Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 21 April 2012 15:49

እንኳን ጠመንጃ ሰጥተኸው እንዲሁም አልቻልነው” – “አንዴም አልተነሳን፣ ግን ለዳግማይ ትንሣይ ያብቃን”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“አንዳንድ ተረቶች ካልተደጋገሙ እንደዘፈን ሰርፀው እልብ ውስጥ አይገቡም፡፡ ስለዚህ ደግመን እንተርካቸዋለን፡፡

አባትና ልጅ፤ አንድ ጅብ በረት እየሠበረ፣ ጊደር እያስደነበረ፣ ከብቶች እየፈጀ ያስቸግራቸዋል፡፡ ስለዚህ፤

“ይሄን ጅብ ብናጠምድና ብንይዘው ይሻላል” ይላል አባት፡፡ የታመመበት አልጋ ላይ ሆኖ፡፡

ልጅም፤

“እንዴት ጅብን ማጥመድ ይቻላል?”ይጠይቃል፡፡

አባት፤

“ቀላል ነው፡፡ እኔ አልጋ ላይ ባልውል በቀጥታ አድነን፣ አነጣጥረን እንገድለው ነበር፡፡ ሆኖም ዛሬ እኔ ከአልጋ መነሳት ባለመቻሌ ኃላፊነቱን ላንተ ለልጄ እሰጥሃለሁ፡፡

ዘዴው እንዲህ ነው፡፡ ጠመንጃዬን ትወስድና አፈ ሙዙ ላይ ሙዳ ስጋ ታስቀምጣለህ፡፡ ያንን ሙዳ ሥጋ በገመድ ታሥርና ገመዱን ከጠመንጃው ቃታ ጋር ታያይዘዋለህ፡፡ ጅቡ ሙዳ ሥጋውን ሲጐትተው ቃታውን ይስበዋል፡፡ የተቀባበለው ጥይት በጉሮሮው ይገባል፡፡ ያኔ ዋጋውን ያገኛል፡፡ ገባህ?”

ልጅ፤

“አዎ አባዬ፤ ዘዴው በደንብ ገብቶኛል፡፡ ዛሬ ማታ በተግባር አውለዋለሁ፡፡” ይላል፡፡ ልጅየው ማታ ጥይቱን ያቀባብልና፣ ሙዳ - ሥጋውን አፈ - ሙዙ ላይ ያሥርና፣ የገመዱን ጫፍ ቃታው ላይ ያሥርና ጠመንጃውን ከብቶቹ በራፍ ላይ ያስቀምጥና፤ ጅቡን ይጠብቃል፡፡

ጅብ ሆዬ፤ ማታ በተለመደው ሰዓት ይመጣል፡፡ የሆነው ነገር ግን የተገላቢጦሽ ነበር፡፡

ልጅ ነገሩ አስደንግጦት ሲሮጥ ወደ አባቱ ይመጣል፡፡

“አባዬ አባዬ?!” ይላል በተሸበረ አንደበት፡፡

አባት፤

“ምነው ልጄ ምን ሆነሃል?”

ልጅ፤

“ኧረ ጅቡ ጉድ አርጐናል!”

አባት፤

“እኮ ንገረኛ ምን አደረገ?

“ጅቡ እኛ እንዳሰብነው ሙዳ ሥጋውን ነክሶ ገመዱን አልጐተተውም፡፡ ይልቁንም ጠመንጃውን በሰደፉ ይዞ እየጐተተ ጠመንጃውንም፤ ሥጋውንም ይዞት ሄደ!” አለው፡፡

አባትየውም፤

“አዬ ልጄ፤ እንኳን ጠመንጃ ሰጥተኸው እንዲሁም አልቻልነው!” አለ፡፡

***

እኛው ሥጋውን ሠጥተን፣ እኛው ጠመንጃ አቀባብለን፤ ጅቡ ብልጥ ሆኖ ጠመንጃችንን ቢወስድብን እዬዬ ማለት፤ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ በምናቅደውና በምንጓዝበት መንገድ ሁሉ ቅንነትን ከብስለት አያይዘን፣ እኛ ባሰብነው መንገድ ብቻ ሳይሆን፤

“አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ጨምሪበት” እንደተባለው አስበንበት፤ ከዕቅድ “ሀ” በተጨማሪ ዕቅድ “ለ”ን አስተውለን፤ ቢቻል ዕቅድ “ሐ”ን ማከል አስፈላጊ መሆኑን ልብ እንበል፡፡ አንድ ፈላስፋ፤ “በዓለም ላይ ስንት ነገሮች ያስፈልጋሉ?” ተብሎ ቢጠየቅ “ሦስት ነገሮች” ሲል መለሰ ይባላል፡፡ “ምን ምንድናቸው?” ሲሉ ጠየቁት፡፡

“አንደኛ ማሰብ” አለ፡፡

“ሁለተኛውስ?” አሉት፡፡

“ማሰብ” አለ፡፡

“ሦስተኛስ?” አሉት፡፡

“አሁንም ማሰብ!” አለ፡፡

አንድ የእኛ አገር የጥንት ዘመን ፖለቲከኛ፤ (ዶ/ር እሸቱ ጮሌ የሚባል ደግሞ በአንድ ወቅት፤ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማህበር ባደረገው ንግግር፤

I have three messages for you:

Number one - “Organize!”

Number two - “Organize!”

And Number three … ብሎ ገና ሳይጨርስ ተማሪው በሙሉ በአንድ ድምፅ “Organize!”  አለና ጨረሰው፡፡

ነገሩ እንግዲህ “ዛሬ ለእናንተ” ሶስት መልዕክት አለኝ - ተደራጁ! ተደራጁ! ተደራጁ!” እንደማለት ነው፡፡ የዛሬው የሀገራችን መሪም በተዘዋዋሪ “ያልተደራጀ ኃይል፤ ኃይል አይደለም!” ይላሉ፡፡ መንፈሱ አንድ ነው፡፡ ሌኒንም፣ ማኦም፣ ቼጉቬራም … ያሉት ይሄንኑ ነው፡፡ የስልሳዎቹ (1960ዎቹ) ዓመታት ትውልድ የሁልጊዜ መልዕክት ይሄው ነው፡፡ የዱሮ የአማርኛ አስተማሪዎቻችን፤

አንተ “ሙዚቃ” አልከው፤ እኔ “ስልት ያለው ጩኸት” አልኩት፤ ሁሉም ያው ነው” ይሉን ነበር፡፡

ስለ ፍትህ - ርትዕም አወራን፡፡ ስለዲሞክራሲም አወራን፣ ስለ አገር አንድነትም አወራን፤ ስለ ጎረቤት አገርም አወራን፣ ስለ ዐባይም አወራን፣ ስለ ፀረ-አሸባሪነትም አወራን ስለ ፀረ-ሙስና … ሙዚቃው ሙዚቃ የሚሆነው ስልት ያለው ጩኸት ከሆነ ነው፡፡ “ተዋንያኑ” ተዋንያን የሚሆኑት ያገሪቱን መሪ ቃል ከላይ እስከ ታች በተፋሰስ እንደበቀቀን (Parochially) ስላነበነቡ ሳይሆን “ተግባራዊ ስልቱ” ከገባቸውና ከተገበሩት ነው፡፡ በአንድ ወቅት በኒው-ዮርክ ታይምስ በወጣ ካርቱን ላይ … ቆፍጠን ቆፍጠን ያሉ፣ ክራቫት ያሰሩ፣ ሳምሶናይት ቦርሳ የያዙ ጎልማሳ ፓርላሜንታውያን ወደ ፓርላማ ህንፃ ሲገቡ ያሳያል - በግራ በር፡፡ ጉባዔው አልቆ በቀኝ በር ሲወጡ ያሳያል - ያው ካርቱን፡፡ የሚወጡት ሰዎች ግን እነዚያ ቆፍጣና ቆፍጣና ጉባዔተኞች፤ ወገባቸው ጎብጦ፣ ግራጫ ጢም አንዠርግገው፣ ከዘራ ይዘው - ባንድ ቃል፤ አርጅተው - አፍጅተው ነው! በአንድ ስብሰባ ሰው ጥቁር ከነጭ ፀጉር ሊያበቅል ይችላል፣ እንደ ጉዳዩ ፀናናነት፤ ማለት ነው! ከዚህ ይሰውረን! በጥቁርና ነጭ ጀምሮ በባለቀለም ፊልም የሚያልቅ ብዙ ትርዒት አለ እንደማለትም ያስኬዳል፡፡

ማሰብ፣ ማሰብ፣ አሁንም ማሰብ የወቅቱ መልዕክት ነው፡፡ “በራቸውን ሳይዘጐ ሌባ ሌባ ይላሉ” እንዳለችው ውሻ፤ “እንኳን ጠመንጃ ሰጥተኸው እንዲሁም አልቻልነው!” የሚለውንም ሀሳብ አለመዘንጋት ከብዙ አባዜ ያድነናል፡፡ የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርብን! መልካም የዳግማይ - ትንሣዔ በዓል!!! አንዴም አልተነሳን ግን ለዳግማይ ትንሣይ ያብቃን!! ገጣሚው እንዳለው “አበሻ ፀሎት ሲፀልይ አንዴም ለመነሳቱ፤ አንዳችም ምሣሌ ሳያይ ለዳግማይ ትንሣይ አብቃኝ፣ ይላል አበሳውን ሊያይ”

 

 

Read 3995 times Last modified on Saturday, 21 April 2012 16:01