Saturday, 21 April 2012 16:10

“ተሻገር ረጋ ብለህ፤ ተሳፈር ረጋ ብለህ“

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)

“ለህይወት ግብ እንድንበቃ የትራፊክ አደጋ ይብቃ!” በሚል መርህ የትራፊክ ደህንነት ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማቅረብ በአንድ ሳምንት ተግባራዊ ከሆኑት መርሐ ግብሮች መካከል ማክሰኞ ሚያዝያ 1 ቀን 2004 ዓ.ም በቸርችል ሆቴል የተሰናዳው የፓናል ውይይት አንዱ ነበር፡፡ በዕለቱ ጥሪ የተደረገላቸውን ሰዎች እየተቀበሉ ያስተናግዱ የነበሩት ዋና ሳጅን አሰፋ መዝገቡ፤ አረፍ እንዲሉ የፈለገ አንዱ ወዳጃቸው “ና እዚህ ጋ ቦታ አለ” ሲላቸው “ቆሜም አደጋው በቀነሰ!” በማለት እየቀለዱ የችግሩ ስፋት ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የመንገዶች ባለስልጣን፣ ፖሊስ ኮሚሽንና የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ከ “ለታሪክ አድቨርታይዚንግ” ጋር በመተባበር ባዘጋጁት መድረክ፣ የተለያዩ  ባለድርሻ አካላት በመገኘት በችግሩ ዙሪያ በስፋት ተወያይተዋል፡፡ የጥናት ጽሑፎችም ቀርበዋል፡፡ በመንገድ ትራፊክ አደጋ የተጎዱ ቤተሰቦችም ተጋብዘዋል፡፡ ወንድሙን በመኪና አደጋ ያጣው ወጣት ደረሰ ፋሲካ ሲናገር፡-

“ወንድሜ በመኪና አደጋ ጭንቅላቱ ላይ ተገጭቶ ነው የሞተው፡፡ የልጇ ሞት የእናታችን ስሜት በእጅጉ ጎድቷታል፡፡ እኔና እሱ በጋራ እንደርስበታለን ብለን ያቀድነው ዓላማ ነበር፡፡ ያንን ብቻዬን ተግባራዊ ማድረግ አልቻልኩም፡፡ በወንድሜ ላይ አደጋው ከደረሰ በኋላ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመስራት ላይ እንገኛለን፡፡ በእኔ ወንድም ላይ የደረሰው አደጋ በሌላ ሰው ላይ እንደማይደርስ ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ የማናውቀው አሽከርካሪና የማናውቀው መኪና እኛን ሊጠብቁ አይችሉም፡፡ እግረኛው፣ አሽከርካሪው፣ ሕግ አስከባሪው … ሁሉም የየራሱን ድርሻ ሲወጣ ግን አደጋው ይቀንሳል፡፡”

“ሲዲሌ” በሚል ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አገራችን የገባው መኪና መቶኛ ዓመት ባስቆጠረበት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያሉት መኪኖች ቁጥር 400ሺህ መድረሱ የተገለፀ ሲሆን በአገሪቱ ካሉት መኪኖች የሚበዛው ቁጥር በአዲስ አበባ እንደሚገኝና በከተማዋ እየጨመረ ለመጣው የትራፊክ አደጋ አንዱ ምክንያት ይሄ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በገዳይነቱ በቀዳሚነት የተመዘገበው የትራፊክ አደጋ 90 በመቶ ያህሉ የሚከሰተው በታዳጊ አገሮች ቢሆንም በዓለም ላይ ከሚገኙ መኪኖች 48 ከመቶ የሚሆኑት ብቻ በታዳጊ አገራት እንደሚገኙ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

በጥናታዊ ጽሑፎች ላይ እንደተጠቆመው በአዲስ አበባ ከተማ ረቡዕና ቅዳሜ ከሌሎች ቀናት በተለየ የመኪና አደጋ በብዛት የሚከሰት ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ በሁለቱ ቀናት ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ ስለሚከናወን ነው ተብሏል፡፡ የሚገርመው ደግሞ አደጋ ከሚያደርሱት መኪኖች 90 ከመቶ የሚሆኑት ምንም ቴክኒካል ችግር የሌለባቸው መሆኑ ነው፡፡ ብዙዎቹ የመኪና አደጋ የሚያደርሱ አሽከርካሪዎችም  ከ5 ዓመት በላይ የመሾፈር ልምድ ያላቸውና የተማሩ የሚባሉ ናቸው፡፡

አደጋ ካደረሱት ሾፌሮች ውስጥ 88.4 ከመቶ የሚሆኑት ወንዶች ሲሆኑ 3.4 ከመቶዎች ሴቶች ናቸው፡፡ 8.2 ከመቶ የሚሆኑት ማንነታቸው አልታወቀም፡፡

የመኪና አደጋ በተደጋጋሚ ከተከሰተባቸው ቦታዎች ቀዳሚውን ስፍራ የያዙት መሥሪያ ቤቶች የሚበረከቱባቸው ቦታዎች ሲሆኑ በቀጣይነት ገበያ፣ ሦስተኛው ደግሞ የመኖሪያ መንደሮች እንደሆኑ በጥናት አቅራቢዎቹ ተብራርቷል፡፡

የማሽከርከር ፍጥነት፣ የመንገዱ ሁኔታ፣ የዕለቱ አየር ፀባይ … የመሳሰሉት ምክንያቶች ለመኪና አደጋ መከሰት አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ በተገለፁበት መድረክ፤ በመኪና በሚደርስ አደጋ የሚጠፋው ሕይወትና የሚወድመው ንብረት እየጨመረ በመምጣቱ ሳቢያ ለረጅም ርቀት ብቻ ሳይሆን ለአጭር ርቀት ጉዞም ወደ መኪና ሲገቡ የሚፀልዩ ሰዎች በዝተዋል ተብሏል፡፡

ባለፉት 10 ዓመታት ለማስተማሪያነትና ለቅስቀሳ ያገለገለው “አሽከርክር ረጋ ብለህ” የተሰኘ ዜማ “ተሻገር ረጋ ብለህ”፣ “ተሳፈር ረጋ ብለህ” በሚል መለወጥ አለበትም ተብሏል፡፡ በትራፊክ አደጋ እየደረሱ ያሉት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምን ያህል ሰፊ እንደሆኑ፣ በመኪና አደጋ እየደረሰ ያለውን ኪሳራ ማዳን ቢቻል ኖሮ ሊነገቡ ይችሉ ስለነበሩ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመኖሪያ ሕንፃዎች ብዛት በንጽጽር ለማቅረብም ተሞክሯል፡፡

የሦስተኛ ወገን የሕይወት ኢንሹራንስ መጀመሩ በዘርፉ ያለውን ችግር ለመቀነስ፣ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ቢታመንም፣ በፊት የነበረው የትራፊክ አደጋ ኢንሹራንስ በኩባንያዎቹ ይታይ የነበረው በአክሳሪነቱ እንደነበር ከመድን ኢንሹራንስ የተጋበዙ ባለሙያ ገልፀዋል፡

በዕለቱ በጥናት አቅራቢዎቹ የቀረቡት መረጃዎች ከፖሊስ የተገኙ እንደሆነ የጠቆሙት ኢንጂነር ፈቃደ ኃይሌ፤ አደጋ ደርሶም በተለያየ ምክንያት ላይመዘገብ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ አመልክተው፣ በትራፊክ እንቅስቃሴው ላይ ያለውን አደጋ ለመከላከል ከምንም በላይ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ሲቪል ሰርቪስ በትራንስፖርት ባለሙያነት በማስተርስ ደረጃ እያስተማረ ያስመርቃል፡፡ ባለሙያዎቹ የት ነው ያሉት? ለልማት ሥራ መንገዶች ከተቆፈሩ በኋላ ክፍት መተዋቸው ለአደጋዎች መከሰት አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ይታያል፡፡ ይህ ለምን ይሆናል? ማንስ ይጠየቅበት? የትራፊክ እንቅስቃሴውን ሰላማዊ ለማድረግ ተጀምረው ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ከታየ በኋላ የተቋረጡ ነገሮች አሉ፡፡ ምክንያቱ ምንድነው? የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል፡፡ ከፌደራል ፖሊስ የመጡ ተወካይ፤ የመንገድ ዜብራ አጠቃቀምን በተመለከተ ከአዲስ አበባ ይልቅ በክልል ከተሞች የተሻለ ሥራ መሰራቱን አመልክተው “በአዲስ አበባ በተማሪዎች፣ በእግረኞች፣ በሹፌሮች፣ በማሰልጠኛ ተቋማት … ትምህርትና የግንዛቤ ሥራ የመስራቱ ተግባር በአዲስ መልክ መጀመር ያለበት ይመስለኛል” ብለዋል፡፡ ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የመጡ ተወካይ በበኩላቸው፤ በቀለበት መንገድ ላይ ባልተፈቀደ ቦታ የሚያቋርጡ እግረኞችን በመያዝ 60 ብር ወይም 24 ሰዓት ለሕብረተሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ሞክረው እንደነበር አመልክተው፤ አፈፃፀሙን ሕጋዊ ለማድረግ ግን ንግድ ቢሮን የመሳሰሉ አስፈፃሚ አካላት ሕጋዊ ውክልና ባልተሰጠን ጉዳይ አንገባም በማለታቸው፣ ጥሩ ውጤት ታይቶበት የነበረውን ጅምር ለማቋረጥ መገደዳቸውን አብራርተዋል፡፡ ከአንበሳ የከተማ አውቶብስ ድርጅት የመጡ ተወካይም የትራፊክ እንቅስቃሴውን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ሕጎችን የማውጣትና የማሻሻል ሥራዎች ቢሰሩም አስፈፃሚ አካላት ኃላፊነታቸውን በሚገባ አለመወጣታቸውን በምሳሌ አስደግፈው ሲያቀርቡ የቤት እንስሳት በመኪና መንገድ እንዳይንቀሳቀሱ የሚከለክል ሕግ ቢኖርም ተግባራዊ መሆን ስላልቻለ በመንገድ ትራንስፖርት የሚጠፋው የሰው ሕይወትና የሚወድመው ንብረት መጨመሩን አመልክተው፤ ለዚህ ችግር ማነው ተጠያቂው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ከ“ጠብታ አምቡላንስ” የመጡት የሕክምና ባለሙያ፤ የመኪና አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ቀዳሚውን እርዳታ በምን መልኩ ማግኘት እንዳለባቸው በሞዴል ማሳያዎቻቸው ለተሰብሳቢዎች ካብራሩ በኋላ፤ በአሁኑ ሰዓት በአገራችን የሚታየው የመኪና አደጋ አገሪቱ ባንዲራዋን ዝቅ አድርጋ ማውለብለብ የሚገባት ደረጃ ላይ ያደረሳት እንደሆነ ከጠቆሙ በኋላ፣  ለውጥ የሚመጣው በንግግር ሳይሆን በተግባራዊ ሥራ እንደሆነ በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡

በፓናል ውይይት፣ በእግር ጉዞ፣ በአደባባይ ቅስቀሳና በመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች ለአንድ ሳምንት የቆየው የትራፊክ ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅት አካል ሆኖ ከሚያዝያ 4 እስከ 10 ቀን 2004 ዓ.ም በኢትዮ ኩባ ወዳጅነት አደባባይ (ድላችን ሐውልት) ለሕዝብ እይታ የቀረቡት 10 ጉዳት የደረሰባቸው መኪኖች፣ ችግሩ ምን ያህል የከፋ መሆኑን በምስክርነት የሚያሳዩ ናቸው፡፡

 

 

 

 

Read 3012 times Last modified on Saturday, 21 April 2012 16:17