Print this page
Saturday, 02 September 2017 12:28

አዳራሹ ባዶ አይደለም!

Written by 
Rate this item
(16 votes)

 የ“እኔ” ስለምንላቸው ተመልካቾች መጻፍ ከፈለግሁ ቆየሁ፡፡ “እኔ” የሌለሁበት ቦታ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ “እኔ” ስል ግን እያንዳንዳችንን ማለቴ ነው፡፡ በእያንዳንዳችን ኅሊና ውስጥ ‹ጉዳይ› የምናደርጋቸው ሃሳቦች ብቻ ሳይሆኑ ሰዎች አሉ፡፡
የእያንዳንዳችን ኅሊና ደግሞ አዳራሽ ነው፤ አዳራሹ መድረክ አለው፤ አትሮኖሱ የተዘረጋውና መጽሐፉ የተገለጠው ለአንድ ሰው ነው፡፡ አንድ ሰው ደግሞ መድረክ ላይ የሚቆመው ዲስኩር ሊያስደምጥ፤ ወይም ትርኢት ሊያሳይ ወይም ሊያሰማ ነው፡፡ ንግግርም ሆነ ትዕይንት ደግሞ ራስን ለማስደሰት ተብሎ ብቻ የሚደረግ አይደለም፡፡ ታዳሚ ይፈልጋል። ታዳሚውን ማስደመም ወይም ማበሳጨት ደግሞ መድረክ ላይ የወጣው ሰው ሚና ነው፡፡
እንደዚህ ዓይነት ነገር ወደ ጭንቅላቴ ሰርጎ መግባት ከጀመረ ዘጠኝ ዓመታት አልፎታል፡፡ ሰውን ሰው ያደረገው ሰው ነው፡፡ ስለ ሰው የማያስብ ሰው የለም፡፡ በዕለቱ እንተውናለን፤ ሲተወንም እናያለን፡፡ የቴአትር ጥበባት ተማሪ ሳለሁ፣ ስለ አዘጋጃጀት ጥበብ ያስተማረን መምሕር ተሻለ አሰፋ ‹Private audience› የሚለውን ቃል ያነሳሳልን ነበር፡፡ “ፕራይቬት ኦዲየንስ” ማለት፣ አንድ ተዋናይ ወክሎት የሚጫወተውን ገፀ ባሕርይ በጥልቀት አጢኖ፣ ገጸ ባህርዩ ማንን አስቦ ነው፣ እያንዳንዱን ቃል የሚናገረው? ማንን አስቦ ነው፣ ድርጊቱን እየተገበረ፣ ሕይወቱን እየኖረ ያለው? ለሚሉ ጥያቄዎች ተዋናዩ ምላሽ እንዲሰጥ የሚያደርግ ፅንሰ-ሀሳብ ነው፡፡
ለምሳሌ ከሼክስፒር ተውኔቶች ውስጥ ኦቴሎን እንውሰድ፡፡ ኦቴሎ የእናቱ ነገር አይሆንለትም፡፡ የእናቱን ስጦታ፣ ያቺን መሀረብ፣ እንደ ማተብ ክር ይሞትላታል። የእናቱ ምስል እየተመላለሰበት ያንፀዋል፤ ያፅናናዋል። እናቱ ናት በውስጡ ያለችው፡፡ በኢያጎ ውስጥ ግን ጎልቶና ደምቆ የሚታየው ኦቴሎ ነው፡፡ ብዙዎቻችሁ እንደምታውቁት፣ የኢያጎ መንፈስ የሚናወፀው ኦቴሎ ከፍ ብሎ ሲታይ ነው፡፡ የአንድ ጥቁር ሰው ጄኔራል መሆንና በበላይ ሹማምንት ተወዳጅ መሆን ኢያጎን ረብሾታል፡፡ የሚገባኝ ቦታ በሌላ ሰው ተይዟል ብሎ ያምናል፡፡ ስለዚህ ኦቴሎ ከክብሩ ዝቅ እንዲል፣ ዝቅ ባለም ጊዜ ያልተገባ ነገር በራሱና አብረውት በሚኖሩት ታማኞቹ ላይ እንዲፈፅም ኢያጎ ነገር መጎንጎን ይጀምራል፡፡
ዴዝዴሞና ከቃስዮ ጋር የተለየ ግንኙነት እንዳላት አስመስሎ፣ ኦቴሎ ለዴዝዴሞና የሰጣት ተወዳጁን መሀረብ ሚስቱ ሰርቃ እንድታመጣለትና ቃስዮ እጅ እንዲገባ አድርጎ፣ ቅናት አረሙን በትዳሩ ላይ ይዘራበታል፡፡ ከላይ በጠቀስነው “ኦቴሎ” ቴያትር ውስጥ፣ የኦቴሎ “ፕራይቬት ኦዲየንስ” ማለት፣ እያንዳንዱ ገፀባህርይ በሕይወቱ ውስጥ ሰፊ ስፍራ የሚሰጠውን  ተመልካች የሚመለከት ይሆናል፡፡ ሰፊ ስፍራ የሚሰጠው ደግሞ ለሚወዱት ብቻ አይደለም፤ ለሚጠሉትም ጭምር እንጂ!
በእያንዳንዱ ድርጊቶች መሃል ይሄ ስሜት አለ። የተማርንም ያልተማርንም ያው ነን፤ ብቻችንን አይደለንም፤ ይዘናቸው ወይም በማይታይ አንቀልባ አዝለናቸው የምንዞራቸው ሰዎች አሉን፡፡ ያለ እነዚህ ሰዎች አንድ ስንዝር ፈቅ ማለት ይከብደናል፡፡ እነዚህ ሰዎች ወዳጆቻችን፣ ወይም ወላጆቻችን፣ ወይም የመሰረትነው የቤተሰብ አባላት ይሆኑ ይሆናል፡፡
ይህንን የተማርኩ ዕለት፣ “ፕራይቬት ኦዲየንስ” የሚባለውን ነገር፣ ‹ለገፀባህርይ አሳሽነት ብቻ› ሳይሆን ወደ የዕለት ተዕለት ሕይወት ማውረድ ፈለግሁ፡፡ አብረውኝ የሚማሩ ተማሪዎችን አሰብኩና፣ ራሴንም ጨመርኩና፣ እነዚህ ተማሪዎች በየኅሊናቸው ይዘዋቸው የሚዞሩ፤ ወደ  ዕድገት ተራራ ባቀኑ፣ ወይም ወደ ውድቀት ሸለቆ በወረዱ ቁጥር፣ ቶሎ ወደ ጭንቅላታቸው ብቅ የሚለው “ተመልካች” ማን ይሆን? ብዬ አሰብኩ፡፡ በየኅሊናቸው አዳራሽ እንዴት ያሉ ሰዎች ወንበሮቻቸውን ይዘው ተቀምጠዋል ብዬ የማይመለከተኝን አሰሳ አካሄድኩ፡፡ እነዚህ ተማሪዎች፣ እንደ ማንኛውም ሰው ሞራላቸው ተሰብሮ ቢወድቅ “እኔን!” ብለው የሚደነግጡላቸው ሰዎች አሏቸው፡፡ በተቃራኒውም፣ “ይበላቸው!” ብለው ክፉውን ሁሉ የሚመኙላቸው ሰዎችም አሏቸው፡፡ ግና ተማሪዎቹ ማንን ደስ ለማሰኘት ወይም ማንን በንዴት ባህር ለማስዋኘት ብለው ነው፣ እየኖሩና እየተማሩ ያሉት? በእልልታና በእሪታቸው ጊዜ ቶሎ ወደ አእምሮአቸው ብቅ የሚለው አንዴት ያለ ሰው ነው? ሕይወት እንድትተውነው ባዘጋጀችላቸው ተውኔት ለመሳተፍ መድረክ ላይ ሲወጡ፣ ከእልፍ አእላፍ ተመልካቾች መሀል፣ ማንን ወይም እነማንን አስበው ነው፣ ትወናቸውን የሚያካሂዱት? ብዬ ራሴን ጠየቅኩ፡፡
አንድ ተማሪ ነበረ፡፡ እድሜው ገፋ ብሏል፡፡ የድርሰትም ሆነ የዝግጅት ዝንባሌ የለውም፡፡ የትወና ተሰጥኦም እንዳልታደለ ያውቃል፡፡ ግን ይማራል፤ ቴአትር ይማራል፤ ቴአትረኛ ለመሆንም ሆነ ለመባል ሳያጓጓውና የመንፈስ ግለት በውስጡ ሳይኖር ይማራል፤ የሚማረው ግን ንቃ የተወችውን ሴት፣ የት እንደደረሰ ለማሳየት ነው፤ አዎን፤ ንቃ የተወችውን ሴት ለማስቆጨት፣ “አመለጥኩሽ!” ለማለት!!
ይህቺን ሴት ይወዳት ነበር፡፡ ገጠር ገብቶ፣ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን በሚያስተምርበት ጊዜ፣ ይህቺ ሴት ብዙ መደናበሮችን አስረስታው ነበረ። ደስታውና ፈገግታው ሞቅ፣ ፈካ እያለ እንዲሄድ አድርጋው ነበረ፡፡ ቆይቶ ግን አንድ ነገር ተፈጠረ። አንድ ቀን ጠረኖቻቸውን ተጠጋግበው ሲያበቁ፣ “ላገባሽ ወስኛለሁ!” አላት፤ ይህንን ስትሰማ ደነገጠች፤ መጀመሪያ አይደነግጡ አደነጋገጥ ደነገጠች፤ ቀጥሎ ሣቋ መጣ፤ ከትከት ብላ ሣቀች፤ ሣቀችበት፤ አሁን ድንጋጤዋን ተረከባት፡፡ በተራው ደነገጠ፡፡ “ሰርፕራይዝ አደርጋታለሁ!” ብሎ አስቦ በተናገረው ነገር፣ “ሰርፕራይዝ” ያደረገውን ምላሽ ሰጠችው፡፡ “ድፍረትህ! እኔ እኮ እዚህ ምንም መዝናናት በሌለበት ገጠር፣ ብቻ ከመሆን ይሻላል ብዬ የፍቅር ጥያቄህን ተቀበልኩህ እንጂ እኔና አንተ እኮ አንመጣጠንም! አንኳኋንም!” አለችው፡፡ ግራ ገብቶት፣ “ለምን?” አለ፡፡ መልስ ለመስጠት ደቂቃ አልፈጀባትም፣ “አንኳኋንም!! እኔ’ኮ ዲፕሎማ አለኝ!! አንተ ደግሞ ገና የቲ.ቲ.አይ. ምሩቅ ነህ! እንዴት ቁልቁል ወርጄ ካንተ ጋር ትዳር ልመስርት?!” አለችው፤ ጥያቄውን በማቅረቡም ታዘበችው፡፡
ምንጭ፡- (ሰሞኑን ለንባብ ከበቃው የደራሲ እንዳለጌታ ከበደ፣ ”ያልተቀበልናቸው”
የወጎች መድበል የተቀነጨበ፤ ነሐሴ 2009 ዓ.ም)

Read 7226 times
Administrator

Latest from Administrator