Print this page
Monday, 13 November 2017 09:55

የኢትዮጵያ እግር ኳስ የኋሊት ጉዞ!

Written by  አበራ ገብሩ
Rate this item
(13 votes)

  ከሰሞኑ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ድርሻ ከሚኖራቸው አካላት አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በፕሬዚደንትነትና በሥራ አስፈጻሚ አባልነት የሚመሩ ወይም የሚያገለግሉ አካላት ምርጫ እንደሚካሄድ በሰፊው እየተገለጸ ይገኛል፡፡ እኔም እንደ አንድ ሀገሩን እንደሚወድ ዜጋ፤ ይህንኑ መሰረት በማድረግ የራሴን አስተያየትና እይታ፣ ሌሎች እግር ኳሱን የሚመለከቱ ሐሳቦችንና ጉዳዮችን ጨምሬ መጻፍ ወደድሁ፡፡
ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ምርጫ በተለይ ለፌዴሬሽኑ የፕሬዚዳንትነት ቦታ በእጩነት የቀረቡትን በሚመለከት በቅርቡ የቀረቡትን ሰዎች ስሰማ፣ በአእምሮዬ ብዙ ጥያቄዎች አነሳሁ፡፡ ይኸውም በመጀመሪያ ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትነት ቦታ በእጩነት እንደሚቀርቡ ከተገለጹት አራት ሰዎች ውስጥ ሶስቱ ቀድሞ በፌዴሬሽኑ ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡ አዳዲስ ሰዎች ወደ ፌዴሬሽኑ እንዲመጡ ለምን እንደማይደረግ አንዱ አጠያያቂ ጉዳይ ነው፡፡ እንደተገለጸው ከቀረቡት አራት እጩዎች አንዱ ብቻ ለፌዴሬሽኑ የኃላፊነት ቦታ አዲስ ሲሆን ሌሎቹን በሚመለከት ግን አንዱ፣ አሁን የሥራ ጊዜውን የሚጨርሰውን ፌዴሬሽን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት ግለሰብ ናቸው። ሁለቱ ደግሞ የቀድሞው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትና ም/ፕሬዚዳንት የነበሩ ናቸው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው አዳዲስ ሰዎች እንዲመጡ መበረታታት ሲገባቸው፣ ይህ እንደማይደረግ እያየን ነው፡፡ ነገር ግን ጥያቄው ለምንድን ነው እንዲህ የሆነው? የሚለው ነው፡፡ መልስም የሚሻ ነው፡፡ ሆኖም ከሁሉም በላይ የሚገርም ሆኖ ያገኘሁት፣ በተለይ ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ እጩ ሆነው የመቅረባቸው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡
 ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎች መልስ የሚሹ ይመስለኛል፡፡ ይኸውም፡-
1.   እኒህ ሰው ከዚህ በፊት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት የነበሩ፣ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜም ፌዴሬሽኑ የትርምስ ቤት የነበረ መሆኑና የሥራ ጊዜአቸውንም ሳይጨርሱ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተገደዱ መሆኑ እየታወቀ፤
2.   ከጥቂት ጊዜያት በፊት ለሌላ ፌዴሬሽን (ለቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን) አጠያያቂ በሆነ ሁኔታ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡ ሰው፤ እንደገና በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ያንን ሳይለቁ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር እጩ ሆነው መቅረባቸው፤
3.   እኒህ ሰው ለቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት ሲወዳደሩ፣ የደቡብ ክልልን ወክለው ለመወዳደር ቢፈልጉም ክልሉ «አልወከልኳቸውም» በማለቱ ሌላ ክልል ማለትም፣ የትግራይ ክልል በእጩነት አቅርቧቸው መወዳደራቸውና ቦታውን መያዛቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በታች የተጠቀሱትን ጥያቄዎች ማንሳት እንችላለን፡፡
ክልላቸው እምነት ያልጣለባቸው ግለሰብ፤ እንዴት የሀገሪቱን የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን እንዲመሩ ይመረጣሉ?
ከዚያም አልፎ በዚህ ሁኔታ ለሌላ ተጨማሪ ኃላፊነት (ለኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንትነት) እንዴት ሊበቁ ቻሉ?
የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትም ሆነ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ለምንና እንዴት ቢፈለግ ነው፣ ከአሠራርና ሥርዓት ውጭ በሆነ መንገድ ድጋፍ የተደረገላቸው?
ክልላቸው ሊወክላቸው ያልፈለጋቸው ግለሰብ፤ ለምን ሌላ ክልል ውክልና ሰጣቸው? ወይም ለምን በሌላ ክልል እንዲሰጣቸው ተፈለገ? 
ምርጫ የሚያካሂዱት ሰዎች፤ ለምን ይህ ሆነ ብለው እንዴት አይጠይቁም? እንዴትስ በዚህ ሁኔታ ይመርጧቸዋል?
በተጨማሪም ያን ጊዜ ለቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን በእጩነት ሊያቀርባቸው ያልፈለገው የደቡብ ክልል፤ አሁን እንዴትና ለምን በእጩነት ሊያቀርባቸው ፈለገ?
4.   መጀመሪያ ክልላቸው ውክልና ሳይሰጣቸው፣ ውክልና እንደሰጣቸው ሆነው ነበር የቀረቡት፡፡ በኋላ ክልሉ «ውክልና አልሰጠኋቸውም» ሲል እሳቸውን መደገፍ ተፈልጎ ነው፣ ሌላ ክልል ውክልና እንዲሰጣቸው የተደረገው? መጀመሪያ ክልሉ ውክልና ሳይሰጣቸው፣ እንደሰጣቸው ሆኖ መቅረቡ በራሱ ሊያስጠይቅ አይገባም ወይ?
5.   ሰውየው በእጩነት ከቀረቡ በኋላ በአንድ የመገናኛ ብዙኃን ቀርበው፣ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ የሰሩትን መልካም ነገር ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ በእሳቸው የፕሬዚዳንትነት ዘመን ብዙ ሊጠቀሱ የሚችሉ ችግሮች እንደነበሩ ይታወቃል። ሆኖም እራሳቸው ስለ እራሳቸው መስካሪ በሆኑበት ሁኔታ መልካም መልካሙን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በብዙዎች እንደሚታወቀው፤ እሳቸው ፌዴሬሽኑን ይመሩ በነበሩበት ጊዜ መነሳቱን ባይፈልጉትም ከነበሩት ችግሮች በጥቂቱ፤ ፌዴሬሽኑ የትርምስ ቤት ሆኖ መቆየቱ፣ የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅተው፣ ዋንጫውን በጨዋታ አሸንፎ እዚሁ ሀገራችን ላይ ማስቀረት ሳይቻል ሲቀር፣ ተሸንፎ የወደቀውን የኢትዮጵያ ቡድን ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረጉት ተገቢ ያልሆነ አሣፋሪ ተግባር፣ ኢትዮጵያን ወክሎ እንደ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ባሉ የአፍሪካ የውድድር መድረኮች ላይ ተሳትፎ ለማድረግ፣ ወደ አፍሪካ ሀገር የሄደ ቡድን በደል ሲደርስበት ዝምታን መምረጣቸውና  እንደ ፌዴሬሽኑ ኃላፊነታቸውም እንደ ዜጋም ምንም አለማድረጋቸው እና ሌሎች ብዙ ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች፣ የዶ/ር አሸብርን ፍላጎት፣ ሀገራዊ ሳይሆን የግል ጠንካራ ፍላጎት ማለትም ከፍተኛ የሥልጣን ጥማትና ጉጉት እንዳላቸው የሚያሳይ ወይም በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል የግል ሰብዕናቸውን ለመገንባት የሚጥሩ ሰው እንደሆኑ ሁኔታው ያሳብቅባቸዋል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የዶ/ር አሸብር እጩ ሆኖ መቅረብ፣ ለእኔ አስገራሚ ሆኖብኛል፡፡  እንደ ዜጋ፤ የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል ብዬ በማሰብም፣ ፌዴሬሽኑ የግለሰቦች የሥልጣን ጥማት ማርኪያና የግል ሰብእና መገንቢያ ሊሆን ስለማይገባው፣ድርጊቱን ልንዋጋው የሚገባ ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
በእኔ እምነት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ፤ ለኢትየጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት ብቁ አይደሉም፡፡ በአሁኑ ሰአት የያዙት ቦታም ቢሆን ተገቢ ያልሆነ ድጋፍ ተደርጎላቸው እንጂ ስፖርቱን ለመምራት ወይም ለቦታው ብቁ ሆነው አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት እጩ ሆነው ሊቀርቡ አይገባም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱም የእሳቸው ዋና ፍላጎት የግል ፍላጎታቸው እንጂ ሀገራዊ ራዕይ ያላቸው ሰው እንዳልሆኑ ከላይ ከተገለጹት ሁኔታዎች ተነስቶ መገመት ይቻላል ወይም ስሜትና ዝንባሌ ኖሯቸው ወደ ስፖርቱ የመጡ አይመስለኝም፡፡ ስሜትና ዝንባሌ አስገድዶት የመጣ ሰው፤ በመጀመሪያ ስሜቱ ወዳዘዘው ስፖርት ፌዴሬሽን ሄዶ ለማገልገል ራሱን ያዘጋጅና ይወዳደራል እንጂ ሁሉም አያምረውም። ስለዚህ ዶ/ር አሸብር፤ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት እጩ ሆነው መቅረብ አይገባቸውም። ከበረቱ ራሳቸውን ከእጩነት ማግለል አለባቸው፤ አለበለዚያም የወከላቸው ክልል ውክልናውን ማንሳት ይኖርበታል እንጂ እጩ ሆነው መቅረብ አይገባቸውም። ይህ ሁሉ ካልሆነም መራጩ ሊመርጣቸው አይገባም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ማስቀመጥ የፈለኩት፣ የሀገራችን እግር ኳስ መሠረቱን ያጣ መሆኑን ነው፡፡ በቀድሞ ጊዜ እግር ኳስ በየአካባቢው በነበሩ ክለቦችና የክለቦች ውድድር ሰፊ ተሳትፎ ነበረው፡፡ የአሁኑ ትውልድ ይህን ስላጣ ስፖርት በተለይ ቀድሞ ይሳተፍበት በነበረው እግር ኳስ ላይ ተሳታፊ ከመሆን ይልቅ ተመልካች ብቻ ሆነ፡፡ የሚከታተለውና የሚመለከተውም የውጭ ሀገር ስፖርት ሆነና እሱ ሊያደርገው እንደማይችል እንዲሰማው የሆነ ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም ራሱ ከመሞከር ይልቅ የውጪውን አድናቂ ሆነ፡፡ የተሳታፊው ቁጥር በጣም ቀነሰ ወይም አነሰ፡፡ ይህ በየአካባቢውና በየሰፈሩ ብዙ የስፖርት ሜዳዎችና በተለይ የእግር ኳስ ሜዳዎችና የስፖርትና የእግር ኳስ ክለቦች እንደነበሩ ማየት ላልቻለው ለአሁኑ ትውልድ ላይመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን በየአካባቢው የነበሩትን የእግር ኳስ ውድድሮች ለሚያውቅ ሰው፤አሁን በሀገራችን ስፖርት አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ከላይ እንደተገለጸው፤ በፊት ስፖርት ማንኛውም ትንሽ ልጅ በአካባቢው የሚደረገውን የእግር ኳስ ውድድር ስለሚመለከት፣ የእግር ኳስ ጨዋታን በጨርቅ ኳስ በመጫወት ገና በለጋነት እድሜው ይጀምራል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ይህ ባለመሆኑ ወጣቶች፤ በአካባቢያቸው ቶሎና በቀላሉ ወደሚያገኙትና መጥፎ ወደሚባሉት ሥነ-ምግባሮች እንዲያዘነብሉ ሁኔታው አስገድዷቸዋል፡፡ እንደ እኔ እምነት፤ እግር ኳስን የምናሳድገው እያንዳንዱ ክልል በሚያሳትፈው አንድና ሁለት ክለብ ሳይሆን በየሰፈሩና በየመንደሩ፣ ገና ከልጅነት ጀምሮ እንደ ስሜቱና እንደ ፍላጎቱ የመጫወትና የመሳተፍ እድል ሲያገኝ ነው፡፡ እያንዳንዱ ክልልም፤ በክልሉ ያለውን ስፖርት ማሳደጉ የሚረጋገጠው፣ ስፖርትን በየቦታውና በየመንደሩ በማስፋፋቱ እንጂ አንድ ክለብ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በማሳደጉ ወይም በማሳተፉ ሊሆን አይገባውም፡፡
ወጣቱ፤ የራሱን የስፖርት ክለብና የእግር ኳስ ክለብ እያቋቋመ፣ በየአካባቢው በሚያደርገው ውድድር፣ እግር ኳሳችንን ልናሳድገው እንደምንችል ፍጹም እርግጠኛ ነኝ፡፡ በየሰፈሩ፣ በየትምህርት ቤቱ፣ በፖሊስና በጦር ኃይሎች ካምፖችና በመሳሰሉት ሁሉ ስፖርቱን በማስፋፋት፣ በተለይ በየሰፈሩና በየመንደሩ በማስፋፋትና በሰፊው በማሳተፍ፣ መሠረቱን ልናሰፋው ይገባል፡፡ በዚህ ሁኔታ እግር ኳሳችንን እናሳድገዋለን የሚል እምነት አለኝ፡፡
ስፖርት ለሁሉም!          

Read 2998 times