮ ነገር ሳያንዛዙ (እንደ ኤፒክ) በአጭር በአጭሩ ቁርጥ ቁርጥ ነው አመላቸው፡ ማነን? ከየት መጣን? (ቅብርጥሴ) ሲገጥማቸው በማይመረመረው ባህሪያቸው የትም ይፈጩና ዱቄቱን ያመጡታል፡፡

ለምሳሌ አሀዱ

ፔርሺያዊቷ አፈታሪክ ዓለም እንዴት ተፈጠረች? ለሚለው የሚከተለውን ይመልሳሉ፡፡

Ormazd  የጥፋት መንፈስ ሲሆን ከባላጋራው Arnman (የፈጠራ መንፈስ) ጋር ዘወትር ይቆራቆሳል፡ (ሃይ ባይ ሽማግሌ በሌለበት ወይም አለም እንኳ ምንነቷ ባልታወቀበት ወይም ታዛቢ፣ ቲፎዞ፣ ምናምን በማይታወቅበት) መቆራቆስ ይሰለቻል፡፡ ሰለቻቸውና ሳይታወቃቸው “እኛው እንታረቅ” ሲሉ ዘፈን አወረዱ፡፡ እራሳቸው ተቀበሉ፡፡ በመጨረሻ ድርድራቸው ስምምነት ላይ የደረሰው ዓለምን ፈጥረው ተወካዮቻቸው የጭለማ እና የብርሃን ኃይላት በየተራ እንዲያስተዳድሯት የሚፈቅድ አንቀጽ አርቅቀውና ፈርመው እንዲሁም ትከሻ ለትከሻ ተሳስመው (ባናረጋግጥም)

ፔርሺያዊቷ እመት አፈታሪክ “ዓለም የተቃርኖ ውጤት ናት” ሲሉን ይሆን ከኛ በቀር ማን ያውቃል? (ፈላስፎች መሆናችን ቀረ)

ለምሳሌ ክልኤቱ

መሬትስ ተፈጠረ፤ ሙሴ በበትር የገመሰው የገማመሰው፣ የከፈለው የከፋፈለው ውሃ ከየት መጣ? ለዚህ ምላሽ ያላት የሰሜን ካሜሩዋዊቷ አፈታሪክ እንቁራሪቷንና ጉርጧን ወይም የባህር ኤሊዋን ይዛ ከተፍ (ፍጥነቷ) እንዲህ እያጫወተችን፤ እንቁራሪት፣ ጉርጥ ወይም የባህር ኤሊ የአለምን እርጥብ ከደረቅ ድንበር አበጁለት (ለምን እንደሆነ ባይገለጽም) ደረቅ መሬት ሁን አሉት፣ ደረቅ መሬትም ሆነ፤ ውሃ ሁን አሉት ውሃም ሆነ ይለናል ካሜሮናዊው የእነ እንቁራሪት ደብተራ፡፡

ምሣሌያዊው ሰለስቱ

ካሜሮናዊው የእንቁራሪት ኦሪት ዓለም ከተደራጀች በኋላ በሁለተኛውም ወር፣ በሁለተኛውም ሳምንት፣ በሁለተኛውም ቀን ከቀኑም በሁለተኛውም ሰዓት Tho –Dino መጣ፡፡ የዚህ አምላክ ተግባር እንደ ውሃ እና ደረቅ ምድሩ ሁሉ እንስሳቱን በወንድና በሴትነት መክፈል፣ (የፆታ ቅልቅል ወይም አንድነት አጋጥሞ ኖሯል?) ከፍሎም የቤትና  የዱር እንስሳቱን መለየት፣ ለይቶም በሰዎች መካከል የወንድና የሴት ሥራን ማደላደል ጨረሰ፡፡

ምሣሌያዊው አርባእቱ

ጥንታዊዎቹ ግሪኮች ያዋጡዋትን አፈታሪክ ደግሞ እነሆ Epimetheus ቤት አንዳች የምስጢር ሳጥን አለ፡፡ ያ ሳጥን አለም ላይ ያሉ በሽታዎች ሁሉ ተለቅመው የተከተቱበት የበሽታዎች እስር ቤት ሲሆን፣ እድሜ ለ Epimetheus አለም …  ከአሸባሪዎቹ በሽታዎች እፎይ ብላ ትኖራለች (እንዲሁም እኛ) ታዲያ ምን ይሆናል የ Epimetheus ሚስት Pandora ጓዳ ዕቃ ለማሰናዳት በምትንጐዳጐድበት በአንድ ጠማማ ውልግድግድ ቀን ሣጥኑን አይታ በግዴለሽነት መክፈት፤ በሽቶች አመለጡ፣ ነፃ ወጡ፣ እኛ ባርነት ገባን፡፡ (ሉሰፈር ከሰማይ ወደ ምድር እንደተወረወረው እና እንደሚያምሰው ይሆን?) ምሣሌ አርባዕቱ ተኩል

አፍሪካዊዎቹ አሻንቲዎች ደግሞ ይሄንን አፈታሪክ አዋጥተዋልና ይመሰገናሉ፡፡

ዋና - ገፀባህሪው ሸረሪት ነው፡፡ Anansi ይሰኛል፡፡ የንጉስ ሰለሞን ጥበባዊ ልክፍት ተጠናውቶት ኖሮ አለምን እየዞረ ከየጥበቡ ቁራሽ ሰበሰበ፡፡ እንደ ማሪያትሬዛ ብር በማሰሮ ሞልቶ ዛፉ ሥር ሊቀብር በማምራት ላይ ሳለ ልጁ አበሳጨው፡፡ ሸረሪታዊ ብስጩቱ ከሸረሪታዊ ትዕግስቱ በላይ ሆኖ በሸረሪታዊ ደምፍላትና ፍጥነት ማሰሮውን ወረወረው፡፡

ተሰበረ፡፡ ያ ሁሉ የጥበብ ናሙና ዛፉ ስር ተበተነ፡፡ Anansi ሆነ ልጁ፡፡ የተበተነውን ጥበብ ለመልቀም አልፈጠኑም (የዘጋባቸው) ጥበቡ እንደተበተነ ባክኖ ቀረ፤ እነሱም ደደብ እንደሆኑ ቀሩ፡፡ የእነሱ ዳፋ ለእኛም ተርፎ፣ የድድብና ውርስ (እንደ ኃጢያት ውርስ) ከዘር ዘር ሲተላለፍብን እዚህ ደርሶ፣ ከዘመነ ዳፍንት የሚያወጣን ማን ቆራጥ ሸረሪት ደግሞ ይመጣ ይሆን?

ምሣሌ አምስቱ

የአፈታሪኮቹ አፋዊ መዝገብ ከዘፍጥረታዊ ወግ ባሻገር እንደፍጥርጥሩ የምጽኣት ቀንን በራዕያዊ ግርማ፣ በትንቢታዊ ኩራት፣ በፍካሬያዊ ሞገስ ያቀርብልናል፡፡ ቀጥታ ወደ ፔሩ፡፡ (የቸኮላችሁ አንባቢያን የመመለስ መብታችሁ እንደተጠበቀ ሆኖ) እዚያ ፔሩ ያለው አፈታሪክ በመጨረሻዋ ቀን ትንሳኤ ቁሳቁሳን ይታወጃል፣ በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ ዋይታ ከዳር ዳር ይናኛል፡፡ እንዲህ የሰው ልጅ ሲጠቀምባቸው የኖረው ቁሳቁሶች በመጨረሻዋ ቀን እንደተደረገባቸው ሊያደርጉ ይነሳሉ፡፡ መጥበሻ ነሽ፣ ምጐጐ ነሽ፣ ማንቆርቆሪያ ነሽ፣ ጋን ነሽ፣ ብዕር ነሽ፣ ብርጭቆ ነሽ፣ ድስት ነሽ፣ መክተፈያ ነሽ…በሠራተኛው መደብ ወኔ፣ ቁጭት፣ ህብረት…በበዝባዡ የሰው ልጅ ላይ መፈክር እያሰሙ ለበቀል ይነሳሳሉ፡፡ የሰውን ልጅ መጥበሻው መጥበሻ፣ ምጐጐው መጋገሪያ፣ ብርጭቆው መጠጫ ወዘተረፈ ያደርጉታል፡፡ ስንቱን ዕቃ ሆነን እንችለዋለን?

ሰአሊ ለነ ቅድስት!! ከአፈታሪኩ የምፅአት ቀን ይሰውረን - አሜን!!

 

 

Read 4066 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 10:38