Saturday, 21 April 2012 16:56

“ስለ ፍቅር” - የቴዲ የፍቅር በረከት!

Written by  ቢኒያም ሐብታሙ binihab@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

እነሆ ነገ የፍቅር ዳግማዊ ትንሳኤ የሚከበርበት ዕለት ነው፤ ቀዳሚዎቹ ቀናት ደግሞ የፍቅር ትንሳኤ የተዘከረበት ሆነው አልፈዋል፡፡ ለመሆኑ ትንሳኤ እንዴት አለፈላችሁ? ለእኔ አሸወይና ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የትንሳኤን የፍቅር መገለጫነት በጥልቅ እንዳስብ ያደረገኝን ምርጥ ሙዚቃ እያደመጥኩ፣ ትንሳኤ ዘ ዳግማዊ ፍቅርን/ዳግማዊ - ትንሳኤን/ እየጠበኩላችሁ ነው፡፡ ታዲያ ዘፈን ሁሉ  ዘፈን አይባልም፤ ዘፈን ወይም ሙዚቃ ስል፣ ቴዲ አፍሮ በአዲስ አልበሙ በቁጥር ሁለት ላይ ያስደመጠንን “ስለ ፍቅር” አይነት ምርጥ ሥራ ማለቴ ነው፡፡

በነገራችን ላይ የቴዲ አፍሮን አዲስ አልበም አደመጣችሁት? እኔም እንደ አብዛኛው አድማጭ አልበሙ ይወጣል በተባለበት ቀን በብርቱ ክርክር በ25 ብር ገዝቼ የቴዲን አዲስ አልበም በጠዋቱ መኮምኮም የጀመርኩት፡፡ ረፈድፈድ ሲል ግን ጥቂት ቅጂ ብቻ ነው የተለቀቀው በሚል ሰበብ፣ ሲዲው ከ40 ብር እስከ 100 ብር ሲሸጥ እንደዋለ በመስማቴ እድሌን እና ክፉ ተከራካሪነቴን አመሰገንኩ፡፡

አልበሙ ከመለቀቁ በፊት በከተማችን አብዛኛው ክፍሎች የተለጠፉትን የቴዲን ፖስተሮች ሳልፍ ሳገድም እያየሁ፣ በጉጉት ስጠባበቅ የነበረው የአልበሙ መጠሪያ የሆነውን የ“ጥቁር ሰው” ሙዚቃንና ትርጉም ለመስማት ነበር፤ ልክ የቀዳሚው አልበሙን “ያስተሰርያልን” ትርጉምና ዘፈን ለመስማት እንደቸኮልኩት ሁሉ፡፡

እናም ሲዲውን ገዝቼ በቅርብ ባገኘሁት ማጫወቻ  (ላፕቶፕ) ውስጥ ስከተው ዘፈኑን ቁጥር አንድ ላይ አገኘሁት፡፡ ሙዚቃውን በጆሮዎቼ እና በስሜቴ እየሰማሁ፣ በአይኔ ደግሞ የሲዲው ሽፋን ላይ የሰፈሩትን ጽሑፎች ማንበብ ጀመርኩ፡፡ “የአልበሙ መታሰቢያነት…” ወዲያው የ“ጥቁር ሰው” ህብረ - ቃል እና ሰም ተገለፁልኝ፡፡ ወርቁን እንደ ቅኔ ደጋግሜ ስሰማው ሊገለጽልኝ እንደሚችል በማሰብ፣ በልቤ አጨብጭቤ ወደ ሁለተኛው ዘፈን አለፍኩ፡፡

ሙዚቃ ቁጥር - 2፣ “ስለ ፍቅር”፤ የሚለው አጀማመሩ ላይ ልክ እንደ ቁጥር -1 ደቡባዊ ቃና የሰማሁ መሰለኝ፡፡ ቀጠልኩ… በከፊል ጉጉታዊ፣ በከፊል ሂሳዊ አኳኋን ጆሮዬን አርዝሜ፤ እንዲያው በደፈናው የደቡብ ከመሰሉኝና ካልገቡኝ ቃላት ቀጥሎ ያሉት የመጀመሪያዎቹ የአማርኛ ሀረጐች ቀልቤን ገዙት…ሙዚቃውን በግርምት ጀምሬ በፀፀት  ጨረስኩት፡፡ ወደሚቀጥለው ሙዚቃ ለማለፍ አልፈለግሁም፤ ደገምኩት፤ እንደገና… ሶስት፣ አራት ጊዜ…የሙዚቃውን ርዕስ አንብቤ ከጠበኩት የፆታዊ ፍቅር ትርጉም በተለየ ስለ አገር የተዜመ መሆኑ የበለጠ ቀልቤን ገዛው፡፡ ለዛውም፣ አገር ስለምንላት ስለ ግዑዟ ተራራና ሸንተረር ሳይሆን ስለ ህዝቧ፣ ለህዝቧ ስለሚገባ ፍቅር መሆኑ የእርካታ ማማ ላይ አወጣኝ፡፡

የሙዚቃው ወርቅ ይገለጽልኝ አይገለጽልኝ ባላውቅም ስለ ሰሙ ግን እንዲህ ለማለት ደፈርኩ - ከሙዚቃ ስንኙ እያጣቀስኩ :-

ስለ ፍቅር ሲባል ስለፀብ ካወራን ተሳስተናል

አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል…

ሲል የህብረትና አንድነታችንን ተፃራሪነት ያሳየናል፤ አንድ ላይ ነን ብለን ብናስብም አንዳችን ፍቅር ሌላችን ጠብ እንደነገሰብን እያዜመ ይቀጥላል ዘፈኑ…

አጥተናል እውነት ነው ተቸግረን ብዙ አይተናል

የመጣነው መንገድ ያሳዝናል…እያለ፡፡ ነገር ግን በእርግጠኝነት የተለያየንበት ምክንያት ማጣታችንና መቸገራችን ብቻ ነው ብሎ ባለማሰቡ ይመስላል የቁጭት ጥያቄ ይሰነዝራል…

እግር ይዞ እንዴት አይሄድም ሰው ወደፊት አይራመድም

አፈር ይዞ ውስጡ አረንጓዴ፣ ለምን ይሆን የራበው ሆዴ…

በማለት፤ ችግራችን ከተፈጥሮ እንዳልመነጨ ውብ እና አንጀት በሚበሉ ቃላት ያንጐራጉራል፤ ከእግር እግር ከአገር አገር፣ እግሩ ቀና፣ አፈሩ መና(ና ጠበቅ ብሎ ይነበብ) እያለ…

ጠይቆ ጠይቆ መልስ ያጣ ሰው ሁሌ እንደሚያደርገው፣ ወደ ኋላ መለስ በማለት የችግሩን ስር መሰረት ለመረዳት ታሪካችንን እንመርምር የሚሉት ስንኞች ደግሞ ይቀጥላሉ…

የት ጋ እንደሆነ ይታይ የኛ ጥበብ መሰረቱ

የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ…በማለት፡፡

ይቀጥልና ደግሞ መሄጃ መንገድ እንደጠፋው፣ የተስፋ ወጋገኑ እንደራቀበት በመግለጽ የእረፍት መንገድ፣ የከንቱ መዋተትና መንከራተት መቋጫን፣ የተስፋ አቅጣጫን ይጠይቃል፡፡ እንዲህ እያለ…

ከአድማስ እየራቀ ምነው ይሄ መንገድ ያባክነኛል

በየት በኩል ብሄድ ወደ እረፍት ሀገሬ ቶሎ ያደርሰኛል

አገራችንን ኢትዮጵያንም ሲገልፃት በአብረቅራቂ ቀለማት፣ በተሽቆጠቆጡ ቃላት መሆኑ አገራችንን በልዩ የስሜት ከፍታ እንድናያት ያነቃናል፤ ያነሳሳናል፡፡

ቀስተ ዳመና ነው የለበስኩት ጥበብ፣ የያዝኩት አርማ

አልጠላም ወድጄ የነብሴ ላይ ፋኖስ እንዳያይ ጨለማ

ይህቺን አርማዋን በቀስተ ዳመና የመሰለች አገር፣ የነብስ ፋኖስ ብርሃኗ ጠፍቶ ለማየት እንደማይፈልግ፤ ፍቅርን እየተማፀነ ይጠይቃል፤

አንተ አብርሃም የኦሪት ስባት

የእነ እስማኤል፣ የይስሃቅ አባት

እንደ አክሱም ራስ ቀርፀሃት ራሴን

በፍቅር ጧፍ ለኩሳት ነብሴን

አብርሃም ከሁለት ነገዶች የተገኙ ልጆች አባት እንደሆነ፣ የፍቅርና የፅናት አባትነቱን ይጠቅስና በእሱ አምሳል እንዲቀረፅ ተማፅኖውን ያቀርባል፡፡ ነብሱ በፍቅር ጧፍ እንድትበራ፤ ልቡ ቀና እንድትሆን፤ የተስፋይቱን ምድር ከንዓን /ዳግማዊት-ኢትዮጵያን/ በአይኑ እስኪያይ ድረስ ልቡ እንዳይዝል፣ ሰውን ለመውደድ እንዳይደክመው ያዜማል፤ አገርኛ በሆነ ሆድ በሚበላ እንጉርጉሮ! …

በል አትዛል ቀና ሁን ልቤ

የህልሜን ከንዓን እንዳይ ቀርቤ

ሰው ለመውደድ ካልኩኝ ደከመኝ

ያኔ ገና ውስጤን አመመኝ …

በነገራችን ላይ አዲሱ የቴዲ አፍሮ አልበም መጠሪያ “ስለ ፍቅር” መሆን ነበረበት ባይ ነኝ፡፡ ይህን ስል ታዲያ “ጥቁር ሰው”ን ሙዚቃን እያሳነስኩ አይደለም፡፡ በግጥምም፣ በዜማም፣ በሃሳብም ጠንካራ መሆኑን መካድ ከቶም የሚቻል አይደለም፡፡ ታዲያ ይህ አልበም “ስለ ፍቅር” መሆን ነበረበት ስል ምክንያቴ የመነጨው ከግማሽ በላይ በሚሆኑት ዜማዎቹ ውስጥ በተለያየ መንገድ ቢሆንም ቴዲ አፍሮ “ስለ ፍቅር” ተቀኝቷል፤ አዚሟልና ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል “ሃያል” የሚለውን ቁጥር 7  ብንመለከት…

ዳገቱ ላይ አትዛል ጉልበቴ

የተራራው ጫፍ ፍቅር ናት እርስቴ

ቀላል ይሆናል ቀና አርገኝ ፅናቴ…

ቀላል ይሆናል (4X) …

በማለት ልክ እንደ ቁጥር 2  (“ስለ ፍቅር”) ዜማው የፍቅር ፅናትን ይለምናል፣ ስለ ነገ ብሩህ ተስፋ በፍቅር ሙዚቃ፣ በሬጌ ይሰብካል፡፡

ደመና ሲያይ መስሎት የጨለመ

አለ ይህ ሰው ሁሉም አከተመ

ደቂቅ ተስፋን ካየናት አርቀን

ነገ ሌላ ይሆናል ብሩህ ቀን

ቀላል ይሆናል (4X) …

በመቀጠልም የባለቅኔውን የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ግጥም በመሃል በሚጣፍጥ አኳኋን አስገብቶ በያሬዳዊ ዜማ፣ በፀናፅልና በከበሮ ታጅቦ ስለ ፍቅር ማህሌት ይቆማል፣ ስለ ፍቅር እግዚኦ ይላል …

አዬ…አዬ…ፍቅር… እያለ፡፡

በመጨረሻ የቅዱስ መፅሃፉን ቃል አስታውሻችሁ ፅሁፌን ላብቃ፡፡ “እኔ እንደወደድኳችሁ እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህች ናት፡፡” ለዚህም ይመስላል ቴዲ አፍሮ የኮንሰርት ሥራዎቹን ሲያቀርብ “እንዋደዳለን? ፍቅር ያሸንፋል!” እያለ የሚናገረው፣ የሚሰብከው፡፡

የዳግማይ-ትንሳኤ በዓል የፍቅር ይሁንልን እያልኩ፣ ትንሳኤ ለዳግማዊቷ-ኢትዮጵያ እመኛለሁ፡፡ ቴዲንም ቃለ-ጥበብ ያውርስልን!! ኢትዮጵያ በፍቅር ለዘላለም ትኑር!

 

 

Read 8069 times Last modified on Saturday, 21 April 2012 16:59