Wednesday, 04 April 2012 10:50

እንደኔና እንዳንቺ

Written by  ተሾመ ገብረሥላሴ
Rate this item
(0 votes)

ዓመታት ነጉደዋል። ቅጠሎችም ደርቀው ረግፈዋል።የተዘራው አጎነቆለ። ያሸተው ተበላ። የምሥራቅ ነፋስ በሔድንበት መንገድ ለእልፍ ጊዜ ተመላልሷል። የጽጌረዳ ግንዶች አያሌ ትውልዶች በላያችን ላይ አለፉ። ለፍቅራችን ቡራኬ ከዚህ ግንድ ቅርንጫፍ የቀጠፍነው እምቡጥ ስንተኛው ትውልድ ይሆን?

እሾኩ አያምም ከተሸረከተው መዳፍ ውስጥ የሚንረዠረዠረው ደም አያስደነግጥም።  አዳም  ለሔዋን ቀጥፎ የሰጣት የጽጌረዳ ዘር ይሄው ነበር። አብርሃም ለሣራ ያበረከተላት ዕምቡጥ የተቀጠፈው ከዚሁ ቅርንጫፍ ላይ ነው። ሰሎሞን ለማክዳ…ከዚያም እኛ…ከዚያም ብዙ የፍቅር ትውልድ። ሲቀጥፍ ሲደማ ሲቀጥፍ ሲደማ በራሱ ደም መስዋዕት በሐሴት ሲጦዝ።በእምብርክክ እየዳኸ ጽጌረዳ ሲሰጥ…ጽጌረዳ ሲቀበል ስንት ትውልድ?

የሚንቀጠቀጡ ሙቅ ከናፍር፤ የታበተ አንደበት፤ ማየት የፈራ ዓይን፤ ረዓድ የገባው ወሽካፋ እግር፤ ይህን ጥግ ስንተኛው የፍቅር ትውልድ ይሆን የተንሾካሾከበት? ነው ወይስ የተፈላለጉ ከንፈሮች ተሸካክመው አንዳቸው በሌላኛቸው ክንፍ በረሩ?

የታበተ አንደበት ተፈታ? የፍቅር ዋጋ በቃላት ተተምኖ መሳው ተገኘለት? የቆምንበት ጥግ ስንቱን የፍቅር ቃል ኪዳን አዳምጦ ይሆን?

ይሔው እንግዲህ ዘመኑ ሮጠና ፈረሱም ሸመጠና አያሌ ሜዳዎች ታለፉ። ብዙ ተራሮችን ተሻገርን። ተቃቅፈን የሔድንበቱ ጫካ ሜዳ ሆኗል።

ስንተኛው አፍቃሪና ተፋቃሪ ትውልድ እንደሆነ እንጃ እንጂ ያው እንደኔና እንዳንቺው ተቃቅፎ በቀስተ ደመናው ወለል ላይ ይደንሳል።

ጨለማው በደፈነበት፣ ሽፍቶች በሚያደፍጡበት ኮሮኮንቻማ መንገድ ላይ መላዕክት መጎናጸፊያቸውን እያነጠፉ፣ ቀንዲላቸውን እያበሩ፣ ስንት ቀን ሸኙን? እኛ ስንመጣ እንቁራሪቶች ጩኸታቸውን ትተው ማዜም የሚከጅላቸው ለምን ነበር? እኛ ስንደርስ የአብሪ ነፍሳት ስስ ብልጭታ፣ እንደትንታግ የሚፍመው ለምን ነበር? አሁንም ያ ቦታና ያ ሰዓት ፍቅር ይንሾካሾክበታል።

ስስ ድምጾች እንደገሞራ ወላፈን በሚጋረፉ ትንፋሾች ታጅበው በጆሮ ሥር ይንቆረቆራሉ።እኔና አንቺ ‘በሁለት ገላ በሁለት ክንፍ’ በበረርንባቸው ሰማዮች ላይ ብዙዎች እያንጋጠጡ ውበትና ትፍስህታችንን በሲቃ አይተዋል።

አጋርነታቸውን በህጻን ፈገግታ ገልጸዋል፡፡ አልፈውም እነርሱም በዚያ ሰዓት የዚያ በረከት ተቋዳሽ ይሆኑ ዘንድ ተመኝተዋል። ፍቅረኞቻቸውን ናፍቀዋል። ገላቸውን በሐሴት ትኩሳት ራሳቸውን አቃጥለዋል። ጸልየዋል። አየሁት ያ! ሰማይ አሁንም ፍቅር ይከንፍበታል። በፍቅር ያበደ ስንተኛው ትውልድ እንደሆነ እንጃ እንጂ ይሄው ከከዋክብቱ ጋር ዓይኑን ይከንዳል፤ ዓይኑን ይገልጣል።

 

 

Read 2292 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 10:53