Monday, 18 December 2017 13:00

የሰማያዊ ፓርቲ ህዝባዊ ስብሰባ ምን ሃሳቦች ተነሱበት?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

”ምሁራን ከአገራዊ የውይይት መድረክ ላይ ለምን ሸሹ?” ተብሏል
           
    ሰማያዊ ፓርቲ “ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት” በሚል መሪ አጀንዳ፣ ባለፈው እሁድ ታህሳስ 1 ቀን 2010 ዓ.ም በአምባሳደር ሲኒማ አዳራሽ ባካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ በመድረኩ እንደሚገኙ ከተጠቀሱት አንጋፋ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና ታዋቂ ግለሰቦች ውስጥ አብዛኞቹ ባይገኙም በተለያዩ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ችግሮች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል፡፡ ፓርቲው ህዝባዊ ስብሰባውን ለማዘጋጀት የተነሳው፣ አገሪቱ የገባችበትን የፖለቲካ አጣብቂኝ በማጤንና ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሴራ ፖለቲካን ወደ ጎን ትቶ፣ አገሪቱን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ መምራት የሚቻልበትን መንገድ ለማፈላለግ በማሰብ መሆኑን  አመራሮቹ ለተሳታፊዎች  ጠቁመዋል፡፡  
አገሪቱ የፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ ለመግባቷም፣ ለ10 ወራት የዘለቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነስቶ ብዙም ሳይቆይ፣ ከወትሮው የተለየ የፀጥታ ዕቅድ ማስፈለጉንና በየቦታው ዛሬም የዜጎችን ህይወት እየቀጠፉና ንብረት እያወደሙ ያሉ ግጭቶች አለመቆማቸውን፣ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ተግባራቸው በተቃውሞና በረብሻዎች እየተቋረጠ መሆኑን ፓርቲው በአስረጅነት ጠቅሷል፡፡ “የእነዚህ ችግሮች መነሻ ምክንያትና መፍትሄው ምንድን ነው?” ሲል ጠይቋል፤ ሰማያዊ ፓርቲ ባለፈው እሁድ ባዘጋጀው የህዝባዊ ስብሰባ መድረክ፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በመድረኩ ላይ እንደሚገኙ ከጠቀሳቸው ጎምቱ ምሁራንና ፖለቲከኞች መካከል ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፣ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፣ ዶ/ር ንጋት አስፋው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪው አቶ ብርሃኑ ደቦጭና ሌሎችም የተገኙ ሲሆን በወቅቱ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች ላይ የየግል ሃሳብና ምልከታቸውን ለስብሰባው ታዳሚ  አጋርተዋል፡፡
“ኢትዮጵያ በእርግጥም ችግር ላይ ነች” ሲሉ ንግግራቸውን የጀመሩት አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፤ በዚህች አገር ድሮ ችግር ሲፈጠር ተግሳፃቸው፣ ቁጣቸው የሚከበር ሽማግሌዎች እንደነበሩ፣ አሁን ግን ተሰሚነት ያለው ሽማግሌ መጥፋቱና ምክሮችን የሚቀበል አካል አለመኖሩ፣ ሀገሪቱን ከድጡ ወደ ማጡ እየወሰዳት ነው ብለዋል፡፡
በአፄ ኃይለ ሥላሴ፣ በደርግና አሁን ባለው የመንግስት ሥርአቶች በርካታ ጉዳዮችን መታዘባቸውን የጠቆሙት ፕ/ር መስፍን፤ በተለይ በንጉሱ ዘመን ቃላቸው የሚከበርና የሚፈሩ፣ ንጉሡ ራሳቸውም ከምክራቸውና ከቃላቸው የማይወጡ የሀገር ሽማግሌዎች እንደነበሩ አስታውሰው፣ ዛሬ ግን በተቃራኒው ሃይ ባይ ጠፍቶ፣ መደማመጥና መከባበር ጠፍቷል፤ የሀገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች መፍቻ ያጡትም ለዚህ ነው ይላሉ፡፡
“የዘቀጥንበት አዘቅት ጥልቅ ነው” ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ከዚህ አዘቅት ለመውጣት ወጣቱ ከተጠመደባቸው የተለያዩ ሱሶች ወጥቶ፣ ለሃገሩ የወደፊት ተስፋ የሚያስብ ወጣት፣ ቁጣቸውና ተግሳፃቸው የሚደመጥ ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ሊፈጠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል። “እያንዳንዳችን እንደ ህዝብ ከማሰባችን በፊት እያንዳንዳችን እንደ ግለሰብና እንደ ሰው ማሰብ ከቻልን ነው፣ ሀገሪቱን ከውድቀት ማዳን የምንችለው” ብለዋል - ፕ/ር መስፍን፡፡
“ከአፄ ምኒልክ ወዲህ ኢትዮጵያ ጥሩ መሪ አግኝታለች ብዬ አላምንም” ያሉት ሌላው የመድረኩ ተናጋሪ  ዓለማቀፉ የህግ ምሁር ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም፤”የአገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች አንዱ መነሻ፣ ጠንካራና ምሉዕ ሰብዕና ያለው መሪ አለመውጣቱ ነው” ብለዋል፡፡
“ዛሬ በመላ ሀገሪቱ ህዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች የስልጣን ናቸው” ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ፤”ይህን የህዝቡን ጥያቄዎች አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት መመለስ አለበት፤ጥያቄዎቹ ሲመለሱም አሁን ያለውን መንግስት ባገለለ ሁኔታ ሳይሆን እሱንም ባካተተ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡  
የኢኮኖሚና ቢዝነስ ባለሙያና የዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶ/ር ንጋት አስፋው በበኩላቸው፤ የሀገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች ብለው ከዘረዘሯቸው አንዱ፣ የምሁራን በአገሪቱ ጉዳዮች ቸልተኝነት ማሳየታቸው ነው፡፡ የአገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል መሪ አለመኖሩና መንግስት የምሁራንን ምክር ይዞ አለመስራቱ አገሪቱንና ህዝቦቿን ብዙ ዋጋ እያስከፈለ ነው ብለዋል፡፡
አገሪቱ በየአቅጣጫው ውጥረት ውስጥ መሆኗን ምሳሌዎችን በመጥቀስ ያብራሩት ዶ/ር ንጋት፤ እነዚህን  ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉም የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ከእልህ ፖለቲካ ወጥተው፣ ኢህአዴግን ያካተተ ተከታታይ ውይይቶች መደረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል። “አንጋፋ የአገር ሽማግሌዎችን፣ አርአያ የሚሆኑ ቅቡልነት ያላቸው ግለሰቦችን፣ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት፣ በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉ የአገሪቱ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ አካላትን በሙሉ ያካተተ ጉባኤ ተዘጋጅቶ፣ ሀገሪቱን ለማረጋጋትና መፃኢ ዕድሏን ለመተለም በስፋት ሊመከር ይገባል” ብለዋል፡፡
ሌላው ስማቸውን ያልጠቀሱ የውይይቱ ተሳታፊ በሰጡት አስተያየት፤ ዛሬ ላይ የአገሪቱ ዋንኛ የፖለቲካ ችግር ከህዝብ ፍላጎት ጋር የታረቀ የፖለቲካ ድርጅት አለመኖር ነው ብለዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንድ ወጥ የሆነና ለመታገል የሚያስችል ርዕዮተ ዓለም እንኳ የላቸውም ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ህዝቡ አማራጭ አልባ በመሆኑ፣ በራሱ ተነሳሽነት ወደ አደባባይ ሊወጣ ችሏል ብለዋል፡፡  
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የብሄር ፅንፈኝነት መኖሩንና በዚያው መጠንም የብሄር አደረጃጀትን የሚከተሉ የፖለቲካ ኃይሎች መበርከታቸውን በመጥቀስም፣ ይሄም አገሪቱን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስዳት ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተሳታፊው ገልጸዋል። “በክልሎች መካከል የተጀመሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችም ከጥቅማቸው ይልቅ ሀገርን የተለያየ ቦታ በመከፋፈል አስተዋፅኦ ሊኖራቸው ይችላል፤ ምክንያቱም የሚደረጉት ግንኙነቶች እውነተኛ ሳይሆኑ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚመስል መልኩ የሚካሄዱ ናቸው” ብለዋል፡፡
ህዝብን ተስፋ ከሚያስቆርጡና ለአመፅ ከሚጋብዙ ሁኔታዎች መካከልም በህዝብ ላይ በደል ያደረሱ ባለስልጣናትና ግለሰቦች ከስልጣን ዝቅ ከመደረግ ወይም ከመባረር በዘለለ በህግ ተጠያቂ አለመደረጋቸው ነው ይላሉ - ተሳታፊው። አሁንም በከፍተኛ ስልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦች፣ በብሄር ሽፋን ግጭቶችን በህዝብ መሃል እየፈጠሩ በዝምታ መታየታቸው ህዝብን ተስፋ ያስቆርጣል፣ ጥርጣሬንም ይፈጥራል ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ዩጎዝላቪያን የበታተኗት በስታዲየም ውስጥ እግር ኳስን አስታከው የሚደረጉ ብጥብጦችና ተቃውሞዎች እንደነበሩ በማውሳት፣ በአገራችንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በእግር ኳስ ጨዋታዎች ላይ እየተከሰቱ  ያሉ ሁከቶች አደገኛ መሆናቸው ተናግረዋል።    
የአገሪቱ ህገ መንግስት ጂኦግራፊያዊ ክልል ብቻ ሳይሆን የስነ ልቦና ክልልንም በህዝቦች መሃል ፈጥሯል ያሉት  የኢራፓ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ፤ ልሂቃን በአዕምሯቸው ክልል ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው አገሪቱ አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦች እንዳታገኝ አድርጓታል ብለዋል። ይሄ በልሂቃኑ አዕምሮ ውስጥ የተቀመጠው ስነ ልቦናዊ ድንበር መጣስ ሲጀመር ነው፣ለአገሪቱ ችግሮች መፍትሄ ወደ ማፍለቅ መሄድ የሚቻለው ይላሉ፡፡ “ያለፈ ቂም፣ በቀልና ቁርሾዎችን በመተውም በተቃዋሚዎችና በገዥው ፓርቲም መካከል አዲስ ግንኙነት መፈጠር አለበት፤ ይህቺ ሃገር የሁላችንም ነች” ሲሉ ተናግረዋል፤ የኢራፓ ፕሬዚዳንት፡፡ ሃገሪቱ በስመ ብሄር ብሄረሰቦች ነፃነት፣ በስነ ልቦና መከፋፈሏም ማብቃት አለበት፤ ክልላዊነት በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ መሸነፍ አለበት ብለዋል- አቶ ተሻለ፡፡
እንደ ምሁርነታቸው ሳይሆን እንደ አንድ የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ዜጋ ሃሳባቸውን እንደሚሰነዝሩ  በመግለፅ ንግግራቸውን የጀመሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩና ተመራማሪው አቶ ብርሃኑ ደቦጭ በበኩላቸው፤ “ለምንድን ነው ምሁራን ከእንዲህ ያለው የአገራዊ ውይይት መድረክ የሚሸሹት?” ሲሉ ጠይቀዋል። በአገሪቱ የፓርቲ ፖለቲካ አለ ለማለት እቸገራለሁ ያሉት መምህሩ፤ ከፖለቲካው መድረክ አብዛኞቹ አዋቂ ግለሰቦች ተገፍተው በአንፃሩ የፖለቲካ ፅንሰ ሃሳቡ የሌላቸው ግለሰቦች መድረኩን መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል። በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ለውጦች ማምጣት ከተፈለገም ከገንዘብ፣ ከስልጣንና ከጥቅም ፍላጎቶች የፀዳ፣ ለስልጣን የማይታገል የዜጎች ንቅናቄ መፈጠር አለበት የሚሉት መምህሩ፤ ንቅናቄውም በአገሪቱ ችግሮች ላይ ውይይት በማድረግ፣ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማፍለቅ የሚችል መሆን አለበት ብለዋል፡፡
አንጋፋው ፖለቲከኛና የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ተመስገን ዘውዴ በሰጡት አስተያየት፤ “የህዝቡ ጥያቄ የነፃነት ጥያቄ ነው” ብለዋል፡፡ ሃሣብን በነፃነት ስለ መግለጥ፣ ሃሣብን በነፃነት ስለ መለዋወጥ፣ስለ ሃይማኖት ነፃነት ነው የህዝቡ ጥያቄ ያሉት ፖለቲከኛው፤” ዋነኛው የሃገሪቱ ፖለቲካዊ ችግር ምንጭ የእነዚህ መብቶች ሙሉ ለሙሉ ያለመከበር ነው” ባይ ናቸው፡፡  
አቶ ግደይ ደገፉ የተባሉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር በበኩላቸው፤የአገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች መነሻዎችን ታሪካዊ ዳራዎችን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ አሁን ያለው ስርአት ዜጎች በራሳቸው ቋንቋ እንዲማሩ፣ እንዲዳኙ ማድረጉና ባህላቸውን እንዲያበለፅጉ ማገዙ መልካም መሆኑን የጠቀሱት ምሁሩ፤ ነገር ግን ኢትዮጵያዊ አንድነት መፍጠር ላይ ከፍተኛ ጉድለት አለበት ብለዋል። በተለይ ከኢትዮጵያዊነት በላይ ብሄርተኝነት መሰበኩ የሃገሪቱ ቀጣይ አደጋም ነው ብለዋል - አቶ ግደይ፡፡
እስከ ደርግ ስርአት መጨረሻ ባለው ጊዜ ባሉት 50 ዓመታት፣የግራ ክንፍና የሊበራል ዲሞክራሲ በየፅንፋቸው ቆመው አገሪቷን ግራ አጋብተዋት እንደነበር ያወሱት ምሁሩ፤ አሁን ያለው የፖለቲካ አስተሳሰብ ደግሞ “እኔ ብቻ ያልኩት ትክክል ነው” በሚል የተቃኘ መሆኑ፣ለሃገሪቱ መፃኢ እድል አደጋ ነው ብለዋል፡፡ ፅንፈኝነት በየትኛውም መልኩ መገደብ አለበት ያሉት አስተያየት ሰጪው፤”ህዝብና የፖለቲካ አመራሮችን ለያይቶ በማየት፣በህዝብ ላይ ጥላቻን መዝራት ተገቢ አይደለም፣ ለሃገሪቱ ህልውናም አደጋ ነው” ብለዋል፡፡
ሌሎች በህዝባዊ ውይይቱ የታደሙ ምሁራንና ግለሰቦችም የተለያዩ አስተያየቶችን የሰነዘሩ ሲሆን መንግስት ህገ መንግስትን ማክበር እንዳለበት፣ የፖለቲካ ውይይቶች በነፃነት መካሄድ እንዳለባቸው፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በስፋት የሚንቀሳቀሱበት እድል መፈጠር እንደሚገባው ተጠቁሟል፡፡ በኢትዮጵያዊነት ላይ የበለጠ መግባባት መፈጠር እንዳለበትም የውይይቱ ተሳታፊዎች አሳስበዋል፡፡    

Read 4213 times