Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 14 April 2012 11:46

ከ‘ቤት ዱቤ’ ወደ ‘ሆድ ዱቤ’…

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው አደረሳችሁማ!

እንግዲህ በዓል ሲደርስ ‘ተነጫነጩ’ ይለን የለ…ነጭነጭ’ እንበል፡፡ ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል.. አንዳንዴ “ለእኛ የተባለ” ማብራሪያ፣ መግለጫ ምናምን ነገሮችን ስሰማ በተዘዋዋሪ … “አቦ፣ ደግሞ ንጭንጫችሁን ጀመራችሁ!” የሚሉን ይመስለኛል፡፡ ለንጭንጭም’ መስፈርት እስኪወጣ እንክት አድርገን እንነጫነጫለን፡፡ ግርም የሚለኝ ነገር ምን አለ መሰላችሁ… ለምንድነው ሥጋ፣ እንቁላል ምናምን ነገር እንደ ‘ቅንጦት’ የሚታየው! አለ አይደል…ልክ እኮ እነኚህ ነገሮች መሰረታዊ ሳይሆኑ ቀርተው ‘ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑትን’ ነገር ከተመገባችሁ በኋላ የሚጨመሩ ነው የሚመስለው፡፡ እዚህ አገር ባዮሎጂ ምናምን ገደል ገባች ማለት ነው!

ምን ይመስልሀል አትሉኝም… የሚመስለኝማ እንዲህ እንድናስብ የሚያደርገን “ይቺኑ አታሳጣኝ!” የምንላት ነገር ነች፡፡ በ‘መኖር’ና በ‘ህይወት መቆየት’ መሀል ያለው መስመር ጠፍቶ አሁን ሁሉ ነገር የ‘ሰርቫይቫል’ ጥያቄ እየሆነ ነው፡፡ “ቀን እስኪያልፍ የምቆረጥመው ሽምብራ አታሳጣኝ” የምንላት ነገር አንዳንዴ አትገርማችሁም! ልክ እኮ ይቺ አገር ከተፈጠረች ጀምሮ “ቀን እስኪያልፍ…” ስትል የኖረች ነው የሚመስለው፡፡ ልክ ነዋ…‘በናፍቆት የሚጠበቀው ቀን’ የትኛው እንደሆነ፣ “ቀን አለፈ” የሚባለው ምን ሲሆን እንደሆነ፣ ‘ቀኑንስ እንዲያልፍ የሚያደርገው’ ማንና ምን እንደሆነ ግራ ይገባችኋል፡፡

አንድዬማ…አለ አይደል… “እንደ ፍጥርጥራችሁ” ብሎ ከተወን ከራረመ፡፡ ልክ ነዋ…የእኛ ነገር ተማጽኖና መለማመን መሆኑ ቀርቶ ወደ ንዝንዝ ሲለወጥበት ምን ያድርግ!

እናላችሁ…እንግዲህ ዓመት በዓልም አይደል…ሥጋ መመገብ የማግኘትና የእጦት ምልክት የሆነባቸው አገሮች ቁጥር ይነገረን፡፡ እንዴ… ሳይንሱም ቢሆን እንደውም ዋናዎቹ ለሰውነት አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች የሚገኙት ሥጋና ሥጋ ተዋጽኦ ውስጥ ነው ይለን የለ! ለባዮሎጂ መምህር የሚሆን ትርፍ ቦታ ካለ ጠቁሙኝማ፡፡ (እግረ መንገዴን…መምህራን ነገርዬው እንዴት ነው፣ “ነብር አየኝ በል!” ምናምን አይነት በ‘ጥሁፍ’ ምናምን የደረሰ ነገር አለ እንዴ!) እኔ የምለው… አይ.ኪዋችን አሁንም አቧራውን እየቃመ ያለው ‘ማሰቢያችን’ ፕሮቲን ስላጠረው አይመስላችሁም!

እናላችሁ… በዓመት አንድና ሁለቴ ለምናገኘው ነገር… “እሱ ቢቀርስ፣ ዋናው ጤፍ ብቻ አይጥፋ!” የምንላት ‘ፍልስፍና’ አሮጌ ሳጥን የተገኘ አሮጌ ‘ብላክ ኤንድ ኋይት’ ፎቶ እያስመሰለችን ነው፡፡ታዲያላችሁ… ለምንድነው፣ “በየቀኑ አንድ ቢያቅተን በሳምንት አንዴ እንኳን ማግኘት አለብኝ…” አይነት አስተሳሰብ የማይኖረን! ቴሌቪዥኑ እኮ በየቀኑ ልጆቻችሁ በጤንነት እንዲያድጉ እንቁላል ሥጋ ምናምን መግቧቸው እያለን አይደል! (እነ እንትና…ፋክትና ፊክሺን ስለተደባለቀ ይህንንም ‘ካላዘሉን’ አናምንም እንዳትሉ!) እናማ…የምሯን እንነጋገር ከተባለ፣ እንደ ሳይንሱ…ከጥቂቶች በስተቀር የተቀረነው ‘ማልኖሪሽድ’ ነን፡፡ እንዲህ ቁርጣችንን ስናውቅ አሪፍ ነዋ!

ቁርጥ መብላት የሀብት ምልክት፣ ክትፎ መብላት የድሎት ምልክት፣ እንቁላል በሥጋ ምናምን  መብላት የቅንጦት ምልክት እንደሆኑ እንድናስብ የሚያደርገንን ቫይረስ ጠራርጎ የሚያወጣልን ሶፍትዌር ይላክልንማ! “ይቺኑ የባቄላ አሹቄን አታሳጣኝ…” ማለት እኛ ላይ የተጣለ ግዝት ምናምን ነገር እየመሰለ ነው፡፡

የምር አሳዛኝ ነው…ሥጋ መብላትና ዓመት በዓል የማይነጣጠሉ አይነት ነገር ሆነውላችሁ… በዓል በመጣ ቁጥር ነጋዴ በሥጋና ሥጋ ተዋፅኦ ላይ ዋጋ እየቆለለ ከምንመገበው ሥጋ ሦስት እጥፍ ክብደት ከላያችን ላይ እያሟሟብን ነው፡፡ “ከማን አንሼ!” የምትለው ‘ተሸናፊ ብቻ የሚበዛባት’ ፉክክር ቀላል መስላችኋለች!

እናላችሁ…ቅቤ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ‘ቅንጦት’ የሚሆንበት ምክንያት የለም! ሥጋ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ‘ቅንጦት’ የሚሆንበት ምክንያት የለም! ወተት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ‘ቅንጦት’ የሚሆንበት ምክንያት የለም! ይኸው ነው፡፡ ለማንኛውም ራሱን ‘እንደ ሰው’ ለሚቆጥር ፍጡር አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፡፡ ታዲያላችሁ…ሥጋ ለመብላት የግድ በዓል መሆን ባለበት ወይም የሀኪም ትዕዛዝ በሚጠበቅበት ሀገር “ጤፉ ብቻ አይጥፋ!” አይነት አስተሳሰብ… አለ አይደል… የሆነ አደንዝዞ የማያነቃንቅ ‘አኔስቴዝያ’ ነገር በሉት፡፡ ሥጋ ስለመመገብ ማሰብ ልክ “ለምን ያለ አቅምህ ትንጠራራለህ!” አይነት ነገር የሚያስብል እየሆነ ሥጋ ለመብላት ማሰብ ልክ የአምስት ሚሊዮን ብር ሎተሪ ለማሸነፍ እንደ መመኘት ‘ፋንታሲ’ ነገር እየሆነ ነው፡፡

ስሙኝማ… አንድ ወዳጄ ምን አለኝ መሰላችሁ… “አሁን አሁንማ ምግብ በልቶ አፍ መጉመጥመጥ የለም፡፡” አሀ… ምግብን ከአፍ ወደ ወደ ውጪ መላክ ቀርቷላ! እናላችሁ…የእነ ስቲኪኒ አገልግሎት “ፈልጎ ማስወገድ” ሳይሆን “ፈልጎ ወደ ውስጥ ገፋ ማድረግ” እየሆነ ነው፡፡

ይህ ጽሁፍ ሲጻፍ በሬ ምናምን በአማካይ ወደ አሥር ሺህ ብር ገብቷል እየተባለ ነበር፡፡ (ሥጋ ቅንጦት አይደለም! ጮክ ብዬ መናገሬ ይያዝልኝማ!) የዝናቡ መጥፋት ሰበብ ሆኖ ኪሎ ቅቤ ሁለት መቶ ብርን የሚዘልባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ ዶሮም ወደ ሁለት መቶ እየተንፏቀቀች ነው ይባላል፡፡ (ቅቤም ዶሮም ቅንጦት አይደሉም!) ይህንን…አለ አይደል… አእምሯችን ውስጥ የሚያስቀምጥልን አጥተን ነው እንዲህ ጥሩ፣ ጥሩው ነገር ሁሉ ለእኛ እንዳልተፈጠረ የምናስመስለው፡፡

እኔ የምለው…በምግብ ሆነ በሌሎች ነገሮች ለተቀሩት ህብረተሰቦች አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ሁሉ እኛ ዘንድ ሲመጡ ለምን ‘ቅንጦት’ እንደሚሆኑ ግርም አይላችሁም! ሌኒን ነው ማነው እሱ… “ጥሩ ጥሩውን ለልጆች…” ሲል በ‘ግርጌ ማስታወሻ’ ምናምን “አሸር በአሸሩን ለሀበሻ” ብሏል እንዴ! እንጠይቅ እንጂ፣ ምን እናድርግ!…ግራ የገባው ‘እንትን ማግባት’ ብቻ ሳይሆን ሌላስ ቢሆን ምን ይገርማል!

የሚመስለኝማ…በቃ፣ ይሄ አስተሳሰብ ከበፊት ጀምሮ የመጣ ይመስለኛል፡፡ “ጮማውን እንቆርጠው ነበር…” ምናምን ሲባል ወሬው መሰረታዊ ነገሮችን ስለማገኘት ሳይሆን ስለ ቅንጦት ነው፡፡ (ሥጋ ‘ቅንጦት’ አይደለም!) እናላችሁ…ሥጋ መመገብ ለተሟሏ ጤንነት አስፈላጊ ነገር መሆኑ እየተረሳ ልክ የክብረ በዓል ማጌጫ አይነት ነገር ሆኖ መቅረቱ ያሳዝናል፡፡ “ስማ፣ መቼ ነው ቁርጥ የምንበላው?” እየተባለ የአምስት ወር ከአሥራ አምስት ቀን ቀጠሮ የሚያዝበት ልማድ ምን ያህል ሥጋን ከቅንጦት ጋር እንደምናያይዘው ‘ምስክር’ አይሆንም!

አንዳንዴ ደግሞ “ሰዉ መሰረታዊ ነገር እንኳን አጥቷል፣ አጅሬ ስለ ሥጋ ታወራለህ…” የሚሉት ነገር አለ፡፡ ስለ ሥጋ መጨነቅ ያለብን መሰረታዊ ስለሆነ ነው! ይኸው ነው፡፡ ሥጋና የሥጋ ተዋጽኦ ማግኘት በባንክ ደብተር ላይ የስድስትና የሰባት ቁጥሮች ሰልፍ ስላለ ሳይሆን.. እንኳን የባንክ፣ የዕድር ደብተርም ባይኖረን ለጤናማ አካል አስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡ እናማ… ጂ ፕላስ ፋይቭ ፓላስ ውስጥ የሚንፈላሰሰው እንደሚያስበው ሁሉ በላስቲክ ቤት የሚኖረው ስለ ሥጋ ቢያስብ ሌሊቱ ሳይጋመስ ‘ይቀሰፋል’ አይነት አስተሳሰብ ካልተነቀለልን የምር አስቸጋሪ ነው፡፡

የሚገርመው እኮ…ይሄ ስንት ዘመን የምንሰማው ኢትዮጵያ በከብት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ምናምነኛ የምንለው ነገር ዘላለም ርዕስ ማሳመሪያ ሆኖ መቅረቱ ነው፡፡ እንደ ከብት ሀብታችን ብዛት እኮ የሥጋ ምግብ በመመገብ ከዓለም ጥሩ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ህዝቦች መሀል መሆን ነበረብን፡፡ ግን ምን ያደርጋል… የቡና አገር እንኳን ሆነን ሌላው በእኛ ቡና ፏ ሲል እኛ በቀን አንድ ስኒ እያቃተን አይደል! እና…እኛ ለማንጠቀምበት፣ ዘላለም በእንቁልልጭ ‘ምራቃችንን እየዋጥን’ በምንኖርበት… ከአፍሪካ ምናምነኛ፣ ከዓለም ምናምነኛ ማለቱ…አለ አይደል… “የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባዬ” አይነት ነገር ሆኖ ይቀራል፡፡

ሥጋ መመገብ የበዓል ማድመቂያ እንደሆነ የምናስበው ነገር የምር መቅረት አለበት፡፡ እናላችሁ… ሰዉ ጥሪቱን እያሟጠጠ፣ ከቁጠባም ከዕቁብም እየተበደረ ለሥጋና ለቅቤ የሚያወጣው እነዚህ ምግቦች የቅንጦት ወይም የክብረ በዓል ማድመቂያዎች ብቻ እንደሆኑ እንዲመስለው ስለሆነ ነው፡፡ አለዛማ… “ቢያንስ በሳምንት አንዴ…” ምናምን ብለን እናስብ ነበር፡፡ስሙኛማ…መቼም ችግር ብልሀት ይፈጥር የለ…አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ለቅርጫ ሥጋ ሠራተኛው አርባ በመቶ እንዲያዋጣና ቀሪውን ስድሳ በመቶ ከቁጠባ ማህበር በሦስት፣ በአራት ወር ብድር እንዲወስድ እየተባለ ነው አሉ፡፡ አንድ ወዳጄ ምን አለኝ መሰላችሁ… “ለቤት መሥሪያ ብድር ከቁጠባ ከዛሬ ነገ እጠይቃለሁ ስል ይኸው ብድር ለቅርጫ ሆና አረፈችው!” ምን ይደረግ… በዱቤ እንብላ እንጂ!

የምር ይገርማል… ብድር ለቤት መገንቢያ መሆኑ ቀርቶ ለሆድ መገንቢያ ሲሆን! እናማ… ሆድ በጎመን ሳይሆን በዱቤ የሚደለልበት ጊዜ መጣላችሁ፡፡ (እኔ የምለው…ብድር ከቤት ወደ ቅርጫ የዞረው ይሄ የሊዝ ነገር ይሄን ያህል ሆድ አስብሶናል ማለት ነው! ቂ…ቂ…ቂ…)

የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… የአንድ ክብደቱ ትንሽ አለፍ ያለው ሰውዬ ታሪክ ትዝ ይላችኋል? እንዴት መሰላችሁ… ሰውዬው በጧት ተነስቶ ቁና፣ ቁና እየተነፈሰ ይሮጣል፡፡ ጓደኛው በዛ ሰዓት የመሮጡን ምክንያት ሲጠይቀው “ክብደት ለመቀነስ ነው” ሲል ይመልስለታል፡፡ ጓደኛ ሆዬ ምን አለው መሰላችሁ… “አንተ፣ አይደለም በሩጫ በኦፕራሲዮንም አትቀንስም፡፡” እንዲህ ከመባል አንድዬ ይጠብቀንማ! እኛ ሩጫ ሳንል፣ ኦፕራሲዮን ሳንል… ይኸው ‘ናቹራሊ’ በግራም ሳይሆን በኪሎ እየቀነስን ያለነውን አያማክረንም ነበር!

የበሬው ሥጋ በሳምንት ያልቃል፣ የበሬው ‘ትዝታ’ ግን ይከርማል፡፡ ልክ ነዋ… ብድሩ በየወሩ ከደሞዛችን ላይ ሲቆነደድ “የዛ የበሬ ጦስ ነው…” ምናምን ማለታችን ይቀራል! ለነገሩ፣ ሰዉ እንዲህ ለመላምትም ለምንም ባስቸገረበት ዘመን ‘ትዝታ’ ጥሎ የሚያልፍ በሬ መገኘቱ..ይህንንስ ማን አየብን ያስብላል!

ግለም፣ ብድር ይስጡን… እኛም እንበደራለን…ደግሞ ለብድር! የምንፈልገውን ያህል ካላበደሩንም አገር እርዳታውና ብድሩ ሲቀንስባት “ምን ያቆናቁናችኋል!” አይነት ነገር ብላ እንደምትቆጣው፣ እኛም እየተቆጣን ትንሽም ቢሆን እናስጨምራለን!

ሀሳብ አለን…ለግዢውም፣ ለቅርጫውም አቅሙ ለሌለን…አለ አይደል… ‘ዳያስፖራዎች’ “ቅርጫ እንኳን መግባት ያቅትህ!” ምናምን ብለው እንዳይዘባበቱብን አሥር፣ አሥር ብር እየከፈልን ከበሬ ጋር ፎቶ የምንነሳበት ዕድል ይመቻችልን፡፡ ዕድሜ ለፌስ ቡክ፣ ለዩ ቲዩብ ምናምን… ፎቶውን አንዴ ‘ለዓለም’ እንበትነዋለና! (ስሙኝማ…አል ጀዚራዎች ከሲታው በሬና ከሲታዎቹ እኛ ጎን ለጎን ያለንበትን ፎቶ ብልጭ አድርገው… “ከሁለቱ በሬው የትኛው ይመስላችኋል!” አይነት ‘ሳታየር’ ምናምን ነገር ሊሠሩብን እንደሚችሉ መጠርጠሬ በመዝገብ ይስፈርልኝማ!) እናማ…‘ዳያስፖራዎች’ በሩን እንኳን አልፈውት የማያውቁት ህንጻ ጎን ፎቶ እየተነሱ እንደሚልኩልን፣ እኛም ከ‘ጣፊያው’ እንኳን የማይደርሰንን በሬ ከጎን አድርገን ብንነሳ ምን ሀጢአት አለው! ከተሞክሮ መማር ማለት እንዲህ አይደል! ቂ…ቂ…ቂ…

እናማ… በ‘ኢለቨን ፐርሰንት ግሮውዝ’ በሬ በብድር ካገኘን…አለ አይደል…ሰቨንቲን ምናምን ፐርሰንት ስንደርስ ይቺ ‘ስታምረን እየቀረችብን’ ያለችውን ዶሮንም በረጅም ጊዜ ብድር ሳናገኝ አንቀርም፡፡ ብቻ ከ‘ቤት ዱቤ’ ወደ ‘ሆድ ዱቤ’…አለ አይደል…አሪፍ ‘ትራንስፎርሜሽን’ አይመስለኝም፡፡

በድጋሚ እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁ! ሞተው በድን የሆኑና እየሞቱ ያሉ በጎ፣ በጎ እሴቶቻችንን ትንሳኤም ለማየት አንድዬ ያብቃንማ!

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

Read 3004 times Last modified on Saturday, 14 April 2012 12:01