Saturday, 21 April 2012 16:18

ኢየሱስን ወይስ ቼ ጉቬራን?

Written by  ቢኒያም መንበረ ወርቅ Yambini77@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

ከአብዛኛዎቹ የእድሜ ቢጤዎቻቸው በተቃራኒ “በኔ ትውልድ” ፍቅር የወደቁት በእጅጉ የምናፍቃቸው ጋሽ ስብሐት ለአብ እንደ እኔ የነፃነት ኑሯቸውን የሚወድላቸው በርከት ያለ ሰው የመኖሩን ያህል ባደረጉ በተናገሩት፣ ባሰቡ በፃፉት የማይደሰቱ ሰዎችም መኖራቸውን መታዘብ ችያለሁ፡፡ በእሳቸው ጉዳይ ዝምታን እንመርጣለን የሚሉ ሰዎች ከሚጠቃቅሷቸው “ደፋር” የጋሼ ንግግሮች መካከል አሁን ላነሳው የፈለግሁት መቼ እንደሰጡት በትክክል በማላስታውሰው ቃለ-ምልልስ ላይ ኢየሱስንና ኤርኔስቶ ቼ ጉቬራን ያነፃፀሩበትን ገለፃቸውን ነው፡፡ በዚያ ቃለምልልስ ላይ ጋሽ ስብሐት እጃቸውን እያወናጨፉ ያሉትን ያስታወስኩትን እንደሚከተለው እደግመዋለሁ፡፡ “እኔ ኢየሱስ በዚህ፣ ቼ ጉቬራ ደግሞ በሌላ አቅጣጫ ተከተለኝ ቢሉኝ እኔ የምከተለው ቼ ጉቬራን ነው፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ የሞተው በሦስተኛው ቀን እንደሚነሳ ስለሚያቀው ነው” ብለዋል፡፡

የኢየሱስ ስቅላትና ሞት እንዲሁም ሞትን ድል መምታት ተደጋግሞ በሚሰበክበት የትንሳኤ ሰሞን ይችን ወግ ማቅረብ “ወቅቷን የጠበቀች” የሚል ሙገሳ ይለገሳት ይሆናል፡፡ ነገርን ነገር ያሳዋል እያሉ ስለ ዘፍጥረት በማውራት የጀመሩትን ወሬ የላንዳች ርህራሄ ወደ ዮሐንስ ራእይ የሚያደርሱ የወሬ አትሌቶችን ዘይቤ መጠቀም ካሰኘም ….የኢየሱስ ስቅለት የጋሽ ስብሐትን የኢየሱስና ቼ ጉቬራን ንፅፅር አስታወሰኝ በለት መቀጠል ይቻል ነበር… ለነገሩ ሜዳሊያ የበሉ የወሬ ዘላዮች የስብሐትን ወሬ “ቼ ጉቬራ ስትል ድሮ ተማሪ እያለን የጨፈረንበትን የአራት ኪሎውን “ቼ” ባር አስታወስከኝ” በሚል ሰበብ… ቼ ባር ውስጥ ስለጠበሷት ቀሽት ልጅ ወደ ማውራት ሊያሸጋግሩት ይችላሉ… ለወሬ ዘላዮች የሚሳናቸው ነገር የለምና፡፡ እንደ አቅሚቲ እኔም እዘላለሁ… (ከስብሐት ለአብ ንግግር ወደ ወሬ ዘላዮች) ወደ ወጌ መም(ትራክ) ልመለስ… (በዝላዩ የተነሳ እያለከለኩ)

ጋሽ ስብሐትን (ከራማቸው ሁሌም ከኛ ጋር ይሁንና) እወዳቸዋለሁ እንጂ… የሚያደርጉትን ሁሉ ዝም ብዬ አልደግምም፤ በሚናገሩት ነገር ሁሉ ዝም ብዬም አልስማማም…፡፡ የእሳቸው መንገድም ይህ አይነቱን “በቀቀናዊ” ባህርይ በእጅጉ ይነቅፋል፡፡ እናም ቀደም ብዬ የጠቀስኳትን ንግግራቸውን፣ አቅሜ ለማየት ከፈቀደልኝ አቅጣጫ ሁሉ ለማየት ሞክሬያለሁ… እነሆ ሙከራዬ፡፡

የሙከራዬ ጉዞ፤ ጋሽ ስብሐት ክርስቶሳውያን ጌታችን… መድኃኒታችን  ወልደ እግዚአብሔር እያሉ አመስግነው የማይጠግቡትን ክርስቶስ ከመከተል ይልቅ ቼ ጉቬራን ለመምረጥ ያቀረቡት ምክንያት ምን ያህል ያሳምናል? በእርግጥ ኢየሱስና ቼ ጉቬራ መነፃፀራቸውስ ተገቢ ነው ወይ? መነፃፀር ካለባቸው የማነፃፀሪያ መስፈርቶቹ ምን ሊሆኑ ይገባል? አነፃፅሮ የመምረጡ ነገር የግለሰቦች ምርጫ ነው? ወይስ ተጨባጭ መነሻ አለው? ከሚሉት ጥያቄዎች መካከል በተወሰኑት ዙሪያ የሚሽከረከር ነው፡፡

ኢየሱስና ቼ ጉቬራ መነፃፀር አለባቸው ወይ? የሚለውን ጥያቄ ለማየት ከመንደርደሬ በፊት፤ የትኛው “ኢየሱስ” ነው ከቼ ጉቬራ ጋር የሚወዳደረው? ከሚለው ጥያቄ ጋር መጋፈጥን ላስቀድም፡፡

የኢየሱስን ባህርይ በተመለከተ የሚቀርቡ አቀራረቦች ከሰውነት ጀምሮ እስከ አምላክነት ይደርሳሉ፡፡ በመሃከል ነቢይነትና ልዩ ፍጡርነትን የመሰሉ ባህርይዎችም ይጠቀሳሉ፡፡ “የትኛው ኢየሱስ?” ማለትም፤ ከተጠቀሱት በየትኛው ባህርይ የታወቀው ኢየሱስን ያመላክታል ማለት ነው?

ከዚች ፅሁፈ ዓላማ አንፃር፣ ጠቃሚ የሚሆኑት ሁለቱ ፅንፎች ናቸው - ሰው ኢየሱስና ፈጣሪው ኢየሱስ፡፡ ከመጀመሪያው አቀራረብ አንፃር ካየናቸው ኢየሱስና ቼ ጉቬራ ሁለቱም ሰዎችና… ሊነፃፀሩም የሚችሉ አቻ ህላዌያት ናቸው፡፡ የተለያየ ዘመን ላይ መከሰታቸውና (ሌሎች ንፅፅሩን የሚያወሳስቡ ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው)፣ ያደጉትን አስተዋፅኦ፣ የከፈሉትን መስዋእትነት፣ የወደቁለትን ዓላማ ትልቅነት መመነሻ አድርጐ ማነፃፀር ይቻላል፡፡ ይሁንና፤ ለክርክር የማይጋብዝ፣ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነትን የሚያገኝ… የንፅፅር መደምደሚያ ላይ ለመድረስ የሚቀል አይመስልም፡፡ የፈለገውን መርጦ ሰው ሊከተል… አሊያም ሁለቱንም ላይከተል ይችላል፡፡ ሁለቱንም በተለያየ ሁኔታና ጊዜ እያለዋወጠ ለመከተልም ነፃነት አለው፡፡

ከሁለተኛው አቀራረብ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከት የምናገኘው ምስል ግን በፍጹም የተለየ ነው፡፡ ሰውና አምላክን ማወዳደር ብርቱካንና ፖምን ከማወዳደርም በላይ የማያስኬድ ንጽጽር ነው፡፡ ከ”ሃሊ ኩሉ” የሆነ አምላክን እጅ ሥራ ከሆነ ፍጡር ጋር በተመሳሳይ ሚዛን ማወዳደር ተገቢ አይመስልም፡፡ ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ የሆነ አምላክ… ለሰው ልጅ የገባውን ቃል ለመጠበቅ፣ በአምሳለ - ሰው ተገልጾ፣ በፍጹማዊ ሕይወቱ ያከናወናቸውን ተግባራት ፍጹማዊነት ዓላማው እንጂ ሕይወቱ ሆኖ ከማያቅ ሰው ጋር ለማነጻጸር የሚያስችል የጋራ መስፈርት ለማውጣትም ይቸግራል፡፡ ፍጹማዊነትንና ኢ-ፍጹማዊነት ለመከተል ለምርጫ ማቅረብም ጥያቄን ከነመልሱ አቅርቦ የመጠየቅን ያህል ቀላል ይመስላል፡፡

እዚህ ላይ ጋሽ ስብሐት የተከተሉት አቀራረብ የትኛውን ነው የሚለውን ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንን በማያወዛግብ መልኩ ለመደምደም ቢያስቸግርም፣ የሁለተኛውን አቀራረብ ወይንም ሁለቱን ባቀላቀለ መልኩ ወደ ማነጻጸሩ እንደገቡ መገመት ይቻላል፡፡ የሁለተኛውን አቀራረብ ለመከተላቸው መነሻ የሚሆነው ሀሳብ ኢየሱስ እንደ ሰው ከታየ፣ በሦስተኛ ቀን መነሳቱን ማወቅም ሆነ መነሳት የሚችልበት የተለየ አቅም ሊኖረው ይችላል ብሎ ለመቀበል የማያስችል አንድ እንኳ ምድራዊ ምክንያት ሊቀርብ አለመቻሉና… የጋሽ ስብሐትም ይህን መቀበል የኢየሱስን አምላካዊ ባህርይ ከሞላ ጎደል ተቀብለዋል፤ ብሎ ለመውሰድ ስለሚያግዝ ነው፡፡ በሦስተኛው ቀን መነሳቱን ማወቅና፣ መነሳት የማይችለውን ቼ ጉቬራን ይችን ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር ካመጣው አልፋና ኦሜጋው ኢየሱስ ጋር ማወዳደር ፍጡሩን ከፈጣሪ በላይ አምኖ ለመከተል የሚችልበት እድል ካለም አምላካዊነትን ከነጣጣውና ግሳንግሱ አለመቀበል ነው ማለት ሊሆን ይችላል፡፡ የጋሽ ስብሐትን አቀራረብ አጠቃሎ ወደ አማኝ ቡድን ከመመደብ ይልቅ… የኢየሱስን አምላካዊነት ከሚያስከትለው ግዴታ ጋር በሙሉ ልብ አለመስማማት ጋር ጠቅልሎ መውሰድ የበለጠ ትክክል ነው፡፡ የጋሽ ስብሐትን ንግግር (ሌሎች ስለእሳቸው ካሉኝ ተጨማሪ መረጃዎች ጋር ደምሬ) ለመገመት ስሞክር፣ የንጽጽራቸው መነሻም ሆነ መድረሻ… ይሄው የኢየሱስን አምላክነት በሙሉ ልብ ያለመቀበል ነው፡፡

አሁንስ ማንን ትከተላላችሁ? ኢየሱስን ወይንስ ቼ ጉቬራን? ሰው ሁሉ ከማንኛውም ዓይነት ብዝበዛና ጭቆና ተላቆ በእኩልነትና በመተጋገዝ የሚኖርበትን የኮሙኒክም ሥርዓት ለመመሥረት የሚገሰግሱ ተራማጅ ትግሎችን ለመደገፍ ከላይ ታች ሲል የሞተውን፣ የአገራት ሰው ሠራሽ ድንበር ሳያግደው… በሰውነት አንድነት ትውልድ አገሩን አርጀንቲናን ትቶ… ከኩባ እስከ ኮንጎ ከዚያም እስከ ቦሊቪያ ድረስ በጽናት የታገለው ሀኪሙን ኤርኔስቶ ጉቬራን (ቼ)ን… ወይንስ ምንም ዓይነት ማስተዋወቅ የማያስፈልገውን ሁላችሁም አብዝታችሀ የምታውቁትን (በተለያየ መልኩ የተገለጠላችሁን) ኢየሱስ ትከተላላችሁ? … እኔ ግን በራሴ ምክንያት፤ መሰቀሉና በሦስተኛው ቀን ሞቶ መነሳቱ ብዙም ሳያሳስበኝ፤ ፍቅርንና ቅንነትን፣ እየሞቱ ማሸነፍን፣ በትንሽነት ውስጥ ትልቅ መሆንን፣ ኅብረትንና መተዛዘንን የሰበከውን ኢየሱስን ከአብዮተኛው ቼ አስቀድሜ በብዙ መልኩ እከተለዋለሁ፡፡ ዝም ብሎ መከተል እኔ ጋ ቦታ የላትም … የቶማስ ከራማ እኔ ጋ ትሰፍር ዘንድ ፍቃድ አላትና አብዝቼ እጠራጠራለሁ!

በመጨረሻም ትልቁን የወሬ ዝላይ እንዲህ ዘለልኩ …

ያወቅነውን ያህል … የገባንን ያህል እንመረምራለን … እውቀታችን በድንቁርና ባህር እንዳለች ደሴት ነች - በጥረታችን በተጋን ቁጥር የምትስፋፋ፣ ስንፍናን በመረጥን ቁጥር ተሸራርፋ ባህር ውስጥ የምትከተን፡፡ እናንተ ባለ ትልልቅ ደሴቶች ይችን ልብ በሉ፡- የተበጣጠስነው ደሴቶች ተሸራርፈን ባህሩ ውስጥ ሳንሰጥም ብንተጋገዝ አህጉር መሆን እንችላለን …

እናም ከፍ ብሎ የቀረበውን ሀሳብ በትንሿ የእውቀት ደሴቴ ላይ ቀምሬ እንደቀደመው ጻፍኳት …

 

 

Read 2703 times Last modified on Saturday, 21 April 2012 16:24