Saturday, 14 October 2017 15:46

ኢትዮጵያን የሚያድናት ፍቅርና አንድነት ብቻ ነው!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(36 votes)

 የዘር ከበሮ መደለቅ ተያይዞ መጥፋትን ያስከትላል
                              

    የዛሬ የፖለቲካ ወጌን የምጀምረው ባለፈው ረቡዕ ለንባብ በበቃው “ሪፖርተር” ጋዜጣ ላይ “ለፖለቲካዊ ጉዳዮች አነስተኛ ትኩረት የሰጠው የፕሬዚዳንቱ ንግግር” በሚል ከሰፈረው ወቅታዊ ዘገባ፤ ትኩረቴን የሳቡትን አንድ ሁለት አንቀፆች መዝዤ፣ ለእናንተ በማካፈል ነው፡፡ (እንድትገረሙ ወይም እንድትደመሙ!) በነገራችን ላይ ልማታዊ መንግስታችን፣ ሁሌም ትኩረቱ ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ይልቅ ‹ልማታዊ› ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ለምን? የሚቀለው ልማት ይመስላል፡፡ የመብትና የዲሞክራሲ ጉዳይ ለኢህአዴግ ሁሌም ዳገት ነው፡፡ (ማን ነበር ኢህአዴግ የነጻነት ታጋይ እንጂ የዲሞክራሲ ፓርቲ አይደለም ያለው?) ከ27 ዓመት የሥልጣን ዘመንና ህዝብ የመምራት ልምድና ተሞክሮ በኋላ ለፈተና ቢቀመጥ ምን እንደሚያገኝ እስቲ ገምቱ? በአጠቃላይ በፖለቲካ ጉዳይ ማለቴ ነው፡፡
በእኔ በኩል፤ በሰብአዊ መብት አከባበር፣ በዲሞክራሲና በዜጎች ነጻነት፣ በፖለቲካ መብቶች፣ ሃሳብን በነጻነት በመግለጽ፣ በሚዲያ ነጻነት፣ በመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ወዘተ-- ውጤት ይሰጠው ቢባል፣ “D” እና “F” መጠጣቱ አይቀርም። (ሰነፍ ተማሪ ነው!!) ባለፉት 27 ዓመታት እንደተገመገመው፤ ኢህአዴግ ልማታዊ መንግስት እንጂ ዲሞክራሲያዊ መንግስት አይደለም! (ግን እኮ ሃጢያት አይደለም፤አለመሰጠት ነው!) በእርግጥ እነ ህውኃት፣ የደርግን አምባገነን መንግስት ለመገርሰስ ወደ ትጥቅ ትግል ሲገቡ፣ የልማት ጥማት አንገብግቧቸው አልነበረም፡፡ የነጻነትና ዲሞክራሲ ረሃብ እንጂ! ቢያንስ ከደርግ ጭቆናና አምባገነንነት መላቀቅ ዋነኛ ዓላማቸው እንደነበር የሚጠራጠር አይኖርም፡፡ ከዚያስ? የዲሞክራሲ ሥርዓት ማስፈን ይፈልጉ ነበር? (መልሱን የሚያውቀው ኢህአዴግ ብቻ ነው!)
እናላችሁ --- ኢህአዴግ ነፍሴ ለኢኮኖሚ ጉዳይ ትኩረት ቢሰጥ ልንፈርድበት አይገባም። ልማት፣ ኮንስትራክሽን፣ ግድብ ግንባታ ወዘተ -- ኮከቡ ናቸው፡፡ የዲሞክራሲ መሠረተ ልማት ግን ተሰጥኦው አይደለም፡፡ ለዚህ ነው “ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት” እያለ እስኪታክተን የሚደሰኩርልን ኢህአዴግ፤ አንዴም እንኳን ዲሞክራሲያችን በስንት ፐርሰንት እንዳደገ ነግሮን የማያውቀው። ለነገሩ ኢህአዴግም ሆነ አይኤምኤፍ በሽንጽ ርሸንጽ ደግ ጨርሶ አያውቁትም፡፡ እኛ ዜጎቹ ግን አሳምረን እናውቀዋለን፡፡ እናላችሁ … ባለፉት 27 ዓመታት፣ የዲሞክራሲያችን አሃዛዊ ዕድገት ኔጌቲቭ ነው!
ከትልቅ ይቅርታ ጋር ወደ ሪፖርተር  ጋዜጣ ዘገባ ልመልሳችሁ፡ እንዲህ ይላል፡-
“የአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካላት የሆኑት ሁለቱ ምክር ቤቶች ዓመታዊ ስራቸውን የሚጀምሩት፣ የአገሪቱ ርዕሰ ብሄር የሚያደርጉትን ንግግር በማዳመጥ ነው፣ የፕሬዚዳንቱን ንግግር ከማዳመጣቸው አስቀድሞ የአገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር ከመቀመጫቸው በመነሳት ይዘምራሉ፡፡”
ማንም አገሩን የሚወድ ዜጋ ሁሉ ከላይ በቀረበው ዘገባ ቢፈነድቅ አይገርምም፡፡ (ግን “አገሩን የሚወድ ዜጋ” ምን ማለት ነው?) እናም … ይሄን አንቀፅ ሳነብ ሁለመናዬን የደስታ ስሜት ወርሮኝ ነበር። ለምን ብትሉኝ ግን … እርግጡን አላውቀውም፡፡ የአገሪቱ ባለስልጣናት፤ ከመቀመጫቸው ተነስተው፣ የአገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር እንደሚዘምሩ ስለተነገረኝ ይሆን? ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ሌላ ያላወቅሁት ስሜት!! ብቻ የደስታ ስሜት ወርሮኛል። ክፋቱ ግን ደስታዬ የሚቀጥለውን የጋዜጣውን አንቀፅ መሻገር አልቻለም፡፡ ለካስ አብዛኞቹ የም/ቤቶቹ አባላት (ባለስልጣናት) የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ስንኞችን አያውቋቸውም፡፡ (“የአገር ፍቅር ግሽበት”! እንበለው ይሆን?!)
“… የሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት ከሆኑት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና በአጠቃላይ ከ600 በላይ ከሚሆኑት የሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት፣ አብዛኞቹ የአገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር ስንኞች አያውቋቸውም፡፡ በመሆኑም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፅህፈት ቤት፤ የአገሪቱ ብሔራዊ መዝሙር ግጥም የታተሙባቸው ወረቀቶችን ለሁለቱም ምክር ቤቶች አባላት ለማደል ተገዷል፡፡” ይላል- የ“ሪፖርተር” ዘገባ፡፡
ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል? ስንት የፖለቲካ ዲስኩር የሚያዥጎደጉዱ የም/ቤት አባላትና የመንግስት ባለስልጣናት፣ እንዴት የሚመሯትን አገር ብሄራዊ መዝሙር ስንኞች አያውቋቸውም?! (አገራቸውን አይወዷትም ማለት ነው?) ግራ ገብቶኝ እኮ ነው፡፡ ወይስ በኢህአዴግ ዘመን ከወጣው ብሄራዊ መዝሙር ጋርም “የማይታረቅ ቅራኔ” አላቸው? (በኢህአዴግ ዝነኛ ቋንቋ መጠቀሜ ነው!) ወይስ ደግሞ እኛ የማናውቀው ሌላ የየግላቸው መዝሙር ይኖራቸው ይሆን? (የየግላቸው ፀሎት እንደማለት!)
በነገራችን ላይ… ሰሞኑን ኢቢሲ “ወቸ ጉድ” በሚል ቃና የዘገበውን አንድ ዜና ሰምታችሁልኛል? የናይጄሪያ የአንደኛ ደረጃ መምህራን፤ የተማሪዎቻቸውን ፈተና ተፈትነው መውደቃቸው ነው ኢቢሲ ነው ኮራ ብሎ የነገረን፡፡ (“የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች” አሉ!) የሚገርመው ታዲያ  በቅርቡ በአገራችን በተደረገ አንድ ጥናት፣ የተወሰኑ የኮሌጅ ምሩቃን፣ የ8ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ወስደው መውደቃቸውን ጠቁሟል፡፡ (ኢቢሲ ግን የናይጄሪያው ወሬ ሲደርሰው የአገሩን አልሰማም!) እናላችሁ … የናይጄሪያ መንግስት በፈተናው የወደቁትን 21 ሺህ መምህራን አባርሮ፣ በሌሎች እንደሚተካ ማስታወቁም ተዘግቧል፡፡
እንደገና ወደጀመርነው ወግ ልመልሳችሁ፡፡ ለመሆኑ የብሄራዊ መዝሙር ዓላማ ምንድን ነው?
“የአንድ አገር ብሄራዊ መዝሙር አላማ በህዝቦች ላይ የብሄራዊ ስሜትን መፍጠር፣ ታማኝነት፣ አንድነትን፣ የጋራ ሰብዕናን፣ ሰላምንና በአገር መኩራትን በሕዝቦች ውስጥ ለማስረፅ ወደር የሌለው መሳሪያ እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡” ይላል- ሪፖርተር፡፡
ምናልባት … እኒህ የኢህአዴግ ሃላፊዎች፤ ጥናቶቹ “የኒዮሊበራል ጥናቶች” ናቸው በሚል ሊያጣጥሉት ቢሞክሩ እንኳን ጋዜጣው፣ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ አራት የተደነገገውንም እንዲህ ይጠቅሳል፡-
“የኢትዮጵያ ብሄራዊ መዝሙር የሕገ መንግስቱን ዓላማዎችና የኢትዮጵያ ህዝቦች በዴሞክራሲ ሥርአት አብረው ለመኖር ያላቸውን እምነት እንዲሁም የወደፊት የጋራ ዕድላቸውን የሚያንፀባርቅ ሆኖ በህግ ይወሰናል”
የጋዜጣው ዘገባ፤ “የኢትዮጵያ ብሄራዊ መዝሙር የአገሪቱ ሕገ መንግስት ጭማቂ ነው፡፡” ሲልም አሳምሮ ይገልፀዋል፡፡ በነገራችን ላይ ባንዲራንም ሆነ ብሄራዊ መዝሙርን አክብረው  ማስከበር ያለባቸው እነዚህ የህዝብ ተወካዮች ወይም የአገር መሪዎች ናቸው፡፡ (አርበኞችማ እንደ ድሮው የሉንም!) ምናልባት ግጥሙ የተፃፈበት ቋንቋ ጠጥሮባቸው ከሆነም ቋንቋው ቀለል እንዲልላቸው ፊርማ አሰባስበው ለሚመለከተው አካል አቤት ማለት ይገባቸው ይሆናል፡፡ መዘመር ግን እንጀራቸው ነው። (ማን ነበር “ንጉስነት እንጀራዬ ነው” ያለው?)
እኔ የምለው ግን… ህዝቡ በብሄራዊ መዝሙሩ ጉዳይ መግባባት ላይ ደርሷል እንዴ? ድንገት ደግሞ የጃንሆይን ብሄራዊ መዝሙር እንዳይዘምር ፈርቼ እኮ ነው!! ምን ናፈቀኝ መሰላችሁ? እንደ አገር፣  በጋራ የምንስማማበት አንድ ጉዳይ! ይሄ “የኢትዮጵያ ነው” ሲባል ሁሉም በደስታ የሚያጨበጭብበት! ሁሉም በሆታ ስምምነቱን የሚገልፅበት! (ነገር የተበላሸው ግን መቼ መሰላችሁ? ሁሉንም ነገር ፖለቲካ ማድረግ የጀመርን ጊዜ!) ክፉ አባዜ!!
ግን ግን… መቼ ነው ስለ አገር ጉዳይ መናገር ሲጀምሩ እንኳን ዜጎቻቸውን የሌሎችንም አገር ሰዎች (ባዕድ ጭምር) ስሜትና ቀልብ ሰቅዘው የሚይዙ ፖለቲከኞች (የህዝብ ተወካዮች) የምናፈራው? መቼ ነው የአገር ፍቅር ስሜታቸው  የሚጋባ መሪዎች የሚኖሩን? (ኢህአዴግ ነፍሴ መቼም በዚህ አልታደለም!)
በነገራችን ላይ ስለ አገር ፍቅር ስሜት ወይም ስለ አገር ወዳድነት ከማንሳታችን በፊት ከእውነት ጋር እርቅ መፍጠር ሳይኖርብን አይቀርም፡፡ ከሃቅ ጋር!! (እውነት እዚህ አገር በአፍጢሟ ተደፍታለች!) ለምን መሰላችሁ? ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት … ሁሉ ነገራችን በፖለቲካ ግራሶ ተለውሷል፡፡ እውነት በፖለቲካ ተለውጣለች፡፡ ዕድሜ ለአውራው ፓርቲ! ኑሮአችን ሳይቀር ፖለቲካ ሆኗል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት-ፖለቲካ! ድርቅ-ፖለቲካ! የዶላር እጥረት- ፖለቲካ! የህዳሴ ግድብ - ፖለቲካ! የባቡር ፕሮጀክት-ፖለቲካ! የትምህርት ፖሊሲ-ፖለቲካ! የአካባቢ ጥበቃ- ፖለቲካ! ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ-ፖለቲካ! ኢትዮጵያዊ አንድነት-ፖለቲካ! የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ- ፖለቲካ! ሥራ አጥነት-ፖለቲካ! የቱሪስቶች ቁጥር መቀነስም ሆነ መጨመርም-ፖለቲካ!... ዕድሜ ለኢህአዴግ ነፍሴና ለዳያስፖራ ፖለቲከኞች … በህይወት የመቆየት የዕድሜ ጣራ (Life expextancy) ሳይቀር ፖለቲካ ሆኗል፡፡ ይሄ ማለት ምን ማለት መሰላችሁ? ፖለቲካ ውሸት ወይም ቅጥፈት! ሆኖላችኋል፡፡
እናላችሁ … ስለ አገር ፍቅር ስሜትም ይሁን ስለ ኢትዮጵያዊ አንድነት ማውራት ከመጀመራችን በፊት ፖለቲካን በእውነት መለወጥ አለብን፡፡ ፓርቲና ፖለቲካ ስምሙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ፓርቲና ፕሮፓጋንዳ ስምሙ እንደሆኑት፡፡ አገርና ፖለቲካ ጨርሶ አይስማሙም፡፡ አገርና ፕሮፓጋንዳም እንዲሁ፡፡ ህዝብ ከዚህ ምን አተረፈ ብትሉኝ … የጥላቻ ፖለቲካ ብቻ ነው! ህዝብ ያተረፈው በዘር መከፋፈልና መቧደን ነው! አገር ከዚህ ያተረፈችው ምን መሰላችሁ … እርስ በርስ የማይተማመኑ፣ መሪዎቻቸውንም የማያምኑ ህዝቦችን ነው!! በዚህ ፖለቲካ እውነትን ተክቶ በሚሰራበት ዘመን፣ የሃይማኖት መሪዎች እንኳን ሳይቀሩ ፈጣሪን ትተው መንግስትን፣ ሃቅን ትተው ፖለቲካን ሲሰብኩ ሰምተናል (ያውም በካድሬ ቋንቋ!) የሚፈራና የሚከበር ሽማግሌ በአገር ሰማይ ላይ ያጣነውም እኮ ለዚህ ነው፡፡ (ሃቅ በሌለበት የአገር ሽማግሌ አይኖርም!)
በመጨረሻ የአገራችንን አንገብጋቢ ወቅታዊ ጉዳይ እናንሳ፡፡ የዘር ከበሮ መደለቅ! እናላችሁ --- ጉዳዩን በመሸሽ ወይም ዳር ዳር በማለት ብዙም የምናተርፈው ነገር አይኖርም፡፡ እንደውም ወደ ጥፋት አቅጣጫ የምናደርገውን ጉዞ ያፋጥነዋል። በኦሮሚያ - ሶማሌ ክልል አዋሳኝ የተፈጠረውን ግጭት በአፋጣኝ ምላሽ ባለማስጠታችን የደረሰውን ሰብአዊ ውድመት አስቡት፡፡ ከሞት የተረፉት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለው፣ በድንኳንና በመጋዘን ተጠልለዋል። ዕድሜ ዘመናቸውን ያፈሩትን ሃብትና ንብረት አጥተዋል፡፡
አሳዛኝ የታሪካችን አካል ነው፡፡ ለ26 ዓመታት የዘመርንለት ፌደራሊዝም ለእንዲህ ዓይነቱ ሰው ሰራሽ ችግር መፍትሄ ከሌለው፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት እንዳሉት አፍ ሞልቶ፣ ፌደራሊዝሙ እያበበ ነው ማለት ያዳግታል፡፡ አሁንም መንግስት ነገሮችን በጥንቃቄ ካልያዘ፣ ያስፈራል፡፡ የዘር ከበሮ መደለቅ ተያይዞ መጥፋት ያስከትላል፡፡ ኢትዮጵያ የምትድነው በዚህ ወይም በዚያኛው የሥርዓት ዓይነት ሳይሆን በአንድነትና በፍቅር ብቻ ነው!!
 ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!! ህዝቦቿንም በፍቅር ይሙላቸው!!

Read 8894 times