Saturday, 14 April 2012 11:52

ሞትና ሢኦል ተሸነፉ ፤ ኃጢያትና መርገምት ወደቁ

Written by  ከበደ ደበሌ ሮቢ
Rate this item
(1 Vote)

የቤተ ክርሥቲያን ራስ የሆነው ኢየሡሥ ክርስቶስ፤ ከ2000 ዓመታት በፊት በእሥራኤል ፍልሥጤም ሠላሣ ሶስት ዓመታት እንደ ሠው ሥጋ ለብሶ ከኖረ በኋላ፤ ዓርብ ዕለት ከቀኑ በዘጠኝ ሠዓት ግድም በጌተሠማኒ ጐሎጐታ ሲሰቀል ኃጢያትና መርገምት አብረውት ተሠቀሉ፡፡ የቤተ መቅደስ መጋረጃዎች ተቀደዱ፤ ፀሐይና ጨረቃ ተጋረዱ፡፡ ክርስቶስ ሲሰቀል አብረን ተሠቅለናል ብለው ያምናሉ ክርስቲያኖች፤ ሞትን ድል አድርጐ ሲነሳም አብረን ተነስተናል፡፡ ኢየሡሥ ክርስቶስ ዓርብ ዕለት ተሠቅሎ ቅዳሜ ሌሊት ለእሁድ አጥቢያ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሠዓት ግድም ከሞት ተነሥቶአል፡፡ ህያውን ከሙታን መሀል ስለምን ትፈልጋላችሁ፤ ኢየሡሥ ተነስቶአል ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ይሄ ሞትን አሸንፎ የመነሣት ቅጽበትና ሂደት ነው በክርስቲያኖች ዘንድ ትንሣኤ ብርሃን የሚሠኘው፡፡

ኦርቶዶክስ ካቶሊክና ወንጌላውያን ኢየሱስን እግዚአብሔር ወልድ (የእግዚአብሔር ልጅ) ሲሉት፤ የይሆዋ ምሥክሮች ደግሞ የእግዚአብሔር ልጅና የበኩር ፍጡር ነው ብለው ያምናሉ፤ ሙሥሊሞችና ባሃኢዎች ነቢይ ይሉታል ኢየሡሥን፤ አይሁዶች ተራ ሠው ነው ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ ታላቅ ሰብዕና ያለው ነው ይላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ሥፍራ መሲሁ (አዳኙ)፤ የታረደው በግ፤ የዓለም መድኃኒት (መድኃኔዓለም)፤ አማኑኤል፤ ይለዋል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት በተነሣበት (ትንሣኤ ብርሃን በሆነበት) ጊዜ፤ እርሱ ከመወለዱ በፊት እንኳ ሞተው የነበሩ ከመቃብር ወጥተው በቅድስት ከተማ ሲዘዋወሩ ታዩ (ትንሣኤ ሙታን ሆነ) ተብሎ በታላቁ ክርስቲያናዊ መጽሐፍ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ አዲስ ኪዳን ላይ ተጽፎአል፡፡ ስለዚህም ነው በትንሣኤ ብርሃን ሞትና ሲኦል የተሸነፉት፤ ኃጢያትና መርገምት ወደቁ የሚባለው፡፡ የመላው ዓለም ክርስቲያኖች ይሄንን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት የተነሳበትንና ትንሣኤ ብርሃን የሆነበትን ዕለት ሀሴት በማድረግ በታላቅ ክብርና ፍሰሀ የሚያከብሩት በዚህ ምክንያት ነው፤ በመሲሁ መሠቀል ዓለም ስለዳነ፤ የኃጢያት ሥርየት ስለሆነ፤ ዘላለማዊ ህይወት…፡፡

ለሁለት ወራት ያህል በፆምና በፀሎት ሲተጉ የቆዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን እና ሌሎች የክርስቲያን ክፍሎች ክርስቲያን ምዕመናን በትንሣኤ ብርሃን ፋሲካ ይሆንላቸዋል፤ በሆታ በሽብሸባ እና በዝማሬ በዜማ፣ በቅዳሴ  ደስታና ፀጋ ተመልተው ኢየሱስ ከሞት ተነስቶአል እያሉ ፋሲካን በተድላና በደስታ፤ በፍቅርና በሀሴት ይቀበሉታል፡፡

እንደ ማንኛውም ታላቅ አስተሳሰብ የክርስቶስ ኢየሱስ ክቡር አስተምህሮዎች በመጀመሪያ እምብዛም ተቀባይነት አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህ ያ ሁሉ የአይሁድ ህዝብ ለሮማዊው ገዢ ለጲላጦስ ስቀሎ ስቀሎ ስቀሎ ብለው አሣልፈው ሰጡት፡፡ ወንበዴውን በርባንን ፍታና ኢየሱስን ስቀለው አሉት፡፡ የጲላጦስ ሚስት ክላውዲያ የመሲሁን ንፅህና በህልሟ አይታ ነበርና ለንጉሥ ባሏ፤ ይህ ሰው ንፁህ ነውና በዚህ ሰው ላይ አንዳች ክፉ እንዳታደርግ ስትል አስጠነቀቀችው፡፡ ጲላጦስም ኢየሱስን የአይሁድ ህዝብ በከሰሰውና ባጐሣቆለው ሀሳዊ መሢህ (የሀሠት አዳኝ) እያለ በተሣለቀበት ወቅት፤ በዚህ ሠው ላይ አንዳች አላገኘሁበትም ነው ያለው በተደጋጋሚ፡፡ ይሁንና በዚያ ዘመን የጥንት ሮማውያን ከአውሮጳ ወደ ሠሜን አፍሪቃና ወደ መሀከለኛው ምሥራቅ መጥተው አይሁድን በወታደራዊ የበላይነት ይገዙ ስለነበር በዚህም ምክንያት የጲላጦስ ሥልጣን የፖለቲካ ሥልጣን በመሆኑ፣ የአብዛኛውን ህዝብ ድምጽ (ማጆሪቲውን) መስማት ወይም ማክበር ነበረበት፡፡ በሽፍትነት ዘመን ወላጅ አባቱን ጨምሮ የገደለውን ወንበዴውን በርባንን ፈትቶ ኢየሱስን ስቀሉት ያላቸው እና አሳልፈው የሰጡትን መልሶ አሳልፎ የሰጣቸው፤ አይሁድ ሁሉ ሁሉም በአንድ ድመጽ ስቀሎ (ኢየሱስን ስቀለው) ስላሉት ነው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ተሸክሞ እየተገረፈ እየተሰደበና እየተዋረደ፤ በጉሥቁልናና በድቀት በጌተሠማኒ ሽቅብ ወደ ጐሎጐታ ተራራ አናት ሲወሠድ ያዘኑለት ጥቂት ሴቶችና መስቀሉን ጥቂት መንገድ ስለተሸከመለት ህመሙ የተሰማው ዮሴፍ የተሰኘ አይሁድ፤ እንዲሁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዘሙርት ናቸው፡፡ የጲላጦስ ሚስት ክላውዲያ የግርፋቱን ቁስል ደምና ላብ እንዲጠርግበት ተደብቃ ፎጣ ሰጥታዋለች፡፡ በመገረፉ ቁስል ተፈውሰሃል ይላል መጽሐፍ ቅዱስ፡፡

አይሁድ ክርስቶስ ከመወለዱ አስቀድሞ በጥንት የብሉይ  መፃሕፍት ይመጣል ተብሎ ቃል የተገባልን መሲህ መጥቶ፤ ከሮማ ባርነት አርነት ያወጣናል ብለው ሲጠብቁ የነበሩት፤ ሮማውያን አይሁዶችን በወታደራዊና በፖለቲካ የበላይነት ተጭነው ይገዙ ስለነበር ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሄም ከተወለደ በኋላ፤ ከሮማ ባርነት ብቻ ሳይሆን ከራሳችሁ እሥራት መፈታት አለባችሁ ነው ያለው ለህዝብ ሁሉ፡፡

የአይሁድ ህዝብ ግን አዳኛችሁ ይመጣል ተብሎ በእግዚአብሔር አብ ቃል የተገባው ትክክለኛው መሢህ (እውነተኛው አዳኝ) ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ለመቀበል አልቻሉም፤ ወይም አልፈቀዱም፡፡ ስለዚህ አሁን ከ2000 ዓመት በኋላ (በዛሬው ዘመን) እንኳ የወይን ጠጃቸውን በሁለት ብርጭቆ ሞልተው ወይ አስሞልተው አሥር ደቂቃ በፀጥታ የሚጠብቁ አይሁዶች አሉ፡፡ በነዚህ አሥር ደቂቆች ውስጥ በጥንት ነቢያት ይመጣል ተብሎ የተነገረን መሢህ ከመጣ፤ ይሄንን ወይን አብረን እንጠጣዋለን ብለው ነው ከሁለት ብርጭቆ ወይን ጋር አሥር ደቂቃ የሚጠብቁት፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሠቀለና ከተቀበረ በመቃብሩ ላይ ትልቅ ደንጊያ ከተጫነ በኋላ፤ ጲላጦስ የናዝሬቱ ኢየሱስ የይሁዳ ንጉሥ ብሎ ፃፈ፡፡

በዚህን ጊዜ አይሁዳውያን ስለምን እንደዚህ ትጽፋለህ ብለው፤ ለዚህ ሀሳዊ መሲህ የንጉሥነት ክብር አይገባውም በሚል መንፈስ ጠየቁት፡፡ ሮማዊው ንጉሥ ጲላጦስም የፃፍኩትን ጽፌያለሁ ብሎ በጽንአት ቆመ፡፡ ጲላጦስ ይህን ያደረገው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የእግዚአብሔር አብ ኃይልና ክብር መኖሩን በመንፈሱ ወይም ከፍ ባለ አእምሮው በውስጡ ያውቅ ስለነበር ነው፡፡

ህዝቡ እንዲፈርድበት አሣልፎ የሰጠውን መሢህ ይሰቅሉት ዘንድ ለአይሁድ (መልሶ) አሣልፎ የሠጣቸው ደግሞ የሮማ ገዢ የበላዮቹን የፖለቲካ መርሆ ማክበር ስላለበት ወይም ስለነበረበት ነው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ በመጀመሪያ በአካል የታየው ለማርያም መግደላዊት ሲሆን፤ የተገለጠው ደግሞ ለማኦስ መንገደኞች ነው፡፡

ማርያም መግደላዊት ኢየሱስን በጣም ትወድደው ስለነበር በሌሊት ኢየሱስ በተቀበረበት የመቃብር ሥፍራ ተገኘች፡፡ ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ (ተፈንግሎ) አየች፡፡ ጌታዬን ወዴት ወስደውት ይሆን ብላ ማልቀስ እንደጀመረች ድምጽ ሰማች፤ በዚህን ጊዜ ረቡኒ ብላ በድንጋጤ ተጣራች፡፡

በሂብሩ ወይ በእብራይስጥ ቋንቋ ረቡኒ ማለት መምህር ሆይ ማለት ነው፡፡ አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ?...ህያውን ከሙታን ሥፍራ ስለምን ይፈልጉታል፤ ኢየሱስ ተነስቶአል…የሚል ድምጽ በመጣ ጊዜ የመግደላዊት ማርያም ለቅሶ ሀዘንና ድንጋጤ ወደ ደስታ እና መደነቅ ተቀየረ፡፡ የማኦስ መንገደኞች አጋሰሶቻቸውን እየነዱ ከንግድ ሲመለሱ፣ ሀዘን ባጠለመው ፍቅር እያወሩ ነበር፡፡ ያንን የዮሴፍ ልጅ ሰቀሉት፤ እንዴት ዓይነት በጐ ሰው ነበር መሠላችሁ…እያሉ ያወራሉ፡፡ አንድ የማያውቁት ሰው አብሮአቸው ከነሱው ጋር እያወራ ይጓዛል፡፡ ብዙ ተጉዘው መኖሪያ መንደራቸው ደረሱ፡፡ እንስሶቻቸውን አራግፈው ወደ ቤታቸው ሲገቡ ያ የማያውቁት ሰው ወደ ቤታቸው ገብቶ አረፍ እንዲል ይጋብዙታል፡፡ ሁሉም በአንድነት ሆነው ተሰባስበው እንደተቀመጡ ገበታ ይቀርባል፤ ያ የማያውቁት ሰው ገበታውን ባርኮ ቀድሶ መብሉን ቆርሶ ለሁሉም ቡራኬ ሠጣቸው፡፡ ቆርሶ የሠጣቸውን ቡራኬ በቀመሱ ጊዜ የውስጥ ዓይኖቻቸው ተገለጡ፤ በዚህም ጊዜ እንዴ ይሄ የዮሴፍ ልጅ አይደለም እንዴ? ለካ በመንገድ ላይ በተናገረ ቁጥር ልባችን ይቀልጥ የነበረው ስለዚህ ነው…እያሉ እጅጉን ተደነቁ፡፡ እነሱ በመደነቅ ድንጋጤ ውስጥ ሳሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዓይናቸው ተሠወረ…

ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተፀንሶ፤ በከብቶች በረት ውስጥ ከተወለደ በኋላ በምድር ላይ የኖረው ለሠላሣ ሶስት ዓመታት ነው፤ ከዚህ ዕድሜ በላይ ኖሮአል የሚሉ የክርስቲያን የመለኮት ሊቃውንት አሉ፡፡ ሲወለድ ለህዝብ ሁሉ የምሥራች ተነገረ፡፡ እነሆ ደስ ይበላችሁ አዳኛችሁ በዳዊት ከተማ ተወለደ፡፡ ዕድሜው ሠላሣ ዓመት ሲሆን በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቁ ዮሐንስ አማካይነት ተጠመቀ፡፡ ሲጠመቅም በእርግብ አምሣል የእግዚብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ አረፈ፡፡ ድምጽም ከሰማያት መጣ:- የምወድደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት…፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ድምጽ በብዙ ሥፍራዎች የሚገልፀው እንደ ብዙ ውሆች ድምጽ ብሎ ነው፡፡መሢሁ ዕድሜው ሠላሣ ዓመት ሲሞላ ለአርባ ቀንና ሌሊት በበረሃ በፆምና በፀሎት ከተጋ በኋላ፤ ቀጥለው ባሉት ሶስት ዓመታት ህዝቡን አስተማረ፡፡ ድውያንን ፈወሰ፤ ሙዋቲውን አስነሳ፡፡ የታመሙትን አዳነ፤ አጋንንትን አወጣ፤ ለዓለም ሁሉ ታላቅ ተስፋን ሰጠ፡፡ እንደሚሰቀል በእርሱም ሞት ዘላለማዊ ህይወት እንደሚሆን፤ ሞትና ሲኦል እንደሚሸነፉ፤ ኃጢያትና መርገምት እንደሚወድቁ፤ በሶስተኛውም ቀን ሞትን ድል አድርጐ እንደሚነሳ የተስፋ ቃል ሠጠ፡፡ በተሰቀለና  በተቀበረ ማግሥት አይሁድ፡- ያ ሀሣዊ መሢህ በሶስተኛው ቀን ከሞት እነሣለሁ ብሎን ነበር … በማለት ያሾፉ ያላገጡት ስለዛ ነው፡፡ ኢየሡሥ ክርስቶስ አርባ ቀንና ሌሊት ሲፆም በዲያብሎስ ተፈትኖአል፡፡ ዲያቢሎስ በአብዛኛው ኢየሡሥን የፈተነው ወይ የተፈታተነው ተስፋ በማስቆረጥ ነው፡፡ አሁን ይህቺን ዓለም አንድ ሠው ሊለውጥ የሚችል ይመስልሃል? እያለ ዙሪያውን ይዞረዋል፡፡ እንደሚያገሣ አንበሳ ዙሪያውን ይዞረዋል ይላል መጽሐፍ ቅዱስ፡፡ ኢየሡሥ ለፀሎት ከተንበረከከበት ይነሣና እባቡን በኃይል ይረግጠዋል፡፡ በመፅሀፍ ቅዱስ ላይ አንተም የዘንዶውን ራሥ ቀጠቀጥህ ለኢትዮጵያ ሠዎችም ምግብ አድርገህ ሠጠሃቸው … ተብሎ ተፅፎአል፡፡ ዲያብሎስ፡- እውነትስ የእግዚአሔር ልጅ ከሆንክ ይሄንን ድንጋይ ወደ ዳቦነት ቀይረው ሢለው፤ ሠው በእግዚአብሔር ቃል ጭምር እንጂ በእህል ብቻ አይኖርም ተብሎ ተፅፎአል ብሎ ነው የሚመልስለት፡፡ እውነትስ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ ከዚህ ገደል ላይ ተፈጥፈጥ ሲለው፤ ጌታ አምላክህን አትፈታተነው ተብሎአል ነው የሚለው ኢየሱስ፡፡ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በሁዳዴ የሚፆሙት ይሄንን የኢየሡሥ ክርስቶስን ፆም ፀሎትና የዲያቢሎስ ፈተና እንዲሁም በመሲሁ የመሠቀያ ወራት ጉሥቁልናውን ስቅለትና ትንሣኤውን መነሻና መሠረት አድርገው ነው፡፡ ኢየሡሥ ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ በምድር ላይ ለአርባ ቀናት ከደቀ መዘሙርቱና ከህዝቡ ጋር ቆይቶአል፡፡ ከአርባ ቀናት በኋላ ወደ ሠማያት አምላክ አርጓል፡፡ በመፅሀፍ ቅዱስ ከኢየሡሥ በተጨማሪ ወደ ሠማያት አምላክ አርገዋል የሚባሉ ኤሊያስና ሄኖክ ናቸው፡፡

በምድር ላይ በነበረባቸው አርባ ቀናት እርሡ ከሄደ (ወደ ሠማያት አምላክ ካረገ) በኋላ፡- የእውነት መንፈሥ  (የእግዚብሔር አብ መንፈሥ፤ መንፈሥ ቅዱስ …) ወደ ዓለም እንደሚመጣ በህዝቦች ውስጥም እንደሚሠራ የተሥፋ ቃል ሠጥቶአል፡፡ ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮዎች አንዱ የሥላሴዎች አንድነትና ሶስትነት (አንድነት በሶስትነት ሶስትነት በአንድነት) ትሪኒቲ (ምሥጢረ ሥላሴ) ነው፡፡ ይኸውም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የሚለው ነው፡፡ እግዚአብሐር አብ፡- የሠማያት አምላክ (አባት) ነው፤ ወልድ፡- የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሡሥ ክርስቶስ ነው፤ መንፈሥ ቅዱስ፡- የእውነት መንፈሥ የእግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ በሥመ አብ ወወልድ ወመንፈሥ ቅዱስ ይላሉ አበው ሲባርኩና ሲቀድሡ፡፡

ኢየሡሥ ክርሥቶስ ወደ ምድር ተመልሶ በታላቅ ግርማና ክብር እንደሚመጣም የተሥፋ ቃል ሰጥቶአል፡፡ ከእግዚአብሔር አብ በቀር እርሱ ራሱ ኢየሡሥ እንኳ ቢሆን በማያውቀው ጊዜ እንዲህ ነው እንዲያ ነው በማይባልበት ሁኔታ በድንገት ይመጣል፡፡ ይህ የተሥፋ ቃል ተግባራዊ በሚሆንበት ወቅት በዚህች ዓለም የሚታዩ ምልክቶች በመፅሀፍ ቅዱስ ላይ ተፅፈዋል፡፡ በዮሀንስ ራዕይ፡- ዮሀንስ የተባለው የእዚአብሔር ነቢይ ከኢየሡሥ ክርስቶስ ልደት በኋላ በፍጥሞ ደሤት ብቻውን ሆኖ የእግዚአብሔርን ድምፅ ይጠባበቅ ነበር፡፡ በዚህ መጠባበቅ ወቅት ለዮሀንስ በብርሀን መንፈሥ የተገለጠ ተአምራዊ መባል የሚያንስበት ድንቅ ክንዋኔ አለ፡፡ Revelation ይለዋል እንግሊዝኛው፡፡ ይህ ራዕያዊ ክንዋኔ ዕውን የሚሆነው መሢሁ (ኢየሡሥ ክርስቶስ) በታላቅ ክብር በደመናት ከሠማያት ሲመጣ ነው፡፡ ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ሃይማኖቶችም በመጨረሻ የሚመጣው የአምላክ ነቢይ ኢየሡሥ ነው ብለው የሚያምኑ አሉ፡፡ ኢየሡሥን ወዳጆቹ ደጉ መምህር ሆይ ሲሉት ደግ ለምን ትሉኛላችሁ ደግ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው ብሎ ይመልሥላቸዋል፡፡ በመፅሀፍ ቅዱስ ሌላ ሥፍራ ደግሞ ኢየሡሥ ክርስቶስ፡- እኔን ያየ አብን አየ ይላል፡፡

በዛሬው ዘመን ኢየሡሥ ክርስቶስ ከአሁን አሁን ይመጣል ብለው የሚጠባበቁ በርካታ የመላው ዓለም ክርስቲያን ምዕመናን አሉ፡፡ ነገ እሁድ መጋቢት 7 ቀን 2004 ዓ.ም ለኢትዮጵያውያን ክርሥቲያኖች ፋሢካ ነው፤ ትንሣኤ ብርሀን፡፡ ለአገሬ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ክርስቲያን ምዕመናን ከፍ ባለ አክብሮትና በቃል ለመግለፅ በሚቸግር ፍቅር፡- እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሠዎ!

ሠላምዎ ይብዛ! በፍቅር!

Soli.Deo. Gloria!

 

 

Read 7809 times Last modified on Saturday, 14 April 2012 11:58