Saturday, 07 April 2012 09:36

ስብሐት እና ሄሚንግዌይ አንድ ናቸው

Written by  ሳሊሌ ማርግ
Rate this item
(0 votes)

ሄሚንግዌይን አደንቀዋለሁ … ታዲያ ሄሚንግዌይ ተደንቆ ስብሐት ሊቀር ነው? …… ግራጫውን መልክ አድንቄ ጠይሙ ሊቀር … እንዴት ተደርጐ?! ቀለማቸው እና የሚፅፉበት ቋንቋ ይቅርና በሌላው ነገራቸው ሁለቱን ደራሲዎች አንድ ለማድረግ ልሞክር …

ስብሐት የተወለደው አድዋ ነው፤ ሄሚንግዌይ ደግሞ ኦክፖርክ (ኤሊኖይስ)፡፡ ሄሚንግዌይ በ1899 እ.ኤ.አ ነው የተወለደው፣ ስብሐት ደግሞ በአበሻ አቆጣጠር 1929 … ሁለቱም በተወለዱበት አመት ላይ ሁለት ዘጠኝ ቁጥሮች አሉባቸው፡፡ ስለዚህ አንድ ናቸው፡፡ …  ምን ነክቶኛል … እኔ ኮከብ ቆጣሪ ነኝ እንዴ … ዘጠኝ የሙሉነት ቁጥር ነው … ምናምን ብዬ ስደምር ራሴን አልታዘብም ….!?

ይቅርታ! አሁን ወደ ቁም ነገሩ ልምጣ፡፡ የሁለቱም ደራሲዎች ህይወት አልፏል፡፡ የፈጠሩት ታሪክ፣ ስኬታቸው፣ አርአያነታቸው ግን ለዘላለም አያልፍም፡፡

የሁለቱም ደራሲዎች ፊት  በነጭ ፂም የተሸፈነ ነው፤ “ነበር” ለእነሱ የምንጠቀመው ቃል አይደለም፡፡ ከጊዜ ወረተኝነት መዳፍ ያመለጡ፤ አማልክት ናቸው … እያንዳንዱን ዘመን እና ትውልድ ይነካሉ እንጂ አይነኩም፡፡)

የሁለቱም ደራሲዎች የድርሰት ጥንካሬ… ሸክላው ፀሀፊ ወደ እምነበረድ ደራሲ የተለወጡት ያፈቀራትን ሴት ካጡ በኋላ ነው፡፡ … ሎጂካል ላይሆን ይችላል ድምዳሜዬ፤ ግን ጉዳዬ አይደለም፡፡ ስብሐትም እንደ ሄሚንግዌይ  የራሴ፣ የግሌ ናቸው፡፡ የእኔ የሆኑት ያነበብኳቸው ለት ነው፡፡ በምናብ ክንፍ እንድበርር ላደረጉኝ ሁሉ ክንፉ የውሰት ስላልሆነ አልመልስላቸውም፡፡

ስብሐት ሀናን አጥቷል፤ ሄሚንግዌይ ደግሞ ወጣት የጦርነት ጋዜጠኛ ሆኖ እየሰራ እግሩ ላይ አደጋ በደረሰበት ጊዜ ስታስታምመው በፍቅር የወደቀላትን ሴት አጥቷል፡፡ ከማጣት በፊት የነበሩት ወጣቶች ሸክላዎች ነበሩ፡፡ ሸክላ ከአፈር ትንሽ ነው የሚጠነክረው፤ ይሰበራል፡፡ ሳይሰበር መጠንከሩን ከቀጠለ፣ እምነ በረድ ይሆናል፡፡ “ከነጭ እምነ በረድ እና ከጥቁሩ የትኛው ይበልጣል? በማለት የሚጠይቅ ስለ እምነበረድ እውቀት የሌለው ሰው ነው፡፡ ስራው ያውጣው!

ሁለቱም ደራሲዎች በህይወት ዘመናቸው አራት አራት ሚስት አግብተዋል፡፡ ሁለቱም ወይኒቱን (መፍረስ) ይወዳሉ፡፡ ሁለቱም ግጥም መፃፍ ላይ ያን ያህልም ናቸው፡፡ ሄሚንግዌይ  በውቅያኖስ ላይ ተጉዞ ትልልቅ አሣ አጥምዷል፡፡ ስብሐት በሰፊ ንባብ ላይ ኖሮ …(በንባቡ ሳይሆን በአኗኗሩ) ወጣቱን ትውልድ አጥምዷል፡፡ ሁለቱም ቁጡ የሚሆኑባቸው ጊዜአት አሉ፡፡ ሁለቱም እንዳሻቸው ኖረው እንዳሻቸው የሞቱ ናቸው፡፡

ሄሚንግዌይ በወጣትነቱ ፓሪስ ሄዶ እየኖረ የመጀመሪያውን ድርሰቱን ለመጨረስ በሚሞክርበት ጊዜ አማተር ቦክሰኛም ሆኖ ነበር፡፡ አንድ ምሽት እዚሁ ፓሪስ ከተማ በተካሄደ የፕሮፌሽናል ቦክሰኞች ግጥሚያ ላይ …ከተጋጣሚዎቹ አንዱ፣ አግባብ ባልሆነ ሁኔታ ሌላኛውን ይነርተዋል፡፡ (በቦክስ ግጥሚያ ላይ አግባብ ያልሆነ አመታት ምንድነው? ያላችሁ እንደሆነ “እኔ ምን አውቄ!” እላችኋለሁ) አንድ ወጣት ከተመልካቹ ወንበር ተነስቶ ሪንጉ ውስጥ ዘሎ ይገባል፡፡ አግባብ ያልሆነው ሰው ላይ የራሱን አማተር ቡጢ ይሰነዝር ጀመር፡፡ ይህ አላግባብ የሆነ ጥቃትን የማይወድ ወጣት ገና ታዋቂነት ደረጃ ያልደረሰው ኸርነስት ሄሚንግዌይ ነበር (ነው)

ዘሪቱ በመባል የምትታወቀው ዘፋኝ “ያንቡሌ ይከፈትላችሁ” በማለቷ ውዝግብ መነሳቱ ይታወሳል፡፡ መጀመሪያ ላይ ሁሉም ውርጅብኙን ዘሪቱ ላይ አድርጐ ነበር፡፡ ከፂማሙ ደራሲ በስተቀር፡፡ እሱ በሰጠው አስተያየት ተቀጥቅጣ አለአግባብ ልትጣል የነበረችው ከባድ ሚዛን ዘፋኝን…ከባዱ ሚዛን ደራሲ “ኤነርጂ ፊልዱን” ዘርግቶ ከልሏታል፡፡  ሄሚንግዌይ እና ስብሐት አንድ ናቸው፡፡

ጋዜጠኛው :- የሄሚንግዌይ የደረት ፀጉር አርቴፊሻል ነው፤ ብሎ ስም ባጠፋ ጊዜ ቢሮው ድረስ ሄዶ የስም አጥፊውን ፊት ወይንም እጅ ደረቱ ላይ አሽቶ እውነተኛ ፀጉር መሆኑን እንዲገባው አድርጓል፡፡

ሁለቱም ደራሲዎች በራሳቸው ህይወት ዘመን አፈ ታሪክ እና ተረት ሲሆኑ ለማየት ታድለዋል፡፡ ሁለቱም ከሆኑት በላይ ትልልቅ ገድሎች ተወርቶባቸዋል፡፡ ሲወራባቸውም በራሳቸው ጆሮ ለማድመጥ ችለዋል፡፡ የስብሐት የንግግር ድፍረት ከሄሚንግዌይ የተግባር ድፍረት የሚተናነስ አይደለም፡፡ አንደኛው ከኮርማ ጋር በአካል ተዋግቶ ያውቃል፤ ጭንቅላቱ ላይ የኮኮናት ፍሬ ተወራርዶ ይፈረክሳል ይባልለታል፡፡ ሌላኛው፤ ከበሬ አስተሳሰብ ጋር በፅሁፉ እና ንግግሩ ይዋጋል፡፡ ሁለቱም አንድ ናቸው፡፡

ሁለቱም ጀግና ይወዳሉ፡፡ ጀግና ለመሆን የሚሞክሩበት መንገድ ግን… ከተራው (እነሱ ከሚያደንቁት) ጀግንነት በጣም የበለጠ ነው፡፡ … ሁለቱም ምርጥ አጭር ልብወለድ ፀሀፊዎች ናቸው፡፡ ከሄሚንግዌይ ለእኔ የምትበልጥብኝ Big two hearted river ነች፡፡ ከስብሐት ደግሞ “ቢራቢሮ”፡፡ ሁለቱም ለኔ የሚበልጥብኝ ስራ ቢኖራቸውም እርስ በራስ ሲነፃፀሩ ግን አይበላለጡም፡፡

ለስብሐት ሴቶች ትልቅ ስፍራ አላቸው፤ ለሄሚንግዌይ ደግሞ አደኑ፣ አሳ ማጥመዱ፣ ቦክሱ፣ የጦር ሜዳ ጥናቱ … ወዘተ፡፡ እነዚህ ነገሮች በደራሲዎቹ ትልቅ ስፍራ ቢሰጣቸውም … ከፍተኛው ስፍራ ግን ክፍት የተተወው ለፅሁፍ ነው፡፡ … ሁለቱም ወደ እድሜ ማክተሚያቸው የሰሩት የረባ ስራ አልነበረም፡፡ … ሄሚንግዌይ እንኳን… ለካ “ሽማግሌውና ባህሩን” በሀምሳ ሁለት አመቱ ፅፏል … ረስቼዋለሁ ጃል! … ስብሀት በሀምሳ ሁለት አመቱ “ሽማግሌውና ባህሩን” ሆኗል፡፡ ሽማግሌው ራሱ … ባህሩ የንባብ ዕውቀቱ፡፡

ሁለቱም አንድ ናቸው፡፡ … ከዚህ በላይ ለማመሳሰል ባልጥር ይሻላል፡፡ ለማመሳሰል በጣም በመፍጨርጨር … ለያይቻቸው ቁጭ እንዳልል፡፡

 

 

 

 

Read 2480 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 09:39