Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 14 April 2012 11:46

ትልቅ ተመኝ ትልቅ እንድታገኝ!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የመንትዮቹ የስኬት ምስጢር

ሁላችንም በትልቁ ማሰብ ይገባናል የሚለው የሮበርት ሹለር የስኬታማነት መመሪያ መፅሃፍ፤ አብዛኞቹን ችግሮቻችንን የሚፈጥርብን ሌላ ሳይሆን የገዛ ራሳችን ውስን አስተሳሰብ ነው ይላል፡፡ ደራሲውም መፅሃፉም ልክ ብለዋል፡፡ በጣም በርካታ የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮች የቅርብ አሳቢነት ወይም የውስን አስተሳሰብ ካባቸውን ሲገፈፉ እልም ብለው ይጠፋሉ - እስከ ወዲያኛው፡፡ “Success is Never Ending Failure is Never Final” የተባለው መፅሃፍ አዘጋጅ ዶ/ር ሮበርት ሹለር፤ ሁላችንም ከጆንና ግሬግ ራይስ መማር እንችላለን ይለናል፡፡ ለመሆኑ እኒህ ግለሰቦች እነማን ናቸው? መንትዮች ናቸው፡፡ ሚሊዬነሮች፡፡ ዝነኞች፡፡ እኒህ አሜሪካዊ ወንድማማቾች ስኬታማ፣ ደስተኛና በእርካታ የተሞሉ ናቸው፡፡

ወንድማማቾቹ ሦስት ጫማ ቁመት የነበራቸው መሆናቸው ሳያንስ በፈተና ላይ ፈተና የተጋፈጡ ቢሆኑም የዛሬው ማንነታቸው ሲታይ ተአምር ከሚለው ውጭ የሚገልፃቸው ቃል የለም፡፡

በሆስፒታል ውስጥ የተወለዱት መንትዮቹ፤ ከወላጅ ቤተሰቦቻቸው ጋር የመኖር እድል የተነፈጉ ናቸው፡፡ እዚያው ሆስፒታል ትተዋቸው ነበር የጠፉት - ወላጆቻቸው፡፡ ምርመራ ሲደረግላቸው ከነበራቸው ቁመት በላይ ማደግ (መርዘም) እንዳማይችሉ ተረጋገጠ፡፡ ሁለቱን ወንድማማቾች ተቀብሎ የሚያሳድግ ቤተሰብ ለማግኘት መንግስት ለዘጠኝ ወራት ደፋ ቀና ብሏል፡፡

የማታ ማታ ግን እንደ ዕድል ሆኖ አሪፍ፣ አፍቃሪና ክርስትያን የሆነ ቤተሰብ ተገኘላቸው፡፡ እዚያ ቤት ውስጥ ለዛሬው እፁብ ድንቅ ማንነታቸው ያበቃቸውን እንክብካቤና ፍቅር እየኮመኮሙ አደጉ፡፡

ወንድማማቾቹ ሌላ ሃዘንና ድንጋጤ የደረሰባቸው አሳዳጊዎቻቸው የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች ሳሉ በሞት በተለዩዋቸው ወቅት ነበር፡፡ አዝነውና ደንግጠው ግን አልቀሩም፡፡ ብዙም ሳይቆዩ ወደ ሪል እስቴት ሥራ ዘው ብለው ገቡ፡፡ ከዚያም  በሚዲያዎች እየቀረቡ ተመክሮአቸውን ማጋራት ጀመሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1979 ዓ.ም “Real people” የተሰኘ የቲቪ ፕሮግራም ላይ በእንግድነት በመቅረብ ሰዎች ትልቅ ትልቁን እንዲያስቡ አበክረው ተናገሩ - እነዚህ 5 ጫማ ቁመት ያላቸው ወንድማማቾች፡፡ ሰዎች በሚናገሩት መደመማቸው እነሱም ዛሬም ድረስ በሚያደርጉት ንግግሮች ስኬታማነታቸው ቀጥሏል፡፡ ጆን አንድ ጊዜ እንዲህ አለኝ ይላሉ - ዶ/ር ሹለር፤ “ብዙ ሰዎች እኔን እና ግሬግን ይመለከቱና ዕድለኞች ናችሁ ይሉናል፡፡ ለእኛ ግን ዕድል ማለት ሥራ ነው፤ ጠንክረን በሰራን ቁጥር ዕድል የበለጠ ፊቷን ወደኛ ታዞራለች፡፡

“አየህ…ሁሉም ሰው በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በህይወቱ የሚጐድለው ነገር አለ፡፡ እንደ ግሬግና እንደኔ ያሉ ሰዎች የቁመት ጉድለት (እጥረት) አለባቸው፤ ሌሎች የገንዘብ እጥረት ይኖራቸዋል፡፡ አብዛኞቻችን የልምድ እጥረት አለብን፡፡ ነገር ግን አሪፍ ምሳሌ የሚሆነን ከዛሬ ሦስት ሺ ዓመት በፊት በእስራኤል የነበረ ዳዊት የተባለ አጭር ታዳጊ ጐልያድ ከተባለ የፍልስጤም ግድንግድ ጋር የገጠመው ፍልሚያ ነው፡፡

በእርግጥም ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው፤ ዳዊት እጁን ወደ ቦርሳው ልኮ ድንጋይ አወጣና የሰማይ ስባሪ የሚያህለውን ሰውዬ ግንባር እንካ ቅመስ አለው፡፡ ጐልያድ በፊት ለፊቱ መሬት ላይ ተፈጠፈጠ፡፡

“ነገር ግን በዓለማችን ላይ እንዲህ በድንጋይ ግንባራቸውን መፈንከት ያለባቸው ሌሎች የሰማይ ስባሪዎችም አሉ - ቅድመ ብያኔ፣ አሉታዊ አስተሳሰብ፣ በራስ የመተማመን ችግር፣ ተስፋ ቢስነት፡፡ ነገርዬው የዳዊት አይነት ነው፡፡ አንዳንዶቻችን ከዘመናችን የሰማይ ስባሪዎች ጋር ለመጋፈጥ ተገቢው መሳሪያ አለን ብለን አናስብም፡፡ ሆኖም ሁላችንም ወኔያችንን ካንቀላፉበት መቀስቀስ አለብን፤ ወደ ራሳችን ጠልቀን ገብተን ድንጋያችንን በማውጣት የዘመናችን የሰማይ ስባሪ ላይ መወርወር ይገባናል፡፡ አየህ ውጤታማ ለመሆን… ራሳችን ካለን በላይ አንጠየቅም፡፡ ያለንን ሙሉ በሙሉ እንድንጠቀም እንጂ”

ወንድምዬው ግሬግ ደግሞ እንዲህ ሲል አክሏል፤ “ጆንና እኔ ወላጆቻችን ጠንካራ ክርስትያናዊ መሰረት በውስጣችን ባይተክሉብን ኖሮ… ያንን ሁሉ ማሳካት አይቻለንም ነበር፡፡ ሰዎች ይመለከቱንና ስኬታማነታችንን ይናገራሉ፡፡ ጆንና እኔ ግን እውነተኛው የስኬት ምስጢር ደስተኝነት ነው ብለን እናምናለን - በቃ ማናቸውንም ነገሮች ሰትሰራ ደስተኛ መሆን፡፡”

ምንጊዜም ደስተኞች የሆኑት ሁለቱ ሰዎች አሉ ከተባለ ያለጥርጥር እኔና ጆን ሳንሆን አንቀርም  የሚለው ግሬግ፤ ምክንያቱ ደግሞ ሌላ ሳይሆን ያለንበትን ሁኔታ እንደ ችግር አለመመልከታችን ነው ብሏል፡፡

ጆን በመጨረሻ ሃሳቡን ሲቋጭም “አየህ ብዙ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ እንደሰበብ ያቀርቡታል፡፡ ነገር ግን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ብትሆን የመጨረሻ አቅምህን ተጠቅመህ ስኬታማ መሆን አያቅትህም” ብሏል፡፡

ሦስት ጫማ ቁመት ያላቸው መንትያ ወንድማማቾች ደስተኞች ናቸው፡፡ በተፈጥሮአዊ ሁኔታቸው ሃዘንና ምሬት ውስጥ አልገቡም፡፡ ስኬታማ ናቸው - ሚሊዬነሮች!! እንዴት ልትሉ ትችላላችሁ…ምክንያቱ ዘወትር ለሚሊዬን ህዝቦች የፍቅርና የመነቃቃት ሰበብ መሆናቸው ነው፡፡ ከአንደበታቸው የማይጠፋው አባባል ደግሞ “ምን ጊዜም በትልቁ አስቡ!” የሚል ነው፡፡ እነሱን ለዕፁብ ድንቅ ስኬት ያበቃቸው በትልቁ ማሰባቸው (Thinking big) እንደሆነ ያውቃሉዋ! ታዲያ እኒህ ሰዎች በአድናቆትና በፍቅር ቢጥለቀለቁ ምን ያስደንቃል? የዘሩትን እኮ ነው ያጨዱት!! ሠናይ የትንሳኤ በአል ይሁንላችሁ!!

 

 

Read 4192 times Last modified on Saturday, 14 April 2012 11:51