Saturday, 21 April 2012 16:25

“በድሮ ጊዜ ሥጋ የሚባል ምግብ ይመገብ የነበረ …”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

የዚህ አገር ነጋዴዎች በጣም የሚያበዙት አይመስላችሁም! አለ አይደል … ነገረ ሥራቸው ሁሉ … የሰውን “ስስ ብልት” እያዩ “ጉሮሮ ሲጥ አድርጎ” መቀበል አይነት ሆኗል፡፡ ገና ለገና እዚህና እዛ ላይ “መቶ ሁለት መቶ ብር ተጨማሪ ወጪ መጥቶብኛል፤” አይነት ነገር ተብሎ እኛ ላይ ሺህና ሁለት ሺህ መጫን አለበት እንዴ! ምነው እኛ ዘንድ ሲደርስ “ቅብብሎሽ” የፍራንክ ነገር ብቻ ሆነ!

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እንኳን ለዳግማይ ትንሳኤው አደረሳችሁማ!

ስሙኝማ … እነ “ሚት” እና “ኤግ” ምናምን ዘንድሮ ሠሩልን አይደል! (አዎ… አሁንም ከሆድ ወሬ አልወጣንም!”) እናላችሁ …. ይቺን ለ”ብታምኑም ባታምኑም” ቀጣይ ዕትም ሙሉ ምዕራፍ መሆን የምትችል ነገር ልንገራችሁማ፡፡ በቀደም የሆነ ገበያ ላይ አንድ የጂብለርታርን ቋጥኝ የሚያክል በሬ ስንት ሲጠራ ነበር አሉ መሰላችሁ! … አርባ ሦስት ሺህ ብር! ታምናላችሁ! ልድገመውና … አርባ ሦስት ሺህ ብር! (በነገራችን ላይ በዚሁ አገባቡ “በሬ” የሚለው አዲስ የ”መኪና ሞዴል” ስም እንዳልሆነ ግንዛቤ ይግባማ!)

ሠላሳና ሀያ ሺህ ብር ጥሪማ ተውት፡፡ እኔ የምለው … ጥያቄ አለን፤ እነዚህ የከፍተኛ አክስዮን ዋጋ የሚመስል ብር ሲጠራባቸው የነበሩ በሬዎች … በውስጣቸው “ንዑስ በሬዎች” ይዘዋል እንዴ! ብቻ … ለከርሞ ሸጎሌ ከብት ገበያ አንድ አሥሩን ደርድሬ ብታገኙኝ እንዳትደነቁ፡፡ አሀ … እንዲህ በአቋራጭ ዲታ መሆን እያለ … “ስሙኝማ …” እንትናዬ … ቅብጥርስዮ ማለት ምን ያደርጋል!

የምር ግን … የዚህ አገር ነጋዴዎች በጣም የሚያበዙት አይመስላችሁም! አለ አይደል … ነገረ ሥራቸው ሁሉ … የሰውን “ስስ ብልት” እያዩ “ጉሮሮ ሲጥ አድርጎ” መቀበል አይነት ሆኗል፡፡ ገና ለገና እዚህና እዛ ላይ “መቶ ሁለት መቶ ብር ተጨማሪ ወጪ መጥቶብኛል፤” አይነት ነገር ተብሎ እኛ ላይ ሺህና ሁለት ሺህ መጫን አለበት እንዴ! ምነው እኛ ዘንድ ሲደርስ “ቅብብሎሽ” የፍራንክ ነገር ብቻ ሆነ!

እናላችሁ … “ሰው ከፋ” ምናምን ነገር ስንባባል እኮ ዋና ማስረጃዎቻችን ነጋዴዎች ሆነዋል፡፡ (የሆነ የከብት ገበያ ላይ ሸማቾች አንገዛም ብለው አድመው ዋጋ እንዲስተካከል አድርገዋል የተባለችው የሬድዮ ወሬ ተመችታኛለች፡፡ አሀ … እኛም እንዲህ ስናመር “የግዱን ይገዛታል” የሚሉትን ነገር ይተውንላ!)

የምር … ለሚመለከተው ጥያቄ አለን፡፡ የበሬ የበግ ምናምን ዋጋ የሆነ ተመን ይውጣልንማ! በቃ… በቀደም ኢ.ቢ.ኤስ ጣቢያ ላይ ሲነግሩን እንደነበረው እኛም ዘንድ በግና በሬ ላይ ዋጋ ይለጠፍልን፡፡ (ስሙኝማ … በቀደም ኢ.ቢ.ኤስ ላይ ሌላ ምን ተስማማኝ መሰላችሁ … እንጀራ እንኳን) አልፎላት “ኤክስፓየር ዴት” ሲጻፍለት ደስ አይልም! እኛ ዘንድ እኮ፣ በተለይ ከተወደደ በኋላ … ዛሬ ቀን ተጋግሮ ነገ ማለዳ እንደ ኮቾሮነት የሚቃጣው የጤፍ አይነት መጥቶብን ግራ ገብቶናል፡፡ የሆነ የጤፍ “የምርት ጥራት” ሰርተፊኬት ምናምን ነገር ይፈጠርልንማ!)

ምን ይመስለኛል መሰላችሁ … እዚህ አገር “ተከራክሮ ገበያ” ነገር ካልቀረ ዘላለም እንደታለብን እንኖራታለን፡፡ አሀ … ሦስት ሺህ ብር የተጠራውን ነገር “ምላስ ያለው” በክርክር ስምንት መቶ ብር ሲወስድ የእኔ ቢጤው “እንደ ወረደ” ደግሞ ሁለት ሺህ ዘጠኝ መቶ ብር የሚታለብበት ምን አይነት ቢዝነስ ስትራቴጂ ነው!

ለነገሩ … እንግዲህ ጨዋታም አይደል … አልታወቀንም እንጂ የ”ሥጋ አምሮታችን” የቀነሰ አይመስላችሁም! ልክ ነዋ … አሁን ዘፈኖች ላይ “ዳሌዋ እንደ ኢንዶኔዥያ ሱናሚ ሲገላበጥ …” ምናምን የሚባል ነገር ትሰማላችሁ? “የእኔ ጌታ፣ በግራና በቀኝ በኩል እኮ እንደ ሪንጎ ሁለት ሽጉጥ የታጠቀች ነው የሚመስለው …” አይነት አድናቆት የቀረው የ”ሥጋ አምሮታችን” ስለቀነሰ ነው የሚል ጥርጣሬ አለን፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ቸብ ማድረግ እንኳን የፋራ ነገር ሆኗል አሉ፡፡

እናማ በአብዛኛው የግዷን ይገዛታል አይነት ነው፡፡ እኛን በዓይናችሁ ለማየት “የተጠየፋችሁ” ነጋዴዎች ይቺን ስንኝ ከየንግድ ፍቃዳችሁ ጎን ለጥፉልንማ …

እንቆቅና እሬት አስደቁሼ ጠጣሁ፣

እኔ እንደ ሰው ነገር የሚመረኝ አጣሁ፡፡

ስሙኝማ … ይቺን ነገር ድንገት አውርተናት ከሆነም እንድገማትማ … ሰውየው የሆነ ጓደኛውን ካገኘው ቆየት ብሏል፡፡ እናላችሁ ሌላ ሰው ሁለቱን እየጋበዛቸው ሳለ ጓደኝየው … ምን አለፋችሁ  … የእንቅቡም የሰፌዱም ሳይቀረው ይጠርግላችኋል፡፡ በቃ … ትሪው ላይ የሆነ “ክሊር ኤንድ ፕሬዘንት ዴንጀር” አይነት ነገር ይጋረጥበታል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ይሄኔ ሀፍረት የገባው ጓደኝየው ለጋባዡ ምን ቢለው ጥሩ ነው … “እኔ በፊት ሳውቀው አንድ ሆድ ብቻ ነበረው፡፡” አሪፍ አይደል! በዚህ ዘመን ከ”ቅጥያ ሆድ” ይሰውረንማ! የምር … ቢቻል እኮ አንዳንዴ “እድሳት ላይ ስለሆነ ለጊዜው አገልግሎት አይሰጥም” ብለን የሆዳችንን የተወሰነ ክፍል “አውት ኦፍ ሰርቪስ” ማድረግ ብንችል … አለ አይደል … የባንክ ደብተራቸውን ብቻ የሚያስቡ ነጋዴዎች መጫወቻ አንሆንም ነበር፡፡

ስሙኝማ … ከትርምስ መሀል ደህና ነገር መፈለግም አሪፍ ነው፡፡ የ”በግ ይገዛ ዶሮ…” የባልና ሚስት ጭቅጭቅ ዘንድሮ በጣም የሚቀንስ አይመስላችሁም! እንዲህ ከሆነም … እንኳን አንድዬ ለዚህ አበቃን የሚያስብል ነው፡፡ ልጄ … “አሁን ያንቺ ባል ሻኛው የሚንጎማለል ሙክት መግዛት አቅቶት ነው ይቺን ከወፍ ያልተሻለች ዶሮ የገዛሽው?” ከሚል የጎረቤት “ሎቢዪስት” መገላገልም አንድ ነገር ነው፡፡

(አንተ ወዳጄ… በፋሲካ ማግስት “ብዙ ሚስቶች በሰው ወሬ እየተመሩ የሚባሉትን እሺ አይሉም …” ምናምን እያልክ ስታማርር የነበርከው … የተከለከልከው ወይስ የቀረብህ ነገር አለ እንዴ! አንተ ነገሩን “ብማርሽ አይማረኝ” ነገር አታድርገዋ! ልጄ … እሷስ ምን ታድርግ! የቁርጥማት መድኃኒቱም እኮ እንደ ዶሮ በአምስት ሽልንግ አይገኝም፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…)

ስሙኝማ … እግረ መንገዴን፣ ሰውየው አሉ በሚስቱ ነገር ብስጭት ብሏል፡፡ እናማ ለወዳጆቹ ምን ይላቸዋል መሰላችሁ … “የእሷ ጭንቅላት ልክ እንደ በር እጀታ ነው፡፡” እነሱ “ምን ማለትህ ነው?” ብለው ሲጠይቁት ምን መለሰ መሰላችሁ … “ማንም እንደፈለገ ያሽከረክረዋላ”!

ማንም እንደፈለገ የሚያሽከረክረው “ጭንቅላት” አይስጠንማ!

ስሙኝማ … መአት የቅርጫ ማህበራት ፈረሱ አሉ፡፡ ቀሺሙ ነገር ግን ብዙዎቹ የከፈሉት ገንዘብ “ከብቱ ተወዷል” እየተባለ የተመለሰላቸው መቼ መሰላችሁ … ቅዳሜ ማታ! ምን አይነት የለየለት ክፋት ነው! አማራጭ እንኳን ሊፈልጉ በማይችሉበት ሰዓት “ለዛሬው አልተሳካም” አይነት ነገር የምር … የቅንነት አስተሳሰብ አይደለም፡፡ አንዳንዶቹም የከፈሉበትን ሊወስዱ ሲሄዱ አርባና ሀምሳ ብር ለመጨመር ተገደዋል፡፡

እናላችሁ … የዕቁቡ፣ የአክስዮኑ፣ የአብሮ አደጉ የምናምኑ ማህበር ሁሉ (አብዛኛውን ጊዜ ከግለኝነትና ከራስ ወዳድነት የተነሳ) ሲንኮታኮቱ “ምንም ቢሆን አይፈርስም” ያልነው የቅርጫ ማህበር እንኳን ሲፈርስ የሆነ ቀሺም ነገር ነው፡፡

እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… አንድ ወዳጄ በሺህ አምስት መቶ ብር አንዲት ፌስታል ያልሞላ አንድ መደብ የቅርጫ ሥጋ ይዞ ሲሄድ ምን ቆጨው መሰላችሁ …”የአንድ ሺህ ብር አክስዮን ለመግዛት ገንዘቡን ከየት አምጥቼው ስል ቆይቼ ፌስታል የማትሞላ ሥጋ በሺህ አምስት መቶ!”

(እንትና … ነፍስ ጡሯ ለመገላገል ስንት ጊዜ ቀራት? የወዳጅነቴን ምክር ልስጥና ምን ብለህ ተሳል መሰለህ … አምላኬ እስክትገላገል ድረስ ሥጋ አማረኝ ካላለችኝ አንድ ወረቀ ዘቦ ምንጣፍ ላገባ…” ምናምን ብለህ ተሳል፡፡ አሀ … “የዶሮ ማነቂያ ሽንጥ በዓይኔ ዞረ” ብትል ምን ይውጥሀል! ምናልባት እኛን ወዳጆቼ አሉልኝ ምናምን ብለህ እንዳትሞኝ …”ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ…” ምናምን የሚሉት ተረታ ተረት ባልተጻፈ ስምምነት እንደሰረዝነው እወቅልንማ!

እናላችሁ … ይኸው ወዳጄ የገባበት ቅርጫ ሥጋው በመደብ በመደብ ተከፋፍሎ እያለ አንዱ ሰውዬ … “ይሄ እኮ ለታሪክ መቀመጥ ያለበት ነው…” እያለ በዲጂታል ካሜራ ያነሳው ነበር አሉ፡፡ ልክ ነዋ … ነገ ልጆቹ “አባዬ፣ ሥጋ ማለት ምን ማለት ነው?” ያሉ እንደሆነ ስዕላዊ መግለጫ መስጠቱ ስለሚያስቸግር … አለ አይደል … ፎቶውን አሳይቶ “ይኸውላችሁ ሥጋ የሚባለው …” እያሉ ለማስረዳት ይቀላል፡፡

እንደውም ምን ይመስለኛል መሰላችሁ … ነገርዬውን በጊዜ እያስተካከልነው ካልሄድን የልጆች “ቤድታይም ስቶሪ” ምናምን ነገሮች …”በድሮ ጊዜ በአንድ አገር የምትኖር ውብ ልዕልት ነበረች…” ምናምን ከማለት ተለውጦ … “በድሮ ጊዜ ዓመት በዓል ሲመጣ ሥጋ የሚባል ምግብ የሚበላ ዶጮ የሚባል አንድ ህጻን ልጅ ነበር …” ሊሆን ይችላል፡፡

“አይመጣንም ትተሽ ይመጣልን ያዢ…” የሚለው አባባል ከዜማ ጋር ተዋህዶ በሲንግል ይለቀቅልንማ!

ስሙኝማ … እንግዲህ ጨዋታም አይደል … “የሠርግ ቪዲዮ ማሳመሪያ” ቁርጥ ሥጋ እንዴት ሊሆን ነው! ሀሳብ አለን … ዶሮ ማነቂያዎች … “ሽንጥ ፎቶ ለማንሳት ሁለት መቶ ብር፣ ለታላቅና ታናሽ መቶ ሀምሳ ብር …” አይነት ቢዙ የማይጀምሩሳ! እና … በቪዲዮው ማለቂያ ላይ “ምስጋና” በሚለው ስር “በዚህ የሰርግ ቪዲዮ ላይ የሚታየውን ሽንጥ እንድናነሳ የተባበሩንን የዶሮ ማነቂያ ሉካንዳዎች እናመሰግናለን…” ምናምን ማለት ይቻላል፡፡

ስሙኝማ … ነገራችን ሁሉ ማጋነን መሰለ አይደል! የምር … ዘንድሮ ብዙ ነገሮች ራሳቸው ከመግነናቸው የተነሳ እናጋን ብንልም የምንሄድበት መንገድ እየጠበበን ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት “በሬ ሠላሳ ሺህ ብር ተጠራ” ብንል “እንደው በልክ እንኳን ማጋነን አትችልም!” እንባል ነበር፡፡ የዘንድሮ ገበያ እኮ ለቀሺም የፍቅር ኮሜዲ ፊልም እንኳን ያስቸግራል! “ለሰርጋችን ሰንጋ ብጠይቅ አርባ ሦስት ሺህ ብር አሉኝ …” የሚል ሙሽራ … አለ አይደል … ሙሽሪቱ “ገና ሳንጋባ እንዲህ የተተረተረ እቤቱ ስገባማ አቃጥሎ ይገድለኛል …” ብላ የፍጥምጥም ቀለበቱን አፍንጫው ላይ ትወረውርለት ነበር፡፡

የምር እኮ … “ዶሮ መቶ ብር ገባ…” ተብሎ ድፍን አገር ሱባኤ ምናምን የሚቀመጥ ይመስል የነበረበት ጊዜ እኮ በጣም ቅርብ ነው!

እናማ … ከዚህ ሰሞኑ የዋጋ “እብደት” ጀርባ በዋናነት ያሉት ነገሮች ምን መሰሏችሁ … “ራስ ወዳድነት’ና “አልጠግብ ባይነት’፡፡ የዳግማይ ትንሳኤ ቅልጥም ከተገኘ ወደ ቅልውጥ ነገር ልሂድ መሰለኝ! “በድሮ ጊዜ ሥጋ የሚባል ምግብ ይመገብ የነበረ …” አይነት የተረት አጀማመር ላይ እንዳንደርስ አንድዬ ይጠብቀንማ!

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

Read 3239 times Last modified on Saturday, 21 April 2012 16:33