Saturday, 21 April 2012 16:05

ማርቲን ሉተር ኪንግ ፊተኛውና ኋለኛው

Written by  ከበደ ደበሌ ሮቢ
Rate this item
(5 votes)

ሁለት ናቸው፤ ፈተኛውና ኋለኛው፡፡

ሁለቱም ቄሶች ናቸው፤ አንዱ፡- የካቶሊክ ፕሪስት፤ ሌላው የፕሮቴስታንት ፓስተር፡፡ ሁለቱም ታላላቅ ሠብዕናዎች ናቸው፤ አንዱ፡- ለጥቁሮችና ለነጮች የእኩልነት መብት የታገለ ጥቁር አሜሪካዊ የአትላንታ ጆርጂያ ልጅ፤ ሌላው፡- ለፕሮቴስታንት (ጴንጤ ቆንጤ) ከካቶሊክ ማህፀን ውስጥ መፍለቅ ምክንያት የሆነ ነጭ አውሮጳዊ የጀርመን ጉተምበርግ ዩኒቨርሢቲ ልጅ፡፡ ሁለቱም ዶክተሮች ናቸው፤ አንዱ፡- ከአምሥት መቶ ዓመታት በፊት በጉተምበርግ ዩኒቨርሢቲ የፍልሥፍናና ሥነ መለኮት (ቲዮሎጂ) ሌክቸረር፤ ሌላው፡- ከስልሣና ሠባ ዓመታት በፊት በአትላንታ ጆርጂያ የመጥምቃን አብያተ ክርስቲያናት ሚኒስትርና በሠላማዊ የትግል ሥልት ለህዝቡ መብቶች መከበር ለመታገል ራሡን አሣልፎ የሠጠ ከፍተኛ የንግግር ችሎታ ያለው አንደበተ ርቱዕ ጥዑመ ልሣን አፈወርቅ ገና በወጣትነቱ ከነፍሥ ግድያ ቡድን በተተኮሠ ጥይት የተገደለ፤ በፍትህና በእኩልነት ለተኳለች አሜሪካ መፈጠር ተራራ ላይ ወጥቶ፡- I have a dream (ህልም አለኝ ስለ አገሬ) ያለ፤ በባራክ ሁሴን ኦባማ የመጀመሪያው የአሜሪካ  ጥቁር ፕሬዚዳንት ሆኖ መመረጥ ታላቅ ህልሙ የተፈታለት፤ ዋይኒ ዳየር እንዲህ ብሎ የሚገልፀው (Dr. Maritin Luther King, Jr. was a Babtist minister & Passionate fighter for Civil rights through nonviolent Action. He was felled by an Assassin’s in 1968.)

ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ [ፊተኛው (Senior) Sr.] ከአሜሪካዊው ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ [ኋለኛው (Junior) Jr.] የሚለየው በአስተሣሰቡ ምክንያት የተሣደደ እንጂ በአዲስና ታላቅ ሃሣቡ ተቃዋሚዎች የተገደለ ባለመሆኑ ጭምር ነው፡፡ በዛሬው ዘመን በመላው ዓለም ለሚገኙ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትና ብዙ መቶ ሚሊየን ክርሥቲያን ምዕመናን መከሰት ምክንያት የሆነው ይሄ ሰው ነው፡፡

ከሃያ ዓመታት በፊት በአርባ አራት የአፍሪቃ አገሮችና በመሀከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ የአረብ አገሮች ላይ አሠሣና ዳሠሣ አዘል ጋዜጣዊ ምርምር ያደረገው የ Los Angeles Times ሪፖርተር ዴቪድ ላምፕ The AREBS (አረቦች) በተሠኘ መፅሀፉ (የኛው ነቢዩ ኢያሡ፡- አረቦችና እሥራኤሎች በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ በተረጐመው ጥናቱ) ሲነግረን እንዲህ ይላል፡- በኢራንና በኢራቅ ውጊያ ወቅት የኢራኑ ሻኽ አያቶላ ሆሚኒ  ዕድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሠ አምሥት ሺህ የኢራን ታዳጊ ህፃናትን አንገታቸው ላይ “መንግሥተ ሠማያት (ጀነት) መግቢያ” ነው ያለውን ቁልፍ እያንጠለጠለ  (ብትሞቱ እንኳ ጀነት ትገባላችሁ፤ ይሄ ጀነት የምትገቡበት ቁልፍ ነው ብሎ) በኢራቅ ወታደሮች በተቀበሩ ፈንጂዎች ላይ መሠጋቸው፡፡ ይሄ የሆነው ቢበዛ ከሃያ ሁለት ዓመታት በፊት ነው፡፡

ከአምሥት መቶ ዓመታት በፊት በጀርመን አገር የካቶሊክ ካህናት የእግዚአብሔር መንግሥት መግቢያ (To The Kingdom of God) የሚል ካርድ መሸጣቸውን በመቃወም ከእነርሡው መሃከል የወጣ የካቶሊክ ቄስ አፈንግጦ መቃወሚያውን በጉተምበርግ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የግንብ ዓምድ ላይ በምሥማር በገደገደ ጊዜ፡- ፕሮቴስታንት የተሰኘው የክርስቲያን ክፍል (Sect) ከካቶሊክ ማህፀን ውስጥ ብቅ አለ፡፡ ፕሮቴስታንት፡- ያፈነገጠ ማለት ሢሆን፤ በዛሬው ዓለም የምናያቸው ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት [Evangelical Churches ወይም (Pentcostal Church)] የዚህ ማፈንገጥ ውጤቶች ናቸው፡፡ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት (ገነት) የምንገባው በሚሸጥ ካርድ አይደለም ብሎ በፅኑ የተቃወመው፡- ጀርመናዊው ቄስ ዶክተርና ሌክቸረር ማርቲን ሉተር ኪንግ (የፊተኛው) ነው፡፡ ይህን ታላቅ ሠው ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያውያን ጋር ያስተዋወቀው፡- የቴዎድሮስ ሞት ለቴዎድሮስ ዕረፍት ለኢትዮጵያ ሀፍረት ነው ያለው፤ ስለነሶቅራጥስ ነቢዩ መሀመድ ካርል ማርክስ ቡድሀ ጉታማ (ልዑል ሲድሀርታ) ሞሀንዳስ ካራሞቻንድ ማህተመ ጋንዲ የፃፈልን፤ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋዎች ከፃፉ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ደራሢያን አንዱ የሆነው ደፋርና የአስተሣሰብ እሥራትን የሠበረ (የተለቀቀ የተላቀቀ) ደራሢ አቤ ጉበኛ ነው፡፡ አቤ ጉበኛ ራሱ በታላቅ አስተሣሰቡ ምክንያት ተቀጥቅጦ የተገደለ ዘመን የማይሽረው ሃሣበ ትጉህ ኢትዮጵያዊ ሊቀ ፅሁፍና ልዕለ ሠብ ነው፡፡

ዋነኛ የሠው ልጅ ሠብዕና መለኪያው በተግዳሮትና ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ልባዊ ወዳጅና ፅኑ አጋር ሆኖ መገኘቱ ነው፤ የሚለው ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ [Junior (Jr.)] ኋለኛው ታላቅ ሠብዕ ነው፡፡ እንደ አንዳንዶች አገላለፅ ትልቁና ትንሹ ማርቲን ሉተር ኪንግ፤ ያላልኩት የሥፍራና የዘመን ልዩነት እንጂ ሁለቱም ታላላቅ ሠብዕናዎች በመሆናቸው እና ትልቁና ትንሹ የሚለው አገላለፅ ጁኒየርና ሲኒየር ለሚለው አቀማመጥ ስለማይመጥን ወይም እውነቱን በምልዓት የማሣየት አቅሙ ውሡን ስለሆነ ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ ፊተኛውና ኋለኛው ማለት ይሻል ይመስለኛል፤ ይሄም ቢሆን … ልክ ልክክ የሚል አቻ ፍቺ ሆኖ አላገኘሁትም፤ ይሁንና የተሻለ ነው፡፡ ሁልጊዜ የተሻለው ይመረጣል፡፡

ማርቲን ሉተር ኪንግ ልክ የዛሬ ሠማንያ ሶስት ዓመት በአሜሪካን ሀገር USA አትላንታ ጆርጂያ ነው የተወለደው፡፡ በአውሮጳውያን የዘመን አቆጣጠር (Gregorian Calendar) በ1929 ወይም እና በእኛ በኢትዮጵያውያን አቡሻኽር (Julian Calendar) በ1921 ዓ.ም፤ በወቅቱ በጥቁሮችና በነጮች መሀከል የዘር ልዩነት (Racism) ፖሊሲ በምታራምደው አገር ጥቁር አፍሪቃዊ ከሆኑ ቤተሠቦች ተወለደ፡፡ እርሡ ከመወለዱ ሠማንያ ዓመታት ቀደም ብሎ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አብርሀም ሊንከን ነጭ ሆኖ ሣለ በጥቁሮችና በነጮች ላይ ፍትሀዊ አቋም በማራመዱ በሥውር ከታጠቁ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ተመትቶ ተገድሏል፤ ከአሜሪካ ታላላቅ መሪዎች አንዱ የሆነውና አንድም ቀን ትምህርት ቤት ሳይሄድ ራሱን ያስተማረው አብርሀም ሊንከን ከባለቤቱ ጋር ቲያትር በመመልከት ላይ እያለ ነው የተገደለው፤ ከመገደሉ በፊት በዋዜማው ሌሊት በነፍስ ገዳዮች እንደሚገደል በህልሙ አይቶ ነበር፡፡ ከማርቲን ሉተር ኪንግ ጋር የሚያመሣሥላቸው አሜሪካዊ ዜግነታቸውና ሠብአዊ ተፈጥሮአቸው እንዲሁም ፍትሀዊ የፖለቲካ አቋማቸውና፤ ሁለቱም በዚህ እውነትና ፍትህን መሠረት ባደረገ አቋማቸው ምክንያት በታጣቂዎች መገደላቸው ነው፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ የተገደለው በዚህች ምድር ላይ ሠላሣ ዘጠኝ ዓመታት (ለህዝቡ መብቶች በመጋደል) ኖሮ ነው፤ እ.ኤ.አ በ1968 ወይም በእኛ በ1960 ዓ.ም፤ ልክ የዛሬ አርባ አራት ዓመት፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ የጥቁሮችን የጭቆና ቀንበር ከጥቁር ህዝቦች ጫንቃ ላይ አንስቼ በነጮች ጫንቃ ላይ ልጫን አላለም፡፡ ጭቆናና አድሎአዊነት ተወግዶ ሁሉም እኩል ይሁን ነው ያለው፡፡   ለመጀመሪያ ጊዜ ይሄንን ሠው ከኢትዮጵያውያን ጋር ያስተዋወቀው በጥበብ ቤተሠቦችና በብዙኃን ዘንድ እምብዛም የማይታወቀው አያሌው ቀኖ የተባለ ኢትዮጵያዊ ምሁርና ተርጓሚ፡- ማርቲን ሉተር ኪንግ በተሠኘ መፅሀፉ ነው፡፡

አንድ መፅሀፉ፡- የአንድ ቤተ መፃህፍት ያህል የዕውቀት ሙላት ያለው፤ ከሃያ መፃህፍት በላይ የፃፈው እና የሥምንት ልጆች አባት የሆነው አሜሪካዊው ተመራማሪ የዩኒቨርሢቲ ሌክቸረር ደራሢና ሀሣበ ትጉህ ዶክተር ዋይኒ ደብሊዩ ዳየር Wisdom of the Ages Sixty days to Enlightenment በሚል ርዕሥ በፃፈው መፅሀፉ ስለ ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ አውሥቷል፡፡

በዚህ ተወሺ በታላላቅ ሠብዕናዎች እምቅ ምጥንና ቅንብብ ጥናቶች ጢም ባለ መፅሀፍ ገፅ 251 ላይ ማርቲን ሉተር ኪንግ ሠላማዊ የትግል ሥልት (NONVIOLENCE) የሚል ምዕራፍ አግኝቷል፡፡

ሠላማዊ የትግል ሥልት ከመቅፅበት የጨቋኞችን ልብና አእምሮ የሚማርክ ወይ የሚለውጥ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ ለነፍሣቸውና ለንፁህ ልባቸው ታማኝ በሆኑት ሠብአዊ ተፈጥሮ ባላቸው የሠው ልጆች ውሥጥ መሥራት ይጀምራል፤ ራሥን ማክበር ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንደ አዲስ ያሣያቸዋል፤ በተፈጥሮ ያላቸውን ነገር ግን ያላቸው መሆኑን የማያውቁትን ያውቁ ዘንድ ለጥንካሬያቸውና ለብርታታቸው የበለፀገ ሠብአዊ ባህሪ ጥሪ ያደርጋል፤ በመጨረሻም በነርሡ ውስጥ በመዳረሥ በነቃ ንቃት ወደ እውነተኛውና ትክክለኛው እውነትና እውነታ ይመጡ ዘንድ ለዚህ ክብር ያበቃቸዋል፡፡

ይህ የማርቲን ሉተር ኪንግ ድምፅ እና የእኔው የአማርኛ ትርጓሜ ነው፡፡

The non-violent approach does not Immediately change the Heart of the Oppressor. It first does something to the Hearts & Souls of those committed to it. It gives them A new self Respect; It calls up resources of strength & courage that they did not know they had. Finally it reaches the opponent & So stirs his conscience that reconciliation becomes a reality.

ዋይኒ ዳየር፡- ይህ የማርቲን ሉተር ኪንግ አባባል 2600 ዓመታት ወደ ኋላ ወስዶ ቡድሀ ጉታማን ያስታውሰኛል … ይላል፡፡

ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ በሚናገርበት ጊዜ ለሠላማዊ የትግል ሥልት ራሣቸውን በሠጡ ሠዎች ነፍሥና ልብ ውስጥ የሚሠራ ሥራ አለ፡፡ የሚናገረው ስለ ህዝቡ የእኩልነት መብቶች ወይም በመደቦች መሀከል ስለሚከወን ግብግብ ብቻ አይደለም፡፡ ጢም ያለ ሠላም የተመላ ልብ እንዲኖረን ራሣችንን እስካዘጋጀን ድረስ ከዚህም በላይ የሆነውንና በውስጣችን በተፈጥሮ እንደተሠራ የማናውቀውን ላቅ ያለ ሠብዕና እንድንቀዳጅ ጥንካሬና ብርታት እንዲኖረን ጉልበት ነው የሚሠጠን፤ ወይም ነፍሣችንን ከህዝቡ መብት ትግል ላለፈ (ከትግሉ በኋላ ለሚቀጥል ዘላቂ ህይወታችን) ከፍ ላለ ብቃት ነው የሚያሠናዳት፡፡ በተፈጥሮ ያለንን ነገር ግን እንዳለን የማናውቀውን ከፍ ያለ ሠብዓዊ ፀጋ ነው በንግግሩ የሚያሣየን፡፡

እንዲያውም ዋይኒ ዳየር የማርቲን ሉተር ኪንግን ሠብዕና ከቡድሃና ከኢየሡሥ ክርስቶስ አድራጐት ጋር ከተጣመረ ለእግዚአብሔር ከቀረበ ባህሪ ጋር ነው የሚያመሣስለው፡፡ በአጭሩ ቁርጥ ቁምጥ ባለ አገላለፅ ዋይኒ ዳየር፡- የማርቲን ሉተር ንግግር ወደ እግዚአብሔር የማሣደግ አቅም አለው ነው ያለው፡፡

በ2010 (ወይም በእኛ 2002 ዓ.ም.) ይህቺ ዓለም ሁለት ታላላቅ ድሎችን ተቀዳጅታለች፡፡ ይኸውም የባራክ ኦባማ የአሜሪካ አርባ አራተኛው ፕሬዚዳንት ሆኖ መመረጥ፤ እና በደቡብ አፍሪቃ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ መካሄዱ ናቸው፡፡ ለዚህች ዓለም ሁለቱም ድሎች ያላቸው መልክ (ባህሪ) ፖለቲካዊ ገፅታ ነው፡፡ በዘር መድልኦ ፖሊሲ ምክንያት ጥቁር ሠው መርቷት በማያውቀው አሜሪካ የአፍሪቃ ኬንያዊ ሥረ መሠረት ያለው ባራክ ኦባማ መመረጥ ከአሜሪካን ልብና አእምሮ ላይ የሬሢዝም የመጨረሻው ጥርሥ መነቀሉን አበሠረ፡፡ በክፍለ ዘመን ለሚለካ ለተለጠጠ ዕድሜ የጥቁርና የነጭ የዘር መድልኦን በይፋ ህጋዊ አስተዳደሯ ጭምር አድርጋ አንሰራፍታ በኖረችው ደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ መካሄዱ የአፓርታይድ የመጨረሻው ጥርሥ መነቀሉን ተናገረ፡፡

I have a dream (ህልም አለኝ ስለ አገሬ) በሚል በጐና ቆራጥ ራዕይ ባለው ንግግሩ የሚታወቀው ማርቲን ሉተር ኪንግ በጥይት ነው የተገደለው፡፡ ለጥቁሮች እኩልነት የታገሉና ትግሉን የመሩ ማልኮልም ኤክስና ሌሎች ጥቁር አሜሪካውያንም አሉ፡፡ ኦባማ ሲመረጥ ጥቁር አሜሪካዊው ቄስና የህዝቦች መብት ታጋይ ጄሢ ጃክሠን በደስታ ፍንቅል ብሎ እምባው በዓይኖቹ ግጥም ክንብል ብሎ ነው የታየው፡፡ ነጭ የሆኑ  የፖለቲካ ሳይንቲስቶችና ሊቃውንት ስለ ኦባማ የሠጡት አስተያየት ደግሞ ለአሜሪካና ለዓለም ተሰውሮ የኖረ ድል መበሠሩን፤ የማርቲን ሉተር ኪንግ ህልም መፈታቱን ነው ያመለከተው፡፡

የዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግን ሠላማዊ የትግል ሥልት (ሠላማዊ ሠብዕና) Nonviolence ፅንሠ ሃሣብ መርሆው አድርጐ ቢሊዮን ህዝቦችን ለድል ያበቃ ሌላው ሠው የህንድ የነፃነት አባትና የአዲሢቲ ህንድ ነቢይ መባል የሚያንሰው፡- ሞሀንዳስ ካራሞቻንድ ማኅተመ ጋንዲ ነው፡፡ ጋንዲ፡- ህንድና ፓኪስታንን ከእንግሊዞች ቅኝ አገዛዝ ነፃ ያወጣው በሣድያግራሃ ሣትያግራሃ (ሠላማዊ የትግል ሥልት) መርሆ ነው፡፡ በመጨረሻ ሁለቱ አገሮች ነፃ ከወጡ ከአንድ ዓመት በኋላ ሙስሊሞችንና ሂንዱዎችን ለምን እኩል ወደድከን (ለምን አንደኛችንን አስበልጠህ አልወደድክም) ካሉ ታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይት እ.ኤ.አ በ1948 (በእኛ በ1940 ዓ.ም) ተመትቶ ተገድሏል፡፡

ከሂንዱኢዝም ሃይማኖት አስተምህሮ አንዱ፡- አሂምሣ ነው፤ ሠላማዊ ሠብዕናና ተፈጥሮን ማክበር የሚል፡፡ ጃይኒ ሲኪ የተሰኙ የሃይማኖቱ ክፍሎች (Sects) አሉ፡፡ ጃይኒ፡- ማለት ራሥን መተውና ሠላማዊ ሠብዕና Self Denial & nonviolence ማለት ነው፡፡ አቀራረቡ ይለያይ እንደሆነ እንጂ በማናቸውም ሃይማኖት አስተምህሮ ወይም ከፍ ባለ ፍልሥፍና ውስጥ የሠላማዊ ሠብዕና (Nonviolence) መርሆ ንድፈ ሃሣብ አለ፡፡ በሌሎች ከፍ ባሉ ታላላቅ አስተሣሰቦችም ጭምር ይሄ አለ፡፡

ዶክተር ማርተን ሉተር ኪንግ በ1940ዎቹና ሃምሣዎቹ ውስጥ ይሄንን ንድፈ ሃሣብ አንግቦ ብቅ ያለ የህዝቦች መብት ታጋይና በዓለም ታሪክ አንዱ ታላቅ ሰብዕና ነው፡፡

ዶክተር ዋይኒ ዳየር የዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግን ሠላማዊ የትልግ ሥልት (ወይም ሠላማዊ ሠብዕና) መርሆን መነሻና መድረሻው አድርጐ የዚህ መርሆ አካል ለመሆን ይረዳሉ ያላቸውን ነጥቦች በሚከተለው አኳኋን አስቀምጧል፡፡

ከማናቸውም ሠላማዊ ላልሆነ ፀብ ከሚጋብዝ ድርጊትና እንቅስቃሴ ራሥን መግታት፤ እናም የሠላም መጠቀሚያ “የጦር” ዕቃ መሆን፤ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የሃይማኖት አባቶችና መንፈሣዊ መምህሮቻችን ጉልበት የሚሠጡን ይሆናል፡፡

ወደ የዕለት ተዕለት ህይወትህ የበዛ ሠላም ለማምጣት የሚያስችልህን ሥራ በየቀኑ መሥራት፤ ተመሥጥኦና በአርምሞ ለመቀመጥ (ለመቆየት) የሚያስችል ጊዜ እንዲኖርህ ማድረግ፤ ዮጋ (ን) መለማመድ፤ ግጥምና ቅኔዎችን እንዲሁም የመሳሰሉትን ማንበብ፤ በመፈታት መንፈሥና በነፃነት በእግሮችህ የምትንሸራሸርበትን ሁኔታዎች መፍጠር፤ ከመብልና ከፍቅር በቀር አንዳች ከማያውቁ ህፃናትና እንሥሣት ጋር መጫወት፤ እናም ከዚህ በተጨማሪ የማፍቀር ስሜትህን የሚያጐለብቱና መፈቀርን የሚያሣድጉ ማናቸውንም በጐ እና ደጋግ ነገሮችን ሁሉ የማድረግ ባህሪን ማበልፀግ፤ ይህም በተፈጥሮ ወዳለህ ሆኖም እንዳላህ ወደማታውቀው ተፈጥሮአዊ ከፍታና አምላካዊ ባህሪ ለማደግ ይረዳሃል፡፡

ሠላማዊ ላልሆነ ግፊት የሚዳርጉ ሁኔታዎችን ከህይወትህ ውስጥ ማስወገድ፤ ጥላቻ የተመሉ ድርጊቶችን የማሣወቅ ተግባር ያላቸው የመገናኛ ብዙኃን ገለፃዎች ሲቀርቡ ሠብአዊነት የጐደላቸው ድርጊቶች ሁሉ በሠው ልጅና በተፈጥሮ ላይ ያደረሡትን ሁለንተናዊ ጉዳት አስታወሥ፡፡ ከዚሁ ጋር በበጐነትና በደግነት የተመሉ ሺህ ምንተሺ አደራጐቶች መኖራቸውን ተገንዘብ፡፡

ይሄንን የጥንት ቻይናውያን አባባል ጨምሬ ላስታውሥህ እወድዳለሁ፡- The Sage does dot talk, the talented ones talk, And the Stupid ones argue አሮጌው ሠው አይናገርም፤ ያንቀላፋል፤ የፀጋ ሥጦታ ያለውና የተካነው ጐበዙ ሠው ይናገራል፤ እናም ደደቡ ሠው ከሥምምነት ላይ ይደርሣል፡፡

የቻይና ትልቁ የፍልሥፍና መፅሀፍ፡- የሚያውቁ አይናገሩም፤ የሚናገሩ አያውቁም ይላል፡፡ እንደዚህ (የኢትዮጵያዊ) ፀሀፌ አስተሣሰብ፡- ይሄ ቻይናዊ አባባል የእውነት የነፀረ መዳረሻ አይደለም፡፡ መናገር ሲገባ፡- የግድ መናገር ያስፈልጋል፤ መናገር በማያስፈልግበት ሁኔታ ደግሞ ያለመናገር ይመረጣል፡፡ የሠው ልጅ ከመናገር መቆጠብ ያለበት የሥንፍናን ወሬ እና ከጉዳት በቀር ጥቅም የሌላቸውን ነው፡፡ ቅዱስ ቁርዓን በጐ ይናገር ያለበለዚያ ዝም ይበል ይላል፡፡ መፅሀፍ ቅዱስ በኃይልህ ጩህ አትቆጥብ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ … ስለ ዲዳው አፍህን ክፈት ይላል፤ ከሥንፍና ወሬ ባሻገር የሠውን ልብና አእምሮ ለማነፅ ጉልበት ለሌለው አንደበት ደግሞ፡- ሞኝ ዝም ሢል ብልህ ይመስላል … ተብሎ ተፅፎአል፡፡

የዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ንግግር እስከ ዛሬው ዘመን እንኳ የብዙዎችን ልብና አእምሮ ማርኮ ሠርጿል፤ I have a dream (ህልም አለኝ ስለ አገሬ) ነው ያለው አጥንት ድረስ በሚዘልቅ ኃያል ጥዑም ሞገሥ (Grace) ባለው ባለግርማ ድምፅ፡፡

ሠላምዎ ይብዛ!  በፍቅር!

Soli. Deo.Gloria!

 

 

Read 4877 times Last modified on Saturday, 21 April 2012 16:10