Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 07 April 2012 08:53

የቀይ መስቀል ማህበር አመራር አጥፊዎች በሕግ መጠየቅ አለባቸው!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከደመወዝ ጭማሪ ጋር የተገናኘ ወንጀል ተፈጽሟል

ከ7 ሚ.ብር በላይ ኪሳራ በማህበሩ ላይ ደርሷል

አንጋፋው የሰብአዊ ተቋም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ፈጥኖ በመድረስና ለዜጐች ሰብአዊ አገልግሎት በመስጠት ተወዳዳሪ የሌለው መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ መንግስትም ይህን ከግምት በማስገባት አደረጃጀቱንና አሰራሩን በአዋጅ ደንግጐ ሲሰራበት ቆይቷል፡፡ ማህበሩም እስከ  ቅርብ ጊዜ ድረስ በአመራሩና በአሰራሩ የከበረ፤ በሚሰጠው አገልግሎት የተመሰገነ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ የአሰራርና የመልካም አስተዳደር ችግር የገጠመው መሆኑን የማህበሩን ሠራተኞች፣ የቀድሞ አመራሮቹንና ተቆርቋሪ ወገኖችን ዋቢ በማድረግ የተለያዩ ጋዜጦች ሲዘግቡ ታይተዋል፡፡

በመሰረታዊነት ከሚጠቀሱ ችግሮች ዋና ዋናዎቹ ማህበሩ የግለሰቦች መጠቀሚያ መሆን፤ በሠራተኖች ላይ ግፍና በደል መፈፀም፤ የሕዝብ ሀብት መዘረፍ፣ ለእርዳታ የመጣውን እህልና ቁሳቁስ ለግል ጥቅም ማዋል፤ በዘርና በእምነት በመጠራራት የሥራ መደቦችን መያዝ፤ ማህበሩ ከቅርንጫፎች ጋር ያለው ግንኙነት መቋረጥ፤ የማህበሩ ቦርድ ኃላፊነቱን ለመወጣት የተሳነው መሆን፤ የሕይወት ትራንስፖርት ያለአግባብ መሸጥ፤ የፍልውሃ ሁለገብ ፕሮጀክት ሕንጻ ሥራ ለተቋራጩ ከፍተኛ ክፍያ ቢፈፀምም ምንም ሳይሰራ መቋረጡ፤ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች በተለያዩ ጋዜጦች ከመውጣታቸውም በላይ ለመንግስት አካላት በአቤቱታና በጥቆማ መልክ መቅረባቸውንና ምንም እርምጃ አለመውሰዱን የማህበሩ ሠራተኞች ይናገራሉ፡፡

በቅርቡ ደግሞ ከእርዳታ እህል ግዥ ጋር በተገናኘ ሙስና ተፈጽሟል በሚል የፌደራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን የተወሰኑትን የማህበሩን ሠራተኞች ይዞ ምርመራ ጀምሯል፡፡ ኮሚሽኑ የተጠርጣሪዎቹን የክስ ሂደት ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡ የማህበሩ ብሔራዊ ቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል ተገነ እና ዋና ፀሐፊዋ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ወርቁ ባለፈው ሳምንት የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ወጥቷል፡፡

የማህበሩ አመራሮች “…በወቅቱ የእህል ግዥውን አከናውኖ ለተረጂዎቹ የእርዳታ አቅርቦቱን በፍጥነት ማድረስ አስፈላጊ ስለነበር መደበኛ ጨረታ አሰራርን መከተል አልተቻለም፡፡ በመሆኑም በውስን የጨረታ አሰራር እንዲከናወን ተወስኗል” ብለዋል፡፡ ይህ ውሳኔ የተሰጠው በማህበሩ ዋና ፀሐፊ ነው፡፡ ይህ ሐቅ ገሃድ ወጥቶ እያለ ውሳኔያቸውን በሌላ ውሳኔ የሻሩት ዋና ፀሐፊዋ ሌሎችን ጥፋተኛ በማሰኘት ራሳቸውን ነጻ የሚያደርግ መግለጫ መስጠታቸው አግባብ ስላልሆነ ሚዛናዊ ለመሆን ያህል ሂደቱ ምን እንደሚመስል እንመልከት፡፡

የማህበሩ ዋና ፀሐፊ ውስን ጨረታ በአስቸኳይ እንዲወጣ በሰጡት ውሳኔ መሰረት የማህበሩ ም/ዋና ፀሐፊ የአገልግሎት ዘርፍ ነሐሴ 17 ቀን 2003 ዓ.ም ለስምንት ድርጅቶች በጻፈው ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለሚያካሂደው ሰብአዊ አገልግሎት በእርዳታ የሚከፋፈል 8,100 ሜትሪክ ቶን በቆሎ (maize) 810 ሜትሪክ ቶን ቦሎቄ (beans/pulses)፣ 725 ሜትሪክ ቶን ፋሚክስ (CSB/famix) 270,000 ሊትር የምግብ ዘይት (edible oil/vegetables) ለመግዛት እንደሚፈልግ ገልጾ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ፈጥኖ በመድረስ ስቃይና መከራቸውን ለማቃለል ይቻል ዘንድ በዝርዝር ለቀረቡትና የጥራት መለኪያ ደረጃቸው በአባሪው በተያያዘው መሰረት በሞያሌ ከተማ በተዘጋጀው ጊዜያዊ ግምጃ ቤት አጓጉዞ ለማስረከብ በሜትሪክ ቶን የመሸጫ ዋጋ (price/mt) ፣ የማጓጓዣ ዋጋ (transportation cost/mt) ጠቅላላ የመሸጫ ዋጋ (total price)፣ የክፍያ ሁኔታ (terms of payment) ፣ የዋጋ ማቅረቢያው የሚቆይበት ጊዜ (validity date) ፣ የማቅረቢያ ጊዜ (delivery date) እና የጥራት ደረጃ (quality standard) በመጥቀስ የዋጋ ማቅረቢያ ሰነዳቸውን ከናሙና (sample) ጋር እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2003 ዓ.ም ድረስ ለግዥ ዋና ክፍል ገቢ እንዲያደርጉ ጋብዞ፣ ጨረታው ነሐሴ 25 ቀን 2003 ዓ.ም ከቀኑ በ9፡00 ሰዓት እንደሚከፈት አስታወቀ፡፡ በዚህም መሰረት የተጋበዙት ድርጅቶች የጨረታ ሰነድ አስገቡ፡፡

የማህበሩ የአብይ ግዥ ኮሚቴ ነሐሴ 25 ቀን 2003 ዓ.ም ከቀኑ በ9፡00 ሰዓት ባካሄደው ስብስባ፣ ለውድድር ከቀረቡት ስምንቱ ተጫራቾች አምስቱ በተለያየ ምክንያት ሲቀሩ፣ ሶስት ድርጅቶች ማለትም ወረታ ኢንተርናሽናል፣ አብዱልሐኪም አብዱሰላም እና ነስራ አብዲ ለውድድር አቀረበ፡፡ በዚህም መሰረት ወረታ ኢንተርናሽናል ብር 102 152 458 00፣ አብዱልሐኪም አብዱሰላም ብር 100 584 900.00 እና ነስራ አብዲ ብር 105,940,000.00 በማቅረባቸው አብዱልሐኪም አብዱሰላም ዝቅተኛ ዋጋ በማቅረቡ፣ ዋጋው የሚቆይበት ጊዜ አንድ ወር በመሆኑ፣ ጠቅላላ አቅርቦቱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሚጠቃለል በመሆኑ ብልጫ አግኝቶ ተመረጠ፡፡

የማህበሩ የሰው ኃይል አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት መምሪያ በ27/12/2003 ዓ.ም ለዋና ፀሐፊዋ፣ ባቀረበው የውስጥ ማስታወሻ ከቀረቡት ተጫራቾች ውስጥ አብዱልሐኪም አብዱሰላም ጨረታውን በብር 100,584,900.00 ማሸነፉን ገልጾ ለውሳኔ አቀረበ፡፡ ዋና ፀሐፊዋ በበኩላቸው ለኦዲትና እንስፔክሽን አገልግሎት በላኩት ማስታወሻ የቀረበው የጨረታ ኮሚቴ ቃለ ጉባኤ ከነደጋፊ ሰነዶቹ ከማህበሩ ደንብና መመሪያ አኳያ ተመርምሮ ውጤቱ በአስቸኳይ እንዲገለጽ አስታወቁ፡፡ የኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎትም የዐቢይ ጨረታ ኮሚቴ ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ከማህበሩ የግዥ ደንብና መመሪያ ጋር ተገናዝቦ ተቀባይነት ያለው መሆኑን አረጋገጠ፡፡ ዋና ፀሐፊዋም በዚሁ መሰረት ግዥው እንዲፈፀም በ27/12/2003 ዓ.ም አዘዙ፡፡

የማህበሩ ም/ዋና ፀሐፊ የአገልግሎት ዘርፍ ነሐሴ 27 ቀን 2003 ዓ.ም ለአብዱልሐኪም አብዱሰላም በጻፈው ደብዳቤ ጨረታውን ማሸነፉን አስታውቆ፣ ከማህበሩ ጋር ውል በመፈራረም ከአደጋ መከላከልና ዝግጁነት መምሪያ ጋር በመመካከር የእርዳታ እህል አቅርቦቱን እንዲጀምር አሳሰበ፡፡ በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርና አብዱልሐኪም አብዱሰላም የእህል ንግድ አከፋፋይ ነሐሴ 30 ቀን 2003 ዓ.ም የእርዳታ እህል ግዥ ውል ተፈራረሙ፡፡ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በኩል የፈረመው የዋና ፀሐፊዋ ተወካይ ነው፡፡

ወረታ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በቁጥር ወረ/127/03 በ03/13/03 ለማህበሩ በጻፈው ደብዳቤ፣ በጨረታው ሂደት ላይ ቅሬታ እንዳለው ገልጾ እንደገና እንዲታይ ጠየቀ፡፡ በመቀጠልም የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወደ ማህበሩ ዋና ፀሐፊ ቢሮ በየቀኑ ከመመላለሳቸውም በላይ የማህበሩን ሠራተኞች ማስፈራራት ተያያዙ፡፡ ድርጅቱ ያቀረበውን ቅሬታ ዐቢይ ኮሚቴ ጳጉሜ 3/2003 ዓ.ም መርምሮ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ከስምምነት በመድረስ ለውሳኔ አቀረበ፡፡

የጨረታ ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ የደረሳቸው የማህበሩ ዋና ፀሐፊ መስከረም 2 ቀን 2003 ዓ.ም ለዐቢይ ጨረታ ኮሚቴ በጻፉት ደብዳቤ ጨረታው ከአካሄድ አንጻር ጉድለት ያለበት በመሆኑ፤ ማህበሩ አላስፈላጊ ብር 5,186,025,00 ስለሚያወጣ አና በጥቅል ዋጋ ለመስማማት የሚያስገድድ ምክንያት ባለመኖሩ ጨረታው ሙሉ በሙሉ መሰረዙንና በምትኩ በአስቸኳይ ግልጽ ጨረታ ማስታወቂያ ወጥቶ የአቅራቢዎች ሂሳብ ከተሰበሰበ በኋላ ግዥው እንዲፈፀም እንደሚደረግም ገለጹ፡፡ አያይዘውም በጨረታው ሂደት ተሳታፊ የነበሩት በግልጽ ጨረታው ላይ መሳተፍ እንደሚችሉ ተገልጾ እንዲጻፍላቸው አሳሰቡ፡፡

በዚሁ መሰረት ዋና ፀሐፊዋ መስከረም 3 ቀን 2003 ዓ.ም ለአብዱልሐኪም አብዱሰላም ለወረታ ኢንተርናሽናል እና ለነስራ አብዲ በጻፉት ደብዳቤ ጨረታው መሰረዙንና ድጋሚ በሚወጣው ጨረታ መሳተፍ የሚችሉ መሆኑን አስታወቁ፡፡ በመሆኑም የጨረታው ሂደት ተቋጨ፡፡

ጨረታው መሰረዙንና ሂደቱ መቋጨቱን ተከትሎ ግልጽ ጨረታ እንዲወጣ በተወሰነው መሰረት መስከረም 12 ቀን 2004 ዓ.ም በወጣው ሄራልድ ጋዜጣ ግልጽ ጨረታ ማስታቂያ ወጣ፡፡ በወጣው ጨረታ መሰረት ወረታ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ፌመን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ጄ ኤች ኤስ ኤፍ ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ሶሬቲ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ፣ አግሮ ፕሮም ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወነ የግል ማህበር፣ ደልማ አግሪ ቢዝነስ፣ ኤስ ኤች ኤስ ኢንተርናሽናል ጠቅላላ ቢዝነስ ፒኤልሲ እና ገነት አድዬ ጉባ ተወዳደሩ፡፡ ጨረታው በሂደት ላይ እያለ ማህበሩ ከተወዳዳሪዎቹ አንዱ ከሆነው ወረታ ኢንተርናሽናል ጋር ከ8,100 ቶን እህል ውስጥ 4,860 ቶን (48,600 ኩንታል) በብር 37,822,950.00 እንዲያቀርብ ጥቅምት 16 ቀን 2004 ዓ.ም ውል ፈፀመ፡፡ በማህበሩ በኩል ውሉን የፈረሙት ዋና ፀሐፊዋ ናቸው፡፡ ዋና ፀሐፊዋ የፈረሙትን ውል በዕለቱ አፀደቁ፡፡

ወረታ ኢንተርናሽናል በዕለቱ ለማህበሩ በጻፈው ደብዳቤ፤ 50% የቅድሚያ ክፍያ እንዲለቀቅለት ጠየቀ፡፡ ዋና ፀሐፊዋ በ17/2004 ትክክለኛነቱ ይረጋገጥ በማለት ለውስጥ ኦዲት መሩ፡፡ የውስጥ ኦዲት በበኩሉ በ22/2/2004 ለዋና ፀሐፊዋ ባቀረበው ማስታወሻ ታይቶ ትክክለኛነቱ መረጋገጡን ገለፀ፡፡

ዋና ፀሐፊ በ27/02/2004 ዓ.ም ለግዥ ክፍል (ለአቶ አዲሱ) በላኩት ማስታወሻ በተረጋገጠው መሰረት፤ የቅድሚያ ክፍያ እንዲዘጋጅ አዘዙ፡፡ ክፍያው በጥያቄው መሰረት ለወረታ ኢንተርናሽናል ተፈፀመ፡፡

መስከረም 22 ቀን 2004 ዓ.ም ድጋሚ የወጣው ግልጽ ጨረታ ሳጥን ተከፍቶ ዋጋ ከታወቀ በኋላ ታሸገ፡፡ በዚህ ሁኔታ ከወረታ ኢንተርናሽናል ጋር የተፈጠረው ግንኙነት ተጧጧፈ፡፡ በማስከተል ዋና ፀሐፊዋ ጥቅምት 22 ቀን 2004 ዓ.ም ለጨረታ ኮሚቴ በላኩት ማስታወሻ “የሞያሌ እህል እርዳታ ግልጽ ጨረታ ማውጣታችን ይታወሳል፡፡ ይህንኑ ጨረታ መመሪያ እስከሚሰጥ ድረስ እንዲቀመጥ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ይህንን ሥራ ማጠናቀቅ ስላለብን አስፈላጊውን ግምገማ ለማካሄድ የታሸገው ተከፍቶ ሥራው እንዲቀጥልና ውጤቱን ለሰኞ ዝግጁ ማድረግ እንዲቻል እንድትንቀሳቀስ አሳስባለሁ” በማለት መመሪያ ሰጡ፡፡ በዚሁ ማስታወሻ አናት ላይ “አቶ አዲሱ፤ አቶ ብርሃኔ ይህንን አስፈጽሙ” በማለት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

አምስት አባላት ያሉት የጨረታ ኮሚቴ ከዋና ጸሐፊዋ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት፣ ጥቅምት 24 ቀን 2004 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ጨረታው በተከፈተበት መሰከረም 22 ቀን 2004 ዓ.ም በጨረታ ሳጥኑ የተገኙት የዋጋ ማቅረቢያ ፖስታዎች ስምንት መሆናቸው ተረጋግጦ፣ በኮሜቴው ከተፈረመባቸው በኋላ በአካል ለቀረቡት ተጫራቾች ዋጋው ተነቦ ፖስታዎቹ በጨረታ ሳጥኑ ውስጥ እንዲገቡ ተደረጎ፣ ሳጥኑ ታሽጎ እንዲቆይ መደረጉ እና ጥቅምት 24 ቀን 2004 ዓ.ም የጨረታ ሳጥኑ እንዲከፈት፣ የዋጋ ማወዳደሪያ ተዘጋጅቶ በአስቸኳይ እንዲቀርብ በተላለፈው ትዕዛዝ መሰረት፤ ኮሚቴው ለስብሰባ ተጠርቶ በድጋሚ ሳጥኑ መከፈቱን በቃለጉባኤው አተተ፡፡

የጨረታ ኮሚቴው ጥቅምት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባው፣ በቆሎ ለማቅረብ ከተወዳደሩት 5 ተጫራቾች ውስጥ ጄ.ኤች.ኤስ.ኤፍ ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዝቅተኛ ዋጋ በማቅረብ አሸናፊ መሆኑ ተወሰነ፡፡ ባቄላ/ቦሎቄ ለማቅረብ ከተወዳደሩት 6 ተጫራቾች ውስጥ አግሮ ፕሮም ኢንተርናሽናል፣ ሶሬቲ ኢንተርናሽናል እና ደልማ አግሪ ቢዝነስ እያንዳንዳቸው 270 ሜትሪክ ቶን አንዲያቀርቡ ኮሚቴው ተስማማ፡፡ አልሚ ምግብ ለማቅረብ ከተወዳደሩት ውስጥ ኤስ.ኤች.ኤስ ኢንዱስትሪያል ጀኔራል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እንዲያቀርብ ኮሚቴው ተስማማ፡፡ ዘይት ለማቅረብ ከተወዳደሩት ውስጥ ወረታ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እንዲያቀርብ ኮሚቴው ወሰነ፡፡

ማህበሩ ህዳር 27 ቀን 2004 ዓ.ም ለጄ. ኤች.ኤፍ በጻፈው ደብዳቤ፣ በኢትዮጵያ ሐራልድ እ.ኤ.አ. መስከረም 23/2011 በወጣው የጨረታ ማስታወቂያ፤ በቆሎ ለማቅረብ ተወዳድሮ አሸናፊ ሆኖ መመረጡን አስታወቀ፡፡ በማያያዝም ወዲያውኑ ከማህበሩ ጋር ውል በመፈራረም ስራውን እንዲጀምር አሳሰበ፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት በወጣው ጨረታ መሰረት ድርጅቶች የተወዳደሩት 81,000 ኩንታል በቆሎ ለማቅረብ ነው፡፡ የጨረታ ውጤቱ ጥቅምት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ከመታወቁ በፊት የማህበሩ ዋና ጸሀፊ ከተጫራቾቹ አንዱ ከሆነው ወረታ ኢንተርናሽናል ጋር ጥቅምት 16 ቀን 2004 ዓ.ም የ48,600 ኩንታል አቅርቦት ውል ተፈራርመዋል፡፡ ይህ ዓይነት አካሄድ ምን ሊባል እንደሚችል ለአንባቢያን፣ ለመንግሥትና ለሕዝብ ትተናል፡፡

ሌላው አስገራሚ ነገር ወረታ ኢንተርናሽናል በጨረታው ተወዳድሮ ለእያንዳንዱ ኩንታል ያቀረበው ዋጋ ብር 694,00 ሲሆን ተሸንፏል፡፡ ሆኖም 48,600 ኩንታል በቆሎ በብር 37,822,950 የተሰጠው እያንዳንዱ ኩንታል በብር 778,25 ሂሳብ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ማህበሩ ብር 5,783,400 ሆን ተብሎ እንዲያጣ ተደርጓል፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ለመንግሥት ትተናል፡፡

እንደዚሁም ሌላው አስገራሚ ነገር አሸናፊ መሆኑ በይፋ የተገለጸለት ጄ.ኤች.ኤስ. ኤፍ እንዲያቀርብ የተሰጠወ 16,200 ኩንታል በቆሎ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም 16,200 ኩንታል በቆሎ ለማን እንደተሰጠ/እንደሚሰጥ አይታወቅም፡፡ አሁንም ለወረታ ኢንተርናሽናል ኩንታል በብር 778,25 ሂሳብ የሚሰጥ ከሆነ ማህበሩ ብር 1.9 ሚሊየን አካባቢ ያጣል፡፡ ይህ ማለት ገንዘቡ ለግለሰቦች ይሆናል ማለት ነው፡፡

እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ የቀድሞ ጨረታ የተሰረዘው ብር 5,000,000.00 ያህል ለማትረፍ ከሆነ በሁለተኛው ጨረታ ከብር 7,000,000.00 በላይ ኪሳራ ማህበሩ ላይ ማድረስ ለምን ተፈለገ? በምን መለኪያና መስፈርትስ ነው ድጋሚ የወጣው ጨረታ በሂደት ላይ እያለ ከተጫራቾቹ አንዱ ከሆነው ወረታ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር የግዥ ውል የተፈጸመው? ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት የማህበሩ አመራሮች ቢሆንም ይህን ያገጠጠና ያፈጠጠ ጥፋት ለማጋለጥ አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ ሁሉም መረባረብ አለበት፡፡ የሥነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጠው መግለጫ፤ ማህበሩን ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ሊያሳጣው የሚችል የማጭበርበር ሙከራ መደረጉን ገልጿል፡፡ የማህበሩ አመራሮችም በድጋሚ በተደረገው ግልጽ ጨረታ ከብር 5,000,000.00 በላይ ለማትረፍ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ይህን እንዲካሄድ ያዘዙት፣ የጨረታ ኮሚቴውን ውሳኔ ያጸደቁት፣ ግዥ እንዲፈጸም ያዘዙት ዋና ጸሐፊዋ ናቸው፡፡

ሂደቱ ስህተት ካለበት መሰረዝና ሌላ ጨረታ እንዲካሄድ ማድረግ ተገቢ ቢሆንም ራሳቸውን ከስህተቱ ወይም ከጥፋቱ ነጻ አድርገው ሌሎችን ተጠያቂ የሚያደርጉበት ምክንያት የለም፡፡ የተጠያቂነት ጉዳይ ከተነሳ እርግጠኛ ጉዳት በማህበሩ ላይ የደረሰው በሁለተኛው ጨረታ እንጂ በመጀመሪያው ጨረታ አይደለም፡፡ በእርግጥ ከደረሰው የገንዘብ ጉዳት መጠን እና ከጨረታው ሂደት አንጻር ሁለተኛው ጨረታ መሰረታዊ ችግር ያለበት ነው፡፡ ይህም ማለት በኩንታል በብር 119,00 ብልጫ 4,860 ቶን በቆሎ ግዥ ውል በብር  37, 822,950.00  ለወረታ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መሰጠቱ፣ ሁለተኛው ጨረታ በሂደት ላይ እያለና ራሱ ወረታ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ተጫራች ሆኖ እያለ ጨረታው ሊከፈት ሳምንት ሲቀረው የእህል ግዥ ውል የተፈጸመ መሆኑ፣ ወዘተ… መሰረታዊ የሕግ ጥሰትና በወንጀል የሚያስጠይቅ ነው፡፡ ምንም እንኳን ለጊዜው የኮሚሽኑን ሠራተኞች በማታለልና በመደለል ይህን እውነት ከጎን ለመተው ቢሞከርም መንግሥት በሆነ ወቅት ምን እየተደረገ ነው ማለቱ አይቀርም፡፡ በዚያን ጊዜ በዚህ ሕገወጥ ድርጊት ተሳታፊ የሆኑት ሁሉ ይጠየቃሉ፤ አሁን አንገታቸውን የደፉት ሠራተኞች ቀና ብለው ሲሄዱ እነሱ በተራቸው አንገታቸውን መድፋት ብቻ ሳይሆን የውርደት ካባ ይከናነባሉ፡፡

ሌላ ያገጠጠና ያፈጠጠ ወንጀል የተፈጸመበት ገጽታ ከደመወዝ ጭማሪ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ኩሩ ተቋም ነው፡፡ የሚመራበት ሕግ፣ አደረጃጀት፣ የደመወዘ ስኬልና የሰው ኃይል አመራር መመሪያ አለው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው የዋና ጸሐፊ ደመወዝ 9,120.00 ሲሆን ከሌሎች ጠርቀም ያሉ ጥቅማ ጥቅሞቹም ተካቶበታል፡፡ አሁን ዋና ጸሀፊ ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት ወ/ሮ ፍሬሕይወት ወርቁ ማህበሩን ለማገልገል ግዴታ ገብተው፣ ማህበሩም ከላይ የተገለጸውን ደመወዝ ለመክፈል ተፈራርመዋል፡፡ ሆኖም ትንሽ እንደቆዩ ከቦርዱ አመራሮች ጋር ተመካክረው ከሕግ ውጪ የራሳቸውን ደመወዝ ከ9,120.00 ወደ ብር 25,000.00፣ ሌሎች ራሳቸው በዘመድ አዝማድ ያመጧቸውን ምክትል ዋና ጸሀፊዎች ደመወዘ ከብር 7,000.00 ወደ ብር 15,000.00፣ በዝምድና የቀጠሩትን የሕግ ባለሙያ ቴዎድሮስ አላምረውን ደመወዝ በተቀጠረ በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ከብር 5,665.00 ወደ ብር 7,300 አሳድገዋል፡፡ የሕግ ባለሙያው ጠበቃ ሆኖ ሲሰራ የጥብቅና ፈቃድ ሳይመልስ በቀይ መስቀል ማሀበር ተቀጥሮ ሲሰራ በመገኘቱ በፍትህ ሚኒስቴር የጠበቆች ዲሲፕሊን ኮሜቴ ክስ ተመስርቶበታል፡፡ ይህ ዓይነት ሠራተኛን ያላካተተ የደመወዘ ጭማሪ በየትኛውም መስሪያ ቤት ተደርጎ አይታወቅም፡፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሕዝብ፣ የአገርና የመንግሥት ጥቅም የሚረጋገጥበት ሰብአዊ ተቋም ነው፡፡ ከብር 500.00 በላይ የአገልግሎትና ግዥ እና ሌሎች ማስታወቂያዎች የሚወጡት በሬድዮ፣ በጋዜጣና በቴሌቪዥን ሲሆን፣ አነስተኛ ከሆነ ደግሞ እስከተወሰነ ገደብ ፕሮፎርማ በማሰባሰብ እና በንዑሰ ጨረታ ኮሚቴ ታይቶ ነው፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ማስታወቂያ የሚወጣው በኢትዮ ጆብ ኔት አማካይነት ነው፡፡ ይህ ድርጅት ያለጨረታና ውድድር እስከ ብር 30,000.00 የሚደርስ የአገልግሎት ግዥ ይሰጠዋል፡፡ ድርጅቱ ማስታወቂያ የሚያወጣው ከሌሎች ጋር ተወዳድሮ የተሻለ ዋጋ በማቅረቡ ሳይሆን የተለየ የጥቅም ግንኙነት ስላለው ነው፡፡ የኢትዮ ጆብ ኔት ባለቤት የብሔራዊ ማህበሩ ቦርድ ምክትል ፕሬዚዳንት ወንድም በመሆኑ ከማህበሩ ዋና ጸሐፊ ጋር የሶስትዮሸ የጥቅም ግንኙነት ስላለው ነው፡፡

ይህን የአገርን ጥቅም የሚጐዳ፣ ሰብአዊ ተልዕኮ ያለውን ማህበር ስም የሚያጎድፍ፣ የአገራችንን ክብርና ዝና የሚያቀጭጭ ተግባር እንዲቆም እና አጥፊዎችም በሕግ እንዲጠየቁ ሁሉም እንዲረባረብ እንዲሁም የማህበሩን ሠራተኞች እንዲታደጉ እንጠይቃለን፡፡

የማህበሩ ሠራተኞችና ተቆርቋሪዎች

 

 

Read 3553 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 09:02