Saturday, 14 April 2012 10:42

አውሮፓ አደጋ ላይ ናት!

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

ራሳቸውን የሚያጠፉ ግሪካውያን ቁጥር 18 በመቶ ጨምሯል

አውሮፓ የአለማችን ቀደምት ስልጣኔ ከፈለቀባቸው አህጉራት አንዷ ናት፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ ዝናቸው ገኖ የሚተረክላቸውና ለአለም ከፍተኛ የእውቀትና የስልጣኔ ብርሀን ያበሩ ፈላስፎችን ያበረከተች አህጉር ናት፡፡ አውሮፓ እንኳን የራሷ ዜጐች ይቅርና በስደት የሄዱባት ሠዎችም ቢሆኑ ስለ እለት ጉርሳቸውና የአመት ልብሳቸው ጨርሰው የማይጨነቁባት፤ በእድገትና ብልጽግና የታደለች፤ በተትረፈረፈ ሀብት የተባረከች አህጉር ናት፡፡ እነሆ አውሮፓ እድገት ብልጽግናና የላቀ ሀብትን አላማውና ግቡ ባደረገ፤ ሠርቶ በማይጠግብ ታታሪ ሠራተኛ ህዝብ የታደለች አህጉር ናት ወዘተ … እያሉ ቢነግሯችሁ ሊሠለቻችሁ ይችላል፡፡

አውሮፓውያንም ቢሆኑ ይሄንኑ እየሰሙና ዓለም እስካለች ድረስ ይሄ ሃቅ ሳይዛባ እንደሚዘልቅ ከልባቸው እያመኑ ነው የኖሩት፡፡ እድገትና ብልጽግና ለአውሮፓውያን ገና እንደተወለዱ የሚጐናፀፉት የመወለድ መብትና ፀጋቸው ነው፡፡ ለአውሮፓውያን ችጋርና በሽታ፣ የአፍሪካ አህጉር ተለይቶ የተሠጣት የአርባ ቀን እድሏ እንጂ እነሱን መቼም ቢሆን ሊነካቸው እንደማይችልም አጥብቀው ያምናሉ፡፡

ስለዚህ ዋነኛው ትኩረታቸው መቼም ቢሆን ከቶም ሊነካቸው ስለማይችለው ችጋርና በሽታ መጨነቅ ሳይሆን፣ የተጐናፀፉትን የእድገትና የብልጽግናን ፀጋ በተቻላቸው መጠን በእንዴት ያለ አኳኋን መጠቀምና እያንዳንዷን የህይወታቸውን ቀን በደስታና በተድላ ማሳለፍ እንደሚችሉ ማሰብ ነበር፡፡

በዚህ የተነሳም እለት ተእለት አገራቸውን ከገነቡበባትና በመግቢያችን ላይ ለተዘረዘሩት ገድሎች ካበቁበት ትግል እያፈገፈጉ፣ የተለየ የስራና የሀብት አጠቃቀም ባህል ባለቤት እየሆኑ መጡ፡፡ ከማምረት ይልቅ የተመረተውን መጠቀምን ብቻ መረጡ፡፡ እንደ በፊቱ በማይናወጥ ቁርጠኝነትና ትጋት ከመስራት ይልቅ የግል መወሠኛ ምክር ቤቶችና ፓርላማዎቻቸው ውስጥ ሳምንታዊ የስራ ሠአትንና የጡረታ መውጫ እድሜ ቅነሳን ዋነኛ የህግና የፖሊሲ የክርክር አጀንዳዎት አደረጓቸው፡፡

መንግስቶቻቸውም ለዜጐቻቸው ከሚያቀርቡት እጅግ ብዙ የመንግስት ድጐማ የተደረገበት አገልግሎቶች በተጨማሪ፣ ይህን የህዝብ ጥያቄ በመቀበል ሳምንታዊ የስራ ሰአትንና የጡረታ መውጫ እድሜን በሠአታትና አመታት እንዲቀንስ አደረጉ፡፡ በእነዚህ ድርጊቶችና እርምጃዎች ብቻ ሳይወሠንም በካዝናው ያለውን ጥሪት ብቻ ሳይሆን ስለ መጭው ጊዜ ጨርሶ ሳይጨነቅና ሀሳቡን ሁሉ ጣል አድርጐ ከሌሎችም በከፍተኛ መጠን እየተበደረ መጠቀሙን ለአመታት ዋና ጉዳዬ ብሎ ተያያዘው፡፡ የተሻለና ተጨማሪ ድጐማ ለህዝቡ የሚያቀርብ፣ በብድርም ሆነ በፈለገው ዘዴ የተለያዩ የልማት ፕሮግራሞችን ወዘተ በመንደፍ፣ አስፈጽማለሁ ማለት በፖለቲከኞች ዘንድ ዋነኛ የምርጫ ፉክክር አጀንዳዎች ሆነው ብቅ አሉ፡፡ እንዲህ ያለው ቅጥ ያጣና የተበላሸ አሠራር እየተለመደ መምጣቱ ሊፈጥር የሚችለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለማስረዳትና ለማስጠንቀቅ መሞከር የወንጀል ያህል መቆጠር ጀመረ፡፡

እንዲህ የሚያደርጉ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ዋነኛ የህዝብ ጠላቶች ተቆጠሩ፡፡

የአውሮፓ ህዝብ ከማምረት ይልቅ ጥቂቶች ያመረቱትን በመጠቀም መደሰትና መዝናናትን በመምረጥ እንደልባቸው ሲሽሞነሞኑ፣ መንግስቶቻቸውም ያለ የሌለ ጥሪታቸውን አሟጠው በብድር ያሻቸውን ሲያደርጉ፣ ሀገሮቻቸው ግን ኢትዮጵያውያን “ውሀ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” እንደሚሉት ዓይነት ቀውስ ውስጥ መዘፈቅ ላይ ነበሩ፡፡

አውሮፓውያን ቀላል የመውጫ ዘዴ ወደሌለው ጥልቅ የኢኮኖሚ አዘቅት ውስጥ መዘፈቃቸውን የተረዱት እጅግ ዘግይተው፣ ለዚያውም ደግሞ ሳይታጠቁ በድንገት ነበር፡፡ ያኔ የአዘቅቱን የጥልቀት መጠን ለመገመት አንገታቸውን አስግገው ኢኮኖሚያቸውን አጐንብሠው መመልከት ሲጀምሩ፣ በአይናቸው ማየት የቻሉት የአዘቅቱን ዲካ አልነበረም፡፡ ለምን ቢባል? መልሱ ቀላልና አጭር ነው፡፡ የገቡበት የኢኮኖሚ አዘቅት ዲካው በቀላሉ የማይታይ እጅግ ጥልቅ ነበርና ነው፡፡ በጆሮዋቸው ግን አንድ ሙዚቃ መስማት ችለዋል፡፡ የሀገራቸው ኢኮኖሚ ከገባበት አዘቅት ስር ሆኖ ለህዝቡ በዱብ እዳነት መከሠቱን “እነማን ናቸው እኔን እሚንቁ? ደረስኩባቸው ሳይታጠቁ” የሚለውን የጀብዱ ዘፈን በከፍተኛ ድምጽ በማዜም፣ ድሉን ለራሱ እያከበረ ነበር፡፡

ዛሬ ይህን እውነታ አውሮፓውያን በምንም አይነት ሁኔታም ቢሆን ሊክዱና ሊያስተባብሉ የሚችሉበት አንደበት የላቸውም፡፡ የኢኮኖሚው ድቀት የያዛቸው ጨርሰው ባላሰቡትና ይሆናል ብለው ባልገመቱት ሁኔታ ነበር፡፡

አውሮፓውያን እስከ አለም ፍፃሜ ድረስም ቢሆን እንኳን በሙሉ አይኑ ቀርቶ በሾርኒም ቢሆን ሊያየን ይችላል ብለው ጨርሰው የማይገምቱትን ድህነት፣ ነፍስ ዘርቶ አካል አበጅቶ ቆሞ ድንገት ያገኙት፣ ረጅሙ የደስታና የፌሽታ ሌሊት አልፎ የጥዋቷን ጀንበር ለማየት ገና የቤታቸውን ደጃፍ እንደከፈቱት ነበር፡፡ ያኔም ቢሆን በቀላሉ እንደሚያሸንፉት ገምተው፣ በግልምጫ አቅምሠውት ደጃፋቸውን በመዝጋት በመጣበት እግሩ እንዲመለስ ለማድረግ ሞክረው ነበር፡፡ ይህንን ሲያደርጉ እነሱ ያልተገነዘቡት ጉዳይ ግን ደጃፋቸው ላይ የቆመው ድህነት፣ እንዲህ በዋዛና በግልምጫ ብቻ የሚመለስ አለመሆኑን ነበር፡፡ በሁዋላም በተለያየ ዘዴ ከመንግስቶቻቸው ጋር በመሆን ከወዲያ ወዲህ ቢፍጨረጨሩም፣ እያደባ በቀስታ ከመጣው ድህነት አይን ብቻ ሳይሆን ጠንካራ እጅም መገላገል ሳይቻላቸው ቀረ፡፡

ኢትዮጵያውን እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥማቸው ጉዳዩን በደንብ የሚገልፁበት አንድ አባባል አላቸው፡፡ ሰው የዘራውን ያህል ያጭዳል ይላሉ፡፡ አውሮፓውያን ከእነ መንግስቶቻቸው አሁን ያጨዱት ለአመታት ሲዘሩት የባጁትን ነው፡፡ አውሮፓ አሁን የእድገት፣ የብልጽግናና የተድላ አህጉርነቷ ቀርቷል፡፡ በፈንታው ችግር፣ ድህነት ግራ መጋባትና ተስፋ መቁረጥ ተረክቧታል፡፡ የእነዚህ ችግሮች ጥፍራም እጆች ከሁሉም በከፋ መልኩ ጨምድዶ በመያዝ ስንዝር አላላውስ ያላት ደግሞ ግሪክን ነው፡፡ ግሪክን አሁን ባለችበት ሁኔታ ላይ ቆሞ “ሀገሪቱ እኮ አቻ የለሽ የስልጣኔና የእውቀት ምንጭ ናት” በማለት የሚናገር ሠው የሚያገኘው መልስ፤ ያ ያለፈና ያረጀ ታሪክ ነው፤ የዛሬዋ ግሪክ በከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ የተያዘችና ህዝቧም በደረሠበት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት የተነሳ ከድህነት ጋር ግብግብ የገጠመ ነው የሚል ነው፡፡ የግሪክ ህዝብ ከግራ ከቀኝ ሰቅዞ ከያዘው የኢኮኖሚ አዘቅትና ድህነት የሚታደገው አካል  ፍለጋ የእውር ድንብሩን መባዘን ከጀመረ ድፍን ሶስት አመታትን አሳልፏል፡፡ የመንግስታቸውም ታሪክ ከህዝቡ ታሪክ የተለየ አይደለም፡፡ ልዩነት አለው ከተባለ “ለዚህ ውድቀት ያበቃህን አንተ ነህ” በሚል በገዛ ህዝቡ ለማያቋርጥ ከፍተኛ ውግዘት መዳረጉ ብቻ ነው፡፡ የግሪክ መንግስት ከዚህ እጅግ አስጨናቂ የኢኮኖሚ ቀውስ ለመውጣትና በመጠኑም ለማገገም የሚረዳ ከፍተኛ የነፍስ አውጪኝ ብድር፣ አባል ከሆነችበት ከአውሮፓ ህብረት በተለይ ደግሞ ከጀርመን ለማግኘት ቢችልም፣ ከችግሩ ጥልቀት አንፃር የተገኘው ብድር እዚህ ግባ የማይባል ሆኖበታል፡፡

ከሌሎች አበዳሪ ሀገራትና የገንዘብ ተቋማት ተጨማሪ ብድር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ግሪክን ለተጨማሪ ሀፍረት ዳርጓታል፡፡ እናበድራለን የሚሉ ሀገራት ለብድራቸው ማስያዣ እንድታቀርብ የሚጠይቋት ነገሮች፣ ግሪክን ለተለያዩ መራራ ቀልዶች መነሻ አድርጓታል፡፡ እርግጠኛነቱን ግሪክ ራሷ ባታረጋግጠውም ፊንላንድ ብድር ለመስጠት ግሪክ ታሪካዊውን ጥንታዊ ቅርሷን አክሮፖሊሲን በማያዣነት እንድታቀርብላት መጠየቋና ይህም የግሪካውያንን ብሔራዊ ቅስም እንደሠበረው በሠፊው ተወርቷል፡፡

ይህ ሁሉ ፈተናና ውርደት በቂ ያልሆነ ያህል “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ በአበዳሪ ሀገራትና ተቋማት፣ በተግባር ላይ እንድታውለው የተጣለባት በርካታ የበጀት ቅነሳ ቅድመ ሁኔታዎች የግሪካውያንን የኢኮኖሚ ፈተና ጨርሶ ሊቋቋሙት የማይችሉበት ደረጃ ላይ አድርሶታል፡፡

ግሪካውያን መንግስታቸው የሚወስዳቸውን የበጀት ቅነሳ እርምጃዎች በመቃወም በተደጋጋሚ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞአቸውን ገልፀዋል፡፡ ይህ ግን ከፖሊስ ቆመጥና የአድማ መበተኛ ውሀ በቀር ያተረፈላቸው ነገር የለም፡፡ እለት ተእለት ከስራ መቀነስ፣ የግብር መጨመር፣ የደመወዝና የጡረታ አበል ቅነሳን ማንም ሊታደጋቸው አልቻለም፡፡

ከስራ የተፈናቀሉ ግሪካውያን የእለት ኑሮአቸውን መግፋት አቅቷቸው ህይወታቸውን ለማቆየት በዘመድ አዝማዶቻቸው ቤት ተጠልለዋል፡፡ ችግሩ በእጅጉ የባሠባቸውና ክፉኛ ያደቀቃቸው፣ በተለይ በጡረታ አበል የሚተዳደሩትን ነው፡፡ ለእነዚህ ሠዎች በቀን ሶስቴ መመገብ የምር ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡ ብዙዎች ይህን ፈተና ለመቋቋም በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች ውስጥ የተሻለ ምግብ መፈለግን ዋነኛ ስራቸዉ አድርገውታል፡፡  ይህ ሁኔታ በርካታ ግሪካውያንን ለከፍተኛ የስነ ልቦና ቀውስ ዳርጓቸዋል፡፡ ነገርዬውን ጨርሶ ለመቋቋም ያልቻሉት ደግሞ ራሳቸውን በራሳቸው በማጥፋት እፎይ ማለትን መርጠዋል፡፡

እናም ለግሪካውያን አሁን አሁን ራስን ማጥፋት ተራና የተለመደ ክስተት ሆኖአል፡፡ ራሳቸውን የሚገድሉ ግሪካውያን ቁጥርም እ.ኤ.አ በ2010 ዓ.ም ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በ18 በመቶ ጨምሯል፡፡ በአቴንስ ከተማ ብቻ በ25 በመቶ ማሻቀቡም ታውቋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ግሪካውያን በየአደባባዩና በሀገራቸው ፓርላማ ህንፃ ደጃፍ ላይ ተኮልኩለው መንግስታቸውን ሲያወግዙና ሲራገሙ ውለዋል፡፡ በዚህም እለት እንደተለመደው ከፖሊሲ ጋር ተጋጭተዋል፡፡ ይህንን ተቃውሞአቸውን የቀሠቀሠው፣ መንግስታቸው የወሠደው አዲስ የበጀት ቅነሳ እርምጃ ሳይሆን አንድ የ70 አመት አዛውንት ጡረተኛ የደረሠበትን የኑሮ ቀውስና ችጋር በሽማግሌ አቅሙ መቋቋም ባለመቻሉና ራሱን በመግደሉ ነበር፡፡ ዲሚትሪ ክሪስቶላስ የኬሚስትሪ ባለሙያ ነበር፡፡ ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ አባት የነበረው ዲሚትሪ፤ ፋርማሲውን የሸጠው በ1994 ዓ.ም ነበር፡፡ በሚያገኘው የጡረታ በአል ኑሮውን ሲገፋ የነበረው ዲሚትሪ፤ ግሪክ በገጠማት የኢኮኖሚ አዘቅት ሳቢያ በወሠደችው ከፍተኛ የበጀት ቅነሳ እርምጃ የጡረታ አበሉ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀነሰበት፡፡ በተረፈው ገንዘብ እንደምንም ብሎ የእሱንና የቤተሠቡን ኑሮ ለመግፋት ቢታገልም፣ ችጋሩን ለመቋቋም የሚበቃ አቅም ማግኘት ግን አልቻለም፡፡ ነገሩ ከአቅሙ በላይ ሆኖ ቁራሽ ዳቦ ከምግብ ጠረጴዛው ላይ ለእሱና ለቤተሠቡ ማስቀመጥ ሲያቅተው፣ የሽማግሌ ሠውነቱን እየጐተተ በጠዋት ከቤቱ ወጣና ወደ ዋናው የአቴንስ ከተማ አደባባይ ተጓዘ፡፡ እዚያ እንደደረሠም የያዘውን ሽጉጥ አውጥቶ ራሱን ገደለ፡፡

ምስኪኑ ዲሚትሪ ክሪስቶላስ ራሱን ከመግደሉ በፊት ጽፎ ያስቀመጠው መልእክት እንዲህ ይላል፡-

“መንግስት ያለ አንዳች የእርሱ እርዳታ ላለፉት ሠላሳ አምስት አመታት ብቻዬን በከፈልኩት የጡረታ መዋጮ ላይ የተመሠረተውን የህልውናዬን መሠረቶች ድምጥማጣቸውን አጥፍቷቸዋል፡፡ የእድሜ መግፋት እንደ ልቤ ተሯሩጦ ለመስራት አላስቻለኝም፡፡ ስለዚህ ህይወቴን ለማጥፋት ከዚህ የተሻለ መላ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ህይወቴን ለማቆየት በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ የተጣለ ምግብ ስፈልግ ከመዋልም ተገላገልኩ፡፡” አሳዛኝ ክስተት ይሏል ይሄ ነው!

 

 

Read 3929 times Last modified on Saturday, 14 April 2012 11:02

Follow us on twitter

Due to an error, potentially a timed-out connection to Twitter, this user's tweets are unable to be displayed.