Saturday, 07 October 2017 14:48

እምዬ ኢትዮጵያንና ገዢዎቿን አናምታታ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(18 votes)

አገርን መንከባከብ ሳናጣት ነው

   የጥንቱ የአልባንያ ኮሙኒዝም አቀንቃኙ “ኢህአዴግ ነፍሴ”፤ ደርግን ከአራት ኪሎ ቤተ መንግስት አስፈንጥሮ (የስንት ዘመኑን ትግል፣ የሰኮንድ አስመሰልኩት አይደል!?) የስልጣን መንበሩን ወይም ወንበሩን የተቆናጠጠ ሰሞን ምን ያልተባለ ነገር አለ?! (በርግጥ ወዲያውኑ ሶሻሊዝምን መሳቢያ ውስጥ ከትቶ “ነጭ ካፒታሊዝም”ን እንደሚከተል ለዓለም ማወጁን እናውቃለን! (ተሸወድኩት ያሉት የወቅቱ የአገሪቱ ርዕሰ ብሄር፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ነበሩ!) እናም …ለሩብ ክፍለ ዘመን በምርጫም በእጅ ጥምዘዛም እኛንና እምዬ ኢትዮጵያን ገዛን፡፡ (በአፍሪካ በምርጫ ብቻ ህዝብ ተገዝቶ አያውቅም!) እናላችሁ --“ካፒታሊስት ነኝ” ማለቱ ጠቅሞታል፤ ለአገር ውስጥም ለውጭም፡፡ (የገንዘብ ብድርና ድጋፍ ማን ይሰጠው ነበር?!)
እናላችሁ …ያኔ … “የአፍሪካ የነፃነትና የዲሞክራሲ ቀንዲል”፣ “የእኩልነትና ፍትሃዊነት ተምሳሌት”፣ “የሰላም ታጋይ”፣ “የብሄር ብሄረሰቦች ሰገነት” ወይም ገነት ወዘተ… በሚል ብዙ ተደንቋል፤ ተሞግሷል። (በማንም ሳይሆን በራሱ!) በርግጥ በኋላ ላይ ከምዕራብ አገራት መሪዎች፣ አስደንጋጭ የሆነ፣ ዱብ ዕዳ አድናቆት ሳያገኝ አልቀረም፡፡ ፓርቲው ሳይሆን የፓርቲው መሪ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፡፡ (መሬት ይቅለላቸውና!) ሌሎችም አፍሪካውያን ግን ነበሩ፡፡ የእንግሊዙ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ይመስሉኛል …. የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሩዋንዳ መሪዎችን፤ “ወጣት ዲሞክራት መሪዎች” (ቃል በቃል ባይሆንም) ሲሉ ያወደሷቸው። (እንደው ለለውጥ ብለው መሆን አለበት!)
እርግጠኛ ነኝ በኋላ ግን ሳያዝኑ አልቀሩም - ለችኮላቸው!! የእኛን እንግዲህ ለጊዜው ሆድ ይፍጀው ብለን እንተወው፡፡ የቀሩት ሁለቱም ግን አሳፋሪ እንጂ አኩሪ አልነበሩም፡፡ የኤርትራው አገራቸውን ከቅኝ ግዛት አላቀቅኳት ብለው የመጨረሻ ባርነትና እንጦሮጦስ ውስጥ ዶለዋታል። የሩዋንዳው መሪ ደግሞ የሥልጣን ቆይታቸውን ለማራዘም፣ህገ መንግስት ሲፍቁ፣ ከህዝባቸው ተቃውሞ ተነስቶባቸው ነበር፡፡ (እኒህ ዓይነተኛ የአፍሪካውያን መሪዎች መገለጫዎች ናቸው!) በነገራችን ላይ ኢህአዴግ የገባ ሰሞን -- ሙገሳና ውደሳው በግለሰብም ደረጃ ይንጸባረቅ ነበር፡፡ (ወዶ ዘማቾች ውለው ይግቡ!) እናላችሁ… ያን ሰሞን አንዱ የኢህአዴግ ነፍሴ፣ “ቀንደኛ ደጋፊ”፤ አገሩን ሊጎበኝ ከውጭ ለመጣ የ “ያ ትውልድ” የቀድሞ ወዳጁን ያገኘውና ስለ አዲሱ መንግስት ይተርክለት ጀመር… ከእንግዲህ ህዝቦች እውነተኛ የሥልጣን ባለቤት መሆናቸውን፣ በአገሪቱ ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ መመስረቱን፣ ብቻ ..ምን አለፋችሁ..  የኢህአዴግ መራሹን መንግስት፤ ፀጋዎችና በረከቶች አዘነበበት፡፡ “ፀሃዩ መንግስታችን!” ማለት ብቻ ነው የቀረው፡፡ (“ፀሐዩ ንጉሳችን” ይባል እንደነበረው!)… የአገሪቱ ሰማይ ላይ ገና አሁን የማትደበዝዝ ጠሐይ መውጣቷን…. ህዝቦች በነፃነት እንደሚንበሸበሹ፣ ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች ገነት እንደምትሆን፣ የሰብአዊ መብት በማክበር ለአፍሪካ አርአያ መሆናችን እንደማይቀር…ወዘተ እስኪሰለቸው ድረስ ደሰኮረለት፡፡ (“ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ” እንደሚሉት ዓይነት!)
ከውጭ የመጣው የቀድሞ ወዳጁም፤ ሁሉንም በትዕግስት ካደመጠ በኋላ (የ60ዎቹ የጨሰ ፖለቲከኛ መሆኑን ሳይረሳው አልቀረም - የዋሁ አፍቃሪ ኢህአዴግ!) እናም አድምጦ አድምጦ፤ “ወዳጄ”፤ እባክህ እሱንም አታክረው!!” አለው አሉ፡፡ (አሉ ነው እንግዲህ!) በርግጥ ትክክለኛ ምክር ነበር። (የሰማው የለም እንጂ!) ይታያችሁ …ገና ሥልጣን ላይ ተሞክሮ ያልታየ የበረሃ ፓርቲን፣ ገና የትጥቅ ትግሉን ፈትቶ ያልጨረሰ ነፃ አውጭ ፓርቲን … የዲሞክራሲና የነፃነት ሃዋርያ አድርጎ መሳልና መወከል  ጭፍንነት ነው፡፡ በጭፍን መደገፍ! (ግን እኮ ከተባሉት ውስጥ ብዙዎቹን፣ኢህአዴግ ዛሬም አላሳካቸውም!)
ወደ “አታክረው” ልመልሳችሁ፡፡ እናላችሁ … የአገራችን ብዙዎቹ ችግሮች በቅጡ ቢመረመሩ መንስኤያቸው በቀጥታ ከ“ማክረር” ጋር የተገናኘ መሆኑ አይቀርም፡፡ (ኢህአዴግ ነፍሴ ደግሞ በተፈጥሮው “ማክረር” ይወዳል!) የብሄር ፖለቲካን - ማክረር! - “የድሮ ሥርዓት ናፋቂዎች” ብሎ ፍረጃን- ማክረር! “በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር” በሚል - ማክረር! “በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ አንዲት ጥይት አትተኮስም” የሚለውን ምኞት ወለድ ዲስኩር- ማክረር! (ትልቅ ዋጋ አስከፍሎታል!) ተገንጥላ ነፃነቷን ካወጀች አዲስ አገር ጋር  ፍቅርን- ማክረር! (ጦሱ ለአገር ተርፏል!) “ነፃና እንከን የለሽ ምርጫ” በሚል ለምዕራባውያን ፍጆታ ሲባል - ማክረር! (ግን የኋሊት ጉዞ ነው የተረፈን!) ብቻ….ነገሮችን ያለቅጥ በማክረሩ፣ “ኢህአዴግ ነፍሴ” በራሱ ላይ ዙሩን አክርሯል፡፡ አገርንና ህዝብን ደግሞ ለጥፋት ዳርጓል፡፡ የብርሃን ጭላንጭሎችን አዳፍኗል፡፡ (ስንዝር ወደፊት ተጉዘን፣ ብዙ እርምጃዎች ወደ ኋላ ዳክረናል!)
ኢህአዴግ፤ የብሄር ፖለቲካን በማክረሩ ምን ተፈጠረ? ብዙ በጎሳና በጎጥ የታጠሩ፣ ዜጎችና የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ አሸን ብቻ አይደለም የፈሉት፡፡ አገሪቱን ለአስከፊ የዘረኝነት አደጋ አጋልጧታል፡፡ (የተቀበረ ፈንጂ በሉት!) ዛሬ ከ25 ዓመት የፌደራል ሥርዓት ተሞክሮ በኋላ… በኦሮሚያና በሶማሊያ ክልሎች፣ አስፈሪና አሳፋሪ የዜጎች እልቂትና መፈናቀል ተከስቷል፡፡ (ያውም በገዛ አገራቸው!) አምባገነን የክልል መንግስታትና የጎሳ መሪዎች እንዲሁም የዘር ፖለቲካ ልሂቃን ተፈጥረዋል፡፡ አብጠዋል፡፡ (መካድ ሳይሆን ማረቅ ነው የሚበጀው!) የፈረደበት ጎሰኝነት (በዛሬ ቋንቋ “የተለጠጠ ብሄርተኝነት”) እነ አፄ ቴዎድሮስና አፄ ምኒልክ የፈጠሩትን “ኢትዮጵያዊ አንድነት” አፈር ድሜ አስግጦታል፡፡ (ዕድሜ ለኢህአዴግ!) አያሌ በምንም የማይግባቡ “ዘረኞች” የፌስቡክ ትውልድን አፍርቷል- ኢህአዴግ ነፍሴ!
በኢትዮጵያዊነት ላይ ብቻ ሳይሆን በብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ከስምምነት ላይ ያልደረሰ ህዝብም ፈጥሯል፡፡ ይሄ ድል ነው ውድቀት? (“ባንዲራ ጨርቅ ነው” የተባለ ጊዜ ነገር ተበላሸ!) እናላችሁ … ዘንድሮ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ለ10ኛ ጊዜ የሚከበር ቢሆንም አደባባይ ይዘን የምንወጣው ባንዲራ ግን የተደበላለቀ ሆኗል፡፡ የአንድ አገር አይመስልም፡፡ ለደመራ በዓልና ለኦሮሞ የእሬቻ በዓል ህዝቡ ይዞ የወጣውን የባንዲራ ዓይነት መቃኘት ነው፡፡ ግማሹ “ሌጣውን ባንዲራ”፣ ግማሹ ባለ ኮከቡን፣ ግማሹ ደግሞ “የሞ አንበሳን” (የንጉሱን ዘመን) ባንዲራ፣ በእሬቻ በዓል ላይ ደግሞ የሚበዛው የኦነግን ባንዲራ ይዞ ነው የወጣው ተብሏል፡፡ (ብሄራዊውን ሰንደቅ ዓላማ በዓይኔ አየሁ የሚል አታገኙም!) የሃይማኖት ተቋማትም ሳይቀሩ ሌጣውን ባንዲራ ሲያውለበልቡ በደመራ በዓል ላይ ታይተዋል፡፡ (በክልል ከተሞች!) “ጉድ ነው”… እያልኩ አይደለም! (በአሜሪካ ብሄራዊ መዝሙር ሲዘመር በተቃውሞ የሚንበረከኩ፣ “የፖሊስ ጭካኔያዊ ድርጊት ሰለባ ነን ባዮች” ሚሊዬነር ስፖርተኞች፤ እነ ትራምፕን እያንጨረጨሩ ነው!) ግን የእኛና የአሜሪካ ለየቅል ነው፡፡ በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን ባለኮከቡን ሰንደቅ ዓላማ አስከብራለሁ ብሎ፣ ኢህአዴግ ነፍሴ ወደ ጉልበት እንዳይገባ ይጠንቀቅ፡፡ (ጥበብ እንጂ ጉልበት ውጤት የለውም!) ህዝቡ ባንዲራውን ለምን ጠላው? ከመንግስት ተቃውሞ ጋር የተያያዘ ይሆን? ማጥናት፣ መመርመር ይጠይቃል። መፍትሄውን ለማግኘት፡፡ አብላጫው ህዝብ የማይፈልገው ከሆነ ደግሞ በህዝበ ውሳኔ መወሰን ነው፡፡ የቅሬታ ዕዳዎቻችንን እየቀነስን፣ ለቀጣዩ ትውልድ ቀለል ያለ ሸክም፣ ብናስረክበው ደግ ነው፡፡ (ከተቻለ ባዶ ሻጥን!)
እኔ የምለው ግን… ምነው እንዲህ ህብረትና አንድነትን ፈራን? ምነው እንዲህ ፍቅርን ፈራን? (የጤና ምልክት አይደለምና ያስፈራል!) የባለቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን የ“ፍርሃት” ስንኞች ትዝ አሉኝ፡፡
“.. ፈራን ፍቅር ፈራን
የነፍስን አንደበት ዘጋን
ህብረት ፈራን… ፍቅር ፈራን
ልጅነት የለገሰንን
የፍቅር ዓምላክ በጥበቡ… በረቂቅ ያለበሰንን
ህብረት ፈራን … ፍቅር ነሳን…”
አዎ ፈርተናል!! አንክድም!! ለነገሩ ህብረትና አንድነትን ብንፈራ አይፈረድብንም፡፡ ፍቅርንም ብንፈራ አይፈረድብንም፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ብንፈራም ማንም ሊፈርድብን አይችልም፡፡ ኢህአዴግና የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች (ልሂቃንን ጨምሮ!) ለዓመታት የለፉበትን … አበክረው የተጉበትን እኮ ነው  እያፈስን ያለነው! (ትላንት የዘራነውን ዛሬ እያጨድን ነው!) በአገር ውስጥ ኢህአዴግና ተቃዋሚ የጎሳ ፖለቲከኞች፣ ከውጭ “ዘረኛ” የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች፤ ላለፉት 25 ዓመታት፣ በአገሪቱና ህዝቧ ላይ ምንድነው  ሲዘሩ የከረሙት? ፍቅርን? ኢትዮጵያዊነትን? አንድነትን? የአገር ፍቅር ስሜትን? አገር ወዳድነትን? (አንደኛውም መልስ አይደለም!)
ለዓመታት ብሄርተኝነት እንጂ መች ኢትዮጵያዊነት ተሰበከ? የክልሎች አርማ እንጂ መች ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ ደምቆ ተውለበለ? የብሄር ፍቅር እንጂ መች የአገር ፍቅር በውስጣችን ተቀጣጠለ? (ፌስቡክ ምስክር ነው!) በዓመት አንዴ በሚከበረው “የብሄር ብሄረሰቦች ቀን” እንኳን ባለፈው ታሪካችን፣ አንዱ ብሄር ለሌላው ብሄር ያደረገው ቅንጣት በጎ ነገር መች ተጠቅሶ ያውቃል?! (የበዳይነትና የተበዳይነት ስሜት እንጂ!)
እንደውም ህዝባችን ጎሰኛ መሪዎችና ፖለቲከኞች የዘባረቁትን ሁሉ ስለማይሰማ ነው እንጂ (አያምናቸውማ!) እስካሁን ተላልቀን ማንም አይተርፍም ነበር፡፡ ግን ደግሞ ይህቺን አገር ፈጣሪ ይወዳታል፡፡ ህዝቡም ጨዋና አርቆ አሳቢ ነው። ለዚህ ብቻ ነው የተረፍነው፡፡ (ተዓምረኛ አገርና ህዝብ!)
አንዳንዴ ሳስበው፣ የጎሳ ፖለቲከኞች… አገርና ህዝብ የሚባለው ነገር ጨርሶ የሚያስጨንቃቸው አይመስለኝም፡፡ ከዛሬ 100 ዓመት በፊት በአንዱ ብሔር ስም ገዥዎች (ነገስታት) በሌላው ብሄር ላይ የፈፀሙትን ግፍና በደል ከተደበቀበትና  ከተቀበረበት ፈልፍለው በማውጣት፣ ማስታወሻ ሃውልት የሚተክሉት፣ ለምንድን ነው? እውነት ለዚያ ህዝብ (ለአያት ቅድመ አያቱ!) አስበው ነው? ተቆርቁረው? ጨርሶ አይመስለኝም!! የህዝብና ሰላምና ፍቅር ምቾት የማይሰጣቸው፣ “ጭር ሲል አንወድም” ባይ ቂመኞች በመሆናቸው ነው። የህዝብ እልቂት ቁጭ ብለው የሚያልሙ፣ ኢ-ሰብአዊ ፍጡራን!
 ሌላው የማይመቸኝ የኢህአዴግና የጎሳ ፖለቲከኞች “ጨዋታ” ምን መሰላችሁ? ኢትዮጵያን (ጥላ ከለላችንን!) ጨቋኝ አድርገው መሳላቸው ነው። (ጠማማ የፖለቲካ ቁማር!) እናላችሁ … “የምኒልክ ኢትዮጵያ”፣“የጃንሆይ ኢትዮጵያ” ወዘተ የሚል ጨዋታ መሳይ መርዝ የመጣው… በዚህ ፕሮፓጋንዳ ውስጥ ነው፡፡ (ውጤቱ ደሞ ዛሬ ያለንበት ሁኔታ ፈጥሯል!)
እውነት ለመናገር ግን አገር… ህዝቦቿን ለይታና ከፋፍላ በድላ ወይም ጨቁና ታውቃለችን? በዳዮች፤ ገዢዎች እንጂ እንዴት አገር ትበድላለች!? ለዓመታት እስኪሰለችን ድረስ ስንሰማው የከረምነው የፖለቲካ ዲስኩር ግን ይኼ ነው፡፡ የምኒልክም ሆነ የጃንሆይ አሊያም የደርግ ወይም ደግሞ የኢህአዴግ ኢትዮጵያ- የሚባል ነገር የለም (ቁማር ነው!) ኢትዮጵያ አንድ ናት! የሚለያዩት ገዥዎቿ ብቻ ናቸው፡፡ (በእርግጥ ኢትዮጵያና ገዢዎቿ መላዕክና ጭራቅ ማለት ናቸው!) ሁሉም ባይሆኑም!!
እናላችሁ …አገርን ቅዱስም ሰይጣንም የሚያደርጓት መሪዎቿ ናቸው! አገርን ገነትም ሲኦልም የሚያደርጓት ገዥዎቿ ናቸው! አገር ግን ያላትን ሀብትና ፀጋ፣ ለህዝቦቿ ሁሉ “እነሆ በረከት” ከማለት ወደ ኋላ ብላ አታውቅም፡፡ (የትምና መቼም!) አገር ብሄር ብሄረሰቦቿን አበላልጣ የምታይበት ዓይን የላትም፡፡ ለአማራው አድልታ ኦሮሞውን የምትበድልበት… ለትግሬው ወግና ሶማሌውን የምትጨቁንበት … ወዘተ-- ልብም ተፈጥሮም የላትም፡፡ እነ ኢህአዴግ ግን ከእነሱ በፊት ያለችውን ጦቢያ በሆነ ሰበብ ስለማይፈልጓት የፖለቲካ ቁማር ውስጥ ገቡ፡፡ (ግብግቡ ከታሪክ ጋር እኮ ነው!)
እስቲ አንድ ጥያቄ ላንሳ፡፡ በደርግ ዘመን ለተፈጀው ትውልድ፣ (በቀይ ሽብርም በነጭ ሽብርም!) ተጠያቂው ማነው? በጦርነት ለተማገደውስ ወጣት? (ሁሉም ወገን የየራሱ ድርሻ ይኖረዋል!) ግን በዋናነት በሥልጣን ላይ የነበረው አምባገነኑ ሶሻሊስት የደርግ አገዛዝ ተጠያቂ ነው፡፡ እኔ እስከዛሬ ድረስ ለዚህ አሰቃቂ እልቂት፤ ተጠያቂዋ ኢትዮጵያ ናት ያለ፣ የ‹ያ ትውልድ› አባል አልገጠመኝም፡፡ አገር ህዝቦቿን አትፈጅም ወይም አታስፈጅም፡፡ እነ ኢህአዴግና የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች፤ ኢትዮጵያውያን በከንቱ እንደሚወነጅሏት (ያውም እያወቁ) የታወቀ ነው። የትም ዓለም ላይ ቢሆን … ለደጉም ለክፉውም የሚሞገሱትና የሚወቀሱት የዘመኑ ገዥዎች እንጂ አገር በምን ጦሷ! “ኢህአዴግ ነፍሴ” እና የብሄር ፖለቲካ ልሂቃን ግን ለብሄሮች ጭቆናና በደል፤ ኢትዮጵያን ቁጥር 1 ተጠያቂ አድርገው ቁጭ አሉ። ለዚህ ነው ብሔር አቀንቃኞች፤ አንድነት ወይም “እምዬ ኢትዮጵያ” ሲባል የሚያንገሸግሻቸው፡፡ ውጋት የሚይዛቸው፡፡
እኔ የምለው… ኢህአዴግ ሥልጣን ከለቀቀ በኋላ ላከናወናቸው የልማት ሥራዎች፣ ዕውቅናውን መውሰድ ያለበት ማነው? ኢትዮጵያ ናት ወይስ ልማታዊው መንግስት? (ለባለሁለት አሃዝ ዕድገት፣ በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገቡ፣ ዜጎች ኪስ የገባ ባይኖርም!ወዘተ)  በአንፃሩ ደግሞ … ለበደሉስ? ለሰብዓዊ መብት ጥሰቱስ? ለጎሰኝነትና ለጠባብ አመለካከቱስ? በቅጡ ላልተከበሩ የህገ መንግስቱ አንቀፆችስ? በሞሳኞች ለተሞላው ሥርዓትስ? እንኳን ሊፋፋ ኮስምኖ፣ አንድ ሃሙስ ለቀረው ነፃ ፕሬስስ? (ሦስት ፍሬ ለቀሩት የግል ጋዜጦች?) ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበና ጭራሽኑም እየተዘጋ ለመጣው የፖለቲካ ምህዳርስ? እያሽቀለቆለ ለመጣው የትምህርት ሥርኣቱስ? በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ ለሚፈፀመው ወከባና እስርስ? በየጊዜው ለተቃውሞ ወጥተው ህይወታቸውን እንደዘበት ለሚነጠቁ አያሌ የአገሪቱ ዜጎችስ? (“የሰለጠነ ፖሊስና አስለቃሽ ጭስ የለኝም” በሚል ተልካሻ ሰበብ!) በህዝቦች መካከል ለተፈጠረው የዘር ክፍፍልና ጥላቻስ? ሳስቶ ሊበጠስ ለደረሰው የኢትዮጵያዊ አንድነት ስሜትስ? ከአዲሱ ትውልድ ልብና አዕምሮ ውስጥ እንጥፍጣፊ የሰንደቅ ዓላማ ፍቅር ለመጥፋቱስ? ወዘተ… ወዘተ ለሁሉም በደሎችና ጥፋቶች ተጠያቂው፣ ለሩብ ክ/ዘመን ሥልጣንን የሙጥኝ ብሎ የዘለቀው ኢህአዴግ መራሹ፣ ልማታዊ መንግስታችን እንጂ ጨርሶ እምዬ ኢትዮጵያ ልትሆን አትችልም!! እናም ኢትዮጵያን በዳይ አድርጎ መኮነን የተጣመመ የፖለቲካ ቁማር እንጂ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡
 ምን መሰላችሁ… የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ለማክበርም ሆነ ለማስከበር አንዲት ኢትዮጵያ ታስፈልገናለች፡፡ አንዲት ጠንካራ ኢትዮጵያ! አንዲት የጋራ አገር! ዛሬ አገርነታቸውን እንደ ዘበት ያጡትን የዓለም አገራት… ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ የመን፣ ሌላም ሌላም ተመልከቱ፡፡ ያሳዝናሉ፡፡ ይሄን የምንሞግተውም እኮ ኢትዮጵያ የተባለች አገር በመኖሯ ነው፡፡ አንዱ ክልል የሌላውን ክልል ህዝብ ማፈናቀል ከጀመረ ግን ወደነዚያ የተበታተኑ አገራት በፍጥነት እየገሰገስን ነው፡፡ (ፈጣሪ ይጠብቀን!)
ለማንኛውም ግን ስለ ብሄር ብሄረሰቦች ወይም ህዝቦች የሚሰማኝንና ሃሳቤን የገለጠልኝን አንዲት አንቀፅ፣ ከአንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ (ነፍስ ይማር!) “በዕዳ የተያዘ ሕዝብ” መጽሐፍ ላይ እነሆ፡-
“…የኢትዮጵያውያን ደም የተከበረ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ክቡር ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ብሔረሰቦችዋ በሙሉ ኃይልዋና ክብርዋ ናቸው፡፡ በአዲሱ ዓለም የለውጥ (የአብዮት) ሱፐርሶኒክና ሚሳይል ናቸው። ሌላ አገር የሌለው ሀብትና አለኝታ ናቸው…።” እውነቱ ይኸው ነው!! ኢትዮጵያና ብሄር ብሄረሰቦቿን መነጣጠል አይቻልም!!
በመጨረሻም እምዬ ኢትዮጵያን በቴዲ አፍሮ ዜማ እናወድሳትና ወጌን ልቋጭ፡፡ (በዚያውም “የቴዲ አፍሮ ኢትዮጵያ” የሚሏት ምን እንደምትመስል፣ እግረመንገዳችንን እንያት - በግጥምና በዜማ!!)
እነሆ “ኢትዮጵያ” ከሚለው ዜማው ጥቂት ስንኞች፡-
“… እንኳን ሰማይ ላይ ባንዲራሽን አይቶ
ስምሽ ሲጠራ ማን ዝም ይላል ሰምቶ
እንኳን ሰማይ ላይ ባንዲራሽን አይቶ
ኢትዮጵያ ሲባል ማን ዝም ይላል ሰምቶ ..
በሰማዩ ላይ ሲታይ ቀለም
የእሷ ነው እንጂ ሌላ አይደለም
የመጪው ዘመን ፊት ናት መሪ
ዛሬ ዓለም ቢላት ኋላ ቀሪ
ተዉኝ ይውጣልኝ ልጥራት ደጋግሜ
ኢትዮጵያ ማለት ለእኔ አይደል ወይ ስሜ!...”
ይኼኔ ነው “ጥበብ ትብራልህ” የሚል ምርቃት የሚያስፈልገው - ለጦቢያ ፍቅርና ክብር ላቀነቀነው ቴዲ አፍሮ!!
ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!  
ህዝቦቿም በብልፅግና በረከት ይንበሽበሹ!

Read 8390 times