Saturday, 07 April 2012 07:47

በዓመታዊ ገቢ ሞውሪንሆና ሜሲ በሳምንታዊ ደሞዝ ሮናልዶ ይመራሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በዓመታዊ ከፍተኛ ገቢ ለተጨዋቾችና አሰልጣኞች የወጣን ደረጃ የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ እና የሪያል ማድሪዱ ጆሴ ሞውሪንሆ እንደሚመሩ ታወቀ፡፡ ባለፉት 12 ወራት ሊዮኔል ሜሲ በደሞዝ እና በተለያዩ የስፖንሰርሺፕ ገቢዎች 33 ሚሊዮን ዩሮ  እንዲሁም ጆሴ ሞውሪንሆ 14.8 ሚሊዮን ዩሮ እንዳገኙ ፍራንስ ፉትቦል ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ አረጋግጧል፡፡ ሜሲን በመከተል የሎስአንጀለስ ጋላክሲው ዴቪድ ቤካም በ31.5 ሚሊዮን፤ የማድሪዱ ክሪስትያኖ ሮናልዶ በ29.2 ሚሊዮን፤ በሩስያው ክለብ አንዚ ማካቻካላ ያለው ሳሙኤል ኤቶ በ23.3 ሚሊዮን፤ የማንችስተር ዩናይትዱ ዋይኔ ሩኒ በ20.6 ሚሊዮን፤ የማን ሲቲዎቹ ሰርጅዮ አግዌሮ እና ያያ ቱሬ በ18.8 እና በ17.6 ሚሊዮን፤ የቼልሲው ፈርናንዶ ቶሬስ በ16.7 ሚሊዮን፤ የሪያል ማድሪዱ ካካ በ15.5 ሚሊዮን እንዲሁም የባየር ሙኒኩ ፊሊፕ ላሃም በ14.3 ሚሊዮን ዩሮ  የዓመት ገቢያቸው እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ አግኝተዋል፡፡ጆሴ ሞውሪንሆ ዘንድሮም 14.8 ሚሊዮን ዓመታዊ ገቢ በማግኘት የአሰልጣኞች ሊግን በገቢ የበላይነት ሲቆጣጠሩ 3ኛ ዓመታቸው ነው፡፡ ሞውሪንሆ ደሞዝ ብቻ ሳይሆን በስፖንሰርሺፕ ገቢያቸውም ተሳክቶላቸዋል፡፡

በአውሮፓ እግር ኳስ ተጨዋቾችን በሚፈልጉ ትልልቅ የስፖርት ኩባንያዎች ሞውሪንሆ እኩል ተፈላጊ ሆነዋል፡፡ የ49 ዓመቱ ጆሴ ሞውሪንሆ በእግር ኳሱ  በጋዜጣዊ መግለጫዎች ድራማ በመፍጠር፤ አስገራሚ አስተያየቶች በመስጠት፤ በሜዳ ላይ ቡድናቸውን ለመምራት በሚያሳዩት ተግባር፤ በጎል የደስታ ገለፃቸውና፤ ለፎቶ በሚመች አኳኋናቸው ዛሬም መነጋገርያ ናቸው፡፡ በአወዛጋቢ ስብዕናቸው እና በራስ መተማመናቸው ብዙዎች ሊሆኗቸው እንዲፈልጉ አድርጓል፡፡ ሞውሪንሆ በኳስ ሜዳ ውጤታቸውና ከሜዳ ውጭ ከፍተኛ የሚዲያ ትኩረት ማግኘታቸው ትልልቅ የስፖርት ኩባንያዎች አብረዋቸው ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዲያሳዩ ምክንያት ሆኗል፡፡ በስፖንሰርሺፕ ብቻ የሚያገኙት ዓመታዊ ገቢ ከስኮላሬና ማራዶና እንዲሁም ከሌሎች 15 የአውሮፓ አሰልጣኞች ዓመታዊ ደሞዝ የሚስተካከል ነው፡፡ ሞውሪንሆ ለስታድዬም ትኬቶች መሸጥ፤ ለቴሌቭዥን ስርጭቶች ተመልካች መሟማቅ፤ ለስፖርቱ መወደድ በአጠቃላይ ለእግር ኳስ ንግድ የሚመች ስብእና መያዛቸው ገቢያቸውን አሳድጎታል፡፡በቼልሲ፤ በኢንተር ሚላንና ዛሬም በሪያል ማድሪድ ሞውሪንሆን የመሰለና ውድ ተከፋይ በአውሮፓ እግር ኳስ አልተገኘም፡፡ሪንሆ ከአሰልጣኝ ስራቸው ውጭ በሞውሪንሆነታቸው በየዓመቱ በማስታወቂያና ስፖንሰርሺፕ ስራ ተጨማሪ 4.3 ሚሊዮን ዩሮ ያገኛሉ፡፡በፍራንስ ፉትቦል ደረጃ መሰረት ቼልሲን ከለቀቁ በኋላ በፓሪስ ሴንትዥርመን በቅርብ ግዜ መስራት የጀመሩት ካርሎ አንቸሎቲ ሞውሪንሆን በመከተል በ13.5 ሚሊዮን ዩሮ ዓመታዊ ገቢ 2ኛ ናቸው፡፡  ባለፈው የውድድር ዘመን ከሞውሪንሆ በተሻለ በአውሮፓም ሆነ በአገር ደረጃ ከፍተኛውን ስኬት ያስመዘገበው ባርሴሎና አሰልጣኝ የሆነው ፔፕ ጋርዲዮላ በ9.5 ሚሊዮን ዩሮ 3ኛ ነው፡፡ ከ1 እስከ 10 ባለው ደረጃ 4 የእንግሊዝ እግር ኳስ አሰልጣኞች የገቡ ሲሆን 2 የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞችም ተካትተዋል፡፡ በአርሰናል 7 ዓመታትን ያለዋንጫ የዘለቁት  አርሰን ቬንገር በ9 ሚሊዮን ዩሮ በእንግሊዝ እግር ኳስ ከፍተኛውን ገቢ በመያዝ እየመሩ በአራተኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ በሩስያው ክለብ አንዚሂ ማቻካላ ያሉት ጉስ ሂድኒክ በ8.6 ሚሊዮን ዩሮ በ5ኛ ደረጃ ሲመዘገቡ ከእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን የለቀቁት ፋብዮ ካፔሎ ባለፈው 12 ወር 8.5 ሚሊዮን ዩሮ በመከፈል 6ኛ ናቸው፡፡ የ80 ዓመቱ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በ8 ሚሊዮን ዩሮ ዓመታዊ ገቢ ሰባተኛ ሲሆኑ፤ በሩስያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት 7 ሚሊዮን ዩሮ የሚከፈላቸው ዲክ አድቮካትና፤ የቻይናን ብሄራዊ ቡድን  በ6.1 ሚሊዮን ዩሮ ከሚያሰለጥኑት ጆሴ ካማቾ ያነሰ ክፍያ በማግኘት በ5.9 ሚሊዮን ዩሮ በ10ኛ ደረጃ የሲቲው ሮበርቶ ማንቺኒ ሆነው ተጠቅሰዋል፡፡  በሳምንታዊ ደሞዙ ከፍተኛውን በማግኘት የሚመራው የሪያል ማድሪዱ ክርስትያኖ ሮናልዶ ሲሆን 45,1215 ፓውንድ በሳምንት ስለሚከፈለው ነው፡፡ የቡድን አጋሩ ሪካርዶ ካካ ደግሞ በሳምንት 313,371 ፓውንድ እየታሰበለት ሁለተኛ ደረጃ ይሰጠዋል፡፡ የማንችስተር ዩናይትዱ ዋይኔ ሩኒ በሳምንታዊ ደሞዙ 263,824 ፓውንድ ያገኛል፡፡  የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ 250,739 ፓውንድ በሳምንት ሲከፈለው፤ ፒዮል 218ሺ ይታሰብለታል፡፡ ሌሎች የክለቡ ወሳኝ ተጨዋቾች ዣቪ 187 559 9ውንድ እንዲሁም ኢንዬስታ 85 248 ፓውንድ የሚከፈላቸው ናቸው፡፡ የቼልሲ ተጨዋቾች በደሞዝ ክፍያ ከፍተኛውን በማግኘት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከቼልሲ ተጨዋቾች ዲድዬር ድሮግባ 221,641 ፓውንድ ፤ፍራንክ ላምፓርድ  213,127 ፓውንድ፤ፈርናንዶ ቶሬስ 210,568 ፓውንድ ጆን ቴሪ 200,589 ፓውንድ ሳምንታዊ ደሞዝ  አላቸው፡፡ በጀርመን ያሉ ምርጥ ተጨዋቾች በሳምንታዊ ደሞዝ ከእንግሊዝና ስፔን ክለቦች እጅግ የወረዱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል በባየር ሙኒክ ያሉት ሽዋንስታይገር 97,420 ፓውንድ ፍራንክ ሪበሪ 63,935 ፓውንድ መከፈላቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡

 

 

 

Read 5049 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 07:51