Monday, 18 September 2017 10:25

“የኢትዮጵያ ከፍታ” እንዴት? በምን?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(14 votes)

 • የ”ፍቅር ቀን” ማለት ተቃዋሚዎች ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር እራት ሲበሉ---
      • የቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ”፤የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያጅብ ድንቅ ዜማ ነው---
         
     ልማታዊ መንግስታችን፤የሚሊኒየሙ 10ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ፣መጪው ዘመን “የኢትዮጵያ ከፍታ” ይሆናል ብሏል፡፡ እኛም ቢሆን ነው ብለን ተቀብለናል። መንግስትን ማመን አስቸጋሪ ቢሆንም (ማንኛውንም መንግስት ማለቴ ነው!) መተኪያ ለሌላት ለአንዲት ውድ እናት አገራችን፣እርሙን ሸጋ ቢመኝ (በአደባባይና በስሟ ማለቴ ነው!) ማጣጣልና አለመቀበል፣ መንግስትን ሳይሆን ኢትዮጵያን መበደል ነው፡፡ ለዚህም ነው እኔ፣ ይሄን በተስፋ የታጀበ የአዲስ ዘመን መልካም ምኞት መግለጫ፤ የመመረቅ ቱባ ባህል ባለቤት በሆነው የጉራጌ ብሔረሰብ ቋንቋ፣ ሦስት ጊዜ “ኬር--ኬር--ኬር--ይሁንልን!” ብዬ የተቀበልኩት፡፡ “አሜን” ማለቴ ነው። ግን እኮ ነገርዬው፣ ምኞት ይሁን የአቋም መግለጫ አሊያም የ10 ዓመት ዕቅድ ወይም ደግሞ GTP ወይም ልማታዊ መፈክር--- እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡ የኢትዮጵያ ከፍታን “ኬር” ብዬ ተቀብያለሁ ስላችሁ ግን ጥያቄና ሙግት የለውም ማለቴ አይደለም፡፡ በደንብ ነው ያለው። ጥያቄም ሙግትም፡፡ ለምሳሌ ከፍታው እንዴት፣መቼና በምን ---- እንደሚመጣ ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን የእኔ ቢጤ በርካቶችም መረጃውን ይፈልጉታል፡፡ የኢትዮጵያችን ጉዳይ እኮ ነው፡፡ የአገራችን ጉዳይ!
በነገራችሁ ላይ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አገርን በተመለከተ በተለይ ኢትዮጵያን እየጠቀሱ ሲናገሩ  ብዙም አልገጠመኝም፡፡ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ አብዛኞቹ የኢህአዴግ መሪዎችም እንደዚያው ናቸው፡፡  ኢትዮጵያን ብዙም የሚያደንቋት አልመሰለኝም፡፡ (አገሪቷን ሳይሆን ስሟን!) ኢትዮጵያ የሚለውን፡፡ ንጉሱ ወይም ደርግ ያወጡላት ስም እየመሰላቸው አይወዱትም፡፡ ህዝቡን ፈርተው ወይም ምክንያት አጥተው ይሆናል እንጂ ገና ሥልጣን እንደያዙ፣ ከባንዲራውና ከብሄራዊ መዝሙሩ ጋር አብረው ስሙን ቢለውጡት ደስ ይላቸው ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ (አሁን ሳይሆን ያኔ ማለቴ ነው!) አሁንማ ---- የኢትዮጵያ ቀንን እስከ ማወጅ፣ መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው እስከ ማለት ተላምደዋታል፤ ተቃርበዋታል፡፡ (የአገር ስም ድንገት ይለወጣል እንዴ?)
በቀውጢ ሰዓት ለአንድ አመት ያህል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉት (ሥልጣንና የዛፍ ላይ እንቅልፍ አንድ ሆኖ የለ!) አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ህዝባዊ ተቃውሞው ተጋግሎ በነበረበት ወቅት ከሸገር ሬዲዮ ጋር ያደረጉትን ኢንተርቪው ሰምቼዋለሁ፡፡ በተለይ ሲጨርሱ ያሉት ትዝ ይለኛል - “እናንተ እንደምትሉት፣ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!” ብለው ነበር፡፡ ቆይ ግን ምን ለማለት ነው? እሳቸውስ ምን ነበር ማለት የሚፈልጉት? ወይስ የሸገርን “ኮፒራይት” ለማክበር ብለው ይሆን? (“ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር” የሚለው መፈክር ብቸኛ ባለቤት እንዳለው አላውቅም ነበር!)
 እናላችሁ --- የ60ዎቹ አብዮተኞች፣ የ”ያ ትውልድ” አባላት--- ሁሉም ባይሆኑም በአገር ፍቅር ጉዳይ ቀዝቃዛ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ለነገሩ የትግላቸው መነሻም የብሄር ብሄረሰቦች መብት እንጂ የአገር አንድነት አልነበረም። (የአገር ፍቅር ስሜት ባይኖራቸው አይገርምም ለማለት ነው!) አንድ የደርግ ጄነራል በጻፉት ግለ ታሪክ መጽሐፋቸው ላይ እንደጠቀሱት፤ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ  በዚያድባሬ ከሚመራው የሶማሊያ ወራሪ ሃይል ጋር ጦርነት በገጠሙበት ወቅት የኢህአፓ ወጣቶች፣ የኢትዮጵያ ሚሊሻን በውጊያው እንዳይሳተፍ፣”ጭቁን ጭቁንን አይወጋም” የሚል ፕሮፓጋንዳ በመሙላት  ያስኮበልሉ ነበር ይላሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ኢህአፓን እንደሚጠሏት ጽፈዋል፤ጄነራሉ፡፡ (እንኳን እሳቸው እኔም ለመጥላት ዳዳኝ!) እና ታዲያ ይሄ የጤና ነው ትላላችሁ? ሶሻሊዝም ድሮም ጤና ኖሮት አያውቅም፡፡  
ቅድም ጠ/ሚኒስትሩን ያነሳሁት ያለ ነገር አይደለም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት ከዳያስፖራ ኢንቨስተሮች ጋር ያደረጉትን ውይይት በቴሌቪዥን ተከታትዬ ነበር - እንደ አጋጣሚ፡፡ እናላችሁ--ምድረ ዳያስፖራ የቢሮክራሲውን ችግር፣ለኢንቨስትመንት እንዴት አስቸጋሪ አገር እንደሆነች፣ የግብር የእፎይታ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ወዘተ--- ብዙ አወሩ፡፡ ብዙ አማረሩ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም ሰሙ ሰሙና አንጀት ላይ ጠብ የምትል አጭር ምላሽ ሰጧቸው፡፡
“የውጭ ኢንቨስተሮች እዚህ ቢማረሩ፣ ጥለው ሌላ አገር የመሄድ ሁለተኛ ዕድል አላቸው፤ እናንተ ግን ሌላ አማራጭ የላችሁም፤አንድ አገር ብቻ ነው ያላችሁ፤ ስለዚህ ቢሮክራሲውንም ችግሩንም እየተጋፋችሁ መስራት ነው ያለባችሁ፤ ከኢትዮጵያ በቀር ሌላ አገር የላችሁም!”
ይሄን ጊዜ የአዳራሹ ድባብ ተቀየረ፡፡ የአገር ዳያስፖራ ከመቀመጫቸው ተነስተው --- ለዚህች አንጀት ላይ ጠብ ለምትል ንግግር በደማቁ አጨበጨቡላቸው - ያውም ዘለግ ያለ ጭብጨባ፡፡ (ፈረንጅ Standing oviation የሚለው ዓይነት!) ያቺን የጠ/ሚኒስትሩን አገር ላይ የምታጠነጥን ቅመም ንግግር መቼም አልረሳትም፡፡ ድንቅ ናት፡፡ (እንኳን ለዳያስፖራዎቹ ለእኔም ጭምር!)
የሚሊኒየሙን 10ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የአዲስ ዓመት ልዩ የአቀባበል ዝግጅት ሃሳብ (ለምሳሌ የፍቅር ቀን፣የኢትዮጵያ ቀን፣የንባብ ቀን ወዘተ--) አመንጭተዋል የተባሉት “ልማታዊ አርቲስቶች”፤ ተከፍሏቿል የተባለው 20 ሚሊዮንም ይሁን 1ሚሊዮን ብር ለሁለት--- ለእኔ ጉዳዬ አይደለም፡፡ እኔ ትኩረቴ በሰሩት ሥራ ላይ ነው፡፡ ሃሳቦቹ አዲስ በመሆናቸው አድንቄአቸዋለሁ፡፡ ግን አንዳንዶቹ ህይወት እንዲዘሩና በአገር ፖለቲካ ላይ ትርጉም ያለው ልዩነት እንዲፈጥሩ አሊያም አይረሴ እንዲሆኑ ማድረግ ይችሉ ነበር፡፡ ከልማታዊነታቸው ቀነስ አድርገው ለኢትዮጵያ ፍቅር ቢያደሉ! እናም “የፍቅር ቀን” ሲከበር የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ከጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር እራት እንዲበሉ ሃሳብ ማቅረብ  ይችሉ ነበር፡፡ ከዚህ በላይ የፍቅር ተምሳሌት ከየት ይመጣል? (ጠይቀው ፊት ተነስቷቸው ከሆነ ሌላ ታሪክ ነው!) እሱንም ብናውቀው ግን ስለ ኢህአዴግ ነባራዊ ሁኔታ ፍንጭ ይሰጠን ነበር። ለ10 ቀናት እያንዳንዱን ዕለት በበጎ እሴቶች እየሰየመ ያከበረውን በዓል፣ ከልቡ ነበር ወይስ እንደተለመደው  የፖለቲካ ጨዋታ? መቼስ ኢህአዴግን መጠርጠር አያስኮንንም፤ ባይሆን ያጸድቃል እንጂ!
እኔ ልማታዊ አርቲስቶቹን ብሆን ኖሮ (በሌላ አነጋገር ሚሊየነር አርቲስቶቹን ብሆን እያልኳችሁ ነው!)የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያጀብ ነጠላ ዜማ እንዲለቀቅ በፕሮፖዛሌ ውስጥ አካትት ነበር፡፡ ዘፈኑ ከየት ይመጣል? ዘፋኙስ? የዘፈን ግጥሙስ? አያስጨንቅም፡፡ ዜማው ቀድሞ ተሰርቷል፡፡ ወደ ውስጣችን ማየት ብቻ ነው፡፡ የማን መሰላችሁ? የቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም መጠሪያ የሆነው፣ “ኢትዮጵያ”! ለኢትዮጵያ ከፍታ፣”ኢትዮጵያ”ን የሚያሞካሽ፣ሰማይ ላይ የሚሰቅላት ድንቅ ዜማ! ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩን ጨምሮ የኢህአዴግ አንጋፋ መሪዎች “የኢትዮጵያ ቀን” በተከበረበት ጳጉሜ 5፣ ምሽት፣ በሚሊኒዬም አዳራሽ፣ ኢትዮጵያ በሚለው ዘፈን ከቴዲ ጋር እያቀነቀኑ፣ በፍቅር ሲያብዱ ማሳየት - በኢቢሲ ሳይሆን በ”ቃና” ቴሌቪዥን፡፡ እግረ መንገድም መንግስትንና ኢህአዴግን ሲያስተችና ሲያስነቅፍ የከረመውን የቴዲ አፍሮ የኮንሰርት እገዳና የአልበም ምረቃ በተመሳሳይ ምሽት በማካሄድ፣መንግስትንም ቴዲንም ነጻ ማውጣት፡፡ በዚህም ሁለቱም አሸናፊ ይሆኑ ነበር፡፡ ሁለቱ ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም፡፡ ፕሮፖዛሉ የእኔ ቢሆን ኖሮ ማለቴ ነው!  
አሁን ወደተነሳንበት “የኢትዮጵያ ከፍታ” እንመለስ። እናላችሁ --- ከሁሉ አስቀድመን፣ “የኢትዮጵያ ከፍታ” በሚለው አገላለጽ ትርጉም ላይ መግባባት ላይ ልንደርስ ይገባል፡፡ ለኢህአዴግ ከፍታ ምንድን ነው? በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ከፍታ? ሃሳቡ የቱንም ያህል ቅዱስ ቢሆን አገራዊ መግባባት ላይ መድረስ ካልተቻለ፣ በአንድ ዓላማ እኩል መራመድ አንችልም፡፡  ቢሆን ቢሆንማ ሃሳቡን ለህዝብ ውይይት አቅርቦ ግንዛቤ ማስጨበጥ ተመራጩ መንገድ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ነፍሴ ግን  አስቦና አቅዶ የጨረሰውን ህዝብ ላይ መጫን ነው የለመደው፡፡ ልክ ህግና አዋጅ እንደሚጭነው፡፡ እናም በአዲስ ዓመት መባቻ ላይ ድንገት እንደ ዱብዕዳ ወይም ሰርፕራይዝ የነገረንን “የኢትዮጵያ ከፍታ” ትርጉምና የአፈጻጸም ሂደት በዝርዝር ሊያብራራልን ይገባል፡፡ (በኋላ “የአፈጻጸም ችግር” ምናምን እንዳይለን እኮ ነው!)
ለኢህአዴግና ለልማታዊ መንግስታችን፣ እቺን ታህል ጥቆማ ከሰጠነው አሁን ወደ ራሳችን መላምትና ግምት ልንገባ እንችላለን፡፡ (መረጃ ሲያጥር ከመላምትና ከግምት ውጭ አማራጭ የለም!) እንዳለመታደል ሆኖ ኢህአዴግ አዲስ ዕቅድ ወይም ሃሳብ ሲያቀርብ ብዙ ጊዜ የምንቀበለው በአዎንታዊ ስሜት ሳይሆን በአሉታዊ ስሜትና በጥርጣሬ ነው - “ደሞ ምን አስቦ ይሆን?”  “ከምሩ ነው ወይስ የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር?” በሚል ጥርጣሬ፡፡ (ከ25 ዓመታት የሥልጣን ዘመን በኋላም ተዓማኒነት አለመፍጠር ጥናት የሚያስፈልገው ችግር ነው!) እናላችሁ ---- ከፍታውንም በተመሳሳይ ስሜት ብንቀበለው አይፈረድብንም፡፡ ከኢህአዴግ ጋር እስከ ዛሬ የዘለቅነው በእንዲህ ዓይነት ግንኙነት ነው፡፡ ምናልባት የኢትዮጵያ ከፍታ ሲመጣ ሁኔታው ይለወጥ ይሆናል፡፡ (ያለዚያማ ምኑን ከፍታ ሆነ?!)
በነገራችን ላይ ኢህአዴግ፣ ተሳካለትም አልተሳካለትም፣ “የኢትዮጵያ ከፍታ” ብሎ የተነሳው ከልቡ ከሆነ፣ (ጊዜ መግዥያ ካላደረገው!) በአዲሱ ዓመት የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ቆርጦ ተነስቷል ማለት ነው፡፡ ግን እንዴት ነው አውራው ፓርቲ ወይም መንግስት የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ማምጣታቸውን ማወቅ የምንችለው? ቀላል ነው፡፡ ንግግርና ተግባር መጣጣማቸውን ማጤን ብቻ ይበቃል። እናም የምር ከሆነ ---- ያለ ምንም አንጃ ግራንጃ፣ የለውጥ ፍንጮችን ማየት እንጀምራለን፡፡ ለውጡ የሚጀምረው በእርግጥም የባህሪ ለውጥ ከማምጣት ነው፡፡ ህዝብን የሚመለከቱበት ዓይን፣ለተቃዋሚዎች ያላቸው አመለካከት፣ከፍታዋን ለተመኙላት ኢትዮጵያ የሚሰጡት ክብርና ዋጋ ይለወጣል፡፡ ከፓርቲ በፊት አገርን ያስቀድማሉ፡፡ ህዝብን ያከብራሉ። ህዝብን ስለሚያከብሩም ቃል የገቡለትን ምንም ሳያጓድሉ ይፈፅማሉ፡፡ ከአምና ተንከባለው ለመጡ የህዝብ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የአገራቸው ጉዳይ ያገባቸዋል ብለው ማሰብ - ማመን ይጀምራሉ፡፡ (“የኢትዮጵያ ከፍታን” በፈረንጅ አፍ፣ “The Rise of Ethiopia” ብንለውስ?) ያው ኢህአዴግ ከአማርኛ ይልቅ እንግሊዝኛ ይቀናዋል በሚል ነው፡፡ (“ዴሊቨሮሎጂ” ምን ነበር?)  
እናላችሁ --- በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩል ያሳትፋሉ፤ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር ለመወያየት- ከጥላቻ የፀዳ ግንኙነትና መግባባት ለመፍጠር ዝግጁ ይሆናሉ። ፍንጩንም በጥቂት በጥቂቱ ግን ደግሞ ቶሎ ቶሎ ያሳዩናል፡፡ በነገራችን ላይ “የኢትዮጵያ ከፍታ”ን ልዩ የሚያደርገው፣ቀድሞ እንደ ትንቢት ስለተነገረን እንጂ ባለፉት ዓመታት ያላየነው የዘመን ዓይነት እኮ የለም። “ዘመነ ዝቅታ፣ ዘመነ ሁካታ፣ ዘመነ እሪታ፣ ዘመነ ኳኳታ፣ ዘመነ ድንፋታ፣ዘመነ እፍታ”----ይሄው አሁን ደግሞ “ዘመነ ከፍታ” ይመጣል ተብለናል፡፡
እናላችሁ ---- አንዳንድ ልማታዊ ጋዜጠኞች የኢትዮጵያ ከፍታ እውን የሚሆነው በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ  ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ ላለፉት 10 ዓመታት ይሄ ሁሉ መሰረተ ልማት ተገንብቶ፣ የባቡር መስመር ተዘርግቶ፣ዓለምን ያስደመመ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገባችን በእነ ዓለም ባንክ እየተነገረን --- ለምንድን ነው “የኢትዮጵያ ከፍታ” ያልመጣው? ብዙ የሚጎድሉን ነገሮች ስላሉን ነው፡፡ ከፍታ ባለ ሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ብቻ አይለካም። ከልማቱ ጎን ለጎን፣ የዲሞክራሲና የነፃነት ሥርዓቱ መስፋትና መጎልበት አለበት፡፡ ባህል ሊሆን ይገባዋል፡፡ የዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር ይኖርበታል፡፡ ያኔ ነው የኢትዮጵያ ከፍታ ማለት፡፡ ህገ-መንግስታዊ መብቶች ሳይሸራረፉ ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያለ አንዳች ፍርሃትና ስጋት ሰላማዊ ትግላቸውን ያካሂዳሉ፡፡ የምርጫ ሰሞን የሚታሰሩ የፓርቲ አመራሮች ወይም አክቲቪስቶች  አይኖሩም፡፡ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ህገ መንግስታዊ መብታቸውን የጣሱ የመንግስት አካላት፣ ለፍትህ ልዕልና በነጻነት በሚሰራ ፍ/ቤት ተገቢውን ቅጣት ያገኛሉ፡፡ ያኔ ነው የኢትዮጵያ ከፍታ ማለት፡፡
የምርጫ ሰሞን በጉጉት የሚጠበቅ እንጂ ዜጎች በተቃውሞና በግጭት እንዳይሞቱ የምንሰጋበት የፍራቻ ወቅት አይሆንብንም፡፡ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በድርድር የሚደርሱበት የምርጫ ቦርድ ተቋማዊ ቅርፅ ቦርዱን በሁሉም ወገኖች ዘንድ ነፃና ተዓማኒ ያደርገዋል። የእነዚህንም ለውጦች ፍንጭ ከ2010 የአዲስ አበባ መስተዳደር ምርጫ አንስቶ ማየት እንጀምራለን፡፡
“የኢትዮጵያ ከፍታ” ማለት እንደለመደብን ሁለት እርምጃ ወደፊት ተጉዘን አራት እርምጃ ወደ ኋላ  መመለስ ማለት ፈጽሞ አይደለም፡፡ ሁልጊዜም ወደፊት መራመድ… ሁልጊዜም መሻሻል… ሁልጊዜም ማደግ ነው፡፡ “የኢትዮጵያ ከፍታ”፤ ህዝብ በፈለገው (በመረጠው) ፓርቲ ወይም መሪ ሲተዳደር ማለት ነው። “የኢትዮጵያ ከፍታ”፤ የኢትዮጵያ ቀንን በዓመት አንድ ጊዜ ሳይሆን፣ ከባህሪና ከእምነት ጋር በገቢር ተገምዶ ሁሌም ቢሆን ከልቦናችን የማይጠፋ ትልቅ ትርጉምና ቦታ ያለው ደማቅ ክብረ-በዓል አድርገን መውሰድ ስንጀምር ነው። “የኢትዮጵያ ከፍታ”፤ ህዝብን በጎሳና በዘር ለያይቶ ከሚያናክስ ኋላ ቀር ፖለቲካ ተላቀን፣ ለአንዲት አገር በጋራ ስንቆም ነው፡፡ የብሄር ብሄረሰቦች መብት የሚከበረው አንድነቷና ሉአላዊነቷ የተጠበቀ አንዲት ጠንካራ አገር ሲኖረን መሆኑን ስንገነዘብ ነው። “የኢትዮጵያ ከፍታ”፤ ለስኬታማ ሰዎች ተገቢውን አድናቆትና ክብር ስንቸር ነው፡፡ “የኢትዮጵያ ከፍታ”፤ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ከዓለም ጋር ለመራመድ ስንጣጣር ነው፡፡ “የኢትዮጵያ ከፍታ”- ለዕውቀት ክብር ስንሰጥ ነው፡፡  
የመከባበር ቀንን በዓመት አንዴ፣ ለሚዲያ ፍጆታ፣ በጳጉሜ ወር ብቻ የምናከብረው ሳይሆን መታወቂያ ባህላዊ እሴታችን  ሲሆን ነው- “የኢትዮጵያ ከፍታ” እውን የሚሆነው፡፡ መሪዎቻችን የሚከበሩ ሲሆኑ (እኛም ስናከብራቸው)፣ ምሁራኖቻችን የሚከበሩ ሲሆኑ (እኛም ስናከብራቸው)፣ የአገር ሽማግሌዎቻችን የሚከበሩ ሲሆኑ (እኛም ስናከብራቸው)፣ የሃይማኖት አባቶቻችን የሚከበሩ ሲሆኑ (እኛም ስናከብራቸው) ወዘተ… በዚህች ምድር መከባበር ሲሰፍን ነው - “የኢትዮጵያ ከፍታ” ማለት፡፡
ቅሬታዎችንና አለመግባባቶችን ድንጋይ በመወራወርና (“ሃሳብ መወራወርያ መድረክ በማጣት” እንደተባለው!) ጥይት በመተኮስ ለመፍታት ከመሞከር ኋላ ቀር ባህል ወጥተን፣ በውይይትና በንግግር መፍትሄ ለማምጣት ስንታትር ወይም በጭፍን ድጋፍና በጭፍን ተቃውሞ ከመፈራረጅ ወጥተን በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ ሥልጡን ፖለቲካ ማራመድ ስንጀምር ነው- “የኢትዮጵያ ከፍታ”፡፡ ለዜጎች ህይወት እውነተኛ ክብር ስንሰጥ… የወገኖቻችን ስደትና መከራ ከምር አስጨንቆን…ሁላችንም ለመፍትሄው ስንተጋ ነው- “የኢትዮጵያ ከፍታ”፡፡ በፖለቲካም ይሁን በኢኮኖሚ አሊያም በሌላ ምክንያት ከአገራቸው ርቀው በስደት ላይ ያሉ ወገኖቻችንን፣ (የመንግስት ተቃዋሚዎችንም ይጨምራል!) በቅንነትና በደግነት ለአገራቸው አፈር ስናበቃቸው ነው - “የኢትዮጵያ ከፍታ”፡፡ የአገራቸውን ዳር ድንበርና ነፃነት ለማስጠበቅ ደማቸውን ላፈሰሱና አጥንታቸውን ለከሰከሱ (በየትኛውም ሥርዓትና መንግስት) ጀግኖቻችን ተገቢውን ክብርና ቦታ ስንሰጥ ነው - “የኢትዮጵያ ከፍታ”፡፡ ያኔ “የዛሬዋን ኢትዮጵያ ለሰሩልን አረጋውያን ክብር እንሰጣለን” (አዲስ ዘመን እንዳለው) የሚለው መፈክራችን ትርጉም ይኖረዋል! አገራችንን ከልብ ስንወድ---- ለዕድገቷ በአንድነት ስንቆም----- ለክብሯ በጋራ ስናልም… ያኔ ነው “የኢትዮጵያ ከፍታ”፡፡
መንግስትና አውራው ፓርቲ  ብቻ ግን “የኢትዮጵያን ከፍታ” አያመጡም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ገዢውን ፓርቲ አሸንፎ የስልጣን መንበሩን ከመቆጣጠር ባሻገር ለኢትዮጵያ የሚያልሙትና የሚመኙት፣ ዕድሉን ሲያገኙም የሚተገብሩት ለከፍታው ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ በተፎካካሪ ፓርቲነት ሚናቸው ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበትና ለሰብዓዊ መብት መከበር ከልባቸው መትጋት ከጀመሩ - ያኔ ነው “የኢትዮጵያ ከፍታ”፡፡ ውስጣዊ ችግራቸውንና ቅራኔያቸውን በዱላ ቀረሽ (አንዳንዴም በዱላ ጭምር) ጠብና መቃቃር ከመፍታት ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት ሲጀምሩና ይሄንንም ባህላቸው ሲያደርጉ - ያኔ ነው “የኢትዮጵያ ከፍታ”፡፡
አገራዊ የፖለቲካ ቀውስ ሲከሰት፣ የከፋ እልቂትና ጥፋት ከማድረሱ በፊት “መፍትሄ የሚሆን መላ እነሆ” የሚሉ ብልህና ጥበበኛ የፖለቲካ መሪዎች ሲገኙና በጄ ብሎ የሚቀበል - ጆሮ የሚሰጥ መንግስት ሲኖር-ያኔ ነው “የኢትዮጵያ ከፍታ”፡፡ ከሁሉም በላይ “የኢትዮጵያ ከፍታ” እውን የሚሆነው ግን ለእውነት ክብርና ዋጋ መስጠት ስንጀምር ነው፡፡ እስካሁን ያተትናቸው ሁሉ ሊተገበሩና ሊሳኩ የሚችሉት ከእውነትና ከሃቅ ጋር ስንወዳጅ ብቻ ነው፡፡ (“የእውነት ቀን” አለመሰየማችንን ልብ ይሏል!) እውነት ከምንም ነገር የምትልቅ ውድ እንቁ ናት!!
እናላችሁ ---“የኢትዮጵያ ከፍታ” በእርግጥም እውን የሚሆነው ለእውነት ዋጋ ስንሰጥ ነው፡፡ ከእውነት ተፋተን “የኢትዮጵያ ከፍታ”ን እውን ማድረግ አንችልም። ፌስቡክ ላይ ያገኘኋት ባለ ሁለት መስመር ግጥም ስለ ከፍታ እንዲህ ትላለች፡-
በከፍታ ዘመን በጣም ወጥተን ወጥተን
እንዳንፈጠፈጥ ፓራሹት ይሰጠን!
 በአዲሱ ዓመት  ልባምና አስተዋይ መሪዎችን ይስጠን !

Read 7335 times