Saturday, 14 April 2012 13:08

የባዩልኝ አያሌው ግጥሞች- “ህልመል ሜሌክ”

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(1 Vote)

በ1974 ዓ.ም በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን የቀይ ኮከብ ጥሪ አብዮታዊ ዘመቻን መነሻ አድርጎ በተፃፈው የበዓሉ ግርማ “ኦሮማይ” ረጅም ልቦለድ መጽሐፍ፤ በደርግ ወገን የቆሙ ገፀ ባሕርያት ስለ ኤርትራዊያን አቋም የሚነጋገሩበት ክፍል አለ፡፡ አንዱ ተናጋሪ አካባቢው በተለያዩ ዘመናት በጦር ወረራ ስለተፈፀመበት ሕዝቡ “የኃይል ሚዛኑ ማን ጋ ነው ያለው?” “ከበሮው ሞቅ ብሎ የሚሰማው የቱ ጋ ነው?” እያለ ድጋፍ ይሰጥ እንደነበር በምክንያት እየተነተነ ያቀርባል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ችግር ከጦርነት ጋር በተያያዘ ለብዙ ዓመታት በቀውስ ውስጥ ባለፈ አካባቢ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የተለያዩ ችግሮችን በተጋፈጠ ሕዝብ ውስጥም ሊከሰት ይችላል፡፡

ኧረ ምንድን ነን? ምንድን ነን? … ለአፍታ አለመጠየቅ

ለትውልድ ግድ አለመኖር እየነፈሰው መነጠቅ

ለማን? ለምን? አለማለት ከማንም ጋር መስሎ መውደቅ

ወይም ሸሽቶ ከዳር መውደቅ

እነዚህ ስንኞች ባዩልኝ አያሌው በ2003 ዓ.ም “ህልመልሜሌክ” በሚል ርዕስ ባሳተመው ሲዲ ውስጥ ከተካተቱት 20 ግጥሞች “ዝምታን ማስጌጥ” ከተሰኘው የተወሰዱ ናቸው፡፡ ግጥሙ ከያዛቸው ኃይለ ቃሎች መሐል “ሳይገባው የሚያጨበጭብ”፣ “ሳያምንበት ደጋፊ መስሎ የሚታይ”፣ “ሳይደሰት ለመሳቅ የሚሞክር” ሰው ቁጥር እየበዛ መጥቷል፤ ምክንያቱ ምንድን ነው? ሲል ይጠይቃል፡

ገጣሚው እነዚህን ስንኞች ለመቋረጥ ምን አነሳሳው? ምን ቢያይና ቢሰማ ነው ትላንትን እያደነቀ፣ ዛሬን ለመውቀስ የሞከረው? ዛሬ የሚታየው ችግር ትላንት ውስጥ አልነበረም? ዛሬ ባለው ችግር ውስጥ ያለው ጥሩ፣ አስደሳችና ተስፋ ሰጪ ነገርስ ምንድን ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ያስነሳል፡፡ ምክንያቱም ሰው በቀንና በማታ ሀሳቦቹ መሐል እንኳን ምን ያህል ሰፊ ልዩነት እንዳለገጣሚው “ያልተከደኑ አይኖች” በሚለው ግጥሙ እንዲህ ገልፆታል፡-

ሌ’ት እኮ ነው ሰው የማይዋሽ

ከህሊናው ጋር ችሎት ቆሞ

ቀኑንማ ምን አቅል አለን

ምንስ አለን ፅኑ መንፈስ

ካረፉበት መሸቀጥ ነው

ከመሰለን አብረን መፍሰስ

“ዝምታን ማስጌጥ” በሚለው ግጥም ውስጥ ያሉ ስንኞች በበዓሉ ግርማ “ኦሮማይ” ረጅም ልቦለድ መጽሐፍ ውስጥ ያለን አንድ ኃይለ ቃል እንዳስታወሰኝ ሁሉ የባዩልኝ አያሌው “ማነው ተጠያቂው?” የሚለው ግጥሙ ደግሞ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን “ማነው ምንትስ?” በሚል ርዕስ ከፃፉት ግጥም ጋር በይዘት ሳይሆን በቅርፅ ተመሳስሎብኝ፣ የአሁኑ የትላንቱን እንዳስታውስ አድርጎኛል፡፡ በአንጋፋውና ወጣቱ ገጣሚ ሥራዎች ውስጥ “ዳኝነት ለራስ ነውና” የምትለዋ ሞጋች ሐረግ መደጋገም ነው አንዱ ሌላኛውን እንዳስታውስ ያደረገኝ፡፡

“ሴት፣ እንባ፣ ሳቅ” የሚል ርዕስ ያለው የባዩልኝ አያሌው ግጥምም ስብሐት ገ/እግዚአብሔር በ”ሌቱም አይነጋልኝ” ልቦለድ መጽሐፍ ውስጥ “ህይወት ውስጥ እውነት ብቻውን አይገኝም፡፡ ህይወት እንደ ቡና በወተት ነው፡፡ ወተቱ እውነት ቡናው ውሸት ይሁን፡፡ ግን ይህ ልዩነት ባንጎላችን ውስጥ ይኑር እንጂ ሲኒው ውስጥ ባንድ በኩል ቡና በሌላ በኩል ወተት የለም፡፡ ሲኒው ውስጥ ያለው ቡና በወተት ነው፡፡ … ህይወት ውስጥም በቀኝ በኩል እውነት በግራ በኩል ውሸት አይገኝም፡፡ ህይወት ውስጥ የምታገኘው የእውነትና የውሸት ቅልቅል ነው” የሚለውን ኃይለ ቃል የሚያስታውሱ እነዚህ ስንኞች ቀርበዋል፡-

ማን ያውቃል እውነቱን

ማን ያውቃል ውሸቱን …

ሀሴት ነው መከፋት ከልብሽ ያለውን

ይልቅስ ልንገርሽ ከተቀላቀለው …

ሀሳብ አፋፍ ቆሜ ልቤ ያስተዋለው

ሳቅሽም እንባሽም ሁለቱም ውሸት ነው

አንቺ የተፈጠርሽው ከእነሱ መሀል ነው

እነሱም የኖሩት አንቺ ስላለሽ ነው፡፡

የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህንን “ተወኝ” የሚል ያስታወሰኝ የባዩልኝ አያሌው ሌላው ሥራ “እሽ አትበይኝ” ይሰኛል፡፡ በሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ግጥም በአፍቃሪዋ ብትገፋም፣ ለፍቅሯ ግን ክብርና ዋጋ የሰጠች ሴት ትታያለች፡፡ በባዩልኝ አያሌው ግጥም ማፍቀሩ ሳይጠፋ እንዲቆይለት እሽታን የፈራ ወንድ ታሪክ ነው የቀረበበት፡፡

ሰው መሆን መቼም አይመች

ያገኘውን ይሰለቻል

ዘመኑን ቀን ይታክታል

ስጋ ነፍሱን እንዳልሰዋ

የዛው ቀን ልቡ ይሰንፋል

ከቶስ ለምን ይመስልሻል

እሺታሽን የምሸሸው

እንዳፈቀርኩሽ እንድኖር

ሳገኝሽ እንዳልተውሽ ነው

አገራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ጉዳዮችን ማዕከል አድርጎ በሞትና ሕይወት፣ በተስፋና ስጋት፣ በፍቅርና ጥላቻ … ዙሪያ ከቀረቡት የባዩልኝ አያሌው ግጥሞች መሐል ጥቂት የማይባሉት ፍርሐትን በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ተሽከርክረውበታል፡፡ እሺ አትበይኝ ያለው አፍቃሪ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

“አይምሰልህ” የሚል ርዕስ ያለው ግጥም ሌላኛው ነው፡፡ ለሰው ልጆች ፍርሐት ከሚፈጥሩ ነገሮች አንዱ ሞት ነው፡፡ ሁሉም ሰው ለዘላለም መኖር ቢችል አይጠላም፡፡ የሚቻል ግን አይደለም፡፡ ዘላለማዊነትን ማስቀጠያ አንድ ብቸኛ መንገድ አለ፡፡ ጋብቻ መሥርቶ ራስን ተክቶ ማለፍ፡፡ “አይምሰልህ” የሚል ርዕስ በተሰጠው ግጥም ውስጥ የተረገዘው ልጅ እኔን ይመስላል እያሉ የሚጨቃጨቁ ባልና ሚስትን በቀዳሚነት ያቀርብና ምክንያታቸው ከፍርሐት ጋር የተያያዙ መሆኑን ቀጣዮቹ ስንኞች ያንፀባርቃሉ፡-

እንዳይመስልህ ላንተ አዝነው

አይምሰልህ ሰው ሁን ብለው

ከሞቱ ኋላም ነገ ባንተ መኖር ፈልገው ነው

“ባንክና ባንኮኒ” የሚል ርዕስ የተሰጠው ግጥምም በተዘዋዋሪም ቢሆን ይህንኑ ከፍርሐትና ስጋት ጋር የተያያዘ ሐሳብ ያነሳል፡፡ እኩል የሚደክሙ ሁለት ሰዎች የወር ደሞዛቸውን ሲቀበሉ፣ አንዱ ወደ ባንክ ቤት ሌላኛው ወደ ባንኮኒ (ቡና ቤት) የማዘወተር ልምድ እንዳላቸው የሚጠቁመን ግጥም በመጨረሻ፡-

ሰው ማለት እንዲህ ነው!

ተስፋ ያየ ‘ለታ ወደ ባንክ የሚሮጥ

ገንዘብ ላይ ሀሳቡን ደርቦ ‘ሚቀመጥ

አልኮል ላይ ተሳፍሮ ከሀሳብ የሚያመልጥ

በሲዲ የቀረቡት የባዩልኝ አያሌው 20 ግጥሞች ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) በክራር፣ አለሙ አጋ በበገና ያጀቧቸው ሲሆን የሙዚቃ ቅንብሩን ባደገ በቀለ (ኮራ ስቱዲዮ) እንደሰራው ተገልጿል፡፡

 

 

Read 5371 times Last modified on Saturday, 14 April 2012 13:17