Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 07 April 2012 09:39

የ”ትኩሳት” ሴቶች በፀጉራቸው ይታወቃሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ትኩሳት” ድርሰት ውስጥ ጎልተው የሚታዩት ሴቶች ሶስት ናቸው - አማንዳ፤ ሲልቪ፤ ኒኮል። ያለ ስም የተጠቀሰችውን ሌላኛዋ ሴት እንደ አራተኛ ልንቆጥራት እንችላለን። ስብሃት ገ/እግዚአብሄር፤ የድርሰቱን ምእራፍ ሁለት፤ ይህችን ሴት በመግለፅ ይጀምራል።

“ያን ሰሞን አንዲት ቆንጆ አሜሪካዊት ነበረችኝ። አይኗ ሰማያዊ፤ ፀጉሯ በጣም ንፁህ ቡና አይነት። እጅግ ደስ ትላለች...” (ገፅ19)። ምናልባት፤ የመጀመሪያው አረፍተ ነገር፤ ጎደሎ ነገር ሊመስለን ይችላል። “...ቆንጆ አሜሪካዊት ነበረችኝ”። አሜሪካዊት ምን? አሜሪካዊት ጓደኛ ወይም ፍቅረኛ፤ አሜሪካዊት ሚስት ወይም ውሽማ... በሚል ቢያሟላው ይሻል ይሆናል። ለማንኛውም፤ ፀጉሯ በጣም ንፁህ ቡና አይነት ነው።

“እጅግ አስደሳች ሴት” ተብላ ከተገለፀችው ከዚህች ሴት ቀጥለን የምናገኛት አማንዳን ነው።

“የአማንዳ ፈገግታ ደግና ንፁህ ነው፤ ትንንሽ አይኖቿ ንፁህ ሰማያዊ ናቸው፤ ረዥም ፀጉሯ በጣም ንፁህ ሆኖ፤ ጨረቃ ውስጥ ተነክሮ የወጣ ይመስላል” (ገፅ20)

“ጨረቃ ውስጥ ተነክሮ የወጣ” የሚለው አገላለፅ፤ የስብሃት ኦርጂናሌ ፈጠራ ከሆነ፤ ከውብ አገላለፆች መካከል የሚመደብ ይመስለኛል። የደራሲ አንዱ ብቃት፤ ነገሮችን በደፈናው “ደስ ይላል፤ ይማርካል፤ ያስጠላል፤ ክፉ ነው፤ ደግ ነው” ብሎ መንገር ሳይሆን፤ በተጨባጭ ቀርፆ ማሳየት ነው። ብቃት ያለው ደራሲ፤ ነገሮችን መርጦና ቀርፆ ይገልፅልናል። እኛ አንባቢያን፤ የተገለፀውን ነገር በአይነ ህሊና እያየነው፤ “ይሄ ነገር ደስ ይላል፤ ይማርካል፤ ያስጠላል፤ ክፉ ነው፤ ደግ ነው” የሚል ሃሳብና ስሜት ያድርብናል። “ጨረቃ ውስጥ ተነክሮ የወጣ” የሚመስል ፀጉር አይታያችሁም? የሚያብረቀርቅ ብርማ ፀጉር...። (በእርግጥ ይህን አስተያየት የተመለከተ አንድ የስነፅሁፍ ምሁር፤ ብዙም አልተዋጣለትም። “የጨረቃ ንክር” የሚለውን አገላለፅ በማንበብ፤ ምናብ ውስጥ የግድ አብረቅራቂ ብርማ ፀጉር ላይታይህ ይችላል ብሎኛል። ለምን ብዬ ጠይቄዋለሁ።

ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠኝም። የጨረቃ ቀለም ምን አይነት ነው? በማለት መልሶ በጥያቄ አፋጠጠኝ። እውነትም፤ የጨረቃ ቀለም አስቸጋሪ ነው። አንዳንዴ ብርማ፤ ሌላ ጊዜ ወርቅማ ይመስላል፤ ወደ ሮዝ የሚያደላበት ጊዜም ሳይኖር አይቀርም። “ጨረቃ ውስጥ ተነክሮ የወጣ” የሚለው አገላለፅ፤ በከንቱ እንደባከነ ዘይቤያዊ አባባል የቆጠረውም በዚህ ምክንያት ነው። ገባኝ።

ቢሆንም ግን፤ ሙሉ በሙሉ የባከነ ነው ለማለት አልቻልኩም። የጨረቃ ገፅታ፤ ብርሃን የሚፈነጥቅ ብርማ ሃይቅ ነው እንበል። ያኔ አገላለፁ አሪፍ አይሆንም?) ጨረቃ ውስጥ ተነክሮ የወጣ፤ የሚያብረቀርቅ ብርማ ፀጉር... በአይነ ህሊናችን ስንመለከት፤ “አስደሳች ፀጉር ነው” የሚል ስሜት ሊያድርብን ይችላል። ደራሲው “የአማንዳ ፀጉር አስደሳች ነው” ብሎ ባይነግረንም፤ አስደሳች ፀጉር አሳይቶናል፤ ገልፆልናል ማለት ነው።

ከዚህ ጥሩ የፀጉር አገላለፅ በተቃራኒ፤ ደራሲው የአማንዳን ፈገግታ እንዴት እንደገለፀው ተመልከቱ። ፈገግታዋ “ደግና ንፁህ ነው” ብሎ ነገረን እንጂ፤ አልገለፀውም። ደግና ንፁህ ፈገግታ፤ ምን አይነት ፈገግታ ነው? ድንገት ፊትን የሚያበሩ የአይን ጨረሮች ሲፈነጥቁ፤ ከንፈሮች ድምፅ ማውጣት ሳያስፈልጋቸው ደስታን ለማብሰር ሲገለጡና በነጭ ጥርሶች ሲፈኩ ይሆን? ወይስ፤ በሚፍለቀለቅ የሃሴት ድምፅ ሲታጀብ ነው? ከመሽኮርመም ጋር ሲዋሃድ ነው ወይስ በዚህ አለም ምንም የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ ለማወጅ አንገት ቀና ከማለት ጋር የሚታይ የከንፈሮች፤ የአይኖችና ጠቅላላ የገፅታ ብርሃን? ደግና ንፁህ ፈገግታ ምን አይነት እንደሆነ አልተገለፀም፤ ተነገረ እንጂ።

የሆነ ሆኖ፤ የአማንዳ ፀጉር፤ ረዥምና በጣም ንፁህ ነው። በሚቀጥለው አንቀፅ ላይ የምናገኛት ሲልቪም፤ ንፁህ ፀጉር አላት።

“ወደ ኋላዋ የተለቀቀው ንፁህ ጥቁር ፀጉሯ ያብለጨልጫል” (ገፅ 20)

የሴት ነገር ሁሉ፤ የፀጉር ነገር ብቻ እንዳይመስልብን፤  የአራተኛዋን ሴት ፀጉር ከማየታችን በፊት፤ ስለፍቅር ትንሽ ከመፅሃፉ ልጥቀስ።

ሲልቪና ተራኪው ነው የሚነጋገሩት።

“እንዴት ያለች ሴት ነው ምትመርጠው?”

“እንዳንቺ ያለች” ...

“እንዴት ነው እንደኔ ያለች ሴት ማለት?”

“አእምሮዋን ላከብረው ስችል፤ ጠባይዋን ልወደው ስችል፤ ገላዋን ልመኘው ስችል... በነዚህ ሶስት ነገሮች በቂ ሆና ሳገኛት፤ ሴትዮዋ እንዳንቺ ያለች ናት ማለት ነው” ... (ገፅ53)

ጥሩ ምልልስ ነው። ለተራኪው ፍቅር ማለት፤ የአእምሮ ብቃቷን ከማክበርና ሃሳቧን ከማድነቅ ጋር የተያያዘ ነው - በሃሳብ መማረክ። ጠባይዋና ባህሪዋንም መውደድ ነው ፍቅር ማለት - በመንፈስ መማረክ። ከዚህም በተጨማሪ በአካል መመኘትን ይጨምራል - በስሜት መማረክ። ስብሃት በ30ዎቹ እድሜው፤ ስለ ፍቅር እንዲህ ማሰብ መቻሉ፤ ግሩም ነው። ብዙዎች የዚህን ያህል ብቃት የላቸውም።

ነገር ግን፤ ከአእምሮና ከሃሳብ፤ ከባህርይና ከመንፈስ፤ ከአካልና ከስሜት ጋር አያይዞ ስለ ፍቅር ማሰብ ብቻውን፤ ለደራሲ በቂ አይደለም።

የደራሲ ስራ፤ ስለ ፍቅር ቲዎሪዎችን ወይም    ፅንሰ - ሃሳቦችን ማብራራት ሳይሆን፤ ቲዎሪውን ወይም ፅንሰ - ሃሳቡን በተጨባጭ ቀርፆ መግለፅ ነው። ያንን ቲዎሪ ከያዘ፤ በዚያው መሰረት የሚከበር አእምሮ፤ የሚወደድ ባህርይና የሚጓጉለት ገላ ምን አይነት እንደሆነ ለመግለፅ፤ ነገሮችን መርጦና ቀርፆ በተጨባጭ ህይወትና ነፍስ ዘርቶበት ማሳየት ነው - የደራሲ ብቃት።

ደራሲው፤ የሲልቪንና የተራኪውን ፍቅር በዚህ መንገድ፤ ህይወት ሰጥቶ ማሳየት ቢችል እንዴት ግሩም በሆነ ነበር። አንዱ የሌላውን አእምሮ ሲያደንቅ ለማሳየት፤ ቢያንስ ሁለት ነገሮች ያስፈልጋሉ - አንደኛ የሚደነቅ የአእምሮ ብቃት ምን አይነት እንደሆነ ስሎ ማሳየት፤ ሁለተኛ ይህን የአእምሮ ብቃት ማክበር ወይም ማድነቅ ምን አይነት እንደሆነ ቀርፆ ማሳየት። መቼም፤ የሚደነቅ የአእምሮ ብቃት ለማሳየት፤ አንዱና ትልቁ ዘዴ፤ የገፀባህርያቱ የህይወት አላማና የእለት ተእለት ስራ ላይ ማተኮር ነው።

የልብወለድ ደራሲ የመሆን የህይወት አላማ የያዙት ሲልቪና ተራኪው፤ ጥቂት ስለ ኪነጥበብ ሲያወሩ ይታያሉ፤ የተለያዩ ድርሰቶችን እንደሚፅፉና ስራዬ ብለው እንደያዙትም በመፅሃፉ ውስጥ ተጠቅሷል።

ነገር ግን፤ ወጣቶቹ እንደሚሰሩ ተነገረን እንጂ፤ “አልተገለፀልንም”። ተራኪው ገፀ ባህርይ፤ ከሆነ ሰአት ጀምሮ እገሌ ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ እንደሚፅፍ፤ እስከ ሆነ ሰአትም ቤተ መፃህፍት ውስጥ ልብወለድ ብጤ እንደሚሰራ ተነግሮናል፤ የሲልቪም እንደዚያው። ነገር ግን፤ በሚሰሩት ነገር የአእምሮ ብቃታቸውን ልናይ ይቅርና በተጨባጭ ምን እንደሚሰሩ አልተገለፀም። በአእምሮ፤ በባህርይና በአካል የተዋሃደ ነው የተባለውንም ፍቅር፤ ...ምን አይነት እንደሆነ አላየነውም። እንዲያውም፤ ፍቅረኞች የተባሉትን ወጣቶች፤ ብዙም አናውቃቸውም ማለት ይቻላል።

ይህ ትልቅ የአገላለፅ ድክመት ነው፤ (“በልብወለድ ብጤ” ውስጥ፣ ከዚህ የበለጠ ጥበባዊ አገላለፅ መጠበቅ የለብንም ካልተባለ በቀር)። ወይም ደግሞ፤ ቢያንስ ቢያንስ ሲልቪ ንፁህ ጥቁር ፀጉር እንዳላት እናውቃለን ብለን መፅናናት እንችላለን። እውነትም፤ ከኒኮል ፀጉር ይለያል።

የኒኮል ፀጉር’ኮ፤ አቧራ የተነሰነሰበት ይመስላል (ገፅ 17)። ኒኮል በፀጉሯ ከሌሎቹ ሴቶች ትለያለች። “ንፁህ” የሚል ቅፅል አልተሰጠውማ። በእርግጥ የኋላ ኋላ፤ ያንን “ቅፅል” ተጎናፅፋለች። ተራኪው በታሪኩ መጨረሻ አካባቢ፤ ኒኮልን ሲያያት... በጣም ተለውጣለች። ለዚህም ነው፤ “ፀጉሯ እንደድሮው አመዳም አይደለም፤ ንፁህ ቡናማ ቀለም ተነክሯል” በማለት የሚገልፃት (ገፅ 278) ።

ኒኮል፤ ከሌሎቹ ሴቶች የሚያመሳስል የጋራ ነገር አገኘች ማለት ነው - “በጣም ንፁህ” ከሚባሉት ጎራ ባትሰለፍም። በአጭሩ፤ የአራቱ ሴቶች ፀጉር በደራሲው አገላለፅ የሚከተለውን ይመስላል።

አሜሪካዊቷ - “ፀጉሯ በጣም ንፁህ ቡና አይነት”

አማንዳ - “ረዥም ፀጉሯ በጣም ንፁህ”

ሲልቪ - “ንፁህ ጥቁር ፀጉሯ”

ኒኮል - “ንፁህ ቡናማ ቀለም”

 

 

Read 4191 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 09:44