Print this page
Tuesday, 02 January 2018 09:53

የዶላር እጥረቱ፤ ችግሩና መፍትሄው!

Written by  ተስፋ በላይነህ
Rate this item
(6 votes)


      “አድሎአዊነት፤ ሕገ-ወጥ የዶላር ፍሰት፤ የለጋሾች የዶላር እርዳታ ብክነት፤ የግለሰብ ነጻነት አለመከበር፣ የእኩልነት እጦትና ሕግ አልባነት ሲደማመሩብን፣ አሁን ያለችውን ኢትዮጵያን መፍጠራችን የግድ ነው!--”
    
    ባለፈው ሳምንት “በአስመጭዎች ላይ የተጣለው ደንብ” በሚል ርዕስ ከዶላር እጥረት ጋር የተያያዘ ጽሁፍ ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ ጉዳዩ ወቅታዊ ከመሆኑ አንጻር አንዳንድ ወዳጆቼ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበውልኛል። በዋናነት ግን ለጉዳዩ የሚሆን መፍትሄ  አለማቅረቤን ገልጸውልኛል፡፡
ለዚህ ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ፣ በምጣኔ ሀብት ዙሪያ ዓለም አቀፋዊ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች ሃሳባቸውን ቢሰነዝሩ የተሻለ ነው፡፡ በዘርፉ የተካኑ ልሂቃን ወቅቱን የጠበቀ፤ ሕብረተሰቡን ያማከለና መጪውን ያገናዘበ ድንቅ ደንብ ቢቀርጹ መልካም ነው፡፡ በእርግጥ እንዲህ ቆሞ ያስቀረን ዋናው ጉዳይ ወረቀት ላይ የጎደለን “ድንቅ ደንብ” ሳይሆን በተግባር  የማናሳካው ድርብ ችግር ነው፡፡ ሕጉ በየጊዜው መሻሻሉ ባልጎዳን ነበር፤ የጎዳን ሕጉ ጥቂቶችን ለመጥቀም፤ ጥቂቶችን ለማሳደግ፤ እናም በ“ጥቂቶች” መጽደቁ ነው! ከዚያም በተግባር አለመፈጸሙ ሌላኛው ድርብ ችግር!
“ዶላር ያጠራት አገር” ተሸክመን፤ በሚሊዮን ዶላር የሚገመት እቃ መሸመታችንን ስንመለከት ከመደንገጥም አልፈን ደንዝዘን ብንቀር አይገርምም፡፡ ሦስት የተለያዩ ሃሳቦችን (ክስተቶችን) እንመልከት፤ከዚያም ወደ መፍትሄው እንዝለቅ!
ሐሳብ -1
አንድ ባለ ኮከብ ሆቴል የሚገነባ ባለ ሃብት፤ በሚሊዮን ዶላር የሚገመት እቃ ከውጭ እንዲያስገባ ይፈቀድለታል፡፡ እጅግ ውድ ውድ እቃዎችንም ለቤቱ ይገዛል፡፡ የቤት ውስጥ ማብሰያ እቃዎችን “ኪችን ካቢኔት”፤ ጠርተን በማንጨርሰው የዶላር መጠን (በብር ቢገመት በሚሊዮኖች በሚሆን ገንዘብ) ተገዝቶ ይገባል፡፡ የሚበላው እንኳ የሌለው ሕዝብ ውስጥ ሆነን፣ በሚሊዮን ብር ተገዝቶ የሚገጠም ኪችን ካቢኔት በዶላር አስፈቅደን እናስገባለን!
ቤት ውስጥ ለሚቀመጥ ፒያኖ መጫወቻ፣ ብዙ ዶላር ተፈቅዶ ከውጭ  ይሸመታል፡፡ መኖርያ ቤት የሌላቸው ግለሰቦች በበዙባት አገር፤ መተኛ የሚሆን ፍራሽ በብዙ ዶላር ተሸምቶ ይገባል፡፡ ይህ እንዴት ሆነ…? የቤት ውስጥ ማስዋቢያ እቃዎችን የሚሸምቱ ባለሃብቶች፣ ዶላር ባጠራት አገር መከሰታቸው ለተመልካች አደናጋሪ ገጠመኝ ነው፡፡ በአይኔ ተመልክቼ ደንግጫለሁና!
ሐሳብ -2
የአገር ምጣኔ ሀብት እድገት በግለሰብ ጭንቅላት እድገት የሚመዘን፤ የሚመራና የሚወሰን ጉዳይ መሆኑን ስንቶቻችን እናምናለን? አንድ ልዕልና ያለው ግለሰብ፤ ‹‹ሰው›› የሆነ፣ በሰውነቱ የሚከበርና የሚኮራ፤ ራሱን አክብሮ ሌላውን የሚያከብርና የሚያስከብር፤ የሚያስተውል ግለሰብ ሲኖረን፣ በምን ያህል ዶላር የሚመዘን ሃብት እንደሚሆን መገመት እንችል ይሆን?
ሐሳብ- 3
መንግሥት፣ ምጣኔ ሃብትና ሕዝብ ምንና ምን ናቸው? መንግሥት ሕግን የሚያስፈጽም ሕጋዊ አካል ነው፡፡ ሕግ ከሌለ መንግስት ቢጠነክር፣ ቢያድግ፣ ቢመነደግ ምንም ጥቅም የለውም፡፡ እንደውም ኢትዮጵያ ያለ መንግስት በሕግ ኖራለች፡፡ በ“መንግሥት” ግን ያለ ሕግ መኖር አትችልም! እየሆነ ያለው ይህ ነው!!
እንግዶህ ሶስቱን ሃሳቦች አዋሕደን (አፋጭተን)፣ ከችግሮቹ ተነስተን ወደ ምናገኘው መፍትሔ ለመዝመት እንሞክር፡፡
ችግር
በአሁኑ ወቅት የዶላር እጥረት (ችግር) የሚያሳስባት አገራችን፤ ፍትሃዊና በቁጥጥር የሚመራ የገንዘብ ዝውውር ያላት አገር ብትሆን ይህ ሁሉ ቀውስ ባላጋጠመ ነበር! ጥቂቶች የሚወራጩቡት ጥቂቶች የሚያዙባት አገር ይዘን፣ የዶላር እጥረት መከሰቱ ለሰከንድ እንኳ ሊደንቀን አይገባም፡፡ እጅግ በጣም ቁጥሩ የሚዘገንን ዶላር በተለያየ መልክ እንደሚወጣ ይነገራል፡፡ መረጃውን በየጊዜው የምንሰማው ነው፡፡ ከአፍሪካ በአመት ከስልሳ እስከ ሰባ ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ በሕገ ወጥ መልኩ ይወጣል፡፡ ኢትዮጵያ ሦስት ቢሊዮን ዶላሩን ታሸሻለች! ይህም ችግር የገቢዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በየጊዜው የሚለፍፈው  ነው፡፡
እንደውም በቅርቡ ከፍተኛ ቁጥጥር አድርገናል ሲባል ሰምተናል፡፡ ከዚህ በፊት “በባሌና በቦሌ” ምን ያህል ዶላር እንደተጓዘ ፈጣሪ ብቻ ነው የመዘገበው። ሕገ-ወጥ ገንዘብ ተመልሶ “ሕጋዊ” ሆኖ እንደሚገባ ስንቶቻችን እናውቃለን?
አንድ የአገር ውስጥ ነጋዴ (ላኪ) በውጭ አገር ከሚገኝ ድርጅት ጋር እቃ ለማቅረብ ቢስማማ፤ የአገር ውስጥ ነጋዴው (ላኪው) በውጭ አገር ለሚገኘው ተቀባይ ድርጅት እቃውን ቢልክለት፤ የውጭ ድርጅቱ ዶላር ያስተላልፋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ተገኘ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ 100 ኩንታል ቡና የሚፈልግ ዓለማቀፍ ነጋዴ፤ አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኝ ላኪ ድርጅት ጋር ቢዋዋል፤ የመቶ ኩንታል ቡና ዋጋ በዶላር አስቦ በመላክ ቡናውን ያገኛል፡፡ ዋናው ጉዳይ ምናልባትም የምንዘነጋው፣ እነዚህ ሁለት ነጋዴዎች “የአንድ ሰው” ወይም (አንድ ቤተሰብ) ድርጅቶች ቢሆኑ የሚለውን ነው! በዝርዝር  አልገባበትም!
ሌላው አሁን ኢትዮጵያ ባስገነባቻቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች (በአማርኛ ምን እንደምንላቸው ባናውቅም) ኢትዮጵያ፣ “አዲሲቷ ባንግላዴሽ” የሚል መጠሪያን ካገኘች ሰነባበተች፡፡ አሜሪካ በከፈተችው የላኪዎች ሰፊ መርሃ ግብር የንግድ ትስስር አማካኝነት፤ ኢትዮጵያ ሰፊውን ድርሻ የያዘች አገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ስማቸውን የገነቡ አምራቾች፣ ምርታቸውን ኢትዮጵያ ላይ እያመረቱ፣ ወደ መላው ዓለም ይልካሉ፡፡ አገር ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛ 35 ዶላር ደመወዝ (በወር ከአንድ ሺ ብር በታች) ክፍያ በማግኘቱ (አምራቾቹ ምናልባትም ከአንድ ጥቅል ምርት ብቻ በሚያገኟት ትርፍ ብዙዎቹን መቅጠር በሚያስችላቸው ደረጃ) የተመቻቸ ሜዳ ተፈጥሮላቸዋል። እነ ካልቨይን ክሌይን፤ እነ ቴሚ ሄልፊገ እና የመሳሰሉ “ብራንዶች”፣ “ሜድ ኢን ኢትዮጵያ” የሚል ጽሑፍ በውስጣቸው ይዘው በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ቀርበዋል፡፡ ይህ አንዱና ትልቁ ዶላር የሚገኝበት መንገድ ነው! ይሄ ጉዳይ በተናጠል ሒሳቡ ሊወራረድ የሚገባው ጥቅል ሐሳብ በመያዙና ሰፊ ትንተና ስለሚያስፈልገው ለጊዜው ወደ ጎን እንተወው!
“ነጻነት” የዚህ ሁሉ መሰረት ለመሆኑ አጫጭር ሐሳቦችን እናንሳ! አንድ ግለሰብ ነጻነት ሲኖረው፣ በፍትህ የታነፀ ማሕበረሰብ ውስጥ ተኮትኮቶ ካደገ፤ የተፈጥሮ ነጻነቱን ከውስጥ እምቅ ኃይልና የውጭ ስጦታዎቹን (ችግሮቹን፣ እድገቶቹን፣ ፍላጎቶቹን…) ይዞ ፈጣሪ መሆን ይችላል፡፡
እላይ የጠቀስናቸውን ነጥቦች እርስ በርስ በማዋሃድ ወደ መፍትሄ መሄድ እንችላለን፡፡ አድሎአዊነት፤ ሕገ-ወጥ የዶላር ፍሰት፤ የለጋሾች የዶላር እርዳታ ብክነት፤ የግለሰብ ነጻነት አለመከበር፣ የእኩልነት እጦትና  ሕግ አልባነት ሲደማመሩብን፣ አሁን ያለችውን ኢትዮጵያን መፍጠራችን የግድ ነው!
ግለሰብ በነጻነት ሲኖር፣ በሕግ ሲተዳደር፣ ለሕግ ማደር ሲጀምር፤ አዕምሮውን ኃይል አድርጎ ይቀርባል። ያለ ሥጋት ይንቀሳቀሳል፡፡ ተከባብሮ /በፈቃድ ተፈቃቅሮም/ ይኖራል፡፡ አዕምሮ መስራት ሲጀምር ሰውነታችንም ሆነ አካባቢያችን መስራት ይጀምራል፡፡ የሰው ልጅ ለችግሩ መፍትሄ ለማግኘት የሚያስችለውን የፈጣሪነት ስጦታ ከፈጣሪ ተቀዳጅቷል፡፡
ለእያንዳንዱ ችግሮቻችን መፍትሄ የምናበጀው ግን  ነጻነት ሲኖረን ነው፡፡ ሆኖም ችግር  ብቻውን ፈጣሪ አያደርገንም! ለችግሩ መፍትሄ የሚሻ ፈጣሪ አዕምሮ ያስፈልጋል፡፡ በባርነት የታሰረ ችግረኛ፣ መፍትሄ ከየትም ሊያመጣ አይችልም፡፡
ሁሉንም ምሳሌ ሆነ ሐሳብ ወደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እንመልሰው፡፡ በውድ ዋጋ የሚገቡ የሆቴል እቃዎችን ስናስብ፤ በየገጠሩ ባማረ አሰራር ተጠርበው የሚዘጋጁ፣ ለሆቴሎች የሚሆኑ ምርቶችን የሚያዘጋጁ ግለሰቦች ቢበረታቱ፤ ቢደገፉና ወደ ገበያው ማቅረብ ቢችሉ፤ ጥቅሙ አያሌ ነው፡፡ የኛ ምርት በ“ሜድ ኢን ኢትዮጵያ” መፈክር መሰረት፣ አለም አቀፉን ገበያ ሰብሮ የመግባት አቅምን መቀዳጀት ሲችል ነው፤ ትልቁ የስኬት ጣራ!
“ሜድ ኢን ኦትዮጵያ እንደገና ተነሳ” ስንል፣ የሰው አገር “ሸቀጥ ስም” ተሸክመን መሆኑ፣ ከበሮ ሊያስደልቀን አይገባም፡፡ የዶርዜ ጋቢ ዓለም አቀፍ ዋጋና ተቀባይነት እንዲኖረው፤ “ሜድ ኢን ኢትዮጵያ” ተብሎ እንዲሸጥ ማድረግና ስኬታማ መሆን እንጂ፤ የካልቨይን ክሌንን ስም በዓለም አቀፍ ዋጋ፣ “በረከሰው ጉልበት” ተሰርቶ መሸጡ፣ ለባርነት እጅ ከመስጠት ለይቼ አልመለከተውም!!
ኢትዮጵያ በአፍሪቃ በቀንድ ከብት  ብዛት ቀዳሚ ሆና፤ ብዙ የቀንድ ከብት ቁጥር የያዘ ገበሬ ወደ አለም አቀፍ ገበያ ምርቱን ይዞ፣ ኑሮውን በተጨባጭ ሳያሻሽል “ሜዲ ኢን ኢትዮጵያ እንደገና ተነሳ” ብትሉኝ፣ ሊያሳምነኝ አይችልም፡፡ በአፍሪቃ በቲማቲም ምርት ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስድ ተፈጥሮአዊ ስጦታ ተሸክመን፤ በኢትዮጵያ የተመረተ የቲማቲም ድልህ ይዘን፣ ወደ ዓለም አቀፉ ገበያ በመግባት፣ በመስኖም ይሁን በሜካናይዝድ እርሻ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊ ኢንቨስተሮች ሲሻሻሉ ካላየን፣ “ሜድ ኢን ኢትዮጵያ ተነስቷል” የሚል ዜና ብትነግሩኝ፣ ለእኔ ሽንገላ ብቻ ነው!!  
አሁን ያለውን የዶላር እጥረት ችግር መፍትሄ የምናበጅለት፣ እላይ በተጠቀሱት ጉራማይሌ  ሃሳቦች ፍጭት ነው፡፡ ግለሰብ እና መንግሥት ናቸው አንድን አገር ተጋግዘው የሚያቆሟት!
ግለሰቡ ነጻነት የለውም! መንግሥት ፍትህ አላሰፈነም! ግለሰቡ ለችግሩ የሚሆን መፍትሄ አምጦ መውለድ አልቻለም! መንግሥት መልካም አስተዳደር የገነት ያህል ርቆታል! በሙስና በተጨማለቀ ስርዓት፣ በሙስና የሚገኘው ገንዘብ ወደ ዶላር ተለውጦ ባህር እየተሻገረ፤ ግለሰቦች ባሕር መሻገር አቅቷቸው መሃል ላይ ሰጥመው  ከቀሩ… የዚህች አገር ዕጣ ፈንታዋ ታዲያ ምንድን ነው…? ዶላር ቢያጥረን እንዳይደንቃችሁ፡፡ አይደለም ዶላር ሌላ ነገርም ቢያጥረን እንዳይገርመን!
መፍትሔ
ችግሩ ብዙ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር ግን መፍትሄው አንድ ብቻ መሆኑ ተዓምር ሊመስል ይችላል፡፡ እንደኔ ከሆነ መፍትሄ አንድና አንድ ብቻ ነው! ከዚህ ውጭ መፍትሄ ካላችሁ አቅርቡልኝ! ለጊዜው ግን መፍትሄው፤ “መንግሥት ሆይ! ወንበርህን ለሕዝብ አስረክብ!” የሚለው ድምጽ ነው፡፡

Read 4948 times