Saturday, 07 April 2012 09:39

እንደ ስብሐት

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(1 Vote)

ከአዘጋጁ:- ውድ አንባብያን፤ በዚህ አምድ በአንጋፋው ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር የአፃፃፍ

ዘዬ የተኳሉ ጥበባዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ እንዲሁም ፍልስፍናዊ መጣጥፎችና ወጐች ይስተናገዳሉ፡፡ እግረመንገዳችንንም ዕውቁን የብዕር ሰው ስብአት ለአብን እየዘከርን፡፡ ለአምዱ የሚመጥኑ ጽሑፎችን ብትልኩልን ሚዛን ላይ እያወጣን እንደየሁኔታውና አግባቡ እናስተናግዳለን፡፡

“ከንጉሱ በልጠህ አትድመቅ”

ይህን ታሪክ የፃፍነው የጽሁፍና የፀሀፊዎች አማልእክት በል በል ብለው አነሳስተውን ነው፡፡ ርዕስ አድርገን የመረጥነው ታሪክ ንጉስም ብንሆን ማለትም፣ ገዢ አስተዳዳሪ  አሊያም እንዳቅሚቲ የአንድ ሠውም አለቃ ብንሆን፣ ወይም የንጉሱ ምርጥ ባለሟል ማለትም፣ ባለስልጣን፣ ሚኒስትር፣ የጦር አዛዥ ወዘተ … አሊያም ደግሞ የንጉሱ አገልጋይ ወይም ደግሞ ልክ እንደ እኔ ተራ ዜጋ ወይም በትክክለኛው አገላለጽ ተገዢ ብትሆኑ … በየእለት ተዕለት ህይወታችሁ ውስጥ ድንገት ገብቶ፣ በገሀድም ተፈጽሞ ሊገኝ የሚችል ታሪክ ነው፡፡ እናም ይህን ታሪክ እነሆ በረከት የምንላችሁ፤ በዚህ አሪፍ መንፈስ ተነቃቅተን ነው፡፡ (መነቃቃታችን ቢጋባባችሁም ጭምር)

መላው አለም በተለይ ደግሞ የእነ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋሽንግተን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችልና የቻንስለር ኮንራድ አዘናወር ሀገር፤ የተባበሩት አሜሪካና አውሮፓ ለዘመናት ካሸለበችበት የፖለቲካና ኢኮኖሚ እንቅልፍ ገና አልነቃችም ብለው ችላ ብለዋት ሳለ መንቃትዋን ለአንዳቸውም እንኳ ሳትነግር፣ ያለ አንዳች ኮሽታ መላውን አለም በጠንካራ የኢኮኖሚ መዳፍ ጨብጣ በመያዝ፣ በፖለቲካውም መስክ ልትደግመው ትንሽ የቀራት የጓድ ማኦ ዚዶንግ ሀገር ቻይና፣ ለድፍን አለሙ እነሆ ለእኛም ጭምር ካበረከተችልን ዝነኛ ፈላስፋዎች አንዱ ኮንፊሽየስ ነበር፡፡ ይሄ ፈላስፋ በዘመኑ ለሚያስተምራቸው ተማሪዎቹ እንዲህ በማለት ነግሯቸው ነበር፡- “በምታከናውኑት ማናቸውም አይነት ስራዎች ከንጉሱ በልጣችሁ አትድመቁ፡፡ ሁለት ፀሀይ በአንዴ አይወጣምና!”

ፈላስፋው ኮንፊሽየስ እንዲህ ብሎ ሲያስተምር፣ እኛ እሱ ባስተማረበት ዘመንና ባስተማረበት ሀገር በቻይና ተገኝተን ትምህርቱን ለመከታተል ባንችልም፣ የእሱን የፍልስፍና ትምህርቶች በስስት ወይም በመንገብገብ ስሜት ተነሳስተው አንዷንም እንኳ ሳያስቀሩብን በመጽሀፍ ጽፈው በማቆየት፣ የንባብ ወኔ በነሸጠን ጊዜ ሁሉ እንድናነበው በማድረጋቸው ፈላስፋው ኮንፊሽየስ “ከንጉሱ የበለጠ አታንፀባርቁ” ብሎ ሲያስተምር ምን ለማለት እንደፈለገ ነቄ ብለንበታል፡፡ ለዚህ ላበቁን ደጋግ ሠዎች ስብሀት በሰማይም ሆነ በምድር እንዲሆንላቸው ሽርካችን የሆነውን አምላካችንን እንጠይቀዋለን (ኧረ እንደውም ሪፈር እንልክበታለን)

እንግዲህ ይህን ነቄ ያልነውን ትምህርት በታሪክ አስደግፈን ስናቀርብላችሁ የሚከተለውን ይመስላል፡-

ክፍል አንድ

“ሞአ አምበሳ እምዘነገደ ይሁዳ” በሚል መፈክር ስር፣ የንጉሠ ነገስት ዘውድ ደፍተው መላ ጦቢያውን ይገዙ በነበሩበት ዘመን ስላልተወለድን፣ ኖረን አይተን ባናረጋግጠውም አባባ ጃንሆይ ረጅም ሠው አጠገባቸው እንዲቆም አይፈልጉም ይባላል፡፡ ነፍሳቸውን አንድዬ ይማረውና፣ አባባ ጃንሆይ እንዲህ የሚያደርጉት ታላቁና ድል አድራጊው ንጉሳችን እያለ ከሊቅ እስከ ደቂቅ መሬት እየሳመ እጅ የሚነሳላቸውን ንጉስ፣ ረዥሙ ሠው አጠገባቸው ቆሞ አጭርነታቸውን እንዳያሳጣቸው በመስጋት ነው አሉ! እንዴ … ፀሃዩ ንጉሳችን እኮ እንዲህ የዋዛ ሠው አልነበሩም፡፡ እንኳን ቁም ነገር ላለው ጉዳይ ይቅርና ለዚችም ከባድ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር፡፡

እንግዲህ እኛ አላየንም፣ ግን የንጉስ ነገስቱ ቤተመንግስት ውቃቢዎች ሹክ ያሉንን ነው የምንተርክላችሁ፡፡ በ1953 ዓ.ም ጀነራል መንግስቱ ነዋይ በሞከሩት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የተገደሉትና በጊዜው የንጉሰ ነገስቱ መንግስት የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ራስ አበበ አረጋይንና ሌላውን የመከላከያ ሚኒስቴር ባለስልጣን ጄነራል አብይ አበበን የሚስተካከል የገባው ባለስልጣን አልነበረም፡፡

ለምሳሌ አባባ ጃንሆይ እንዲሁ ሠላም ብሎ እጅ ለመንሳትም ሆነ ለስራ ጉዳይ ወደ ቤተመንግስት ብቻቸውን ወይም ከራስ አስራተ ካሳና ከራስ መስፍን ስለሺ ጋር ሲሄዱ፤ ራስ አስራተ ካሳና ራስ መስፍን ስለሺ ጃንሆይን ጠጋ ብለው ሲያነጋግሩ፣ እነሱ ግን ከንጉሱ ትንሽ ፈቀቅ ብለው ነበር የሚያነጋግሯቸው፡፡ ለምን መሠላችሁ? ራስ አስራተ ካሳና ራስ መስፍን ስለሺ በቁመት ከጃንሆይ ጋር ስለሚተካከሉ፣ ራስ አበበ አረጋይና ጀነራል አብይ አበበ ደግሞ ቁመተ ሎጋ በመሆናቸው ነበር፡፡ በዚህ አድራጐታቸው የተነሳ ጃንሆይ ለራስ አበበ አረጋይና ለጄነራል አብይ አበበ የተለየና ስስ ልብ ነበራቸው አሉ (አሉን ማረጋገጥ ቢከብድም)

ግን ደግሞ ወደውስ ነው እንዲህ የማያደርጉት! አባባ ጃንሆይ እንደ ፍቅራቸው ቅያሜያቸውም እኮ አያድርስ ነው! ወይ ለቢሾፍቱ ቆሪጥ ግብር አሊያም እንደ ወጡ መቅረትን ሊያስከትል ይችላል ይባላል፡፡ (ይባላል ነው!)

የቁመት ነገር ከተነሳ አንድ ምራቂ ታሪክ እነሆ፡- የእኛው የአራት ኪሎ ቤተመንግስት እጣ ክፍሉ ቁመተ አጫጭር ነገስታት እንጂ ሎጋ ነገስታት አልነበረም፡፡ ከአፄ ምኒሊክ ጀምራችሁ ብትቆጥሩ የምታገኟቸው ነገስታትና ገዢዎች ሁሉ አማልእክቶች ቁመት ሲያድሉ ያልነበሩ ወይም ከሠልፉ መጨረሻ ተሰልፈው የነበሩ ናቸው፡፡

የሆኖ ሆኖ የአባባ ጃንሆይን ይህችን ትንሽዬ፣ ነገር ግን ብርቱ ቅያሜአቸውን ልታስከትል የምትችል ጥላቻ፣ ቀድመው ነቄ ያሉት እንደ ራስ አበበ አረጋይና ጄነራል አብይ አበበ አይነት ከፍተኛ ባለሟሎች፣ የኮንፊሽየስን ዘመን የጠገበች ድንቅ ትምህርት በተግባር ማዋላቸውን ያሳየናል፡፡ ሁለት ፀሀይ ባንድ ቤት እንዳይወጣ ነቅቶ በመጠበቅ፣ የዋናውን ፀሀይ ቅያሜና በቅያሜውም የተነሳ የሚመጣውን ቅጣት ማስቀረት፤ ፍላጐቱን በመጠበቅ ደግሞ የንጉሱን ሞገስ በማግኘት አላማን ማሳካት ነው ቁም ነገሩ!

ክፍል ሁለት

ፈላስፎች ብፁአን ናቸው የሚባለውን ሀሰት ነው ብሎ የሚከራከር ደፋር የትም አይገኝም ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ መላእክት ለሌሎቻችን እንደ ትንቢት የሆነውን የወደፊት ነገር ሁሉ ቀድመው ይነግሯቸዋል፡፡ ፈላስፋው ኮንፊሽየስ ይህን ድንቅ ትምህርት ለምዕመናኑ ያስተማረው፣ ወደፊት ትምህርቱን ከመማርና በተግባር ላይ ከማዋል በአዕምሮውም ሆነ በልቦናው የሠነፈ ሎሌ እንደምን ያለ አሳር ሊገጥመው እንደሚችል አማልእክቱ ለሱው ብቻ በጆሮው ሹክ ቢሉት ነው እንጂ የፈረንሳዩን ፀሀዩ ንጉስ ሉዊ አስራ አራተኛን፣ እንኳን በፈረንሳይ ቤተ መንግስት ዘውድ ደፍቶ መንገሱን ይቅርና መፈጠሩንም ኮንፊሽየስ ጨርሶ አይተነብየውም ነበር፡፡ ምንም የማያልቅበት አምላክ ግን ጌታ ሉዊን ከፈረንሳይ ንጉሳውያን ቤተሠቦች ውስጥ መርጦ፣ ቅብአቅዱሱን ቀብቶና ሉዊ አስራ አራተኛ አስብሎ፣ በምድረ ፈረንሳይ ላይ አንዳች አዛዥ ናዛዥ የሌለበት ፈላጭ ቆራጭ ንጉሠ ነገስት አድርጐ አነገሠውና የኮንፊሽየስን ያን የቀደመ ታላቅ ትምህርት እውነትነት በተግባር እንዲታይ አደረገ፡፡ አምላክ የተመሠገነ ይሁን! አሜን!

ፀሀዩ ንጉስ ሉዊ አስራ አራተኛ፣ ልክ እንደ አባባ ጃንሆይ ቁመቱ የሠጠና አይነ ግቡ አልነበረም፡፡ ነገር ግን እንደ ግርማዊነታቸው ማጠሩን እንዳያሳጡት በሚል ቁመተ ሎጋ ሚኒስትሮቹ፣ የጦር አለቆቹም ሆኑ ሌሎች አገልጋዮቹን በአጠገቤ አትቁሙ አይልም፡፡ እርሱ ጨርሶ የማይፈልገው ነገር ቢኖር ሌሎች ከእሱ የበለጠ ደምቀው፣ ከሱ የበለጠ የትኩረት አይን ማረፊያና የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆነው ማየትን ነበር፡፡

ንጉሰ ነገስት ሉዊ አስራ አራተኛ፤ ይህን ፍላጐቱን የያዘው በልቡ እንጂ ለሚስቱ እንኳን ገልጦ ተናግሮት አያውቅም፡፡ ባለሟሎቹም ሆኑ ባለስልጣናቱ የንጉሱን ሀሳብ አንድም በልበ ብርሀንነት አሊያም ጠጠር አስጥለውም ሆነ ዛጐል አስለቅመው ነቄ እንዲሉ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ አለበለዚያ ችግር ነዋ!

የንጉሱ የቅርብ ባለስልጣናትና ባለሙዋሎቹም እጅግ የሚበዙቱ ልክ እንደ ራስ አበበ አረጋይና ጀነራል አብይ አበበ፣ የንጉሱን ልብ ጠልቀው የገቡ ንቁ ከተፎዎች ነበሩ፡፡ ከኒኮላስ ፉኬ በቀር፡፡ ከንጉሱ የቅርብ ባለሟልና ከፍተኛ ባለስልጣናት ውስጥ ኒኮላስ ፉኬ፤ ልበ ቢስ ሞፎ የሚባል ባይሆንም የአለቃውን የንጉሱን የልብ ፍላጐት በግልብጡ የተረዳና በዚህ የተገለበጠ አረዳድ ላይ ተመርኩዞም የተለያዩ ስራዎችን በመስራት የንጉሱን አይንና ሞገስ ለማግኘት የሚጣጣር፣ ልፋ ያለው ባለስልጣን ነበር፡፡

ፀሐዩ ንጉስ ሉዊ አስራተኛ፤ በነገሰበት የመጀመሪያዎቹ አመታት፣ ኒኮላስ ፉኬ ዛሬ የገንዘብ ሚኒስትር እንደምንላቸው፣ የንጉሱ ዋና ገንዘብ ያዥ ወይም ዋናው በጅሮንድ ነበር፡፡ ኒኮላስ ፉኬ ገና በአፍላ ጐረምሳነቱ ጀምሮ በሶስት ነገር የመጣ አይሆንለትም፡፡  ቆንጆ ሴቶች፣ ድል ያለ ፓርቲና ግጥም፡፡ ፉኬ እነዚህ ሶስት ነገሮች ነፍሱ ናቸው፡፡

አጅሬ ገና ደመ ትኩስ ጐረምሳ ሳለ ጀምሮ፣ እዚህ ቀረው የማይባል ድል ያለ ፓርቲ እየደገሰ፣ የፓሪስን ቆነጃጅት ይጋብዝና በተለያዩ የፈረንሳይ እውቅ ደራስያን የተፃፉ ድንቅ ግጥሞችን እያነበበ ልባቸውን በፍቅር ይበላ ነበር፡፡

በኒኮላስ ፉኬ ድርጊት የሚቀኑበት፣ ይሄ የማይረባ ሴት አውል አለሌ እያሉ በድብቅ ሲያሙትና ሲሰድቡት፣ ሌሎቹ ደግሞ የፓርቲውን ድግስ ሁካታ ካጥር ውጪ ሆነው በማዳመጥ፣ ፊታቸውን በምዕራብ አቅጣጫ በማዞር፣ የሲሳይና የፍቅር አማልዕክቶች ከእለታት ባንዱ ቀን ልክ እንደፉኬ እንዲያደርጋቸው፣ ካልሆነም ደግሞ በፉኬ ቪላ ውስጥ ፓርቲ ከተጠሩት ምርጥ የፓሪስ ቆነጃጅት ውስጥ አንዳቸውን እንዲጥልላቸው ባፋቸውም በልባቸውም እየፀለዩ ይማፀናሉ፡፡

ከአመታት በፊት እዚህ እኛ ሀገር አራዶች፣ ቆንጆ የጠፋው ወይም ውብና ማራኪ የሆኑ ቆነጃጅቶችን ለማየት አይኑ የተራበ ችስታ ጐረምሳ፣ ከሰአት በኋላ አራዳ ጊዮርጊስ ጐራ ብሎ ከእነ ክንብንባቸው ይጥገባቸው እያሉ፣ ያራት ኪሎዋ የካቲካላ እመቤታችን ወይዘሮ ታዱ ሲያላግጡብን እንደነበረው አይነት በፓሪስም ቆንጆ የጠፋው ካለ፣ ኒኮላስ ፉኬ ጋር ይሂድ እየተባለ ይነገር ነበር፡፡ አጅሬ ፉኬ የቆንጆ ጠበሳ ዛር የቆመችለት፣ መንጋውን ባንዴ የሚነዳ የሚባልለት ትጉህ ሴት ጠባሽ ነበር፡፡

ይህን የፉኬን የጠበሳ ታሪክ አንብበን የተረዳነው፣ እኛም ምናለ እንደሱ ባደረገን በሚል አለአንዳች የቅናት ስሜት “አበጀህ! ደግ አደረግህ!” ብለን የአድናቆት መልእክታችንን በአክብሮት እንሰድለት ነበር ዛሬ በዚያች በምናውቃትና በተዋብንባት የፓሪስ ከተማ የሚገኝ ቢሆን ኖሮ፡፡ ደግሞስ ድል ባለ እንከን አልባ የፓርቲ ድግስ ላይ ግጥምና ቅኔ ጨምሮ የቆነጃጅትን ልብ የሚያማልል ጠባሽ፤ አበጀህ እንጂ ምን ልንለው ኖሮአል!

የሆኖ ሆኖ ኒኮላስ ፉኬ ከእነዚህ በተጨማሪ እንዲህ ያለውን ቅንጡ ኑሮ የሚገፋበት ገንዘብም አጥብቆ ያፈቅር ነበር፡፡ እንደ ዋና በጅሮንድነቱ ለንጉሠ ነገስቱ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሰውም ነበር፡፡ በ1661 ዓ.ም የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ጁልስ ማዛሪን፤  ከዚህ አለም በሞት ሲለይ የገንዘብ ሚኒስትሩ ኒኮላስ ፉኬ፤ ከንጉሱ ጋር ባለው ጥብቅ ቀረቤታ የተነሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኜ እሾማለሁ ብሎ በልቡ ተማምኖ ነበር፡፡ ንጉሱ ሉዊስ አስራ አራተኛ ግን እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጐ ሊሾመው ይቅርና ይግረመው ብሎ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ አጠፈው፡፡

በቃ ጠቅላይ ሚኒስት ለፈረንሳይም ሆነ ለእኔ አያስፈልገንም አለና ጭጭ አለ፤ ንጉስ ሉዊ፡፡

ይህና ሌሎች አንዳንድ በንጉሱ ላይ ያያቸው ምልክቶች ተደማምረው ኒኮላስ ፉኬን “ንጉሱ ፊት ነስቶኛል፤ በፊቱም ዘንድ ሞገስ አጥቻለሁ” ብሎ እንዲያስብ አደረጉት፡፡ ይሄኔ ታዲያ በቤቱ በረንዳ ላይ እየተንጐራደደ ሲያስብ ቆየና አንድ ሃሳብ ብልጭ አለለት፡፡ የፓሪስን ቆነጃጅት ፓርቲ እየደገሰና ግጥም እያነበበ፣ ልባቸውን ሲበላው እንደኖረው ሁሉ፣ በመላ ፈረንሳይ ሳይሆን በመላው አለም ታይቶም ሆነ ተሰምቶም የማይታወቅ ታላቅና ልዩ ፓርቲ ደግሶ በመጋበዝ፣ የንጉሱን ልብ መብላት እንደሚችል ወሰነ፡፡

ኒኮላስ ፉኬ የፓርቲውን ድግስ ምክንያት በቀጥታ ለሚጠይቀው ቫ ላቪኮምት ተብሎ የተሰየመው የመኖሪያ ቪላውን ተሠርቶ መጠናቀቅ በማስመልከት መሆኑን ቢናገርም፣  ዋናው አላማው ግን የድግሱ የክብር እንግዳ የሆነውን ፀሐዩን ንጉስ ሉዊ አስራ አራተኛን በማስደሰት የቀደመ ተወዳጅነቱን ማደስ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ታላቁን ድግስ አዘጋጀ፡፡

በግብዣው ላይም በአውሮፓ ስመጥር የሆኑ ፈላስፎችና ምሁራን የሆኑት እነ ላፎንቴን፣ እነ ፎሽፎውስልና እነ ማዳም ደሳቪን ሁሉ እንዲገኙ ተደረገ፡፡ ዝነኛው የፈረንሳይ ፀሐፌ ተውኔት ሞልየርም በድግሱ ላይ የሚቀርብና እሱ ራሱም የሚተውንበት ድራማ ጽፎ እንዲያዘጋጅ ተደረገ፡፡ ድግሱም ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ደቡብ እስያ ሀገራት የሚገኙ የምግብ አይነቶችና ምድረ ፓሪሴ ሁሉ ቀምሶት የማያውቀው አይነት፣ ለዚያ ድግስ ብቻ ተብሎ የተሰናዳ ባለ ሰባት ኮርስ ምግብ ነበር፡፡ ተጋባዡ ሁሉ መመገብ ሲጀምር ለንጉሱ ክብር ተብሎ በልዩ ትዕዛዝ፣ በታዋቂ ሙዚቀኞች የተዘጋጀ ሙዚቃ እንዲቀርብ ተደረገ፡፡ ሞልቶ የተትረፈረፈው ምግብ ተበልቶ እንዳለቀ ደግሞ ምድር ያበቀለችው ፍራፍሬ አንዳችም የቀረ የማያስመስል የፍራፍሬ ግብዣ ቀረበ፡፡

ይህም እንዳለቀ ኒኮላስ ፉኬ፤ ወጣቱን ንጉስ እየመራ፣ በልዩ የምህንድስናና የስነ ህንፃ ጥበብ የታነፀውን አዲሱን ቤቱን እያዟዟረ አስጐበኘው፡፡ መቼም የቤቱ ማማር ለብቻው ነው፡፡ በልዩ ጥበብና ዲዛይን በተሰራው የቤቱ የአትክልት ቦታ ትይዩ ባለው ሰገነት ላይ እንደደረሱም፣ በተለያየ ቀለማት ያሸበረቀው የርችት ተኩስ ቀለጠ፡፡ ይህ ሁሉ ግብዣና ትዕይንት ተጋባዡን ሁሉ በአድናቆት ልቡን ሊያቆመው ደርሶ ነበር፡፡ ከዚያም የሞልየር ድራማ ቀረበና እንደገና የተጋባዡ ልብ በአድናቆት ላይ አድናቆት ተጐናፀፈ፡፡

በምድረ ፈረንሳይ ከዚህ በፊት ታይቶ ያልታወቀው ይህ ድንቅ ድግስ፣ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ተካሂዶ አበቃ፡፡ ድግሱ በዋናነት የተዘጋጀለትና የክብር እንግዳም የነበረው ንጉሠነገስቱ ሉዊ አስራ አራተኛ የልቡን በልቡ ይዞ፣ ድግሱን እንደምንም ብሎ በውሸት ፈገግታ ፊቱን ቀብቶ ደስተኛ መስሎ ጨረሰው፡፡ የንጉሱ ልብና ቆሽት ግን በቅናት እርር ድብን ብሎ ነበር፡፡ እዚህ እኛ ሀገር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደምንረዳው እንግዶቹ ሁሉ ወደየመጡበት ለመሄድ ንጉሱን ሲሰናበቱት በህይወት ዘመናቸው ሁሉ እንዲህ ያለ አስደናቂ ድግስ ጨርሶ አይተው እንደማያውቁ በመሀላ ሳይቀር እያረጋገጡ ይነግሩት ነበር፡፡

ወይ ነዶ! እያለ ንጉስ ሉዊ በቅናት ተንገበገበ፡፡ በልቡም “በጅሮንድ ፉኬ ሆይ፤ ለዚህ ድፍረትህ ከእኔ ከፀሐዩ ንጉስ ሌላ ይበልጥ የሚደምቅ ፀሐይ ሆነህ በመታየት ለፈፀምከው ታላቅ ድፍረት፣ የእጅህን ባልሰጥህ አማልዕክቱ እንዲህ ያድርጉኝ እንዲህም ጨምሩብኝ እያለ በንዴ እየተንጨረጨረ ማለ፡፡

ንጉሱን በማስደሰት የፊቱን ሞገስ እንደሚያገኝና ከፍ ያለ የሹመት በረከት እነሆኝ እንደሚባል የተማመነው በጅሮንድ ኒኮላስ ፉኬ፤ በመጨረሻ ንጉሰነገስት ሉዊን ቤተመንግስቱ በር ድረስ ከሸኘው በኋላ “ንጉስ ሆይ ሺህ አመት ንገስ፡፡ ከባለሟሎችህ አንዱ የሆንኩ እኔ ባርያህ ለደፋኸው ዘውድ ግርማ፣ ለንጉሠነገስት ስምህ ክብር ይሆን ዘንድ ይህችን አነስተኛ ድግስ እነሆ አዘጋጅቼልሀለሁ፡፡ በድግሱም የጌታዬ የንጉሠነገስትነት ልብህ ደስ ተሰኝቷል ብዬ በቅንነት ተስፋዬን ጥያለሁ፡፡ ጌታዬ ንጉሠነገስት፤ የልቡን መደሰት በአንደበቱ ቢገልጥልኝ ታዛዡ ባሪያህ አንዷን አለም ሳይሆን ዘጠኙን አለማት በሞላ በእጆቹ እንደያዝኳቸው ቆጥሬ፣ የተቀረውን ምሽትና የሚመጡትንም ቀናቶች ወደር በሌለው የደስታ ስሜት አሳልፋቸዋለሁ፡፡ ጌታዬ ንጉስ ሆይ፤ እንደገናም እልሀለሁ ሺህ አመት ንገስ! ዘውድህና የግዛት ርስትህም ለልጅ ልጆችህ ይሁን፡፡ አለውና ግንባሩ መሬቱን እስከሚነካ ድረስ ለጥ ብሎ እጅ ነሳ፡፡

ፀሐዩ ንጉስ ሉዊ አስራአራተኛ ከዚህ በፊት ያደርገው እንደነበረው፣ ባለሟሉን ኒኮላስ ፉኬን ወደ ደረቱ አስጠግቶ፣ በሁለት እጆቹ እቅፍ አደረገውና “ወዳጅ ባለሟሌ ኒኮላስ ሆይ፤ በእውነት አንተ ድንቅ ሰውና እንከን የማይወጣልህ ባለሟሌ ነህ፡፡ ዛሬ ለእኔ ክብር ብለህ ያዘጋጀኸው ማለፊያ ድግስ በአይኔ ሞገስ አግኝቷል፤ ልቤንም በሀሴት ሞልቶታል፡፡ እንዲህ ያለ እጅግ አስደሳች የሆነ ስራ የሚሠራ ባለሟልን የማይሾምና የማይሸልም ንጉስ እንደ ንጉስ ሊቆጠር አይገባውም፡፡ ስለዚህ ይህ ምሽት አልፎ አዲስም ቀን ሲሆን የስራህን ፍሬ ትበላለህ፡፡ በዚያ ቀን በማለዳውም ደረትህ ለኒሻን፣ ትከሻህ ለወርቅ ካባ፣ ግንባርህም ለራስ ወርቅ ይበቃል፡፡ የንጉሱን የእኔን ልብ እንዲህ እንዳስደሰትከው ሁሉ፣ እነሆ አንተም በልብህና በመንፈስህ ተደስተህ የቀረውን የዛሬን ሌሊት መጭውን ቀናቶች ሁሉ አሳልፍ፡፡ ሂድ በደህናም እደር” ብሎ አሰናበተው፡፡

ያኔ ምንም እንኳ አብረነው ኖረን ደስታ እንዴት እንዳደረገችው ባናየውም፣ ከተፃፈው ታሪኩ እንደተረዳነው የእለቱን ቀሪ ምሽት ያሳለፈው በቃላችን እንዲህ ነው ብለን መግለጽ በማንችለው ወደርና አቻ የለሽ በሆነ ደስታ እንደተዋጠና አይኖቹን በእንቅልፍ ሳይከድን ነበር፡፡ ኧረ ምን ይሄ ብቻ! ሲነጋ ለንጉሱ ቤተመንግስት በተዘጋጀ ልዩ ስነስርአት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ሲሾም የፈረንሳይን ከፍተኛ የክብር ኒሻን ሲሸለምና እንደ ንጉሱ የስጋ ዘመድ በመቆጠር የልኡልነት ማዕረግ ተሰጥቶት፣ የራስ ወርቅ ሲያስር እየታየው፣ የተሰማው የደስታ ስሜት ልቡን ሊያቆመው እየዳዳው ነበር፡፡ ጠዋት ወደ ቤተመንግስት በክብር የሚወስደውና ንጉሱ የሚልክለት ሠረገላ ሲመጣ፣ እንዴት ያለ ልብስ መልበስ እንዳለበት ለመወሰንም ያለውን ልብስ ሁሉ አውጥቶ አንዱን ሲያነሳ ሌላውን ሲጥል ረዘም ያለ ሰአት አሳለፈ፡፡

ታዲያ መቼም ሌሊቱ የቱንም ያህል ቢረዝም መንጋቱ አይቀርምና፣ ነግቶ የመኝታ ቤቱ በር ሲንኳኳ፣ የንጉሱ መልዕክተኞች ሳይሆኑ ራሱ ንጉሠ ነገስቱ ወደ ቤተመንግስቱ ይዞት ለመሄድ የመጣ መስሎት “ንጉስ ሆይ፤ እነሆኝ እዚህ አለሁ” እያለ በታላቅ ጥድፊያ በሩን በርግዶ “ንጉስ ሆይ፤ ሺህ አመት ንገስ! ለእኔ ለአገልጋይ ባሪያህ ክብር ስትል ራስህን ዝቅ አድርገህ አንተው ራስህ ወደቤተመንግስትህ ልትወስደኝ መጣህ፡፡ ንጉስ ሆይ፤ እነሆ እንደገናም እላለሁ ሺህ አመት ንገስ፡፡” እያለ ከፍ ባለ ድምጽ ሲለፈልፍ፣ በከፈተው መኝታ ቤቱ ለመግባት ወደ ውስጥ የሚዘልቅ ሰው ሲያጣ ጊዜ፣ በደስታ ስካር የተበተነውን ቀልቡን ለመሰብሰብ እየሞከረ ቀና ብሎ በሩ ላይ የቆመውን ሰው ሲመለከት በመደናገርና በድንጋጤ የሃፍረት ስሜት ወደ ኋላው ተፈንግሎ ሊወድቅ ምንም አልቀረውም ነበር፡፡ ኒኮላስ ፉኬ እንዲህ ያለ ስሜት ቢሰማው ጨርሶ እንዳትፈርዱበት! ምነው ብትሉ? በሩ  ላይ ቆሞ የጠበቀው ንጉሱ ሳይሆን የንጉሱን ጠላቶችና ተቀናቃኞች በቀንም ሆነ በጨለማ እየለቀመ አፈር ድሜ የሚያስግጣቸው የንጉሱ ዋነኛው አንጋችና የወህኒ ቤቶች አለቃ የሆነው ዲአርተኛ ነበራ! ዲአርተኛ የተባለው የንጉሱ ዋነኛ አንጋች እንዴት ያለ ሰው እንደነበር በቀላሉ እንድታውቁና የኒኮላስ ፉኬን ድንጋጤ በወጉ እንድትረዱት የአገር ቤት ምሳሌ እነሆ ብለናል፡፡

የደርግ መንግስት ማዕከላዊ እየተባለ የሚጠራ አስከፊ የእስር ቤትና ውቃው የሚባል ለጨካኝነቱ አቻ ያልተገኘለት ዝነኛና ትጉህ ገራፊና ወንጀል መርማሪ ነበረው፡፡ የንጉስ ሉዊ አስራአራተኛ ውቃው ደግሞ ዲአርታኛ፣ ማዕከላዊው ደግሞ በፓይረኒ ተራሮች ላይ የሚገኘው አስከፊው እስር ቤት ነበር፡፡ ዲአርታኛም በጌታው በንጉሱ በታዘዘው መሠረት ኒኮላስ ፉኬ ድንጋጤውና መደናገሩ ገና ሳይለቀው እጆቹን የፊጢኝ በካቴና፣ እግሮቹን ደግሞ በሰንሰለት ጠፍሮ በሶስት ጠረንገሎ ወታደሮች አንጠልጥሎ ከሠረገላው ወለል ላይ በመጣል ማረፊያ ቤት ወስዶ ወረወረው፡፡ በጊዜአዊው ማረፊያ ቤት የእጆቹ ካቴናና የእግሩ ሰንሰለት ለአፍታም እንኳ ሳይፈታለት ለሶስት ወራቶች ከታሠረ በኋላ የመንግስት ገንዘብ በመዝረፍ ለግል ጥቅም በማዋልና በስልጣን አለ አግባብ በመጠቀም ወንጀል በንጉሱ ተከሶ ፍርድቤት ቀረበ፡፡ በቀረበበት ክስም ወንጀለኛ ተብሎ እድሜ ልክ ተፈረደበትና በፓይረኒ ተራሮች ወደሚገኘው አስከፊ ወህኒ ተላከ፡፡ በኒኮላስ ፉኬ ላይ ይህ የእድሜ ልክ እስራት ሲፈረድበትና ወደ ወህኒ ሲላክ በቦታው የነበረው ንጉሱ ሉዊ አስራአራተኛ እውነተኛውን ፈግታውን እያሳየ፤ “እነሆ እንደ እጅ ስራህ መጠን ተከፈለህ” አለው፡፡

በሀዘንና በድንጋጤ ቅስሙ የተሠበረውና ነገሩ ሁሉ በህልሙ እንጂ በእውኑ የተፈፀመበት አልመስልህ ያለው ምስኪኑ በጅሮንድ ኒኮላስ ፉኬ “ንጉስ ሆይ፤ የሠራሁትን ሁሉ የሠራሁት ያወጣሁትን ገንዘብ ሁሉ ያወጣሁት እኮ በአንተ ትዕዛዝና ፈቃድ ብቻ ነበር” በማለት የምህረት ጩኸቱን ሲጮህ፣ ንጉሱ የምፀት ሳቅ እየሳቀ “በጅሮንድ ኒኮላስ በእጅጉ የዋህ ነህ፡፡ ፈረንሳይ ያላት ንጉስ እኮ እኔ ብቻ ነኝ፡፡ እኔ ፀሀዩ ንጉስ ሉዊ አስራአራተኛ ነኝ” አለውና የፍርድ ቤቱን አዳራሽ ለቆ ወጣ፡፡

እድለቢሱና አሳዛኙ ኒኮላስ ፉኬም በድንጋጤና በታላቅ ቁጭት አፉ ተለጉሞበት ተጨማሪ አንዲትም ቃል ሳይናገር ደርቆ እንደቆመ የዲአርታኛ ወታደሮች እያዳፉ፣ ወደ አስከፊው ወህኒ ቤት ወስደው ጣሉት፡፡ በዚያም ከአንድም እስረኛ ጋር በምንም አይነት መንገድ እንዳይገናኝ ሆኖ፣ በብቸኝነት በትንሽና ጠባብ ክፍል ውስጥ ለሃያ አመታት በአስከፊ እስር ከማቀቀ በሁዋላ፣ አይኑ ታውሮና ጆሮው ደንቁሮ በሳምባ ምች በሽታ ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡

እንግዲህ ኒኮላስ ፉኬ ስለሞተ የእኛም ትረካ አብቅቷል፡፡ ደግ ነገር መመኘት አሪፍ ነውና ሌላ ጊዜ ደግ ደጉን ልናወጋ ቃል ተገባባተን እንለያይ! ይህቺን “ከንጉሱ በላይ ደምቃችሁ አትታዩ!” የምትለውን አሪፍ ምክር እናንተ እንደሚያስፈልጋችሁ ተጠቀሙበት እንጂ እኛን እዚህ ውስጥ አያገባንም፡፡ እኛን የሚያገባን ጉዳይ ነገርዬዋን አትርሷት እሚለው ላይ ብቻ ነው፡፡ ልክ ነዋ!

 

 

Read 3037 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 09:44