Print this page
Saturday, 18 November 2017 12:42

ማስታወሻ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

 የሄድንበትን እንሄድበታለን ወይ?

   የዚህ መጽሐፍ ዓላማ ያለፈውን ለመውቀስ አይደለም፤ ያለፈ የሚመስለውንና አሁንም በውስጣችን ያለውን እውነት ለማውጣትና ለማሳየት፣ ለመናገርም ነው፤ ያለፈው ትውልድ የፈጸመውንና አሁንም በእኛ ውስጥ ያለፈውን ማውጣት ያለፈውን መውቀስ ሳይሆን ያለውን ለማጽዳት መሞከር ነው፤ አንዳንድ ሰዎች ቀድመው እንደተገነዘቡት አውቃለሁ፤ ለምሳሌ ወይዘሮ ባዩሽ በፌስቡክ የሚከተለውን ብላለች፡- -- ‹‹ኢትዮጵያዊ ራሱን ከመውደድ ያልወጣን ነን፤ አገራዊ ስሜት አልገባንም፡፡›› (ኢትዮጵያዊያን ራሳችንን ከመውደድ አልወጣንም፡፡) የኔ ዓላማ ያለውና ወደፊት የሚመጣው ራሱን ለማስተካከል ራሱን በአለፉት ውስጥ አይቶ ራሱን እንዲታዘብ ነው፤ ራሱን ታዝቦ ራሱን እንዲለውጥ ነው፡፡
በተለያዩ መንገዶች የረዱኝን ብዙ ሰዎች ለማመስገን እፈልጋለሁ፤ ነገር ግን ዘመኑ ወንጀል በንክኪ በሰዎች ላይ የሚለጠፍበት ስለሆነ ማመስገን ማስወንጀል ይሆናልና በደፈናው እግዚአብሔር ከጨለማ ያውጣንና ስሞቻችሁን እየጠራሁ እንዳመሰግናችሁ ያብቃኝ በማለት አልፈዋለሁ፡፡
በ966 አንድ ትንሽ ጽሁፍ ‹‹ኢትዮጵያዊነት፡- ልማት በኅብረት›› በሚል ርእስ አሳትሜ ነበር፤ በዚያ ጽሑፍ ውስጥ የተማሪዎች ንቅናቄ የሚባለውን በጨረፍታ ነቅፌው ነበር፤ አራት ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ ንዑሳን ምሁራን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በረዥሙ ልባሼ እንዳሸጥ አድርገው አንጀታቸውን አራሱ፤ በዚያን ጊዜ እኔ በፓርላማው ለመርማሪ ኮሚስዮን በከፍተኛ ድምጽ እኔ ሳልፈልግ በመመረጤ ተቃጥለውም ነበር፤ ከአራቱ ንዑሳን ውስጥ የኅሊናውን ሬሳ ተሸክሞ የቀረው አንድ ብቻ ነው፤ ሦስቱ የመጨረሻው ጥሪ ደርሷቸው ሄደዋል፤ ይህንን የማነሣው በአገርና በሕዝብ ጉዳይ ጽፎ ወይም ተናግሮ ከየጎሬአቸው እየወጡ የሚሳደቡትንና የሚወነጅሉትን ችላ ለማለት ግድ መሆኑን ለማመልከት ነው፤ በነዚህ ሰዎች ስድብ ተስፋ የምንቆርጥ ከሆነ ሁላችንም ተስፋ-ቢስ እንሆናለን፤ ጦር የሚወረወርብን ከፊትለፊት ብቻ ሳይሆን ከጎንም ነው፤ ትግሉ ከገዢዎቹ ጋር ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ ነን ከሚሉ የሥልጣን ጥመኞች ጋርም ነው፡፡
ሌላም ነገር ለማስታወስ እፈልጋለሁ፤ የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት ግድም ጌቶቻችን ገና የተሳለ ጥርሳቸውን ማሳየት ሲጀምሩ አካሄዳቸው ስላላማረኝ ‹‹የክህደት ቁልቁለት›› በሚል ርእስ አንድ ትንሽ መጽሐፍ አሳትሜ ምን ያህሉ እንደገባው፤ ከገባውም ውስጥ ምን ያህሉን ለተግባር እንደቀሰቀሰው አላውቅም፤ ኢትዮጵያውያን የመናገር እንጂ የመደማመጥ ችሎታ የለንም፤ ስለዚህም አብዛኛው ሲንጫጫ እኛን ለመጉዳት ተግባር የተሰለፉት ሥራቸውን ሲሠሩ እያለቀስን ቆመን እንመለከታቸዋለን፤ ሲሞቱም እናለቅሳለን፤ ለውጭ ተመልካች ጭቆናውና አፈናው፣ ሕግ-አልባነቱ የተስማማን ይመስላል፡፡
ዛሬ ሁላችንም የምናለቅስበት ዕለት የደረሰ ይመስላል፤ ለጨቋኞቹ ገዢዎቻችን የገነቡት ሁሉ የማያድሩበት ቤት እየሆነባቸው ተጨንቀዋል፤ በትዕቢት ዓይኖቻቸውና ልቦቻቸው ተደፍነው ሃያ አምስት ዓመታት ቀርቶ ሃያ አምስት ቀኖች አርቆ የማየት ችሎታ እንደሌላቸው በብዙ መንገድ ብዙ ጊዜ አሳይተውናል፤ ያከማቹት ብር ነፋስ የሚወስደው እየሆነባቸው ነው፤ መሰብሰቡም እየከበደ ነው፤ አንድ ማን እንዳለው የማላውቀው የእንግሊዞች አባባልን ያስታውሰኛል፡- ምንም ሳይጨምር ሁልጊዜ የሚያወጣ ቶሎ ብሎ መጨረሻው ላይ ይደርሳል፤ (By always taking out and never putting in one soon reaches the bottom.) ገዢዎቻችን ቢጠፉም ቢለሙም በሥራቸው ነው፤ እኛ ግን የምንጠፋው በዝምታችንና በወላዋይነታችን ነው፡፡
የኢትዮጵያን ሕዝብ ጠባይና ታሪክ ለተረዳ ያንዣበበብን አደጋ ቀላል አይደለም፤ ከጀመረም በቀላሉ የሚመለስ አይሆንም፤ እንዳያጫርሰን አንጀምረው፤ ከ1966 ዓ.ም ቀደም ብሎ የጀመረው የጎረምሶች የሥልጣን ጥም አሁን ያገረሸበት ይመስላል፤ ከሆነላቸው አዲሶቹ ጎረምሶች ደግሞ ለሚቀጥሉት ሀምሳ ዓመታት ያህል ያተራምሱናል፤ ቁጭ ብሎ መጠበቅና ማየት ነው!
ቅድመ-ነገር
ከሰባ ዓመት ዕድሜ በላይ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን ይህ መጽሐፍ ለብዙዎች የቡና ወሬ፣ ምናልባትም ለጥቂቶች አእምሮን የሚኮረኩር ነገር ያገኙበትና ያዳብሩት ይሆናል፤ መጽሐፉ አእምሮአቸውን የሚኮረኩራቸው ኢትዮጵያውያን የወደፊትዋን ኢትዮጵያ ለመቅረጽ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አልጠራጠርም፤ የማስተዋል አድማሳቸውን ሰፋ አድርገው ለረጅም ጊዜ ጥልቀትና ዘላቂነት ባለው የሚለዋወጥ ለውጥ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አእምሮው እንዲነቃ፣ ኅሊናው እንዲበራ፣ ልቡ ከቂምና ከክፋት እንዲጸዳ አድርጎ ወደጠመዝማዛው የዳገት ጉዞ ውስጥ የሚያስገባውን መንገድ እንዲያገኝና እንዲከተል ማገዝ ይችላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ደግሞ የአጠቃላዩን የዓለም ሁኔታ በልዕለ ኃያላኑ በአሜሪካ፣ በሩስያና በአውሮፓ ፉክክር የሚታመስ መሆኑን፣ የመሀከለኛው ምሥራቅ በእስራኤልና በአረቦች ጥላቻና ፍጥጫ እየቆሰለ የሚደማ መሆኑን፣ የአፍሪካ ቀንድ በልዕለ ኃያላኑና በመሀከለኛው ምሥራቅ ወኪሎቻቸው ለብጥብጥ እየተዘጋጁ መሆናቸውን መገንዘብ ያለምንም ጥርጥር የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመቋቋም ይረዳቸዋል፤ የዓለም ሕዝብ ተያይዟል፤ አንድ ቆራጥ ሰው ብቻውን የዓለምን ሕዝብ ማተራመስ የሚችልበት ዘመን ነው፤ በጥቂት ግለሰቦች አልጠግብ-ባይነት በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በደሀነት የሚደሙበትና የሚሞቱበት ሁኔታ በሙሉ-ዓለም (GLOBALIZATION) ሥርዓት እየታየ ነው፡፡
ዋናው ነገር የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፍርሃት ቆፈን ማውጣት፣ እንደልቡ እንዲያስብና ሀሳቦቹን በግልጽና በአደባባይ ለመወያየትና ለመከራከር እንዲችል ለማድረግ፣ በፈለገው መንገድ እየተደራጀ መሪዎቹን የመምረጥ መብት በተግባር መግለጹን ማረጋገጥ ቁልፍ የእድገት ለውጥ ጠቋሚዎች ይሆናሉ፤ በተለይም የኢትዮጵያ ወጣቶች የእነዚህ መብቶች የተረጋገጡ ባለቤቶች እስቲሆኑ ድረስ የመረረ ትግል ማካሄድ የማይቀር ይመስላል፤ አብዛኛው ወጣት ይህንን ዓይነት የመብቶች ትግል የሚደግፍ ሳይሆን አይቀርም፤ ነገር ግን ለወጣቶች በጣም አስቸጋሪ የሚሆነው ከመብቶች ጋር እኩል ሆነው ጎን ለጎን መሄድ የሚገባቸውን ግዴታዎች መቀበል ነው፤ የመብቶችና የግዴታዎች ሚዛን ካልተሰራና ሁለቱንም እኩል የሚያስተናግድ ሥርዓት ሳይኖር የሕግን የበላይነት መትከል አስቸጋሪ ይሆናል፤ የመብቶችና የግዴታዎች መቆራኘት በቅድሚያ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
ነገ የወጣቶች ነው፤ ትናንት የሽማግሌዎች ነበር፤ ይባላል፤ በትክክልና በጥሞና ካልታሰበበት ይህ የተለመደ አባባል ስሕተተኛ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው፤ እኔ አርባ ዓመት አልፎኝ ወጣት በነበርሁበት ጊዜ ኢትዮጵያን የሚያሽከረክሯት ሽማግሌዎች ነበሩ፤ ‹‹ይሄ ልጅ›› ይሉኝ ነበር! አርባ አራት ዓመት ግድም ሲሆነኝ ኢትዮጵያን የሚያሽከረክሯት ወጣቶች ሆኑና ‹‹ይሄ ሽማግሌ›› ይሉኝ ጀመር! ‹‹ይሄ ልጅ›› ሲሉኝ ልሠራ የምችለውን ብዙ ነገር የማልችል አደረጉኝ፤ እንደዚሁም ‹‹ይሄ ሽማግሌ›› ሲሉኝ በጣም ደካማና ኋላ-ቀር አድረጉኝ፤ ራስን ከፍ ለማድረግ ሲባል ሌላውን ዝቅ ማድረግ የሥልጣን ጥመኞቹን የሚረዳ ቢሆንም ማኅበረሰቡን በጣም ይጎዳል፡፡
አሥራ አምስት ዓመት ከሆነኝ በኋላ የሚበልጠውን ዕድሜዬን የተገዛሁት በወጣቶች ነው፤ እናትና አባቴም የተገዙት በወጣቶች ነበር (ዚያሱ፣ ዘውዲቱ፣ ተፈሪ፣ … መንግሥቱ፣ መለስ)፤ ስወለድ የተሰጠኝ ገዢ ኃይለ ሥላሴ ጉዳቸውን በካባቸው ውስጥ ደብቀው ለአርባ ዓመታት ያህል ገዙ፤ እምሩ ኃይለ ሥላሴ፣ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም፣ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ ማርቲን ወርቅነህ፣ መኮንን ደስታ፣ ይልማ ዴሬሳ፣ … በወጣቱ ተፈሪ እየተደቆሱ ፍሬ-አልባ ሆነው የቀሩ ወጣቶች ናቸው፤ በመንግሥቱ ኃይለ ማርያምም የአገዛዝ ዘመን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች፣ በሆነው ባልሆነው በመንፈስ ብቻ ሳይሆን በአካልም ተደቁሰዋል፤ በወያኔ የአገዛዝ ዘመንም የባሰበት ነበር።
ገነ የወጣቱ ነው ስንል፤ ያለፉትን አርባ ዓመቶች (ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ) በጥሞና እንድናስብ እንገደዳለን፤ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ ሲወድቅ ሳይረከብ እየዘለለ ወንበሩ ላይ የወጣው ወጣት የሚባለው ነበር፤ ለአለፉት አርባ ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያን በቁልቁለት እየነዳ፣ ለሥልጣን መገዳደልን ባህል አድርጎ ወንድምንና ወንድምን እያፋጀ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለችግርና ለችጋር፣ ለስቃይና ለመከራ፣ ለሙስና፣ ለስደትና ለአጉል የዕጽ ሱስ የዳረገ የጎረምሶች አገዛዝ ነው፤ የጎረምሶች አገዛዝ ያለፈውን አያውቅም፤ የሚመጣውን መገመት አይችልም፤ በጊዜያዊ ስሜት ብቻ እየተንደባለለ እንደ ቁልቁለት የሚያስደስተው መንገድ የለውም፡፡
(ከፕ/ር መስፍን ወልደ ማሪያም
“እንዘጭ! - እምቦጭ! የኢትዮጵያ ጉዞ” የተቀነጨበ፤ 2010 ዓ.ም)

Read 7396 times
Administrator

Latest from Administrator