Saturday, 14 April 2012 11:19

ፍቅርና ፖለቲካ ምን አገናኛቸው?

Written by  ተስፋዬ ጎንፋ
Rate this item
(2 votes)

10 የአደጋ ምልክቶች

በ”ፍቅረኛ” ምክንያት፤ ህይወት የሚቃወስባቸው ሰዎች በርካታ ናቸው። የአንዳንዶች ህይወት፤ ከፍቅረኛ ጋር ይበልጥ ይጣፍጣል። ችግር ቢያጋጥም እንኳ፤ አብረው ይወጡታል። እርስ በርስ እየተበረታቱ ኑሮ ይሰምራል፤ ደስታቸውም በፍቅር ይደምቃል። የአንዳንዶች ህይወት ግን፤ በ”ፍቅረኛ” ይመሳቀላል። ደስታቸው ተንኖ እየጠፋ፤ ተስፋቸው ይጨልማል። ህይወታቸውን አበላሽቶ የሚያጠፋቸውን ሰው፤ “ፍቅረኛዬ” ብለው ይዘዋል ማለት ነው። አላወቁማ።

ግን ፖለቲካውምኮ ተመሳሳይ ነው። እንደ አሜሪካ የመሰለ አገር ይፈጠራል - በፖለቲካ። እንደ ሶማሊያና እንደ ሰሜን ኮሪያ የመሰሉ አገሮችም አሉ - በፖለቲካ የሚታመሱ ወይም የሚረገጡ። ህይወትን የሚያበላሽ “ፍቅር” ወይም አገርን የሚያምስ “ፖለቲካ”? እንዴት ሊሆን ይችላል? በእርግጥም፤ ፍቅር ወይም ፖለቲካ አይደሉም ችግሮቹ። ህይወትን የሚያበላሽ መጥፎ አስተሳሰብ ወይም ባህርይ የያዙ ሰዎች ናቸው ችግሮቹ። ግን፤ ለምን እነዚህን ሰዎች በቀላሉ አደብ ማስገዛት አይቻልም? አንደኛ፤ ብዙ ሰዎች ያንን መጥፎ አስተሳሰብ፤ እንደ መልካም የሚቆጥሩበትና የሚሳሳቱበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። በርካታ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎችም እንዲሁ የዚሁ ስህተት ሰለባ ይሆናሉ።

በዚያ ላይ፤ ህይወትን የማበላሸት አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ሰዎች ብልጥ ናቸው። ላይ ላዩን ስንመለከታቸው ደህና ሰው ይመስላሉ። አፍቃሪ ይመስላሉ። ለምን በሉ። አፍቃሪ ባይሆኑም፤ ከአፍቃሪ ምን እንደሚጠበቅ አብጠርጥረው ያውቃሉ። ፍቅር ባይገባቸውም፤ የፍቅር ወግ ወጉን ልቅም አድርገው ተክነውታል። እናም ማስመሰልና መማረክ፣ ማውራትና መዋሸት ይችሉበታል።

አስመሳይ ፖለቲከኞች፤ “ህዝብ፤ ህዝብ” ማለት እንደሚያበዙ ሁሉ፤ አስመሳይ አፍቃሪዎችም፤ “ህይወቴ ነሽ፤ አስብልሻለሁ፤ እሳሳልሻለሁ። ደስታዬ ነሽ፤ ምኞቴ አንቺን ማስደሰት ነው፤ ላንቺ ስል የትም እገባለሁ ...” የሚሉ የፍቅር አባባሎች ከደማቸው ጋር ተዋህዷል። ነገር ግን፤ አባባሎቹን የሚጠቀሙት ፍቅርን ለመግለፅ አይደለም። እንደ ወጥመድና መረብ፤ እንደ ቀስትና መሳሪያ ነው የሚጠቀሙባቸው - አባባሎቹን።

ከዚሁ ብልጠታቸው ጋር፤ የሰው ፊት እና ስሜት እያዩ እንደሁኔታው ፀባያቸውን ይቀያይራሉ፤ “አሳሳልሻለሁ” በማለት ቁጡ ተቆጣጣሪ ይሆናሉ፤ አልያም “ላንቺ ስል እንዲህ ሆንኩልሽ” በማለት አሳዛኝ ሚስኪን ሆነው ይቀርባሉ። እነዚህ ባህርያት፤ የፍቅር ምልክቶች ሊመስሉን ይችላሉ። ግን፤ አደገኛ ናቸው። የሰዎችን ህይወት ያበላሻሉ፤ ለሃዘንና ለመከራ፤ ለጭንቀትና ለብኩን ኑሮ ይዳርጋሉ።

ክፉ የጥፋት ባህርይ ከተጠናወታቸው ሰዎች መራቅ አለብን ይላሉ ዶ/ር አናቤል ቻርቢት። “መራቅ” ብቻ ሳይሆን፤ ባለበሌለ አቅም ሁሉ ሮጦ ማምለጥ ያስፈልጋል የሚሉት ዶ/ር አናቤል ቻርቢት፤ አደገኛውን የውሸት ፍቅር ለመለየት የሚጠቅሙ 10 ምልክቶችን አቅርበዋል። ምልክቶቹ፤ ለወንዶችም ለሴቶችም ተመሳሳይ ናቸው። ግን አደገኛ የፖለቲካ አዝማሚያዎችንም ለማወቅ ይረዳሉ። ምልክቶቹን እንመልከታ - አደገኛ የተባለው ወንድ ወይም ሴት፤ ምን አይነት ይሆኑ?

አፍቃሪ መሳይ ወገኛ፡

አፍቃሪ ለመምሰል ብቻ ሳይሆን፤ በአጠቃላይ የተከበረ ሰው ለመምሰል ተስማሚ ጭንብል ያጠልቃል፤ ታጠልቃለች። ንግግርና ጨዋታ አዋቂ ናቸው። እንደ ቦታውና እንደሁኔታው፤ ተስማሚ አቀራረብና ስርአት አይለያቸውም። በአለባበስና በጌጣጌጥ ምንም አይወጣላቸውም። የመልካም ሰው ምልክቶችን (ወጎችን) ያሟላሉ። ከአፍቃሪ ሰው የምንጠብቃቸውን አባባሎችና ድርጊቶች አንድ በአንድ ይፈፅማሉ - ሰው እንዲሰማቸውና እንዲያያቸው።

ከሁሉም በላይ የሚጨነቁት፤ ሰው ላይ ስለሚፈጥሩት ስሜትና ክብር ነው። “በሰው ዘንድ ተመራጩ አለባበስ፤ ማራኪው አነጋገር፤ ተደናቂው አቀራረብ ምን አይነት ነው?” በሚሉ ጥያቄዎች ይብሰለሰላሉ። ለመልካምነት እና ለአፍቃሪነት ደንታ ባይኖራቸውም ያወሩለታል፤ ይተውኑለታል - እንደ “ጌም” ሆኖ ይታያቸዋላ። ለዚህም ነው፤ የመልካምነትና የአፍቃሪነት ምልክቶች ላይ የሚያተኩሩት። ላይ ላዩን ሲታዩ፤ አማላይና አፍቃሪ ይመስላሉ። ግን መናኛና ወገኛ ናቸው - የሰውን ህይወት የሚያበላሹና የሚያባክኑ ስለሆኑ፤ መጠንቀቅ ይበጃል።

በፖለቲካውስ? ያው እንደ ጊዜውና እንደ አመቺነቱ፤ ጭንብል ይቀያይራሉ። አንዳንዴ የካፒታሊዝም ጭንብል ያጠልቃሉ። እንደ ጌጥ፤ ወግ ወጉን ይፈፅማሉ።

ለምሳሌ፤ የፖለቲካ ምርጫ እንደ ጌጥ ይቆጥሩታል። ለወግ ያህል ነው ምርጫ የሚካሄደው። የፓርላማ ምርጫ ይደረጋል ይላሉ - ግን የፓርቲዎች ፉክክር አይኖርም። ለወጉ ያህል ነፃ ገበያ ይላሉ፤ ግን አብዛኛው ቢዝነስ በመንግስት እጅ ይሆናል። መብት፣ ነፃነት ይላሉ። ስለ መብትና ስለ ነፃነት ለወግ ያህል የማያወራ ፓርቲ የለም። ሁሉም ፓርቲዎች ያወራሉ። ነገር ግን ትችት የሚሰነዝርባቸውን ሰው እንደ ወንጀለኛ እየቆጠሩ ያወግዙታል። ስልጣንና ሃይል ከያዙ፤ የሚተቻቸውን ሰው ያስፈራሩታል። ስልጣን ካልያዙ ደግሞ፤ ስም የማጥፋት ዘመቻ ይከፍቱበታል።

በቃ... ነፃነት፤ ምርጫ፤ ነፃ ገበያ የሚባሉት ነገሮች፤ የምር መልካም ግቦች መሆናቸው ይቀርና፤ የመጫወቻና የማስመሰያ መሳሪያ ይሆናሉ - ለወግ ያህል የሚደሰኮሩ።

ስኬታማ መሳይ ጉረኛ፡

በሄዱበት ቦታ ሁሉ፤ ገናና ሆነው ለመታየት ይጥራሉ። እውነተኛው መልካም ሰው፤ በራሱ ጥረትና ስኬት ይኮራል፤ በህይወቱና በስብእናው ይረካል። እውነተኛው የስኬት ሰው፤ ራሱን ከሌሎች ሰዎች ጋር ማነፃፀርና ማወዳደር አያስፈልገውም። በራሱ ለመርካትና ለመኩራት፤ የሌሎች ሰዎችን አድናቆትና ሙገሳ አይጠብቅም። ግን ደግሞ፤ ማንም ሳይጠይቀውና ሳይከራከረው፤ በየአጋጣሚው ስለራሱ ትልቅነትና ስኬታማነት አይደሰኩርም - እውነተኛው ስኬታማ ሰው።

ስኬታማ መሳይ ሰዎች ግን፤ ውስጣቸው ባዶ ነው። የሰውን ሙገሳ ይፈልጋሉ። ሁኔታቸውና አቀራረባቸው ሁሉ፤ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ የተቀመረ ነው። በአረማመድና በአነጋገር፤ በአሳሳቅና በአቀማመጥ ሳይቀር፤ “ከሁሉም በላይ ስኬታማ፤ አዋቂ እና ሃብታም እንደሆንኩ እመኑልኝ” ብለው ለማወጅ ይጣጣራሉ። ይህ ካልተሳካም፤ ሌሎች ሰዎችን እያጣጣሉና እያንቋሸሹ፤ በፈጣጣ ጉራቸውን ይነዛሉ - አማላይ ሆኖ ለመታየት።

በፖለቲካውም ተመሳሳይ ነው። ጉራውን፤ “ፕሮፓጋንዳ” ልንለው እንችላለን። የፕሮፓጋንዳው አይነት ብዙ ነው። እያጋነኑ፤ ዲሞክራሲ ገንብቻለሁ፤ ድህነት ቀንሻለሁ፤ ኢኮኖሚ አሳድጌያሉ፤ ሁሉም ነገር በሽበሽ ሆኗል እያሉ ሌትተቀን ይጮሃሉ። ወይም ደግሞ እያጋነኑ፤ ምንም የተገነባ የለም፤ የሚቀመስ ጠፋ፤ ኢኮኖሚው እንጦሮጦስ ገባ በማለት ያጣጥላሉ። ዳፕሮፓጋንዳ ለመንዛት የሚዲያ አቅም የሌላቸው ፓርቲዎችም ቢሆኑ፤ ሚዲያውን በእጃቸው እስኪያስገቡ ድረስ ቁጭ ብለው አይጠብቁም። ቢያንስ ቢያንስ ተቀናቃኞችን ከማጣጣልና ከማንቋሸሽ አይቦዝኑም።በፍቅር አለምም ሆነ በፖለቲካው አለም፤ የውሸት አማላይ ወይም ገናና ሆኖ የመታየት አባዜ የተጠናወታቸው ሰዎች ላይ የምናየው ተመሳሳይ ባህሪ፤  የጉራ እና የፕሮፓጋንዳ ሱስ ብቻ አይደለም። ጥላቻቸው ድንበር የለውም።

ንፁህ መሳይ ጠበኛ

በጉራ ብዛት አማላይ ሆኖ ለመታየት ወይም በፕሮፓጋንዳ ለመግነን የሚጣጣሩ ሰዎች፤ ይህን ምኞታቸው ሊያደናቀፍ ወይም ሊያፈርስ የሚችል ሰው ሁሉ ጠላታቸው ነው። ጠላት ተብለው የሚፈረጁት ወገኖች ጥቂት እንዳይመስሏችሁ። ተፎካካሪ ሊሆን የሚችል ሰው ሁሉ ጠላት ነው። ትችት የሚሰነዝር ሁሉ ጠላት ነው። ሳያሞግስ ዝም የሚል ሰውም ጠላት ነው። እንዲህ አይነቱ ሰው፤ ለማንኛውም ችግር፤ ሁሌም ሌሎችን ተወቃሽ ያደርጋል። በራሱ ባህርይ ምክንያት የሚፈጠሩ ስህተቶችንና ጥፋቶችን በሌሎች ላይ ያላክካል። በጠላትነት እየፈረጃቸውም ፀብ ይፈጥራል።

በውሸት (በጉራ) የተገነባው ገናናነት፤ በማንኛውም ሰአትና ቦታ ውሸትነቱ ቢታወቅና እውነታው ቢገለጥኮ ... “ጉድ ይፈላል”። ይህ ደግሞ ከማንም ሰው ሊመጣ የሚችል አደጋ ነው። ስለዚህ “ማንም ሰው” ጠላት ነው። ጉረኛው ሰውዬ ወይም የፕሮፓጋንዳው ጌታ፤ ሁልጊዜ ሰዎችን በጠላትነት እያየ ሁኔታቸውን በፍርሃት ይከታተላል። የሰዎችን አኳሃንና ገፅታ፤ የህዝብን አዝማሚያና ስሜት እየተከታተለ ሃሳባቸውን ለማወቅ በስጋት ያውጠነጥናል።

ይህን ስጋት ለማስወገድና ሰዎችን ይበልጥ ለማሳመን፤ እንደገና ጉራውን (ውሸትን) ይነዛል። ነገር ግን፤ ተጨማሪው ውሸት (ጉራ)፤ ተጨማሪ ስጋት ይፈጥርበታል። እናም፤ ተጨማሪ ሰዎችን በጠላትነት ይፈርጃል። ለስኬታማ መሳይ ጉረኛ፤ ለንፁህ መሳይ ጠበኛ፤ ሁሉም ሰው ጠላቱ ነው። በተለይ፤ አብረውት የሚውሉ ሰዎች እጅግ ያሰጉታል፤ ዋነኛ ጠላት ያደርጋቸዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ከአጠገቡ ያለችውን “ፍቅረኛ”ው እንደ ደመኛ ጠላት ይቆጥራታል።

በፖለቲካውምኮ፤ የአገራችን ፓርቲዎች፤ ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን በጠላትነት ፈረጀው ቁጭ አይሉም። እዚያው ፓርቲ ውስጥም፤ ሽኩቻና ጠላትነት እንደጉድ ነው። ኢህአዴግና ቅንጅትን ጨምሮ፤ ስንት ፓርቲዎች ሲሰነጣጠቁና ሲከፋፈሉ አይተን የለ? የፓርቲ ውስጥ ግምገማውና ሃሜታውም ብዙውን ጊዜ በእርስበርስ ጥላቻ የተሞላ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ የፓርቲ መሪ፤ ምክትሉን አይወደውም። የበርካታ ፓርቲዎች ምክትል ሊቀመንበሮች ብዙ ሰው አያውቃቸውም። ጎላ ብለው ከታዩ፤ ድብቁ ፀብ ፈንድቶ ይወጣላ።

አሳቢ መሳይ ቀናተኛ፡

ወግ ወጉን በማሟላትና በጉራ አማካኝነት፤ በሰዎች ዘንድ የከበሬታና የአድናቆት ስሜት ለማሳደር የሚሞክር ሰው፤ በዚሁ ረክቶና ተማምኖ አይቀመጥም። እርግጠኛ መሆን ይፈልጋል። በውሸት የተገነባው ከበሬታና ገናናነት፤ በሆነ አጋጣሚ ብን ብሎ እንደማይጠፋ ወይም በሌላ ሰው እንደማይነጠቅ ምን ማስተማመኛ አለው? ሰዎቹ በሙሉ ሁልጊዜ አድናቂዎቹና ተከታዮቹ እንዲሆኑ ለማድረግ፤ አንዳች የመያዣና የመቆጣጠሪያ ዘዴ ይፈልጋል። በ”ፖለቲካው” አለም፤ ይህንን “የስልጣን ጥም” ልትሉት ትችላላችሁ። በ”ፍቅር” አለምስ?

ለጉረኛው ሰውዬ፤ የአማላይነትና የስኬታማነት ስሜት በሰዎች ዘንድ ማሳደርና “ተፈቃሪ” ሆኖ መቆጠር፤ ብቻውን በቂ አይሆንለትም። ያ የ”ተፈቃሪነት” ስሜት ነገ ከነገ ወዲያ እንደማይሟሟ ወይም ወደ ሌላ “አማላይ” እንደማይዞር ምን ማረጋገጫ አለው? የመያዣና የመቆጣጠሪያ ዘዴ ይፈልጋል። ክፉ ቅናት ይሄው ነው።

መቼም፤ ሰዎችን መያዝና መቆጣጠር ቀላል አይደለም። እግር ስር ለመረገጥ ጓጉቶና በፈቃደኝነት ተሽቀዳድሞ የሚመጣ ብዙ ሰው ላይኖር ይችላል። ግን ዘዴ አይጠፋም። ሰዎችን እግር ስር አስገብቶ ለመቆጣጠር የመጀመሪያው ዘዴ፤ “ከራሳችሁ በላይ እኔ አስብላችኋለሁ” ብሎ መናገር ነው። ሰላምታ የሚያበዛ ሆኖ ይቀርባል። በየቦታው “ዋና ተቆርቋሪ” ሆኖ ጥልቅ ይላል። እናም የሰዎችን ህይወት መፈትፈትና ማማሰል ይጀምራል። “ዋና ተቆጣጣሪ” ይሆናል።

“ስለማስብላችሁ ነው፤ ስለምጨነቅላችሁ ነው፤ እኔ አውቅላችኋለሁ” በማለት የገባና ተቀባይነት ያገኘ ፖለቲከኛ፤ “እንዲህ አድርጉ፤ እንዲያ አታድርጉ” ብሎ ለማዘዝና ለመከልከል ጊዜ አይፈጅበትም። በእርግጥ ትእዛዞቹና ክልከላዎቹ እየከበዱ ሲመጡ፤ ሰዎች ማጉረምረማቸውና ማማረራቸው አይቀርም። ቢሆንም ግን፤ “ለክፋት ሳይሆን ለናንተው ጥቅም አስቤ ነው፤ ስለምወዳችሁ ነው” ብሎ ያግባባቸዋል። በዚሁ መንገድ ቁጣቸው ከበረደና ከተስማሙ፤ በተጨማሪ ትእዛዞችና ክልከላዎችን እንዲያሸክማቸው የፈቀዱለት ያህል ይሰማዋል። ደግሞም ያደርገዋል። በየጊዜው፤ ጫናው እየከበደ፤ ቁጥጥሩም እየከረረ ይሄዳል።

በፍቅር አለም፤ “አሳቢ መሳይ ቀናተኛ” ላይ የምናየው ባህርይም ተመሳሳይ ነው። ቀን ከሌት ስልክ ይደውላል። በቴክስ ሜሴጅ እረፍት ያሳጣል። ፍቅረኛው ቅሬታ ብታቀርብ እንኳ ችግር የለውም። “ድምፅሽን ለመስማት ፈልጌ ነው። እንዳይመሽብሽ አስቤ ነው። ዝናብ እንዳይመታሽ፤ ፀሃይ እንዳይነካሽ ተጨንቄ ነው” በሚል ማመካኛ ስሜቷን ይፈትሻል። ፍቅረኛው ማመካኛውን ከተቀበለችና ይቅርታ ካደረገችለት፤ በቃ መንገዱ ተከፈተለት ማለት ነው።

አፍቃሪና አሳቢ መስሎ የጀመረው የቁጥጥር አባዜ፤ ይብስበታል። ዛሬና ነገ፤ በስራና በእረፍት ቀን፤ ጥዋትና ማታ፤ በምሳና በሻይ ሰአት፤ ሁሌም የፍቅረኛውን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ይፈልጋል። “እንገናኝ፤ ጠብቂኝ፤ አብረን እንሂድ...” ይላል፤ “ስለምወድሽኮ ነው፤ ስለምትናፍቂኝኮ ነው፤ ህይወቴ ስለሆንሽኮ ነው” የሚሉ ሰበቦችን እየዘረዘረ። ይህንን የሚያጨናንቅ ውትወታ እንደ ፍቅር ቆጥራ ጫናውን ለመሸከም ፍቃደኝነት ካሳየች... በቃ።

“እንገናኝ፤ አብረን እንዋል” ማለቱን ያቆምና፤ “የት ነሽ? የት ገባሽ? የት ወጣሽ? ከማን ጋር ነሽ?” ወደ ሚሉ የአዛዥ ናዛዥ ቁጥጥሮች ይሸጋገራል። “ምን በላሽ? ምን ጠጣሽ?” በሚሉ ፋታ የለሽ ጥያቄዎች የተጀመረው ውትወታ፤ በዚያው አያቆምም። “ምን አየሽ? ምን ሰማሽ?” የሚል ንትርክ ይከተለዋል። ብዙም ሳይቆይ፤ “ያኛው ሰውዬ ምንድነው? ያኛው ጎረምሳ የት ያውቅሻል? በፈገግታ ያየሽው... ስትገለፍጪለት የነበረው ያላየሁ መሰለሽ?” ... የማፋጠጥ ጥያቄና የፀብ ቁጣ ይመጣል። ባለፉት ጥቂት አመታት በአገራችን ሴቶች ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶች በሚዲያ ሲዘገቡ ካስተዋልን፤ ጥቃቶቹ ቀስ በቀስ ወደ መጥፎ ደረጃ የደረሱ እንጂ “ዱብዳ” እንዳልነበሩ መታዘብ እንችላለን።

“በቃኝ”፤ ብላ በምትችለው ፍጥነት ጥላው ካልጠፋች መጨረሻዋ አያምርም። ይቅር እንድትለው ለምኖና ተለማምጦ ቢታረቁ እንኳ፤ የክፉ ሰው ባህርይ በአጭር ጊዜ ይለወጣል ብሎ ማሰብ ትልቅ የዋህነትና አላዋቂነት ነው። ሳምንት ሳይሞላው፤ የክፉ ቅናት አባዜው ይገነፍላል። የፀብ ቁጣ ብቻ ሳይሆን፤ በጥፊ መማታትም ይጨመርበታል። ትማረራለች?

በጥፊ ከተማታ በኋላ፤ ለጊዜው አልቅሶና ምሎ ተገዝቶ ሊያግባባት እንደሚሞክር አያጠራጥርም። ነገሩ በረደ ማለት ነው። በማግስቱ ለሁለተኛ ጊዜ በጥፊ ሲመታት ግን፤ ይቅርታ አይጠይቃትም። በጥፊ መማታት ይለመዳል። እንዲህ እያለ ይቀጥላል። በቡጢና በእርግጫ እየታከለበት፤ በእንጨትና በብረት መደብደብ እየተጨመረበት፤ ህይወቷ የብስጭትና የስቃይ መከራ ይሆናል። በአንዳንዶቹ ላይማ፤ አካል ይጎድላል፤ ህይወት ይጠፋል።

እንዲህ አይነቱ የጥፋት መንገድ፤ በፖለቲካው አለም ሲፈፀም፤ አገር ይታመሳል፤ እልቂት ይፈጠራል። ቀሪዎቹን ምልክቶች አጠር አጠር አድርገን እንመልከታቸው።

አድናቂ መሳይ ቀበኛ፡

“የህዝብን ጥቅም ማስቀደም”፤ “አገርን ማስቀደም” በሚሉ መፈክሮች፤ “ህዝብ፤ ህዝብ” ማለት የሚያበዛ ፖለቲከኛን ተጠንቀቁ። የሂትለር መፈክሮችም እነዚሁ ነበሩ ... “ለህዝብና ለአገር ጥቅም ስንል መስዋእት መክፈል አለብን” እያለ ህዝቡን ጨፈጨፈው፤ አገሩን አወደመው። እንደፎከረው፤ ሚሊዮኖችን መስዋእት አደረገ።

“ህዝብ፤ ህዝብ” ማለት የሚያበዙ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎችን መጠንቀቅ የሚያስፈልገው፤ “መስዋእት” ለመሰብሰብ ስለሚስገበገቡ አይደል? “ህዝብ፤ ህዝብ” ብሎ እየደጋገሙ ማውራት፤ የ”ፍቅር” ምልክት አይደለም ማለት ነው። ልክ እንደዚያው፤ አፍጥጦ ማየትም የአድናቆትና የፍቅር ምልክት ላይሆን ይችላል። የሰውን ህይወት የማበላሸት አባዜ የያዛቸው ሰዎች፤ ፍቅርን አያውቁም። ነገር ግን ለወጉ ያህል አተኩረው ያያሉ - “አተኩሮ ማየት የፍቅር ምልክት ነው” በሚል ስሌት። ምን ዋጋ አለው? ለመቦጨት የጎመጀ ተኩላም አፍጥጦ ያያል።

ቆራጥ መሳይ ጠንቀኛ

“ፍቅር፤ በአንድ ቅፅበት እይታ ነው” ይባል የለ? እውነተኛ ፍቅር፤ አይወላውልም አይደል? ወገኞቹ ይህንን ተከትለው፤ ወከባ ይፈጥራሉ። ለትውውቅ የዘረጉት እጅ ሳይላቀቅ፤ ተጣድፈው “ፍቅር” ያውጃሉ። “ለኔ በዚህ አለም ካንቺ ሌላ ማንም አላገኝም...” ካሉ በኋላ፤ አብረን እንደር ይላሉ። በማግስቱ፤ አብረን እንኑር የሚል መግለጫ ይወጣል። በሳልስቱ ደግሞ፤ በጋብቻ የምንጋባበት ጊዜ ናፈቀኝ ተብሎ ይዘፈናል። ወግ ነዋ፤ እውነተኛ ፍቅር አይወላውልም ተብሏላ። ችኮላው ግን፤ የሰዎችን ህይወት በእጅ ውስጥ ለማስገባት፣ ለመቆጣጠርና ለማበላሸት ነው።

በፖለቲካውም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው። “ዛሬውኑ እንደራጅ፤ ዛሬውኑ ከከተማ እስከ ገጠር ተደራጅ። ዛሬውኑ ልማትና ለውጥ ይንገስ፤ ዛሬውኑ ስልጣን እንያዝ” ... በጥድፊያ የተሞላ ፖለቲካ ስታዩ ተጠንቀቁ። “ያዋከቡት ነገር!” ይሆናል ነገሩ። ጥድፊያው ለጥፋት ነው።  ቁጥጥር ለማጥበቅ፤ የስልጣን ጥም ለማርካት፤ ስልጣን ላይ ወጥቶ፤ በሰዎች ህይወት ላይ አድራጊ ፈጣሪ ለመሆን ሲባል የሚፈጠር ወከባ፤ ማሳረጊያው ጥፋት ቢሆን አይገርምም።

ሚስኪንነት ቁርሱ፡

ወገኛነቱና ጉራው፣ ውሎ አድሮ ሲታይ የተመኘው ያህል ባይሰራለት? በሰዎች ህይወት ላይ አድራጊ ፈጣሪ፤ ነጂ ተቆጣጣሪ የመሆን ህልሙ እውን ባይሆንለትስ? “ፍቅረኛው” ስቃይ በዝቶባት፤ “በቃ” ብትልስ? በፍቅረኞቻቸው ላይ ጥቃት የፈፀሙ ሰዎች ላይ እንደታዘብነው፤ የ”ገናናነት”ን ጭምብል አውልቀው፤ የ”ሚስኪንነት” ጭንብል ያጠልቃሉ።

“እኔ ላንቺ ብዬ ከስሬ፤ ላንቺ ብዬ ከቤተሰብ ተራርቄ፤ ላንቺ ስል ትምህርት አቋርጬ...” ... በቃ፤ አንጀት የሚበላ ሚስኪን ሆኖ ብቅ ይላል። “ላንቺ ቤት ለመስራት፤ መኪና ለመግዛት... ላንቺ ስል ያላየሁት መከራ የለም፤ ላንቺ ስል ማንኛውንም ስቃይ እቀበላለሁ፤ እንደፈለግሽ አድርጊኝ” ... በቃ፤ ሰውን ሁሉ ለማሽቆጥቆጥ ይሞክር የነበረው ጉረኛ፤ እየተሽቆጠቆጠ ራሱን ያዋርዳል - እንዲታዘንለት።

“እህት ወንድሞቼ በልጅነቴ ጥለውኝ ሲጠጉ፤ የመንደር ጎረምሶች ሲሰድቡኝ፤ የሰፈር ዱርዬዎች ሲደበድቡኝ፤ ባልሰራሁት ጥፋት በፖሊስ ስታሰር... ያመንኳት ፍቅረኛዬ እኔን ከድታ ሃብታም ስታገባ” ... በቃ፤ ብዙ ግፍ እንደደረሰበትና ብዙ ችግር እንዳለፈ ይተርካል። ታዲያ እሱ በተራው፤ በሌሎች ሰዎች ላይ ግፍ መፈፀም አለበት? ለማንኛውም፤ ሚስኪን ሆኖ በመቅረብም ሰዎችን መጠምዘዝና ማሽከርከር እንደሚቻል ያውቃል።

ፓርቲዎችም፤ የሚስኪንነትን ጨዋታ ያውቁታል። ቁጡና አስፈሪ ሆኖ መቅረብ የማያዋጣ በሚሆንበት ጊዜ፤ ሁሉን ቻይ ሚስኪን ሆነው ብቅ ማለት ይችሉበታል። “ግፍ አይተናል፤ በትግል መስዋእት ከፍለናል” የሚል መከራከሪያም በሰፊው ይታወቃል። በእርግጥ፤ በግፍ የተገደሉና ሲታገሉ የሞቱ እልፍ ወጣቶች፤ በስልጣን ጉዳይ ስማቸው ሲነሳ ማየት ለህሊና ይከብዳል። ቢሆንም ሲደረግ እናያለን። ቅንጅት እንኳ በአቅሙ፤ በ97 ምርጫ ስልጣን መያዝ እንዳለበት ካቀረባቸው ምክንያቶች አንዱ፤ “መስዋእት ከፍለንበታል” የሚል ነበር። በምርጫው ቀውስ ላይ የተከሰተው አሳዛኝ የወጣቶችን ሞት መጥቀሳቸው ነው። በመስዋእትነት ከሆነማ፤ ኢህአዴግስ?

መገላበጥ ምሱ፡

አንዴ፤ በገናናነት ማሽቆጥቆጥ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሚስኪንነት መሽቆጥቆጥ ምን ይሉታል? መገላበጥ ነው። ይህም ብቻ አይደለም። ዛሬ ወዳጅና አድናቂ ሆነው ይታዩና፤ በማግስቱ ጠላትና ደመኛ ይሆናሉ። ተንከባካቢና አሳቢ ልሁን ሲል የነበረው ሰውዬ፤ ነገ ረጋጭና ደብዳቢ ይሆናል።

ሙስና እራቱ፡

እንዲህ አይነት ባህርይ የያዘ ሰው፤ ፍቅርና ልባዊ ራእይ፤ እውነተኛ የህይወት እርካታና ደስታ ማግኘት አይችልም። ሙሰኛው፤ የሙያ ፍቅርንና ሃብትን ነጣጥሎ በማየት፤ በሃብት ብቻ እርካታ ለማግኘት ይሞክር የለ? ነገር ግን፤ የሃብት ቅዱስነትና እርካታ የሚመነጨው፣ ከሙያ ፍቅርና ከጥረት ነው። በፍቅር አለምም እንዲሁ፤ ፍቅርንና ወሲብን በመነጣጠል፤ በወሲብ ብቻ ለመርካት የሚመኝ አለ። ግን፤ የወሲብ ቅዱስነት በፍቅር ላይ የተመሰረተ ነው።

 

 

 

Read 4562 times Last modified on Saturday, 14 April 2012 11:28