Wednesday, 04 April 2012 10:43

እንደ ስብሐት

Written by  ትዕግስቱ በለጠ
Rate this item
(0 votes)

የስብሃት ለአብ የማያልቁ የብዕር ትሩፋቶች

አንጋፋው ደራሲ ስብሃት ለአብ ገ/እግዚአብሔር ላለፉት 50 ዓመታት በብዕሩ አያሌ ጥበቦችን፣ ፍልስፍናዎችን፣ ሃሳቦችንና እውቀቶችን ሲዘራ የኖረ የሥነ ፅሁፍ ገበሬ ነበር፡፡  እንዳለመታደል ሆነና ግን የሚገባውን ክብርና ዕውቅና ሳያገኝ አለፈ፡፡   ክብር አላገኘም ብቻ ሳይሆን ጫንቃው ከሚሸከመው በላይ የውግዘት፣ የትችትና የነቀፋ ውርጅብኝ ሲዘንብበት የኖረ ደራሲ ነው፡፡ ደግነቱ ሰውየው ስብሃት ነበርና ችሎት ኖሮ አልፏል፡፡ እንደኔ ታዝባችሁ ከሆነ የስብሃት ስራዎች ላይ ውይይት ወይም ግምገማ የሚካሄድ ከሆነ ሃያስያን (ባለሙያዎቹም ሆኑ የልምድ አዋላጆቹ) የሂስ ቢላቸውን እንደጉድ ስለው ነበር ብቅ የሚሉት፡፡ አንዳንዴማ ለእሱ ብቻ የሚወጣ የክት ሞረድ ያላቸው ይመስላሉ - የሂስ ቢላቸውን የሚሞርዱበት፡፡ ከዚያ በኋላማ መሸረካከት ነው - ያለ ስስት! ሃያስያኑ አንጋፋ ደራሲያችን ላይ የትችትና የነቀፋ መዓት ሲያዥጐደጉዱበት ምርኩዛቸው ምን መሰላችሁ? የህብረተሰብ ባህል፣ ወግና ልማድ ነው፡፡ ያኔ የሥነፅሁፍ ባለሙያዎች ሳይሆኑ የባህል ተሟጋቾች ሊመስሏችሁ ይችላሉ፡፡ ከህብረተሰብ ልማድና ባህል የወጣ፣ ያፈነገጠ፣ የዘለለ ወዘተ በሚል ደራሲውን ከሰውየው ሳይለዩ ማብጠልጠል ነው፡፡ (ማነው ሃያሲ እግር የሌለው የሩጫ አስተማሪ ነው ያለው?)

ከሁሉም ደግሞ የሚገርመኝ ምን መሰላችሁ? የጋሽ ስብሃትን ሥራዎች ሲያስተነትኑ ወይም ሲያሄሱ ለምን ሰውየውንና ፀሐፊውን እንደሚያጣቅሱት ነው (በፖለቲካ ቢሆን ኖሮ ማጣቀስ ያስጠይቅ ነበር!)

እንግዲህ ት/ቤት ሲያስተምሩን ሃያሲ፤ የሂስ ስራውን ሲሰራ ሰውየውንና ፀሐፊውን (the man and the writer) መለየት እንደሚገባው ደጋግመው ነግረውን ነበር፡፡ ወይስ ትምህርቱ ስብሃት ጋ ሲደርስ ይከሽፋል? እሱንም እኮ በወጉ መንገር የአባት ነው፡፡ ለምን ቢባል? ደቀመዛሙርቶቻቸውን ከማይገባ መወናበድ ያድኑ ነበራ! ወይስ ቀድሞውኑ ዓላማቸው ይሄው ነበር - ማወነባበድ!

የሃያስያን ትችትና ነቀፋ እንደ ጉድ ከዘነበበት የስብሃት ቀደምት ሥራዎች አንዱ “ሌቱም አይነጋልኝ” ይመስለኛል - ያውም የአርታኢ እጅ የነካካው ጥራዙ! እንደወረደ የታተመውን ቢያገኙትማ በአደባባይ ስቅላት ከማስፈረድ ወደ ኋላ የሚሉ አይመስሉም ነበር - እንደ አያያዛቸው፡፡

የኢትዮጵያ አንጋፋ ድምፃውያንን ሥራዎች እያሰባሰበ “ኢቶፒክስ” በሚል ስያሜ ያስቀረፀው ባለውለታችን ፈረንሳዊው ፋልሴቶ በቅርቡ በኢቴቪ ሲናገር ሰማሁት - ስለስብሃት፡፡

ይሄ የኢትዮጵያ ወዳጅ እንደሚለው፤ የስብሃትን ዱላ የበዛበት የልቦለድ ሥራ (“ሌቱም አይነጋልኝ”ን ማለቱ ነው) ወደ ፈረንሳይኛ ተርጉሞታል፡፡ ያውም የአርትኦት መቀስ የቆራረጠውን ሳይሆን “እንደወረደ” የተፃፈውን፡፡ ስለ ስራውም አድንቆ ተናግሯል - ፋልሴቶ፡፡ (ነቢይ በአገሩ አይከበርም ይሏል ይሄ ነው!)

ቀደም ብዬ እንዳልኩት አንጋፋው ደራሲያችን ሥራውና የግል ህይወቱ እየተደበላለቀ ጫንቃው ከሚችለው በላይ የትችት ናዳ መሸከሙ ብቻ አይደለም የሚቆጨው፡፡ በባህልና ልማድ ጥበቃ ስም የሥነፅሁፍ ሥራዎቹ መብጠልጠላቸው ሳያንስ፣ እንደ ፀሐፊ ተገቢውን ዕውቅና አለማግኘቱም ያብከነክናል፡፡ ሥራዎቹ ለምን የአ.አ ዩኒቨርስቲን የጥናት ትኩረት አልሳቡም ተብሎ ሲጠየቅ፣ ዋናው ሰበብ የነበረው የህትመት ብርሃን ባለማየታቸው የሚል ነበር፡፡ አሁን ግን 10 ያህል ሥራዎቹ ታትመውለታል፡፡ ዛሬስ ትኩረት ስበው ይሆን?

እንደ ስብሃት ሥራዎች ፈር ቀዳጅነትና የተለየ የአፃፃፍ ክህሎት ቢሆን ኖሮ ደራሲው የዩኒቨርስቲውን የክብር ዶክትሬት ማግኘት አይበዛበትም ነበር፡፡ ከአፍሪካ አገራት ፀሃፍት እየተጠሩ፣ የክብር ዶክትሬት ሲሸለሙ ለስብሃት መነፈጉ በምን አሳማኝ ምክንያት እንደሆነ ፈጣሪ ይወቀው፡፡ ለኢትዮጵያ ሥነ ፅሁፍ ዕድገት አስተዋፅኦ በማበርከት ስብሃት ነው ወይስ የአፍሪካ ፀሃፍት የሚቀርቡት?

እኔና እኔን መሰሎቼ እንዲህ ብንጨረጨርም ምናልባት ስብሃት ስለዚህ ጉዳይ በህይወት ሳለ ተጠይቆ ቢሆን ኖሮ “እኔም እሺ ብዬ አልሸለምላቸውም ነበር!” ወይም ደግሞ “እኔን ባለመሸለማቸው ቀረባቸው እንጂ አልቀረብኝም!” ብሎ እንደዘበት ያልፈው ነበር - ማካበድ የማይወደው ስብሃት ለአብ፡፡

እቺ ቁጭት ውስጤ ያቆጠቆጠችው ስብሃት ከማለፉ በፊት ቢሆንም የቀብሩ እለት ከሞቱ እኩል ውስጤን ሲያንገበግበኝ ነበር፡፡እናም ይህቺን ሃሳቤን በውስጤ ስብሰለሰልባት ሰንብቼ ሰሞኑን ጥሩ ሰበብ አገኘሁ፡፡ ይኸውም የስብሃት አዲስ የአጫጭር ታሪኮች መድበል ለንባብ መብቃቱ ነው፡፡ በ128 ገፆች የተቀነበበውን “ቦርጨቅ” የተሰኘ መድበል አንብቤ ስጨርስ እንዴት አንጀቴ ቅቤ እንደጠጣ አልነግራችሁም! ስብሃት እኮ ራሱን በሥራዎቹ የሸለመ ድንቅ ደራሲ ነው አልኩኝ፡፡

ስብሃትን ሸለሙትም አልሸለሙትም ከምርጥ የአገራችን ፀሃፍት በቀደምትነት የሚጠቀስ ስለመሆኑ “ቦርጨቅ”ም ህያው ምስክር ናት! የዚህ መጣጥፍ ዓላማ የመፅሃፍ ቅኝት ነበር - ግን ቁጭት ቀደመብኝ፡፡ ስለዚህ ይቅርታ እጠይቅና ወደ “ቦርጨቅ” እዘልቃለሁ፡፡

በቅርፅ ለየት ከምትለው የስብሃት ታሪክ እንጀምር፡፡ የታሪኳ ርዝመት ሁለት አንቀፆች ብቻ ሲሆን - “እንጐቻ ልቦለድ” ወይም “የአጭር አጭር ልቦለድ” ለሚሏቸው ስያሜዎች የምትመጥን ታሪክ አይደለችም፡፡ “ኩሊ ኩሊ” ይላል - ርዕሷ፡፡ “አቤት እመቤቴ፡፡ ልሸከማ፡፡ አዎን፣ ኩሊ ነኝ…እርስዎ ከእግሬ ምን አሎት? እንኳን አንድ እግር ለምን ግማሽ እግር ብቻ አይኖረኝም? እርስዎ የሚፈልጉት ሸክሙ እዚያ መድረሱን…እሜትዬ፣ ያገሩን ዋጋ ይክፈሉኛ፣ ሌላ ምንድነው…?”

የስብሃት ባለአንድ እግር ኩሊ ከአሸካሚዋ ጋር ውዝግብ የገባ ይመስላል - በክፍያ፡፡ “…ኧረ ጭቦ ነው! ኧረ እንዲህ አይነቱ ነገር ቀርቷል፡፡ እንደ ድሮ እንዳይመስሎት… ማን ነው እሱ የስራህን ግማሽ ዋጋ ብቻ ከፍዬህ ይብቃህ ‘ሚለኝ! ድሮ ቀርቶ! እግዜር ይስጥልኝ፣ እሜትዬ… እንዲህ እየተዛዘኑ ነው ኑሮ ማለት፡፡ ልጅዎን ያሳድግሎት”

አደራችሁን! ከዛስ እንዳትሉኝ… እንኳን እኔ ደራሲውም ከዛ ቀጥሎ ያለውን አያውቀውም፡፡ ለምን ቢባል? ታሪኳ አልቃለቻ፡፡ እቺው ናት የስብሃት እጅግ አጭሯ ታሪክ!!

ቀጥለን የምናያት የደራሲው ዝነኛ ገፀባህርይ አጋፋሪ እንደሻው፤ እንዳሻቸው  የሚፎልሉበት ትርክት ሲሆን “ዘርና አጋፋሪ እንደሻው” የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል፡፡

በዚህ ትርክት አጋፋሪ እንደሻው፣ እንደወትሮው ሞትን መፍራት የታከታቸው ይመስላሉ፡፡

“እንግዲህ ከዚያች ሞትን ለጥቂት ካመለጡዋት የጠላ ትንታ ወዲህ፣ አጋፋሪ እንደሻው ሳይታወቅባቸው፣ የወጣላቸው የተዋጣላቸው ሂያጅ ወጥቷቸው ነበር፡፡ እንዲያውም ሞትን የሚሸሹ እያስመሰሉ ሴት ሲያሳድዱ ነበር እሚሰነብቱት፣ ሴት ሲቀማምሱ ሴት ሲጐራርሱ፣ ሴት ሲጠጋገቡ ነበር የሚከርሙት፡፡…”

አጋፋሪ እንዳሻው አዲስ ዓመል ያወጡት ደሞ ለብልሃታቸው ነው፡፡ ለጊዜው ከሞት ቢያመልጡም አንድ ቀን እጁ ሲገቡ እንዳይቆጫቸው የዘየዷት መላ ናት - ዘር መዝራት!

“ሆኖም አጋፋሪ ሴት ሲሄዱ ለዘር ብለው ይሂዱ እንጂ በህይወታቸው ሙሉ የማትጣፍጥ፣ ልብ የማታጠፋ ሴት ከቶ አጋጥሟቸው አያውቅም፡፡ “ሴት እጣዬ ነዋ!” ይላሉ ለራሳቸው ወይም ለጓደኛቸው… ” አጋፋሪ ሴት ላይ ምርጫ አያውቁም! (አድልኦ መፈፀም ይመስላቸዋል)

“መዝራት ነው!” ይላሉ ለራሳቸው “መዝራት! መዝራት!...አልፎ አልፎ መብቀሉ ይቀራል? ቂ-ቂ-ቂ-ቂቅ!” እያሉ መዝራት ብቻ ሆነዋል - አጋፋሪ፡፡

አጋፋሪ እንደሻው ሞትን የሚሸሹ እያስመሰሉ ያዲሳባን ሴቶች ሲያሳድዱ ሰባ ሰባት ዓመት ሆናቸው፡፡ ሆኖም ግን በከተማዋ ተላላፊ በሽታ መግባቱን ሲሰሙ ደነገጡ፡፡ የዓመታት ትጋቴን በሽታ እምሽክ ሊያደርግብኝ ነው ብለው በስጋት ቆዘሙ፡፡ ቆዘሙናም “አይሆንም” ብለው በወኔ ተነሱ፡፡ “ካዲሳባ ውጭም መዝራት ይኖርብኛል” በማለት፡፡ ሰማንያ ስምንት ዓመት ሲሞላቸው ተልዕኮአቸውን አጠናቀው እፎይ አሉ፡፡ እፎይታው ግን በስጋት የታጀበ ነበር፡፡ ቂጥኝ አውጥተው ነው የመጡት፤ ያውም ምስሬ ቂጥኝ ሳይሆን አደገኛው ማጭዴ ቂጥኝ!! (የዘራኸውን ታጭዳለህ ይሏል ይሄ ነው፡፡)

በዚህ መድበል ከሚተረኩት ትርክቶች የሚበዙት በአጨራረሳቸው ይመሳሰላሉ - አሳዛኝ ናቸው (tragic!)

በሦስት ገፆች ተቀንብቦ የቀረበው “ጥቁር ምላስ” የተሰኘ የአጭር አጭር ልቦለድም (Short Short ይሉታል) እንዲሁ ትራጄዲያዊ አጨራረስ ይስተዋልበታል፡፡ እናት ልጇንና አሮጊት እናቷን ረግማ ከቤት ትወጣለች፡፡ ከገበያ ስትመለስ እርግማኗ ደርሶ ይጠብቃታል - ሰዓሊለነ ቅድስት ይሏል ይሄኔ ነው!

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጠቆምታ (Biblical allusion) ያለው “አቤልን ፍለጋ” የተሰኘው የመድበሉ የመጀመሪያ ታሪክም እንዲሁ አሳዛኝ አጨራረስ ያለው ነው፡፡ የመድበሉ መጠሪያ የሆነው “ቦርጨቅ” ሲጠናቀቅም በተመሳሳይ ሁኔታ ነው - tragic ending የምንለው ዓይነት!! እንዲያም ሆኖ ግን የሚጨፈግጉና ጨለማ የሚያከናንቡ ታሪኮች አይደሉም፡፡ ይልቁንም ሳቅን የሚያጭሩና መዝናናትን የሚፈጥሩ ናቸው - የሚበዙት ታሪኮች፡፡

ታሪኮቹ የምናብ ምጥቀትና ጥልቀት የምናይባቸው ናቸው - በምናብ ይዘውን ይጓዛሉ - የደራሲው የምናብ ጥግ ድረስ፡፡ የቋንቋ አጠቃቀሙንና ስታይሉን በተመለከተ ግን ገጣሚ ሰለሞን ዴሬሳ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በ1991 ዓ.ም የገለፀውን እጋራለሁ፡-

“የስብሃት የአማርኛ አፃፃፍ የትም ባየውና ባይፈርምበትም የስብሃት መሆኑን አውቀዋለሁ፡፡ መጀመርያ መቅለሏ፣ የአረፍተ ነገሩ ማጠር፣ ቁጭ ብለህ የምትነጋገር ነው የሚመስልህ…” እውነት ነው፡፡ የስብሃት ቋንቋ ቀላል ነው - ግን ውበት አያንሰውም፡፡ የተባ ነው - አቅም አለው፡፡ ጋዜጠኛና ሃያሲ አለማሁ ገላጋይ “ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ህይወትና ክህሎት” መፅሃፍ ላይ ስለስብሃት የቋንቋ አጠቃቀም እንዲህ ይላል፡- “ስብሃት በቋንቋው ምትሀት ያስራል፡፡ ከባዱን ያቀላል… ረቂቁን ያገዝፋል… የተኮነነውን ያፀድቃል…” አለማየሁ ያለውን የቋንቋ ትባት በ”ቦርጨቅ” ላይ በደንብ እናየዋለን፡፡ እስቲ “አቤልን ፍለጋ” ከተሰኘው ታሪኩ ጥቂት ቆንጥረን እንይለት፡፡

“አዳም ቁርጡን አወቀ፡፡ ዱላውን ይዞ ወጣ፡፡ ሌቱን በጨረቃ ሲፈልግ አድሮ፣ ጠዋቱን በፀሐይ ሲፈልግ አረፈደ፡፡ ልጁን ሊያገኘው አልቻለም፡፡ ወንዙን ሲሻገር ውሃ ጠጣ፡፡ በረሃ ለበረሃ ይኳትን ጀመረ - ልጁን ፍለጋ፡፡ ፀሐይ ከላይ አሸዋ ከታች ጠበሱት፡፡ ምድር ምጣድ፣ ሰማይ አከንባሎ ጋገሩት፡፡ በውሃ ጥም ጉሮሮው ነቃ፣ ነፋስም ከዳው፣ በቁመናው ፈጣሪ እየቀጣው መሆኑ ታወቀው፡፡ እያለቀሰ ልጁን ፍለጋ ቀጠለ፡፡ ሲፈልግ ውሎ መሸ…” እያለ ይቀጥላል የጋሽ ስብሃት ትርክት፡፡

ከታሪኮቹ ሁሉ የበለጠ ያስደመመኝን ወደ መጨረሻ ያመጣሁት በአጋጣሚ ነው፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ “የእትያልታዬ ልጆች” መነበብ ያለበት ትርክት ነው፡፡ የእትያልታዬ ገብስማ ዶሮ እማሆይ ትባላለች፡፡ ቢጫ ድመታቸው ፈርኦን፡፡ ጌታ ሲሰቀል አነጋግሮታል የተባለው አውራዶሮ ደሞ ሙሴ ይባላል፡፡ ይሄኛው ታሪክ በገፀባህርይ አቀራረፅም ለየት ይላል - ሁለት ዶሮዎች፣ አንድ ድመትና አንድ ሴትዮ የተካተቱበት ታሪክ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ስብሃት እንስሳት ገፀ ባህርያትን እንደልቡ በመጠቀም ቀዳሚው ሳይሆን አይቀርም፡፡ በዚህ መድበል ብቻ ሳይሆን በሌሎችም፡፡

እንግዲህ ቅኝት አይደል የተባባልነው? የቀሩትን ታሪኮች ደሞ መፅሃፉን ገዝታችሁ ወይም ተውሳችሁ አንብቡት፡፡

ግን ጨክናችሁ ብትገዙት ነው የሚሻለው፡፡ 25 ብር ለ”ቦርጨቅ” ሲያንሰው ነው!! በሉ እንግዲህ የስብሃትን የብዕር ትሩፋቶች እያነበብን ሰውየውን እናክብረው!! ዘመን ለማይሽራቸው ድንቅ ስራዎቹም እንዘምርለት!!

 

 

Read 2377 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 10:49