Saturday, 19 August 2017 12:51

ጨው በረንዳ

Written by  አጥናፉ አበራ አክሊል
Rate this item
(6 votes)

 በአጓጉል ጨዋታዎች ላይ መሆናችንን የሚያስጠነቅቀን ወግዱ፣ ልብ አድርጉ፣ አን ስድ፣ አን ወሽካታ የሚል የለመድነው የዘይነባ ሰኢድ ድምጽ ነው፡፡ ጉፍታዋን ተከናንባ እህል ከእንክርዳድ እየለየች፣ ዐይኖቿን ወደምንጫወትበት እየሰደደች፣ ዋልጌነታችንን በተግሳጽ ትከረክማለች፡፡ እንግሊዝኛ መምህራችን፤ Unconditional, uncountable, unbeatable እያለ ሲያስተምረን፣ አን ባለጌ፣ አን ስድ፣ የሚለው የዘይነባ ድምጽ ክፍሌ ድረስ መጣብኝ፡፡ ይቺ “UN” የምትባለውን ቃል መምህሬ ትርጉሟን ነገረኝ፡፡ የዘይነባን አን ትርጉም ግን ሳላውቃት ጥቂት ከታገለችኝ በኋላ ደረስኩባት፡፡ ለካ ዘይነባ “ውሎዬ” ናት፡፡ በተወለደችበት ቀዬ፣ አንተ ባለጌ ለማለት “ተ”ን እየገደፉ፣ አን ባለጌ ማለትን ቀጠሉበት የሚል የራሴ ድምዳሜ ላይ ደረስኩ፡፡
ጊፍቲኮ ማሎ፣ ትለኛለች ከትምህርት ቤት ስመጣ፣ ከቤታችን ምሳ ባለመድረሱ ከእርሷ ቤት ወጥ ለማስጨመር አንከርፍፌ የያዝኩትን ደረቅ እንጀራ፣ ወደ ሰሀኑ እያጠፈች፣ እንደ ባለ መብት ከፊቷ የተገተርኩትን እኔን እያየች፡፡ ድንች በሥጋ፣ ሳድግ ወይ ሳገባ፣ የዘውትር ቀለቤ አደርገዋለሁ የሚል ምኞት ያደረብኝ፣ ብርሃኔ ጅሩ /ባዬ/ ያለ ስስት ደረቅ እንጀራዬ ላይ ደፍታበት፣ የጣቶቼን ግማሽና የከንፈሬን ክፈፍ በወዝ ያራሰችበት ቀን የእርካታዬ መጠን ወደፊት ድንች በሥጋን ከእቅዴ ውስጥ እንዲገባ አስገደደው፡፡
ይህ ለአንድ አጋጣሚ የተሰራ ደግነት ሳይሆን ባስፈለገኝ ጊዜ ሁሉ የባዬ ቤት ቤቴ ነበር፡፡ እርሷ ባደረገችልኝ ቸርነት መጠን እኔም ለእርሷ ደስ የሚላትን ለማድረግ ደስታዬ ነበር፡፡ ባዬ የውስጥ እግሯ ሲታሽላት ትወድ ስለነበር፣ ማታ ማታ አጠገቧ ሆኜ በቫዝሊን እያሸሁ፣ እንደ አዋቂ እያጫወተችኝ አመሻለሁ፣ ብዙ ጊዜ የባዬ ጨዋታ ስለ ሀገር ጉዳይ ነው፡፡ እግሯን መታሸት ይበቃኛል ስለማትለኝ፣ እዛው እግሯ ስር አንቀላፍቼ ፍንግል እላለሁ፡፡ አንዳንዴ ቤተሰቦቼ ይጠሩና ይወስዱኛል፣ አልያ ተቀስቅሼ በደመነፍስ አየር ላይ እንደተንሳፈፍኩ ቤት እደርሳለሁ፤ ራት ስለ መብላቴ አልጠየቅም፣ ምክንያቱም ያመሸሁት ባዬ ቤት ነው፡፡
ፋጢማ መንሱር ከውቅሮ ከመጣች ከ40 ዓመት በላይ ሆኗታል፤ እጇ መድኃኒት ነው፡፡ ወላጆቻችን እኛን ሀኪም ቤት ከመውሰድ ይልቅ በእርሷ ባህላዊ የህክምና ዘዴ ተጠቅመው ከህመማችን ይገላግሉናል።
አፍ መፍታት ላልቻለ ህጻን፣ ለጆሮ ደግፍ፣ ለቦአ፣ ጸጉር አላበቅል ላለ ጭንቅላት የምታዛቸው መንፈሳዊ ምክርና ከእፅዋት ከስራስር የሚዘጋጁ መድኃኒቶች ውጤታማነት አሁን ድረስ ይደንቀኛል። ፋጢማ መንሱር፤ ለኔ በልዩ ስፍራ የማስቀምጣት፣ በየምክንያቱ የምገልጻት መጽሐፈ ምሳሌዬ ናት።  እጇ ሰጥቶ አይጠግብ፣ ሰውን የማስተናገድ ችሎታ፣ ፈጣሪን መፍራትን በኑሮ በየዕለት እንቅስቃሴዋ የምትተገብር፣ ካዘነው ጋር አዛኝ፡፡ አንድ ቀን ማታ ሌባ ቤቷን ሲሰብር እጅ ከፍንጅ ተይዞ፣ እንደ ማሪያም ጠላት ሲቀጠቅጡት  ደረሰች፤ በሌባውና በሰዎቹ መካከል ገብታ አስቆመችና፣ ወደ ሌባው ዙራ፤ “አታ ጓለይ ርቦህ ነው አይደል የሰረቅከው?” ብላ ጠየቀችው፡፡ “አዎ” አለ ሌባው፡፡ “ለአላህ ብላችሁ ተውት” አለቻቸው፡፡ ለመከትከት አሰፍስፈው የነበሩትን ሸኘች፡፡ ሌባው የተመታበትን ትከሻ እያሻሸች፣ “ዋይ እናትህ” ብላ አለቀሰች፡፡ በሌባው እናት ቦታ ራስዋን አስቀምጣ፣ በሌባውም ቦታ ልጆቿን እያሰበች ከልቧ አዘነች፡፡ የኔ ፋጢ እንዲህ አይነት ሰው ናት፤ ሊጎዳት ለመጣ እንኳ የሚራራ ልብ ያላት፡፡
“ዋይ መዘዝ እቲ ብሊ” ትለኛለች፤ ከገበታው ላይ ቅልጥሙን እያነሳች፡፡ “ሰሚኢ እኛ ስናድግ እንዲህ ያለ ነገር አናውቅም፤ ለሀዘንም ቢሆን ለደስታ የሚታረደው ከብት እኩል ይካፈላል፤ በግማሹ ላይ ክር ይታሰርና ባንድ ድስት ይሰራል፡፡ ወጡ ሲደርስና ሲጨለፍ፣ ክር ያለበት ቅልጥም ከወጣ ክርስታያኑ ይበላዋል፣ ክር የሌለውን ደግሙ ሙስሊሙ ይበላዋል፡፡ እሞ ብሊ እሽ መረቅ መረቁን ትለኛች። እንከት አድርጌ እበላለሁ፤ፋጢ ፍቅሯ ምንም የማስበላት ጉልበት አለው፡፡ እናቴ ናት፤ትሰስተናለች፣ ትመርቀናለች፡፡ ትግሪኛ ቋንቋዋን አልሰማውም። “በሀፍቲ እደጊ” የምትለዋን ማሳረጊያዋን ብቻ አውቃታለሁ፡፡ ከተቀደሰው መንፈሷ የሚዘንብብኝን ምርቃት አሚን!...አሚን!… አሚን!... እለዋለሁ። “ያረቢ የጠየክሁትን ሁሉ ጀባ” በእንሾሽላ የቀላ መደፏ ላይ “ቱ…ቱ..” ትልና መዳፏን ከመዳፌ ጋር አጣብቃ አይበሉባዬን ትስመዋለች፤ እኔም የእርሷን እስመዋለሁ፡፡ የፍቅሯ ባለ ዕዳ ነኝ፡፡ በዘመኔ ሁሉ የምተርካት መልካም ሴት፡፡ ወንድሜ ሄኖክ፣ ደም በለበሱ ዐይኖቹ፣ በዋይታ በተዘጋ ጎሮሮ እንዲህ አለ፡- “አደይ ያለችው በገነት ነው፤ ከመስፈርቱ አላጎደለችምና” ከቀብሯ ሲመለስ፡፡
በጥፋቶቻችን የምንገረፍባት ዘነበች የምትባል አለንጋ ነበራቸው፤ ጋሽ ዘሪሁን ጉዴ፡፡ የመንደሩ ህጻናት ከወላጆቻቸው ይልቅ የሚፈሩት እርሳቸውን ነው፡፡ ህጻናቱ የመንደሩን በፍቅር መተዳደሪያ ደንብ ሳያጓድሉ የመኖር ግዴታ አለባቸው፡፡ ትንሽ ቅብጠት ካሳየን፣ ጋሽ ዘሪሁን፣ “ፊደል” ሄደዋል ማለት ነው፡፡ ያም ቢሆን ጥፋታችንን ገልጠው የሚያስለጠልጡን ወላጆቻችን ነበሩ፡፡ እኛም በእርሳቸው በመገረፋችን የምንቋጥረው የቂም ዶሴ አልነበረንም፡፡ የፍቅር ልምጭ እንደሆነ፣ የልጅነት ንጹህ ልባችን መስክሮልናል ባይ ነኝ፡፡
አንዳንዴ ባንዳችን ጥፋት ሁላችንም ታጉረን የምንለጠለጥበት ምክንያት ግር ይለን ነበር። ቆይተን አጥፊው እንዳያጠፋ፣ የኛ ተግሳጽ ያስፈልግ እንደነበር ገባኝ፡፡ ቸልታ፣ ምን አገባኝ፣ እኔ የለሁበትም ማለት ለካ፣ ጥፋትን መተባበር ነው አልን፡፡ በጋራ እንዳንገረፍ፣ ጥፋትን በጋራ መከላከልን ለመድንበት። አሁን አሁን  በቸልታ፣ በእኔ የለሁበትም የሚጠፉ ጥፋቶችን ሳይ፣ ሰብስቦ በጋሽ ዘሪሁን አለንጋ ማስለጥለጥ ነበር የሚል ቁጭት ይይዘኛል፡፡ ከ‹ፊደል› ሲመለሱ በሚያመጡልን ፍራፍሬና ሸንኮራ፣ አካባቢው በዝንብ ይወረር ነበር። አስፓልት  መውጣት፣ ጸጉር ማንጨፍረር፣ በዊግ መሰራት፣ ጥፍር ቀለም መቀባት የመሳሰሉ ሁሉ በጥብቅ የተከለከሉ ነበሩ፡፡ ዕድሜአቸው ለአቅመ አዳምና ሄዋን የደረሱ ወጣቶችን፣ በመኪናቸው ጭነው ከሚሰሩበት ቤተሰብ መምሪያ፣ የጾታ ትምህርት እንዲማሩ ያደርጋሉ፡፡ የሁሉ አባት ነበሩ፣ ሁሉም የእርሳቸው ልጅ፡፡ በልጅነቴ አባቴን በሞት ስላጣሁ፣ ጋሽ ዘሪሁንን በአባቴ ቦታ ተክቼ ኖሬአለሁ። በሞታቸውም ጊዜ፣ አባቴ አባቴ ብሎ የማልቀስን ወግ ያየሁት በእርሳቸው ነው፡፡
በበርበሬና ዘይት የታሸ የጤፍና የስንዴ ቅይጥ ዳቦ ቆሎ፣ ጆሮ ግንዳችን እስኪያመን ከበላን “እታተይ” ከወልዲያ አምጥታልን ነው፡፡ ክረምቱን ከእርሷ ቤት በራፍ ተቀምጠን፣ ዳንቴል በመስራት እንሽቀዳደማለን፡፡ ሰብሰብ ብሎ መቀመጥ፣ እየመጠኑ መሳቅ፣ ከንፈር ገጥሞ ማላመጥ፣ጓደኛ አለማብዛት፣ ንጽህናን መጠበቅን ደጋግማ በመንገሯ ይሰለቸን ነበር፡፡
በኋላ ላይ ተማክረን፣ አስቴር ብለን የኮድ ስም ሰጠናት፡፡ ልክ ለምክር ስትጠራን፣ በሹክሹክታ በሉ አስቴር ሙዚቃዋን ልትከፍትብን ነው ብለን እንሳሳቅ ነበር፡፡ እታቴ (የወርቅ ውሃ) ለኔ የክርስትና እናቴ፣ ለልጅ ፊት የማሳየት ልምድ ባይኖራትም እንኳ በልጅነት ምኞታችን ድፍረት በካርቦን (ጉሎ) የተዘፈዘፈ ነጠላዋን ደብቀን ለብሰን፣ የማገር ስባሪ መዞብን፣ እስክትረሳው አያቴ ሰፈር ከርሜአለሁ፡፡ ኦጵላላስ ተባብለን፣ የሰቀለችውን ቋንጣ ስንቆረጥም፣ ሲባጎው ተበጥሶ አለቀልን ስንል ራርታልናለች። ሳል ሲያመኝ ኑግ፣ አጃ የምታፈላው እርሷ ናት። 16 ቁጥር አውቶብስን የማውቃት በለሊት ጸበል ልታስጠምቀኝ፣ እንጦጦ ኪዳነምህረት ስታመላልሰኝ ነው፡፡
በጸበሉ ቅዝቃዜ፣ እትትት እያለ ጥርሴ ሲንገጫገጭ፣ እንዳልንፈራገጥ አጥብቃ ይዛ፣ በምፈራው ዓይኗ ዓይኔን ውስጥ እያየች፣ “ትወጣታለህ” እያለች ስትዝትብን፣ ከሆዴ ውስጥ ጥቁር ግድንግድ ወጠምሻ ተጎልጉሎ የሚወጣ ይመስለኝ ነበር፡፡ አስተዳደጌን ሳስታውስ፣ እኔን ያላገለገለኝ ማን ነበር እላለሁ፡፡
እኔ የነኚህ ሰዎች ሰፈር ሰው ነኝ - “የጨው በረንዳ”። ጨው በረንዳ ሀገሬ ነው፡፡ ይህ ማንነቴ በመንፈስም ሆነ በአካል እንዲጠረቃ፣ ፋጢማ መንሱር ከውቅሮ፣ ባዩ ከአባዶ፣ ወርቅውሀ ከወልዲያ፣ ጋሽ ዘሪሁን ከሸዋ በጉርብትና የመጡልኝ፣ በተዋጣ ፍቅር፣ በተዋጣ ምግብ፣ በተዋጣ ምርቃት፣ በተዋጣ ተግሳጽ እንዳድግ የተመረጥኩ ዕድለኛ ሴት ነኝ፡፡ በእነኚህ ሰዎች  ምክንያት ኅብረት፣ እኩልነት፣ እኛነትን ተምሬአለሁ፡፡ ማንም የሀይማኖቱንና የዘሩን ከፍታ አልሰበከኝም፡፡ የሰብዓዊነት፣ የኢትዮጵያዊነት፣ የአስተሳሰብ ልቀትን ቀሰምኩበት እንጂ፡፡ ለኔ የሀገር ትርጉም፣ከዚህ በላይም ከዚህ ውጪም አይደለም፡፡
እኔነቴ በእያንዳንዳቸው ቋንቋ፣ በእያንዳንዳቸው ባህል፣ በእያንዳንዳቸው ሀይማኖት ተገጥግጧል፡፡ ሁሉንም በፍቅርና በእኩልነት እንዳይ የሚያስችል ዓይን፣ ገና በልጅነቴ ገጥመውልኛል፡፡ በየጊዜው የሚነሱ የዘርና የሀይማኖት ውዥንብሮችን በዘመኑ ቋንቋ “አይሰማም” ብዬ አልፋቸዋለሁ። ከነኚህ አስተሳሰቦች ወገን መቆም፣ ከተሰራሁበት መሠረት፣ አንድ ብልት እንደ ማጉደልና ውለታን እንደ መካድ እቆጥረዋለሁ፡፡
እኔ የዚህ ሰፈር ሰው ነኝ! በጨው በረንዳ ምርግ አልባ ግድግዳ፣ አጮልቄ የታዘብኩትን፣ ቢሆን የምለውን እንደዚህ ሞከርኩት፡፡ በዚህ መጽሐፍ በየገጹ የምታገኟት እኔን ስትመለከቱ፣ የፍላጎቴን አድራሻ ይጠቁማችኋል፡፡
በተረፈ ከዛጉ ጣሪያዎች ስር አእላፋትን የሚገነቡ ንጹህ ልቦች እንዳሉ ምስክር ነኝ፡፡ አሳች አሳቦችን የምንመክትበትን ጥሩር ላስታጠቁን፣ ጎረቤቶቻችን ወሰን የለሽ ክብር አለኝ፡፡ እኔና እኩዮቼ በተለያየ ከተማና ዓለማት ተበትነናል፤ ነገር ግን ውላችንን እንዳንስት፣ ወደኛ የሚወነጨፉ አፍራሽ አመለካከቶችን በዚህ መንገድ ለማከሰም ቃል አለን፡-
የፋጡማ መንሱር - ልዩነት ቀቅሎ፣ አንድነትን የሚመግብ፣ የጋራ ድስት ተላልፎ ይሰጣል፡፡
የያገባኛል መንፈስ ያሰረጸብን፣ የጋሽ ዘሪሁን አለንጋ  ከግድግዳው ይወርዳል፡፡
በነዚህ ያልተመከተ ሀሳብ ወይ መንፈስ፣ በየእምነቶቻችን ቀዝቃዛ ጠበል ይደፈቃል፤ ያኔ እትትት ጻ እርኩስ መንፈስ፡፡
ምንጭ፡-
(“ጨው በረንዳ” በሚል ርዕስ በቅርቡ ለንባብ ከበቃው የገጣሚ ምሥራቅ ተረፈ፣ የግጥም መድበል ላይ የተወሰደ፤ 2009)

Read 6956 times