Saturday, 21 October 2017 13:36

ለካስ ከስልጣን መልቀቅ ተዓምር አይደለም!?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(69 votes)

 - ኢህአዴግ ፓርቲ ነው “የነፍስ አባት?!”
              - እውነቱን እንጋፈጥ - ለተፈናቀሉት ተጠያቂው ማነው?
            
    በኢትዮጵያም ሆነ በአውራ ፓርቲው ታሪክ፣ እንዳሁኑ ጊዜ አዳዲስና ዱብዕዳ የሆኑ ክስተቶች ተፈጥረው አያውቁም፡፡ (ለጤና ያድርግልን!) ለምሳሌ ካለፉት 2 ዓመታት ወዲህ መንግስትና “ኢህአዴግ ነፍሴ” እንደገጠማቸው ዓይነት የመረረና የገረረ ተቃውሞ (አመፅና እንቢ ባይነትንም ይጨምራል!) ታይቶ አይታወቅም! እንኳን ከ2 ዓመት በላይ የዘለቀ “ቡልዶዘር ተቃውሞ” ቀርቶ ከጥቂት ቀናት የሚዘል ተቃውሞ እኛም ኢህአዴግም… ገጥሞን አያውቅም፡፡ (የተቃውሞ መሪዎቹ ሲታሰሩ ሁሉ ነገር ያበቃ ነበር!) እናላችሁ… የአማራና የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞዎች … ኢህአዴግን ቢያስደነግጡት ወይም ቢያስበረግጉት አሊያም ቁጭ ብድግ ቢያሰኙት (ያውም በስተርጅና!) አይፈረድበትም!! በዚያ ላይ ኢህአዴግ በኮሙኒኬሽን … በዲፕሎማሲ … ህዝብ በመምራት ጥበብ… ወዘተ እስከዚህም ነው፡፡ (ታጋይ ፓርቲ አይደል?!) በዚህም የተነሳ ተቃውሞዎችን በብልሃት ማረጋጋት … በጥበብ ማቀዝቀዝ አይሆንለትም። (ተቃውሞን በአስለቃሽ ጪስ መበተንም እንደዚያው!)  
ዋናው ነገር ግን ተቃውሞው ለኢህአዴግ ዱብ ዕዳ ነው፡፡ ለ40 እና 50 ዓመታት ኢትዮጵያን ለመግዛት ህልምና ራዕይ የሰነቀ ፓርቲ፣  አገሪቱን ከድህነት አላቅቆ ከመካከለኛ ገቢ አገራት ተርታ  ሊያሰልፋት ምሎ የተገዘተ ልማታዊ መንግስት … እንዴት ቆሜለታለሁ (ቆሜበታለሁም ያስኬዳል!) ከሚለው ህዝብ ተቃውሞ (ያውም ያፈጠጠ ያገጠጠ!) …ሊጠብቅ ይችላል? (ግን ደግሞ “እህል ውሃ” የሚባል ነገር  አለ!) እኔ የምለው … መንግስትና ህዝብ “እህል ውሃ” አላቸው አይደል?!  (እንክት ነዋ!)
ሌላው ዱብዕዳ ደግሞ ምን መሰላችሁ? ሁለቱ የኢህአዴግ አንጋፋ አመራሮች፣ አቶ አባዱላ ገመዳና አቶ በረከት ስምኦን፤ በተከታታይ ከሥልጣን የመልቀቃቸው ዜና ነው፡፡ (ተመካክረው ነው እንዴ?) አንዳንዶች የሁለቱን አንጋፋ ታጋዮች ከሥልጣን መልቀቅ፣ በፓርቲው ውስጥ ወይም በመንግስት መዋቅር … ችግር መኖሩን ማሳያ አድርገው ይቆጥሩታል…ሽንቁር ነገር! ሌሎች ደግሞ በመጨረሻው ሰዓት ላይ “ከደሙ ንፁህ ነኝ” ለማለት ነው ስልጣን የለቀቁት ይላሉ፡፡ (ከስልጣን መልቀቅም … ያስመቀኛል እንዴ?!) …
እኔ ግን … ከሁለቱም ወገን አይደለሁም - በአቋሜ። እኒህ ባለሥልጣናት ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን … በኢህአዴግ የ27 ዓመት የሥልጣን ታሪክ፣ ከመንግስት ቱባ ሥልጣን በፈቃዳቸው (ሳይገደዱ!)  በመልቀቅ ፈር ቀዳጅ ናቸውና “አድናቂያቸው” ነኝ፡፡ ከስልጣን ለሚወርድም አድናቂ አለው፡፡ አያችሁ … ለተቀሩት የኢህአዴግ ባለስልጣናት፣ ያለ ስልጣን በህይወት መኖር … መተንፈስ …እንደሚቻል… ተግባራዊ ትምህርት የሰጡልን ባለውለታችን ናቸው፡፡ (እውነት ግን ያለ ስልጣን መኖር ይቻላል እንዴ?) ለምሳሌ እነሙጋቤ .. እነ ሙሴቪኒ እና ሌሎች አፍሪካውያን ግን አይችሉም። ከቤተ መንግስት በቀጥታ ወደ መቃብር ሥፍራቸው ለመሄድ ተፈጥመዋል፡፡ (እስከሚያሸልቡ እንግዲህ ህዝቡ ፈደረበት!)
እኒህ ቱባ ባለስልጣናት … አሁን ነው ትልቅ ሥራ የሰሩልን፡፡ ሥልጣን በፈቃዳቸው ሲለቁ! ለምን መሰላችሁ? ማንም ጎበዝ ሊያደርገው የማይደፍረው የጀግና ተግባር ነው፡፡ (በተለይ ደግሞ ለኢህአዴጎች!) በዚህ ተግባራቸውም ታሪክ ይለወጣል፡፡ እስከ ሞት ጠብታ ሥልጣን ላይ የሙጥኝ ከማለት … በህይወት-በጤና ከሥልጣን መንበር ወርዶ … እንደ ሰው መኖር! እንደኛ!! እንደ ሰፊው ህዝብ!
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል? እኔ ከስልጣን የወረዱበት ምክንያት ብዙም ጉዳዬ አይደለም፡፡ ዋናው መውረዳቸው ነው፡፡ ድሮ እኮ በቂ ምክንያት ቢኖርም ከስልጣን የሚወርድ የለም! (በግድ ካልሆነ!) ለነገሩ አሁን ወቅቱም ፈቅዷል - ከስልጣን ለመውረድ! ይታያችሁ … በ60ዎቹ የተማሪዎች አብዮት ታግለው (የ “ያ ትውልድ” አባልም አይደሉ? !) “ፊውዳሉን የንጉስ” አገዛዝ ጣሉ፡፡  (ጃንሆይ ተገቢውን ክብር የሚያገኙበት ጊዜ ይናፍቀኛል።) ከዚያም ጨቋኝና አምባገነን ያሉትን የደርግ መንግስት 17 ዓመት ታግለው፣ መስዋዕትነት ከፍለው ገረሰሱት፡፡ በዲሞክራሲ፣ በነፃነት፣ በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ፣ በፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት … ሊያንበሸብሹን! ከብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት የላቀ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊያሰፍኑልን! የሚዲያ ነፃነት አውራ የሆነች አገር ሊፈጥሩ! የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ሞዴል ሊተክሉ - አፍሪካውያን በአርአያነት የሚከተሉት!! ሆኖም ግን በ26 ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸው … ሁላችንም አብረን እንዳየነው… የታሰበው ሁሉ አልተሳካም፡፡ (እንደ ባለሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገት ቀላል አልሆነም!)  ጭራሽ ደግሞ ታገልንልህ የሚሉት ህዝብ … አምርሮ ተቃወማቸው! (ይሄም ያለመሳካቱ ምልክት ነው!)
እናም… በብዙ መንገድ ከስልጣን መልቀቃቸው ትክክል ነው (አንዳንዴ ቀልባቸውን እንኳ ይስሙ እንጂ!) እኔም በእነሱ ቦታ ብሆን ኖሮ (የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና!) ያውም በዚህ ቀውጢ ሰዓት … ፓርቲዬና መንግስቴ በግትርነታቸው ከቀጠሉ፣ አብሬ የምንገታገትበት አንዳችም ምድራዊ ምክንያት አይኖርም፡፡ (ያውም በሽምግልና የማረፍያ ጊዜ!!) ስለዚህ ብቸኛ አማራጩ … ሥልጣንን ሳያቅማሙ መልቀቅ ነው!! (ሥልጣን እንደ ልብስ ተወልቆ የሚጣል ነው ለካ!)
እኔ የምለው ግን … ኢህአዴግ የቀድሞ ባህላዊ አሰራሩን ለወጠ እንዴ? የቱን መሰላችሁ? ጠ/ሚኒስትሩን ሳይቀር ፓርቲው በፈለገበት ቦታ ይመድባል የሚባለውን! (ሲፈልግ ሊስትሮ፣ ሲለው ደግሞ የገጠር ወረዳ ሊቀመንበር ሊያደርግ ይችላል ሲባል … ሰምቼ ደንግጩ ነበር) .. በእርግጥ ጠ/ሚኒስትር…የወረዳ ሊ/መንበር ሲሆን አላየንም፡፡ ግን ደግሞ አንጋፋ ታጋዮችና አመራሮች … ከሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄ ሲያቀርቡ፤ “አይቻልም፤ ይሄ ትግሉን መሸሽ ነው” በሚል ክችች እንደሚልም ሰምቼአለሁ-ፓርቲው!! (ኢህአዴግ … ፓርቲ ነው የነፍስ አባት?!)
የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር (መሬት ይቅለላቸውና!) በህይወት ሳሉ ከሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄ አቅርበው ኢህአዴግ ነፍሴ ባለመፍቀዱ፣ በዚህች ምድር ላይ የተመኙትን “ከሥልጣን ነፃ የሆነ” ጥቂት የትንፋሽ ጊዜ (የእፎይታ ዘመን) ሳያጣጥሙ፣ በታመሙበት እስከ ወዲያኛው አሸልበዋል፡፡ (የፓርቲው ጦስ ነው!) እናም በሌሎች የኢህአዴግ አመራሮችና ባለሥልጣናት ላይ ተመሳሳይ አሳዛኝ ክስተት (Tragic!) እንዳይፈጠር ስጋት ነበረኝ፡፡ የአቶ አባዱላ ገመዳ ከስልጣን የመልቀቅ ጥያቄ መልስ ሲያገኝ ግን እፎይ አልኩ፡፡ (የተለወጠው ፓርቲው ነው? ሰዎቹ?) እኔ የምለው… ኢህአዴጎች ሥልጣንን እንደ ትግል … እንደ መስዋዕትነት ይቆጥሩታል የሚባለው ከምር ነው እንዴ? (ቢሆንማ ኖሮ … ይሄ ሁሉ ሙሰኛ አይኖርም ነበር!)
ለማንኛውም እንኳን ፓርቲው አሰራሩን ለወጠ!! (ሥልጣን በቃኝ ለሚሉ የማርያም መንገድ መስጠት ይገባል!) እስቲ አስቡት … አቶ አባዱላም ሆኑ አቶ በረከት… ከ25 ዓመት በላይ የእኛን የህዝባቸውን ወይም የአገራቸው ፍላጎትና ስሜት ሳይሆን የፓርቲያቸውን ደንብና መመርያ እንዲሁም ርዕዮተ ዓለም … እንደ ሃይማኖት ጠብቀው ብቻ ሳይሆን አክርረው (ቅንጣት ሳያጓድሉ!) የማታ ማታ ከስልጣን የመልቀቅ ጥያቄ ሲያቀርቡ … ፓርቲው አልቀበልም ቢላቸው … ምን ይሆኑ ነበር? በፓርቲያቸው ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ (ባይረግሙት ነው?!)
እስቲ ወደ ቁም ነገሩ! እንምጣ፡፡ ወደ ሥልጣን መልቀቁ ወግ!! እናላችሁ …የእነዚህ ሁለት የኢህአዴግ አንጋፋ ታጋዮች … በፈቃዳቸው ከሥልጣን መልቀቅ በየትኛው መመዘኛ የሚደነቅና የሚበረታታ ነው። (ያለነው በጦቢያ ምድር! በኢህአዴግ ዘመን መሆኑን አትርሱ!) ከዚህ በኋላ ምን አለ በሉኝ … ሥልጣን የሙጥኝ ማለት… እድሜ ልኬን ልንገስ ብሎ መሟዘዝ … ሥልጣን አምላኩ መሆን… እንደ ነውር ሊቆጠር  ይችላል - taboo! (እንደኋላ ቀርነት!)  
እናላችሁ … እንደኔ ቢሆን … እነዚህን ሁለት ባለሥልጣናት… ለፈር ቀዳጅነታቸው…ከስልጣን ለመልቀቅ ላሳዩት ዓይነተኛ ወኔና ድፍረት… ለአርአያነታቸው … ቢቻል መሞገስ…ዕውቅና ማግኘት … መሸለም ነበረባቸው ባይ ነኝ፡፡ በአገር ደረጃ ባይሆንም ይሄው እኔ ዕውቅና ሰጠኋቸው፡፡ ለነገሩ ሥልጣን መልቀቃቸው በራሱ ሽልማት ነው፡፡ የሚያተርፉት እንጂ የሚጎድልባቸው ምንም ነገር የለም፡፡ “ሥልጣን መልቀቅ የደፈሩ ጀግኖች!” ይባላሉ- በኢህአዴግም በኢትዮጵያም ታሪክ፡፡ ሌሎቹ የኢህአዴግ ሆነ ባለሥልጣናትስ ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ እኔ ግን ለጊዜው የሌሎቹ አያስጨንቀኝም። ትኩረቴ ሁለቱ ፈር ቀዳጆች ላይ ነው፡፡ ሌላው ከፈለገ ከእነርሱ ሊማር ይችላል፡፡ ከእነሱም የላቀ ፈር ቀዳጅ  ተግባር ሊፈፅም ይችላል፡፡ እናም… ይቻላል ነው የምላችሁ … ከሥልጣን መልቀቅ ይቻላል!! (ተዓምር አይደለም!)
ኢትዮጵያን እየመሯት ወይም እየገዟት ያሉ የኢህአዴግ ቱባ ቱባ ባለሥልጣናት…ትንሽ ማሰቢያቸውን ከተጠቀሙበት… ትንሽ ከአፍንጫቸው ራቅ አድርገው ማሰብ ከጀመሩ … ትንሽ ስለ ነገ ከተጨነቁ … ትንሽ ከፓርቲ ይልቀ ለአገር ቅድምያ ከሰጡ … የማይቻል ነገር የለም፡፡ ዋናው ከራስ ጋር መታረቅ ነው፡፡ ከህሊና ጋር። እናም ሃቅን መጨበጥ! እኔ በአንድ ነገር አምናለሁ። ማንም የፈለገ ክፉ ቢሆን እንኳ…ጦቢያ እንደ እነ ሶሪያ ፍርስራሽ አገር እንድትሆን የሚፈልግ አንድም ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ እንደ ሶማሌ የፈረሰች አገር እንድትሆን የሚያልም አለ ብዬም ለማሰብ ይከብደኛል፡፡ (ይሄን ያህል ክፉ አይደለንማ!) እንደ ሊቢያ ውጥንቅጧ የጠፋ አገር እንድትሆንም የሚያጫት … ጨርሶ አይኖርም። ስለዚህ ይቻላል … ይህቺን አገር ከጥፋት፣ ከቀውስ ከእርስ  በርስ ግጭት፣ ከመጠፋፋት፣ በዘር ተቧድኖ … ከመተላለቅ..ማዳን…መታደግ…ይቻላል፡፡ ራሳችንን ማዳን … መታደግ እንደ ማለት ነው፡፡  
እስቲ ከሥልጣን ጨዋታ ወጣ ብለን ደግሞ ኮስተር መረር ወዳለው እውነታ እንግባ፡፡ ብዙ ጊዜ ከእውነታው ጋር መጋፈጥ እየተሳነን … እየሸሸንም ነው በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ስህተትና ጥፋት የምንሰራው። ከታሪክም የማንማረው! እኔ የምለው ግን … ለእነዚያ በኦሮሚያ-ሶማሌ ክልል አዋሳኝ ግጭት ሳቢያ ለተፈናቀሉ ዜጎቻችን … (ወገኖቻችን) … ተጠያቂው ማነው? ይህችን ጥያቄ ሳንፈራ ሳንኮራ ልንጋፈጣት ግድ ይላል። ችግሩ እንዳይደገም ከፈለግን!! በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ ሴቶች ተገደው መደፈራቸው፣ ነፍሠጡሮች ሳይቀሩ ከቀዬአቸው ተነቅለው መጠለያ ድንኳን ውስጥ መጣላቸው፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ … ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው፣ በጣም የሚያሳዝን ... በጣም የሚያሳም… በጣም የሚያስፈራ… በጣም የሚያስጨንቅ … በጣም ተስፋ የሚያስቆርጥ … ክስተት ነው፡፡ እኒህ ሁሉ ግፍና በደሎች በራስ አገር፣ በራስ ወገን፣ ዕትብት በተቀበረባት መሬት ፈፅሞ አይመልስም። የጠላት ወታደር ድንበር ጥሶ ወገኖቻችን ላይ ጥቃት የፈፀመባቸው ነው የሚመስልም፡፡ በተደጋጋሚ ሲናገር እንደሰማነው ህዝብና ህዝብ አልተጋጨም፡፡ የታጠቁ ሰዎች ናቸው ጥቃቱን የፈፀሙት ተብሏል ጥሩ!! እነማን ናቸው እነዚያ ታጣቂዎች? ህዝብና ህዝብ እንዳይጋጭ፣ ቁርሾ እንዳይቋጥር … መልካም ግንኙነቱ እንዳይሻክር በእጅጉ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ግን ደግሞ በዚህ ሽፋን እንዲህ ያሉት የሰይጣን ቁራጮች … የእጃቸውን ሳያገኙ መቅረት የለባቸውም፡፡ ተገቢውን ቅጣት ሳያገኙ ማምለጥ አይኖርባቸውም፡፡ ከዚህ በላይ ምን የከፋ ወንጀል አለ? ከዚህ በላይ አረመኔነት ከየት ይመጣል? ለዚህ ነው … ተጠያቂዎቹ ተመርምረውና ለፍርድ ቀርበው ውጤቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ መነገር ያለበት!! ይሄን ኃላፊነት መወጣት ያለበት ደግሞ የፌደራሉ መንግስት ነው፡፡ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ እጁን አጣምሮ መጠበቁም ለሱ ያስጠይቀዋል፡፡ ኢህአዴግ መቼ ይሆን ለዜጎቹ የሚደርሰው?! (ያልታደልን ህዝቦች!)

Read 11631 times