Saturday, 24 June 2017 11:09

‹‹አብርሆት›› የሥነ-ልቦና አገልግሎት ማዕከል ሥራ ጀመረ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

     በአምስት የስነ ልቦና ምሩቃን ከአንድ አመት በፊት የተቋቋመው ‹‹አብርሆት›› የስነ-ልቦና አገልግሎት ማዕከል በሳለፍነው ሳምንት በይፋ ተመርቆ ስራ ጀመረ፡፡ ማዕከሉ አራት ክፍሎች ያሉት ሲሆን እነዚህም የህፃናትና የወጣቶች የአዕምሮ ህመምና የጋብቻ፣ የሚዲያ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የስልጠና እና በአደጋ ምክንያት ሰዎች የንግግር ክህሎታቸውን ሲያጡ የሚታከሙበት የንግግር ህክምና ዲፓርትመንቶች እንደሆኑ ታውቋል። በተለይ የህፃናትና የታዳጊዎች ዲፓርትመንት የአዕምሮ እድገትና የንግግር መዘግየትን ጨምሮ ሌሎች እክሎችን ምርመራና ምዘና በማድረግ ህክምና ይሰጣል ተብሏል፡፡ የስነ-ልቦና ጉዳይ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት፣ የስነ ልቦና መንስኤዎችና ወሳኝ መፍትሄዎች ደግሞ በጥናትና ምርምር ክፍሉ ይከናወናል ተብሏል፡፡
ስልጠናን በተመለከተ ማዕከሉ ለተቋማት፣ ለግለሰቦችና በተለይ የስነ-ልቦናና የአዕምሮ ችግር በቤተሰባቸው ውስጥ ላለ ወላጆችና አሳዳጊዎች በየደረጃው እንደሚሰጥም ከማዕከሉ መስራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ሄኖክ ኃይሉ ገልፀዋል፡፡ ከሱስ፣ ከአዕምሮ ህመምና ከተያያዥ ችግሮች ጋር ያሉ ህሙማን ተኝተው መታከምና ማገገም የሚያስፈልጋቸው ከሆነም ለ“ቤዛ” እና “ስጦታ” ከተባሉ የስነ- አዕምሮ ህክምና ማዕከላት ጋር ማዕከሉ ባደረገው ስምምነት የሚታከሙበት ሁኔታ መመቻቸቱም ተገልጿል፡፡
ከሙያው ጋር ለ30 ዓመት እንደሚተዋወቁ የገለፁት ረዳት ፕሮፌሰር ፍሬው ከፍያለው፤ ወጣቶቹ ማዕከሉን ለማቋቋም ከፈቃድ ማውጣት ጀምሮ የገጠማቸው ውጣ ውረድ አልፈው ለዚህ መብቃታቸውን አድንቀው፤ በስራቸው ታማኝና ጠንካራ ሆነው ህዝብን በሀቅ እንደሚያገለግሉ እመተማመናለሁ ያሉ ሲሆን ወደፊትም በሚችሉት መጠን ማዕከሉንና ወጣቶቹን ለመደገፍ ቃል ገብተዋል፡፡ ‹‹አገራችን ላይ ሙያ ተሸጦ የሚተረፍበት ደረጃ ላይ አልተደረሰም›› ያሉት መስራቾቹ፤ “እኛም ሙያ ሸጠን ለማትረፍ ሳይሆን በዘርፉ ያለውን ከፍተኛ ክፍተት በአቅማችን ለመሙላት በጣም መጠነኛ በሆነ ክፍያ አገልግሎቱን ለመስጠት ማዕከሉን አቋቁመናል” ብለዋል፡፡

Read 6499 times